ለምለም መንግሥቱ
በዋና አስፓልት በግራና ቀኝ የሚገኘው የእግረኛ መንገድን በሽክላ ንጣፍ(ቴራዞ)፣የውስጥ ለውስጡን ደግሞ በንጣፍ ድንጋይ በማሳመር ለእግረኛው ምቹ ለማድረግ በመንግሥት እየተከናወነ ያለው ተግባር ይበል የሚያስብል ነው። ሥራውም በህግ እንዲመራም የመንገድ ግንባታ አዋጅ ወጥቷል።
ምንም እንኳን መንግሥት በኃላፊነት ግንባታውን የሚያከናውን ቢሆንም ለግንባታ የሚወጣው ወጪ ግን የህዝብ ሀብት መሆኑ አይዘነጋም። ከነጋዴው ማህበረሰብና ከመንግሥት ሠራተኛ የሚሰበሰበው ግብርም ለዚሁ ዓላማ የሚውል እንደሆነ ይታወቃል። የመንገድ ግንባታም ብዙ መዋዕለ ነዋይ ወጥቶበት የሚከናወን እንደሆነም የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለእግረኛ ተብለው የሚገነቡት የግራና ቀኝ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ለታለመላቸው ዓላማ እየዋሉ እንዳልሆነ መጻፍ ለቀባሪው አረዱት እንደሚባለው ይሆንብኛል። ተብሎ ተብሎ ድካም ሆኖ የቀረ ጉዳይ ነውና።
በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን ያካፈሉን አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የአስፓልት ዳርና ዳር የእግረኛ መንገድ በሸክላ ንጣፍ እያማረ ያለው ለእግረኛው ሳይሆን በጎዳና ንግድና ሱቅ ይዘው ለሚነግዱ ነጋዴዎች ነው ማለት ይቻላል ይላሉ።
እግረኛው አስፓልት ውስጥ ገብቶ ከመኪና ጋር እየተጋፋ እንደሚሄድ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ደግሞ በከፊል ለመኪና ማጠቢያ አገልግሎት መዋሉን፣ በተጨማሪም ለግንባታ የሚውሉ ድንጋይ፣ አፈር፣ ጠጠር፣ አሸዋና ሌሎችም ግብአቶች ማከማቻ ሆነው እንደሚያገለግሉ፣ ከክብደት በላይ ጭነት የያዙ ተሽከርካሪዎችም በነዚሁ የእግረኛ መንገዶች ላይ እንደሚጠቀሙ፣ ከታለመላቸው ዓላማ ውጭ በመዋላቸውና በሚበዛባቸው ጫናም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጎዱ፣ ከጥገና ባለፈ አዲስ ሥራ የሚያስፈልጋቸው ጥቂት የማይባሉ መንገዶች መኖራቸውን ትዝብታቸውን ነግረውናል።
የአስፓልት ዳር የቆሻሻ ውሃ ማስወገጃዎችም ክፍት በመሆናቸው መንገደኛውን ለከፋ ጉዳት እያጋለጡ መሆናቸውም በተደጋጋሚ እየተነገረ ቢሆንም መፍትሄው እጅግ የዘገየና የተዘነጋ እንደሆነም አስተያየት ሰጪዎቹ ይገልፃሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ስርጉት በላይነህ የዛሬ አስር ዓመት ጀሞ አንድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የጋራ መኖሪያ ቤት የዕጣ ዕድለኛ ሆነው ሲገቡ በኮብል ስቶን የተሰራው የውስጥ ለውስጥ መግቢያ መንገዳቸው አሁን የቀድሞ ይዞታው ላይ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
እርሳቸው እንዳሉት በመኖሪያ ቤቱ ፊት ለፊታቸው ግለሰቦች ህንፃ ሲገነቡ ለግንበታ የሚሆን ዕቃ በከባድ መኪና ሲያጓጉዙ የተነጠፈው ኮብል ስቶን ተነቃቅሎ የሚጠቀሙበት መንገድ አፈር ሆኖ በበጋ አቧራው፣ በክረምት ደግሞ ጭቃው መውጪያ መግቢያ አሳጥቷቸዋል። መንገዱን ያበላሹት መልሰው አልሰሩትም።
በመንግሥት በኩልም ተከታትሎ እንዲስተካከል ያደረገ አካል ባለመኖሩ ለመንገድ ሥራው የወጣው ሀብት ባክኖ ቀርቷል። የውስጥ ለውስጥ መንገድ ባለቤት የለውም። በአካባቢያቸው ያለው የውስጥ ለውስጥ መንገድ በከፊል ለመኪና እጥበት አገልግሎት መዋሉንም ይናገራሉ።
ወይዘሮ ስርጉት እንዳሉት በሌላኛው በኩል ደግሞ ያልተፈቀደላቸው ከፍተኛ ጭነት ያላቸው ከባድ መኪኖች በድንጋይ ንጣፍ በተሰራው የእግረኛ መንገድ ላይ በመጠቀም መንገዱን ብቻ ሳይሆን በሚኖሩበት የጋራ መኖሪያ ቤት ላይ የመሰንጠቅ አደጋ እያደረሱ ይገኛሉ። የጭነት መኪኖቹ በመንገዱ እንዳያልፉ የሚኖሩበት የጋራ መኖሪያ ቤት የሰፈረ ሰላም ማህበር የሚያስቀምጠውን የብረት መከላከያ በመገንጠል ነው የሚጠቀሙት።
ይህን ሁሉ ችግር ማህበራቸውም ሆነ ነዋሪው ለክፍለ ከተማው ትራፊክ ጽህፈት ቤትና ለወረዳው አቤት ቢሉም መፍትሄ አላገኙም። ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት ዜጎች እንዲጠቀሙበት የተሰራው መንገድና መኖሪያ ቤት በግዴለሽነት ለጉዳት መዳረጉ እንደሚያሳዝናቸው ያስረዳሉ።
እንዲህ ያለውን ችግር ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ፕላንና ጥናት ኮሚሽንም ደርሶበታል። በ2010ዓ.ም አንድ መቶ ኪሎ ሜትር የሚሆን የግራና ቀኝ የእግረኛ መንገድ ያካተተ በተለይም ሰብሳቢ (ኮሌክተር ስትሪት) ከ20 ሜትር ስፋት በላይ ያለው የእግረኛ መንገድ ላይ በተወሰደው የናሙና ጥናት የተለያዩ ችግሮችን አግኝቷል።
በኮሚሽኑ የቡድን መሪ አቶ የኑስ ዓደም ጥናቱን መሠረት አድርገው እንደገለጹልን፣ ጥናቱ በምስል ተደግፎ የተከናወነ ሲሆን፣ እንደ ስልክና የመብራት ኃይል መሠረተ ልማት አገልግሎት ዝርጋታ ሲከናወን የተቆፈረውን ቦታ ወደነበረበት ሳይመልሱ ክፍቱን ይተዋል።
ባለሙያዎች ለጥገና በሚገቡበትና በሚወጡበት ሥፍራ ላይ ከ50 ሴንቲሜትር በላይ የሚሆን ኮንክሪት ሲሚንቶ በእግረኛ መንገድ ላይ መተው፣ ለመሠረተ ልማት የሚውል ገመድ የተጠቀለለበትን ትላልቅ ጣውላ ሥራውን ባከናወኑበት ቦታ ጥሎ መሄድ፣ የአስፓልት ዳርና ዳር መንገዶች ለንግድ አገልግሎት እየዋሉ መሆናቸው በጥናት ከተለዩት ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
በድንጋይ ንጣፍ የተሰሩት የውስጥ ለውስጥ መንገዶችም ሥራ ዕድል ተፈጥሮ በራስ ኃይል የሚከናወን መሆኑን ያስታወሱት አቶ የኑስ የተጠቃሚውን ምቾት የሚነሱ ከመሆናቸው በተጨማሪ ሲበላሹ በወቅቱ ጥገና እንደማይካሄድባቸው ጠቁመዋል።
እርሳቸው እንዳሉት የባለሙያዎች የዳሰሳ ጥናት ግኝት የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ብቻ እንዲያውቁት የተደረገ ሳይሆን፣ ባለድርሻ አካል የሆኑት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ኢትዮ ቴሌኮምና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እንዲያውቀትና የማሻሻያ እርምጃ እንዲወስዱ ተደርጓል።
የዳሰሳ ጥናት ግኝቱ በተወሰነ ደረጃ ውጤት እንዲገኝ ማስቻሉን የጠቀሱት አቶ የኑስ፣ ለአብነትም በፒያሳና ስድስት ኪሎ አካባቢዎች እንዲሁም የተሻለ ፕሮጀክት እንደሆነ የሚነገርለትና በሥራ ላይ ያለው ከአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት እስከ መስቀል አደባባይ ያለውን የእግረኛ መንገድ ሥራ ጠቅሰዋል።
እነዚህ ከነበረው ክፍተት አንፃር በጥሩ ማሳያነት ቢጠቀሱም ከዚህ በበለጠ በማከናወን መንገዶቹን ለታለመላቸው ዓላማ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።
እንደ አቶ የኑስ ኃላፊነቱ መንገዱን የሚሰራው አካል ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በእግረኛ መንገድ ላይ ንግድ ሲካሄድና ያልተገባ ነገር ሲፈጸም ተከታትሎ ችግሩን እንዲያስወግድ ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው ደንብ ማስከበር ተቋም አጥፊዎችን ለህግ እስከ ማቅረብ የደረሰ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተባብረው ችግሩን በጋራ ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ፕላንና ጥናት ኮሚሽን ችግሮችን በጥናት ለይቶ ከማሳወቅ ባለፈ የወሰደ እርምጃ ካለ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የአዲስ አበባ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን(ማስተር ፕላን)ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል በአዋጅ ቁጥር 52/2009ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ የማስፈፀሚያ ደንብ ረቂቅ አዘጋጅቶ ለማፀደቅ ለሚመለከተው አካል ሰጥቶ ምላሽ በመጠበቅ ላይ ይገኛል። የማስፈፀሚያ ረቂቁ ፀድቆ ሥራ ላይ ሲውል ህግ ለማስከበር ቀላል ይሆናል።
በአዋጁ ከተካተቱት ዋና ዋና ነጥቦችም የህንፃ ከፍታ፣ የመሬት አጠቃቀም፣ የአረንጓዴ ሥፍራዎች፣ የመንገድ መረብና መንገድ የሚያልፍባቸውን፣ የሚገነባው መንገድ ከመዋቅራዊ ፕላን ጋር የተጣጣመ መሆኑን፣ እንዲሁም ፕላን በማውጣት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ያወጣውን ፕላንንም በማየት ደረጃውን የጠበቀ መንገድ እንዲሰራ በማድረግ ኃላፊነቱን ይወጣል።
የግንባታ ህጉ ጥብቅ ነው። ዛሬ በግልጽ መኪና አፈር፣ ድንጋይ፣ ጠጠርና ሌሎችም ለግንባታ ግብአት የሚውሉ ቁሳቁሶችን በከባድ መኪና በማጓጓዝ መንገድ የሚያበላሹ አካላት ከህግ ውጪ ናቸው። በሸራ ሸፍነው ምንም አይነት መንጠባጠብ ሳይኖር ነው ቦታው ማድረስ ያለባቸው። በተግባር ግን እየሆነ አይደለም። ይሄን ሁሉም የሚታዘበው እንደሆነም አቶ የኑስ ይናገራሉ ።
በነዋሪዎችም ሆነ በጥናት ተለይቶ ክፍተቱን ባመላከተው አካል የቀረበውን ሀሳብ የሚጋሩት በፌዴራል ኮንስራትክሽን ሥራዎች ቁጥጥር ባለሥልጣን የትራንስፖርትና ኮሙዩኒኬሽን ግንባታ ሥራዎች የቁጥጥር ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግሥት ነጋ፤ እንዳስረዱት ተቋማቸው የተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት በፌዴራል ደረጃ የሚከናወኑ የሀገር አቋራጭ መንገዶችን መከታተልና መቆጣጠር ቢሆንም፣ በክልል ከተሞች በማዘጋጃ ቤቶች የሚከናወኑ የመንገድ ሥራዎች ላይ የሚስተዋለው ችግር በተመሳሳይ በፌዴራል መንግሥት በሚከናወነው ላይም ይስተዋላል።
አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ያደረገ የመንገድ ሥራ እንዲከናወን የመንገድ ህጉ ላይ ተቀምጧል። ይሁን እንጂ በአስፓልት ዳር ለተለያየ አገልግሎት የተቆፈሩ መንገዶች ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ማድረግ ላይ ችግር መኖሩን ባለሥልጣኑ ለይቷል። ከተለያዩ አካላት ጋርም የተናበበ ሥራ አይሰራም። መሠረተ ልማት የሚዘረጉ አካላት በየራሳቸው እቅድ መንቀሳቀሳቸው የመንገድ ልማት ሥራውን ጎድቶታል።
የባለሥልጣኑ ዋና ኃላፊነት ክፍተቶችን ለይቶ በጥናት ለሚመለከተው ባለድርሻ አካላት በማሳየት እንዲታረም ማድረግ ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ አሁን ባለው ሁኔታ ከእርምጃው በፊት ክፍተቶችን በማሳየትና ግብረ መልሶችን በመስጠት መፍትሄ እንዲያገኝ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
እስካሁን መንገዶችን ኦዲት በሚያደርግ አካል ሳይቀር የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች ቢሰሩም አመርቂ ውጤት አልተገኘም። ምንም እንኳን ሁሉም ድርሻ ያለው ቢሆንም በአብዛኛው ጉዳት እያደረሱ ያሉት መሠረተ ልማት የሚዘረጉ የመንግሥት ተቋማት ናቸው።
መንገድ ለተጠቃሚው ምቹ እንዲሆንና የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ መሰራት እንዳለበት ህጉ ይደነግጋል። ነገር ግን በህግ ታግዞ አሰራሩ መፍትሄ ካላመጣ የግንባታ ህጉም መፈተሸ ይኖርበታል። ምን አይነት ሥራዎች በሰሩ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል በሚለው ላይ ቅድሚያ ከተሰራ በኋላ ወደ ህጋዊ እርምጃ መሄዱም ሌላው አማራጭ በመሆኑ ሁሉንም ፈትሾ በህግ አሰራሩን ማስተካከል እንደሚገባ ያምናሉ።
በፌዴራል ደረጃ የተቀናጀ ሥራ የሚሰራ ተቋም መቋቋሙንና ይህ ተቋም የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ የተሰማሩ አካልት የዕቅድ ሥራዎቻቸውን ተናብበው እንዲሰሩ በማድረግ መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑንም አመልክተዋል። ተቋሙ ገና አዲስ ቢሆንም ወደፊት የተሻለ ውጤት ያስገኛል ብለው ያምናሉ።
ተቋማቸው በፌዴራል መንግሥት በከተሞች ከሚከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ 39 በሚሆኑት የመንገድ ዳር ላይ ለፍሳሽ ማስወገጃ የተሰሩት ክዳን የሌላቸው መሆናቸውን በዳሰሳ ጥናት መለየቱንና ለሚመለከተው አካል ግብረመልስ መስጠቱንና በቀጣይም ግብረመልሱን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች መሰራታቸውንና ለውጡ ላይ ባደረገው ክትትል የተወሰነ ለውጥ ቢገኝም ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ ክትትሉን እንደሚያጠናክር ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።
በክትትል ውጤት የታየባቸው የትኞቹ እንደሆኑም ዳይሬክተሯ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ አዋሽ መንገድን ለአብነት የጠቀሱ ሲሆን፣ በከተሞቹ ክፍት የነበሩ የፍሳሽ ማስወገጃዎች ክዳን ተሰርቶላቸው ተስተካክሏል።
ሀሳባቸውን ካካፈሉት መረዳት እንደተቻለው ክፍተቱ ሰፊ ነው። በእግረኛ መንገድ ላይ የሚታየው ችግር በህግ እየተፈታ አይደለም። አጥፊዎች ባለመጠየቃቸውና አስፈፃሚው አካል በመዳከሙ ህገወጥነቱ ህጋዊ ሆኖ እንዲቀጥል መንገድ ከፍቷል።
ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ምቾቱን ለሚነሳው የተበላሸ የመንገድ ሥራ ማንን መጠየቅ አለበት? መብቱን የሚጠይቅበት አሰራር ይኖር ይሆን? ለነዚህና ሌሎችም ጥያቄዎች የፖሊሰና ምጣኔ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኽተስፋ ምላሽ ሰጥተዋል። ችግሩን እርሳቸውም እንደ አንድ ነዋሪ ታዝበዋል።
ዋና የመንገድ ዳር አስፓልቶች ለመኪና ማቆሚያ አገልግሎት በመዋላቸው የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የመኪና መተላለፊያ ሆነዋል። እርሳቸው እንዳሉት አሁን ባለው ሁኔታ የክፍለ ከተሞችና የወረዳዎች የማስፈጸም አቅም አነስተኛ በመሆኑ ችግሮች እየተፈቱ ሳይሆን እየተባባሰና እግረኛውም እየተቸገረ ነው።
መንገዶቹም ተበላሽተው በክረምት ውሃ እያቆሩ በበጋውም ቢሆን ጉድጓዱ ለመኪና አስቸጋሪ ሆኖ የትራንስፖርት ፍሰቱን እያስተጓጎሉት ይገኛሉ። በቂ የሆነ የመኪና ማቆሚያ አለመሰራቱና የተሰሩትም ቢሆኑ ለተለያየ አገልግሎት መዋላቸው ችግሩን አባብሶታል።
በመሆኑም ህዝቡ የሚሳተፍበት የከተማ አስተዳደር መኖር አለበት፤ የሃይማኖት አባቶች፣ ከጤና፣ ከትምህርትና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡና የተካተቱበት አካላትም አብረው የሚሰሩበት ሁኔታ ቢፈጠር ችግሩ የሚያሰማው አካል ድምጽ ተሰሚነት ሊያገኝ ይችላል። ጫናው ሲበረታ ደግሞ አፋጣኝ ምላሽ ለማግኘት ይረዳል።
ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ተገቢውም አገልግሎት ባለማግኘቱ መብቱን እንደምን መጠየቅ ይችላል? ግብር የሚሰበሰበው የሀገር ደህንነትንም ለመጠበቅ ጭምርም በመሆኑ ግብር ባለመክፈል መብትን ማስጠበቅ አማራጭ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ግን ጫና በመፍጠር ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል።
እየተንከባለለ የመጣው በመንገድ ዘርፉ የሚታየው ችግርና የተነጠቀው የእግረኛ መንገድ እስኪመለስ ድረስ የአስፈጻሚው አካል ጠንካራ ክንድ እንደሚያስፈልግ ግን የሚካድ እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2013