ታምራት ተስፋዬ
እጅግ በጣም ቀዝቃዛ በሆኑ ቦታዎች እንዲሁም ከፀሐይና ከውቅያኖስ አካባቢ እየራቅን በሄድን ቁጥር የህይወት ዋስትናም በዚያው ልክ እየቀነሰ እንደሚሄድ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ለፍጥረታት ህይወት የማይ ስማሙ አካባቢዎች ከሚባሉት ውስጥ በበረዶ የተሸፈነው የዓለማችን አንዱ አህጉር አንታርክቲካ ነው። ለብዙ ጊዜያት ካለው ቅዝቃዜ የተነሳ በዚህ አህጉር ብዙ ፍጥረታት ይኖራሉ ተብሎ አይገመትም ነበር።
ይሁንና ከቀናት በፊት የወጣ መረጃ በቀዝቃዛማው አህጉር ያልተጠበቀ ልዩ ፍጥረት በበረዶ ንጣፎች ውስጥ እንደተገኘ አመልክቷል። የብሪትሽ አንታርክቲክ ጥናት ካሜራ እና ተመራማሪዎች፣ የበረዶ ግግሩን 900 ሜትር ጠልቀው መቆፈራቸው የተገለፀ ሲሆን ፣ ክፍት ከሆነው ውቅያኖስ 260 ኪሎ ሜትር ያክል ርቀት ባለው አካባቢ ከዜሮ በታች 2 ነጥብ 2 ዲግሪ ሙቀት ውስጥ ያልተጠበቀ ልዩ ፍጥረት መገኘታቸው ተገልጧል።
ግኝቱም ሌሎች እስካሁን ያልታወቁ ፍጥረታት በአካባቢው እንዳሉ የሚጠቁሙም መሆኑም ተጠቁ ማል። ተመራማሪዎቹም ግኝቱ ከፀሐይና ከውቅያኖስ አካባቢ እየራቅን በሄድን ቁጥርና በጣም ቀዝቀዛ በሆኑ ቦታዎች ህይወት ዋስትና በዚያው ልክ እየቀነሰ ይሄዳል የሚለውን እምነት ዳግም እንድናጤን የሚያደርግ ነው›› ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር ግኝቱ ከመልስ ይልቅ በርካታ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ መሆኑም አፅንኦት ተሰጥቶታል። በዚህ ጥልቀት ውስጥ እንዴት ሊገቡ ቻሉ፣ ምን ይመገባሉ፣ ለምን ያክል ጊዜ በዚህ ቦታ ቆዩ ፣ ከበረዶው ዓለም ውጭ ከሚታወቁት ጋር ምን ያመሳስላቸዋል ወይንስ አዲስ ፍጥረታት ናቸው፣ የበረዶው ክልል ከምድረ ገፅ ቢጠፋስ እጣ ፈንታቸው ምን ይሆናል የሚሉ ጥያቄዎችንም አስነስቷል።
የብሪትሽ አንታርክቲክ ጥናት መሪ ባዮጂዞግራፈር ዶክተር ሁ ግሪፍዝ ግኝቱ ያልተጠበቀና በቀዝቃዛው ዓለም ውስጥ የተለያዩና ያልታወቁ ፍጥረታት እንዳሉ የሚያሳይና ስለ አካባቢው እስካሁን ያለውን እሳቤ የሚቀይር እንደሆነ ተናግረዋል። ‹‹ጥያቄዎቹን ሁሉ መልስ ለመስጠትም ይበልጥ ወደ እንስሳቱ መቅረብና ማጥናት ግድ ይለናል›› ብለዋል።
በዚህ ርቀት እንዲሁም እጅግ ከባድ ስፍራ ተጨማሪ ጥናቶችን ማድረግ ግን ቀላል እንዳልሆነም ሳይጠቁሙ አላለፉም። የተመራማሪዎችን ጥረት ለማገዝም አዲስ ቴክኖሎጂ የሥራ እስትራቴጂ እንዲሁም ዘመናዊ የሆኑ ትናንሽና በርቀት መቆጣጠሪያ የሚንቀሳቀሱ ካሜራዎችም የግድ እንደሚሉም ተገልጿል። ምንጫችን ኒው ሳይንቲስት ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2013