ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀሳቤቅ አባት)
ያው እንደምታውቁት በማደግ ላይ ያለን ሀገር ነን፣ ብዙ ነገሯ ልክ ባልመጣ ሀገር ላይ ነን፣ የምናየው የምንሰማው ሁሉ የሚያስገርም የሚያስቆጣ ምድር ላይ ነን። በማደግ ላይ ያለች ሀገር… ሁሉ ነገሯ ልክ ያልመጣ ሀገር የህዝቦቿን መሰረታዊ ፍላጎት ታሟላለች ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። መንግስት የዜጎችን ፍላጎት በሙሉ ያሟላል ብሎ ማሰብም አይቻልም።
የሰው ልጅ የህልውና ጥያቄው እንዳለ ሆኖ ለመኖር አመቺ በሆነ አካባቢ ላይ የመኖር ተፈጥሮአዊ መብት አለው። መንግስትም የህዝቦቹን መሰረታዊ ፍላጎት ከማሟላት በዘለለ ለዜጎቹ ጥበቃና ከለላ የማድረግ ህገ መንግስታዊ ግዴታ አለበት። በዚህ በመኖርና ባለመኖር ቀጭን መስመር ላይ የህዝቦች የአስተሳሰብ ርዕዩት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ብዙ ሀገራት የቆሙት በህዝቦቻቸው አስተሳሰብ ተመስርተው ነው፡፡
በየትኛውም ነገር ላይ አስተሳሰብ ቀዳሚው ጉዳይ ነው። በአስተሳሰብ ያልሰለጠነ ማህበረሰብ ስልጣኔ የለም። የሀገር ድህነት ከግለሰብ ድህነት የሚመነጭ ነው። ሀገር የግለሰቦች ጥርቅም ናት። ሀገር የግለሰቦች የአስተሳሰብ ውጤት ናት። በአስተሳሰቡ የበረታ ሀገርና ህዝብ ድሀ ሆኖ አያውቅም። የየትኛውም ሀገርና ህዝብ ስልጣኔ ከአስተሳሰቡ የሚነሳ ነው። የሀገር ብልጽግና በህዝቦቿ አስተሳሰብ ልክ የሚመዘን ነው እያልኩ ነው።
ብዙዎቻችን ካለ ምንም ጥረት ተዐምር እንዲደረግልን የምንጠብቅ ነን። እጃችንን አጣጥፈን ተቀምጠን ስለ እድገት ስለ ብልጽግና የምንመኝ ነን። ከስራ ይልቅ ልመናን፣ ከትጋት ይልቅ ምኞትን ያስቀደምን ብዙዎች ነን።
በረቀቀ ሀሳብ እንጂ በመከነ ሀሳብ ታላቅነት የለም። የእስካሁኑ ውጣውረድና እንግልታችን ሁሉ ካለ ጥረት በመከነ ሀሳብ የፈጠርንው ስለሆነ ነው። የተለያየ አካባቢ ያየሁት ይሄንን ነው.. ስልጣኔ የህዝቦችን አስተሳሰብ መሰረት ያደረገ ነው። በስራና በትጋት የማያምን ጭንቅላት ለሀገር ሆነ ለወገን የሚጠቅመው አንዳች ነገር የለም።
ብዙዎቻችን ካለ ትጋት ብልጽግናን የምንናፍቅ ነን። ካለ ስራ ሀብትና ገንዘብ የምንመኝ ነን። ሳይሰሩ ተቀምጦ መብላት የሀገራችን ቁጥር አንድ የኋላ ቀርነት ምክንያት ነው እላለሁ። እዛም እዚህም የማይሰሩ እጆች በርክተዋል..ራዕይ የሚያደናቅፉ፣ ህልም አምካኞች ለሀገር ወገን ስጋት ሆነው በየቦታው አሉ። ልመናና ሌብነት፣ ዝርፊያና ነጠቃ በበዛባት ሀገር ላይ ሰርቶ መለወጥ እጅግ አዳጋች ነገር ነው።
ከሁሉም በፊት በአስተሳሰባችን ላይ ለውጥ ማምጣት አለብን። ከሁሉም በፊት የይቻላልን መንፈስ በውስጣችን ማስረጽ ይኖርብናል። ዓለም ላይ ያሉ ተአምራቶች ሁሉ በሚሰሩ እጆች..በሚያስቡ ጭንቅላቶች የተፈጠሩ ናቸው።
ሰውነት ታላቅነት ነው.. ታላቅነታችሁን አትገድቡት፣ ተአምር ልትፈጥሩ ወደዚህ አለም መጥታችኋል፤ ሀይላችሁን ወደ ተግባር በመለወጥ ለትውልድ የሚጠቅም ድንቅ ነገር ፍጠሩ እንጂ የበይ ተመልካች አትሁኑ። በዙሪያችሁ ያሉ ባለ ራዕዮችን ተመልከቱ፣ ከጨለምተኝነት ውጡ..እጆቻችሁን በስራ አፍታቱ። ከሚመሰገኑት ውስጥ እንጂ ከሚወቀሱት ውስጥ አትሁኑ።
አዲስ አበባ ላይ ብዙዎቻችንን ካስመረሩ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የዝርፊያ ጉዳይ ነው። ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ገብቶት የድርሻውን ሊወጣ ደፋ ቀና የሚል የመኖሩን ያክል በየጢሻው ተሰግስገው ህልም የሚያጨናግፉ ሞልተዋል። በየቦታው ራሳቸውን በቡድንና በተናጠል ለዝርፊያ አደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች በርክተዋል። ሳይሰሩ የሚበሉ እጆች ማለት እነዚህ ናቸው።
እነዚህ ግለሰቦች እስካልመከኑ ድረስ ለውጥ የለም። እነዚህ ግለሰቦች አመለካከታቸውን እስካልቀየሩ ድረስ እድገት የለም። እነዚህ ግለሰቦች ወደ ስራ ወደ ልማት እስካልገቡ ድረስ ከተማዋ ላይ በሰላም ወጥቶ መግባት አይቻልም። እስኪ አስቡት ላቡን ጠብ አድርጎ ሲሰራ የዋለ ሰው ማታ ወደ ቤቱ ሲገባ በወሮበላ ተደብደቦ ንብረቱ ሲነጠቅ።
እስኪ አስቡት ሀገር ሰላም ብሎ በተቀመጠበት ታክሲ ውስጥ ተሳፋሪ መስለው በገቡ ወንበዴዎች ሲዘረፍ? እስኪ አስቡት የታክሲ አገልግሎት እንሰጣለን በሚሉ የላዳ ታክሲዎች ዘረፋ ሲፈጸም? ሰሞኑን ሜክሲኮ ነበርኩ..አንዲት ሴት ከሰማያዊዋ ታክሲ ኋላ ወንበር ተቀምጣ ስልክ እያናገረች ትታየኛለች.. ከየት መጣ የማይባል አንድ ወጣት ስልኳን ከጆሮዋ ላይ መንጭቆት ሲሄድ የሆነችውን አረሳውም።
በብዙዎቻችን ላይ የደረሰ አሳዛኝ አጋጣሚ ነው። ቦርሳ እስከመቁረጥ የሚደርሱ ሌቦች እንዳሉ ታውቃላችሁ? አንዲት ወጣት ያጫወተችኝን ልንገራችሁ…ቦርሳዬን እንዳልሰረቅ ፈርቼ ከትከሻዬ በማውረድ አንገቴ ውስጥ አስገብቼ ታክሲ እጋፋለሁ..ወዲያው ግን ቦርሳዬን ከአንገቴ ላይ አጣሁት..ዞር ስል አንድ ወጣት ቦርሳዬን ይዞ ሲሮጥ አየሁት..ቀን ነው ምሳ ሰዓት ብዙ ሰዎች በዙሪያዬ ቢኖርም የተከተለው አንድም ሰው አልነበረም።
ውስጡ ብዙ ነገር ስለነበር በጣም ደንግጬ ነበር። የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሁፌን ላስገባ እየሄድኩ ነበር.. ከገዛሁት 2 ወር የማይሞላው ዘመናዊ ሞባይል ከስድስት ሺህ ብር ጋር አብሮ ቦርሳዬ ውስጥ ነበር..በጣም ደንግጬ ስለነበር መናገር ሁሉ አልቻልኩም። እዛው አካባቢ ያሉ ሰዎች በኮንትራት ታክሲ ቤቷ እንዳደረሷት ነግራኛለች። ህግ ባለበት ሀገር ለዛውም በቀን በጠራራ ሰው ንብረቱን ሲዘረፍ ከዚህ በላይ አሳዛኝ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
ይሄ ሁሉ የህይወት ፈተና ይዘን ነው ከህይወት ጋር የምንታገለው። ኑሮን ለማሸነፍ ቀን ከሌት የሚለፋ፣ ከራሱ አልፎ ቤተሰቡን ከፍ ሲልም ሀገሩን ለመጥቀም ወደዚያ ወደዚህ የሚል ሳይሰሩ የሚበሉ…ከሚሰሩ እጆች ላይ የሚቀሙ..ከጉሮሮ ላይ የሚመነትፉ እጆች በበዙበት ከተማ ላይ ወጥቶ መግባት አስፈሪ ከመሆኑም በላይ ለህይወት እጅግ አደገኛ ነው። መዲናዋ የወንበዴዎች ዋሻ እስክትመስል ድረስ በዚም በዛም ቀማኛዎች በርክተዋል።
እንዲህ አይነት አጸያፊ ተግባር ስራ ጠል ከሆነ የመከነ ጭንቅላት የሚመነጭ ነው። አብዛኛው ህዝቧ ወጣት በሆነባት ሀገር ላይ ስራ ፈጥሮ መስራት እንጂ እንዲህ ያለ ነውረኛ ተግባር ከወጣቱ የሚጠበቅ አይደለም። ሰሞኑን በአይነቱ ለይት ያለ የዘረፋ ዘዴ በሚዲያ አድምጫለሁ.. እንደ ሃይማኖት አባት ቆብና መስቀል በመያዝ ተሳፋሪ መስለው በመግባት መሀል መንገድ ላይ ወንጀል የሚፈጽሙ ወጣቶች መኖራቸውን ሰምቻለሁ።
ይሄ ብቻ አይደለም ያማረና የተስተካከለ ቁመና ይዘው በየመንገዱ ገንዘብ የሚጠይቁ ወጣቶች፣ ለአቅመ ልመና ያልደረሱ ጡት ያልጣሉ ህጻናት መንገደኛ እየተከተሉ ሳንቲም የሚጠይቁ በየቦታው አሉ። ስራ መስራት እየቻሉ ልመናን እንደገቢ ምንጭ የሚቆጥሩ፣ ወጣትነታቸውን ለበጎ ነገር ከመጠቀም ይልቅ ለዝርፊያና ለሌብነት ያዋሉ፣ ዝርፊያን እንደመተዳደሪያ የያዙ ሳይሰሩ የሚበሉ በርካታ ወጣቶች ሞልተዋል፡፡
በጣም ያስገረመኝን አንድ እውነት ልንገራችሁ.. ይሄን አጋጣሚ ዛሬ ብቻ አይደለም ሁሌም አወራዋለሁ.. አስራ አንደኛ መጽሐፌን እያከፋፈልኩ ሜክሲኮ አካባቢ ከሚገኝ አንድ መጽሐፍት መደብር በር ተቀምጫለሁ.. ከፊት ለፊቴ ከመኪና ላይ እቃ የሚያወርዱ ወጠምሻ ወጣቶች እየተሳሳቁ ይታዩኛል..ስልኬ ሲጮህ ላወራ ብዬ ከተቀመጥኩበትን ተነስቼ ወደ አንድ ጥግ አፈገፈግኩ።
አንድ ዘመነኛ ወጣት..የቁመቱንና የመልኩን ማማር አጠይቁኝ..ወሬው ንግግሩ ከተሜነቱን ያሳብቃል። የሆነ ጨርቅ ከኪሱ አወጣና አጠገቤ አንጥፎ ስለ ልደታ ማርያም ማለት ጀመረ። እየቀለደ ነበር የመሰለኝ..ግን የምሩን ነበር።
አጋጣሚ ሆኖ ቀኑ በርካታ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከቤተክርስቲያን የሚወጡበት ነበር። ያንን ምክንያት በማድረግ እየለመነ እንደሆነ ገባኝ። በጣም ተገርሜ አየሁት.. እሱ ግን ግርምቴን ከመጤፍ አልቆጠረውም.. እየተግባባን መጣን። ‹ግን እንዲህ ሙሉ ጤነኛ ሆነክ የሚሰጥክ ይኖራል? ስል የመጀመሪያ ጥያቄዬን ወረወርኩለት፡፡
‹በጣም ነው የሚሰጡት..ኢትዮጵያዊያን የአምላክን ስም ጠርተህባቸው ወደ ኋላ አይሉም፡፡› አለኝ፡፡
‹ሁሌ ትለምናለህ? ሁለተኛ ጥያቄዬን አስከተልኩ
‹አዎ..መላ ሳጣ (ብር ሳጣ ማለቱ ) ሁሌ እለምናለሁ› አለኝ።
እውነት ለመናገር ያ ቀን በጣም የተገረምኩበት ቀን ነበር። በውስጤ ተብሰለሰልኩ። ወጣት ጡረተኛ ማለት ይሄ ነው። ኢትዮጵያ አሁን ይሄን ይዛ ነው የምታድገው? በእንዲህ አይነት አስተሳሰብ፣ በእንዲህ አይነት ሞራል ከድህነት እንወጣ ይሆን? ይሄን የመሰለ አቅም፣ ይሄን የመሰለ ወጣትነት ይዞ ለልመና መቀመጡ አናደደኝ።
‹ተጫወት› የሚለው ድምጹ ከሀሳቤ እስኪፈነቅለኝ ጊዜ ድረስ ስለ እሱ እያሰብኩ ነበር። ግብዣውን ወደ ጎን ብዬ ትቼው ሄድኩኝ። ምን አይነት ትውልድ መጣ? ልመናና ሌብነትን እንደ ገቢ ምንጭ የሚያይ ወጣት፣ በጉብዝና ዘመኑ ሀሞቱ ፈሳሳ አብራክ..እያልኩ..ለዚች ሀገር ያገባኛል ባይ ተቆርቋሪ ማን ይሆን? እያልኩ..የሚሰሩ እጆች ወዴት ጠፉ እያልኩ ራሴ እየጠየኩ ራሴ እየመለስኩ ስቴዲየም ደረስኩ። እድሜ ለሜክሲኮ መቼም የማረሳውን ግርምት አስታቅፋ ወደ ቤቴ ላከችኝ።
መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላይ ያድርጉ እንጂ እንዲህ አይነት ወጣት ጡረተኞች በሀገሪቱ በተለያየ ቦታዎች ሞልተዋል። ለሀገር ሸክም የሆኑ፣ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያየለ ወጣቶች ለሀገር ወገን አስጨናቂዎች ሆነው በየቦታው አሉ። አስተሳሰባችንን መቀየር አለብን። ለራሳችንም ለሌሎችም ጠቃሚ ዜጎች እንሆን ዘንድ የሁሉ ነገር መሰረት የሆነውን ጭንቅላታችንን በአዎንታዊ አስተሳሰብ መሙላት ግድ ይለናል።
ያለዛ ሰው አንሆንም። ታላቅነታችን ያለው ታላቅ አስተሳሰባችን ውስጥ ነው። ህልማችን ስኬታችን ያለው እጃችን ውስጥ ነው። ነጋችንን ዛሬ ላይ እንስራ.. በጉብዝናችን ወራት ተአምር እንፍጠር..መስራት እየቻልን መለወጥ እየቻልን ተስፋ እንደሌለው አንሁን።
ዛሬ በሆነውና እየሆነው ባለነው የሚቆጩን ጊዜያቶች ይመጣሉ። እያንዳንዷን ቀን በውድ ዋጋ ማሳለፍ ይጠበቅብናል። መንግስትን መጠበቅ ሳይሆን ስራ ፈጥሮ በመስራት ከራስ አልፎ ለሌሎችም አስፈላጊ መሆን እንችላለን።
ብዙዎቻችንን ያስገረሙ አዲስና ዘመናዊ የሌብነት ዘዴዎች አሉ። በየቀኑ አስማት እስኪመስሉን ድረስ የምንደነቅባቸው የዘረፋ ስልቶች ሞልተዋል። ወጣቱ ይሄን እውቀቱንና ጥበቡን ለሀገር ብልጽግና ቢጠቀምበት እስካሁን ብዙ ለውጦችን እናስተናግድ ነበር። ለሌብነት የሚጠቀምበትን ዘዴ ሀገርና ህዝብ ሊለውጥ ለሚችል ፈጠራ ቢያውለው ተመስጋኝ ይሆን ነበር። ሩጫችን ሁሉ ልዕልናችንን ወደሚያጎድፍ ነገር ነው። ሁሉም ሰው በተሰማራበት የስራ መስክ ውጤታማ መሆን ቢችል እስካሁን ሀገራችን ላይ የተፈጠሩ መከራና ችግሮች አይኖሩም ነበር ባይ ነኝ።
ግማሹ ሲሰራ ግማሹ እየለመነ፣ አንዱ ሲሰራ አንዱ እየነጠቀ፣ አንዱ ሲገነባ ሌላው እያፈረሰ በሚኖርባት ሀገር ላይ ስልጣኔም ብልጽግናም የለም። ቀደም ሲል እንዳልኳችሁ ስልጣኔ አስተሳሰብ ነው..በአስተሳሰቡ ያልሰለጠነ ሀገርና ህዝብ በኑሮው ኋላ ቀር ነው። እንደዚሁም ደግሞ በአስተሳሰቡ የላቀ ማህበረሰብ ድሀ ሆኖ አያውቅም።
ስልጣኔያችን ጭንቅላታችን ውስጥ ነው ያለው..በአመለካከታችን የበረታን ጊዜ ያኔ ሁሉም መልካም ይሆናል ከሁሉም በፊት ግን በአስተሳሰባችን ስልጡን እንሁን እያልኩ ላብቃ። እንደተለመደው ስንብቴን በስንኝ ቋጠሮ አድርጌአለሁ፡፡
የማይሰሩ እጆች የማያስብ ራስ..
ምን ጥቅም የሌለው የእንግዴ ልጅ አራስ
የሀገር ባላደራ የህዝብ እንደራሴ
ባህር የሚያሻግር እንሁን እንደ ሙሴ፡፡
ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2013