ታምራት ተስፋዬ
በኮሮና ቫይረስ ሳብያ በ81 ሀገራት ብቻ ከ20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዓመታት የሚልቅ ቀሪ ዕድሜ መታጣቱን አዲስ የሳይንስ ጥናት አመላክቷል። በjournal Scientific Reports, ላይ የወጣው ይህ ጥናትም በፆታ ንፅፅር ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ውድ የህይወት ዓመታትን ተነጥቀዋል ብሏል።
ጥናቱ የተሰራው የታጣው የመኖሪያ ዘመን ሟቾች በሞቱበት ጊዜ ባላቸው ዕድሜ እና ይኖሩበታል ተብሎ በሚታመነው የዕድሜ ጣርያ ታሳቢ በማድረግ ነው። በ81 ሀገራት የተከሰቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የኮቪድ-19 ሞቶችን ብሎም የየአገራቱን የተቀመጠ አማካኝ የህይወት ጣሪያ ላይ በመመርኮዝ ነው።
ጥናቱ ‹‹በዚህ ስሌት መሰረት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ገና ወደፊት ሊኖር ይቻል የነበረ የ20 ሚሊዮን 507 ሺ 518 ዓመታት ነጥቋል፣ በእያንዳንዱ ሟች በአማካኝ የ16 ዓመታት ዕድሜ ቀንሶበታል››ብላል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተነጠቁት የሕይወት ዓመታት ውስጥ 45 በመቶው ዕድሜያቸው ከ55 እስከ 75 ዓመት ባለው ውስጥ ከሚገኙ ነው። 30 በመቶ የሚሆነው ሕይወት የተነጠቀው እድሜያቸው ከ55 ዓመት ባነሱ ዜጎች ሲሆን 25 በመቶው ደግሞ ዕድሜያቸው ከ75 ዓመት በላይ ከሆኑት ላይ ነው።
በፆታም ወንዶች ከሴቶች በ44 በመቶ የበለጠ ዕድሜን አጥተዋል። ለዚህ ይህን ነው የሚባል ምክንያት መሥጠት ባይችሉም፣ይሁንና በበርካታ አገራት ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ሲጋራ ማጨሳቸው በወረርሽኙ ከተያዙ በኋላ ይበልጥ እንዲቆስሉ ምክንያት ሆኗል የሚል መላ ምት ሰጥተዋል።
በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት በሚባሉት፣ እንደ ኩባ ዶሚኒክ ሪፐብሊክ ፔሩ ከሴቶች ይልቅ ወንዶቹ ብዙ ሕይወት ተነጥቀዋል። ከፍተኛ ገቢ አላቸው በሚባሉ ፊንላንድ እና ካናዳ በመሳሰሉ አገራት ደግሞ ተመሳሳይ አሃዝ መስተዋሉ ተጠቁማል። ለዚህ ደግሞ የህክምና አቅርቦት፣ጥራት እና ክትትል ልዩነት በምክንያትነት ቀርቧል።
በኦፕን ዩኒቨርሲቲ የስታትስቲክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ኮቪን ማኮንዌይ፣ውጤቱ የተለያዩ አገራት የእድሜ ክልል ይፋ የሆኑ የሞት መረጃዎችን በመንተራስ የተሰራ እንደሆነና የወረርሽኙን ሙሉ ምስል እንደማያሳይ ተናግረዋል።
ተጨባጭ የሆኑ መረጃዎችን ማግኘት ቢቻል አሃዙ ሶስት እጥፍ የላቀ ሊሆን ይችላልም›› ብለዋል። ለሞት ባያበቁም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተከሰቱ ህመምና አካል ጉዳቶች ታሳቢ ቢደረጉ ምስሉን ይበልጥ እንደሚያጨልመው አስታውቀዋል።
በሪዲንግ ዩኒቨርሲቲ የማክሮባዮሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሲሞን ከላርክ በበኩላቸው፣‹‹ጥናቱ ወረርሽኙ ምን ያህል የሰው ልጅን ዋጋ እንዳስከፈለው ምን ያህል ውድ ቀሪ ሕይወቶቹን እንደነጠቀው በግልፅ የሚያስረዳ ነው›› ብለዋል። ምንጫችን ቢዝነስ ስታንዳርድ እና ሳይንስ ሚዲያ ኒውስ ናቸው።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2013