ዕድገት ከአካባቢ ይጀምራል። በአካባቢ የሚገኝ ሀብት ደግሞ የዕድገት ሁሉ መሰረት ነው። ያላቸውን የተፈጥሮ ጸጋ የተረዱ፤ ተረድተውም ለመጠቀም የቆረጡ ሀገራት ዛሬ የዕድገት ማማን መቆናጠጥ ችለዋል።
ይህንኑ በመረዳትም የዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር ኢትዮጵያ ያላትን ሃብት ከግምት ውስጥ በማስገባት ዜጎች በሀገራቸው ሃብት ሰርተው እንዲበለጽጉ መጀመሪያ ገበታ ለሸገር ብለው ጀምረው አሳክተው አሳዩ።
ሲቀጥል ገበታ ለሀገር የሚሉ ፕሮጀክቶችን ይፋ አደረጉ። ገበታ ለሀገር በሚል የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ደግሞ የዶክተር አብይ መንግስት ይዟቸው ከመጣቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው።
በአዲስ አበባ የተጀመሩት የአንድነትና የእንጦጦ ፕሮጀክቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ተሰርተው ሲጠናቀቁ ብዙዎቻችንን አስደምመው ነበር። የአሰራር ዘመናዊነታቸው፤ ጥራታቸው፤ ውበታቸው፤ የአካባቢ ስነምህዳር አጠባበቃቸው፤ የአጨራረስ ፍጥነታቸው በሙሉ ኢትዮጵያውያን ቆርጠው ከተነሱ የማይሰሩት ሥራ እንደሌለ ያመላከቱ ነበሩ።
መዝናኛ ፓርኮቹንም የጎበኙ ሰዎች በተለያዩ አለማት ካዩዋቸው ተመሳሳይ ፓርኮች ቢበልጡ እንጂ አያንሱም ሲሉ መስክረዋል። እናም በእነዚህ ፕሮጀክቶች ባለፉት ዓመታት በተበደረች ልክ መልማት ያልቻለችውን ሀገር በራስ አቅም ማልማት እንደሚቻልም አይን የተከፈተበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በአስደማሚ ሁኔታ በጥራትም በፍጥነትም በገጸ በረከትነት ከቀረቡት ፕሮጀክቶች ውስጥ የእንጦጦ ፕሮጀክት ደግሞ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
የመንግሥትን በጀት ሳይጠይቅ በተባበረ ክንድ እውን የሆነው እንጦጦ ፕሮጀክት በቀጣይ ለሚሰሩ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችም ፋና ወጊ ከመሆኑም ባሻገር፤ በገበታ የሀገር ፕሮጀክት ለሚሰሩትም የጎርጎራ፤ የወንጪና የኮይሻ ፕሮጀክቶችም አዋላጅ ሆኗል። የዶክተር አብይ መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ሀገር በቀል ሀብቶችን በመጠቀም ወደ ብልጽግና ማማ መውጣት እንደሚቻልም የገበታ ለሸገር እና የገበታ የሀገር ፕሮጀክቶች ተጨባጭ ማሳያዎች ሆነዋል።
በአዲስ አበባ የተገነቡት የአንድነትና የእንጦጦ ፓርኮች ከመንግሥት ካዝና ሳይነካ በበጎ አድራጊዎችና በባለሃብቶች የጋራ ጥረት በትኩረት የተሰሩ ፕሮጀክቶች ናቸው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዕለት ተዕለት ክትትል ታክሎበት፤ የባለሙያዎች ልዩ ሀገራዊ ፈጠራዎች ተጨምሮበት፤ የባለሃብቶች ከስስት የጸዳ አስተሳሰብ ኖሮበት የሸገር ፕሮጀክት በአስደማሚ ሁኔታ ለህዝቡ በገጸ በረከትነት ሲቀርብ ሌሎች ፕሮጀክቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲተገበሩ የብዙዎቻችን ምኞት ነበር።
ምኞታችንም ዕውን ሆኖ በአሁኑ ወቅት የጎርጎራ፣ የወንጪና የኮይሻ ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ምዕራፍ ተሸጋግረዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው በኦሮሚያ፤ በደቡብና በአማራ ክልሎች የሚገነቡ ሲሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአሳተፈ መልኩ የሚገነቡና የሚያስተሳስሩ ፕሮጀክቶች ናቸው።
ቀደም ባሉት የሸገር ፕሮጀክቶች ህዝቡና ባለሃብቱም በመንግሥት ላይ በቂ እምነት ስለጨበጡም የገበታ ለሀገር ሶስት ፕሮጀክቶች ለመስራት የሚያስፈልገውን የመነሻ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ ከታቀደው በላይ 4ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለማዋጣት ተችሏል። እናም ህዝብ በመንግሥት ላይ እምነት ሲጥልም የሚቆጥበው ሃብት፤ የሚሰስተው እውቀት እንደማይኖር ለሶስቱ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ የተዋጣው ወጪ ምስክር ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተጋረጡባትን መሰናክሎች እያለፈች ዛሬ በአዲስ ጎዳና ላይ ትገኛለች። ከሁለት ዓመታት በፊት የሀገሪቱ ቀጣይነት አጠያያቂ በሆኑባቸው ጊዜያት ወደ ስልጣን የመጣው የዶክተር አብይ አስተዳደር ሀገሪቱ ካለችበት መንታ መንገድ በማውጣት ተስፋ በሰዎች ዘንድ እንዲዘራ አድርጓል።
ከለውጡ በፊት ብዙ የተባለለትና ከሊቅ እስከ ደቂቅ ዕውቀቱን እና ገንዘቡን አዋጥቶ ያስጀመረው የህዳሴ ግድብ ከነበረበት የመኮላሸት ደረጃ ወጥቶ ዛሬ ሁለቱ ተርባይኖች አገልግሎት ሊሰጡና ብርሃን ሊፈነጥቁ የወራት ዕድሜ ብቻ ቀርቷቸዋል። በግድቡ ዙሪያ የነበሩ አለመግባባቶችንም በሰለጠነ ዲፕሎማሲ በመምራት በተደረጉ ድርድሮችም የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር ተችሏል።
እነዚህ ሁሉ አይን ገብ ሥራዎች በሚሰሩበትና ከሀገር ውስጥ አልፎ የውጭ ሀገር ዜጎች እማኝ በሆኑበት ሁኔታ የመንግሥትን ተቀባይነት ለማሳጣትና በአቋራጭም የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት ሲሯሯጡ ይታያሉ።
ማጥፋት እንጂ ማልማት የማይችሉ አንዳንድ አካላት አጀንዳ እየፈጠሩ መንግሥት እየሄደበት ካለው የሽምጥ ጉዞ ለመግታትና ሀገሪቱን የብጥብጥና የሁከት አጀንዳ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።
የኢትዮጵያ ህዝብ ግን መሬት ላይ ያለውን እውነታ በአግባቡ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ለሁከት ለፋፊዎቹ ጆሮ ነፍጓቸዋል። ይባስ ብሎም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሰላማዊ ሰልፍ ለመንግሥት ያለውን አጋርነትና ድጋፍ አሳይቷል። በሌላም በኩል ሁከትና ብጥብጥ እንደሰለቸውና ጊዜ ያለፈበት ስልት መሆኑንም በግልጽ ቋንቋ ነግሯቸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ሁሉንም ለይቷል። በልማትና በጥፋት መካከል ያለውን ልዩነት ለመገንዘብ አይቸገርም። ስለዚህ የጥፋት ኃይሎች በብሄርና በሃይማኖት ሽፋን ህዝብን ከህዝብ ለማጫረስ እየሄዱበት ያለው መንገድ ጊዜ ያለፈበትና በዚህም ለውጥ እንደማይመጣ ሊገነዘቡ ይገባል።
ዛሬ ኢትዮጵያውያን ለሁከትና ለብጥብጥ የሚያውሉት ጊዜ የላቸውም። ትላንት የሸገር ፕሮጀክቶች ተጠናቀው የህዝብ ስሜት እንዳረኩት ሁሉ፤ የጎርጎራ ፤የወንጪና የኮይሻ ፕሮጀክቶች ማራኪ በሆነ መልኩ በፍጥነትም ፤በጥራትም ተሰርተው ለኢትዮጵያውያን በገጸ በረከትነት እንደሚቀርቡ በሁሉም ልብ ውስጥ እርግጠኝነት አለ።
ኢትዮጵያውያን ባለፉት 27 ዓመታት ሪባን ሳይሆን ተስፋ ሲቆርጡ ኖረዋል። ዛሬ ግን የሰለጠነው ዓለም ሁሉ በጥራታቸው፤ በውበታቸውና በግንባታ ፍጥነታቸው የሚማረክባቸውን የሸገር ፕሮጀክቶችን የመሳሰሉ ልማቶችን በመመረቅ ወደ ብልጽግና ግስጋሴ ጀምረዋል።
እንደ ገበታ ለሸገር ሁሉ በገበታ ለአገር ፕሮጀክቶቻችንም የኢትዮጵያዊነታችን ህብር መገለጫዎች አድርገን አሻራችንን እያሳረፍን በጊዜ ዑደት ከጨለማ ውስጥ ወጥተን የነገዋን ኢትዮጵያ አሻግረን ማየት ጀምረናልና፤ ‹ቦ ጊ ዜ ለኩሉ› ብለናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2013