ታምራት ተስፋዬ
የስነ-ምድር ተመራማሪዎች በዓለም ሙቀት መጠን የባህር ጠለል ከፍታ እየጨመረ በመምጣቱ በተለይ ከተሞች በውሃ የመዋጥ አደጋ እንደተጋረጠባቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይታል።
ከቀናት በፊት ይፋ የሆነ አንድ ጥናት ደግሞ ከእለት እለት እየተስፋፋ እና እየጨመረ የመጣው የከተሞች መስፋፋት እና መግዘፍ ምድር መሸከም ከምትችለው በላይ እየሆነ መምጣቱን አመላክቷል፡።
በዩናይትድ እስቴትስ ጂኦሎጂካል ጥናት ኤጀንሲ፣ የጂኦ ፊዚስት ወይንም የስነ-ምድር ተመራማሪ የሆኑት ቶም ፓርሰን የሳንፍራንሲስኮን ሁኔታ አጥንተዋል። በውጤቱ የግዙፍ ከተሞች መስፋፋት ገፀ-ምድርን እየተጫነው እንደሆነ ለመረዳት ችለዋል።
ከጥናቱም ሳንፍራንሲስኮ እድገቷ በጨመረ ቁጥር እስከ 80 ሚሊ ሜትር ወይንም ሶስት ነጥብ አንድ ኢንቺ ድረስ ወደታች እየሰመጠች ነው ተብሏል። አካባቢው በባህር ጠለል ከፍታ መጨመር ምክንያት እኤአ እስከ 2050 ድረስ 300 ሚሊ ሜትር ወይንም አሥራ አንድ ነጥብ ስምንት ኢንች የመስመጥ አደጋ እንደተጋረጠባት ተመላክቷል።
በጥናቱ በከተማዋ የሚገኙ እያንዳንዱን ህንፃዎች በመቁጠር ይዘትና የክብደት መጠናቸውን ተሰልቶ ተቃኝቷል።
የከተማዋ 1ነጥብ 6 ትሪሊዮን ኪሎግራም ፣ ሶስት ነጥብ አምስት ትሪሊየን ፓውንድ ወይንም ስምንት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ቦይንግ 747s. ክብደት እንዳላት ታውቋል።
ይህ አይነት መጠን ክብደትም ከተማን ለማስመጥ በቂ መሆኑ ተጠቁማል። የከተማዋ ህንፃዎች ክብደት ከህንጻ ውጭ ያሉ ሌሎች የትራንስፖርት መሰረተ ልማት፣መኪናዎች እንዲሁም ህዝቡን የማይጨምር በመሆኑ የስጥመት መጠኑ ከ80 ሚሊ ሜትር ከፍ ሊል እንደሚችል ተገምቷል።
‹‹በከተማዋ የሚገኘውን ግዙፍ ከክብደት መጠኑ ከፍተኛ እንደሆነ የሚነገረው የሰንፍራንሲስኮ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በየዓመቱ አራት ሚሊሜትር ወይንም 0ነጥብ አሥራ ስድስት ኢንች እየሰመጠ እንደሚገኝም አመላክታል።
የስነ-ምድር ተመራማሪ የሆኑት ቶም ፓርሰን የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የባህር መጨመር ደግሞ መጪውን ይበልጥ አስጊ እንደሚያደርገው በጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።
ይህ ጥናት ሳንፍራንሲስኮን ላይ ብቻ ቅኝት ያድርግ እንጂ ግኝቱ ለሌሎች ጥናቶች መሰረት የሚሆን እና ከተሞች ሆነ አገራትን ምስል ለመረዳት የሚያስችል መሆኑንም በርካቶች ተስማምተውበታል።
መረጃው እንደሚያመላክቱት፣የኢንዶኔዢያ ጃካር ታ፣ የቻይናዋ ሻንጋይ፣ የታይላንዳ ባንኮክ ፣እንዲሁም የዩናይትድ እስቴትስ ኒው ኦርሊያንስ የመስመጥ ስጋቱ ከተደቀነባቸው ከተሞች መካከል ቀዳሚ ናቸው። ምንጫችን ሳይንስ አለርት እና ሳይንስ ታይምስ ናቸው።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2013