ታምራት ተስፋዬ
ለመስኖና ለንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት በውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለቤትነት በመገጭ ወንዝ ላይ የሚገነባው የመገጭ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ጎንደር ዞን ይገኛል፡፡
ፕሮጀክቱ ከዋናው የግድብ ሥራ በተጨማሪ የውሀ መጥለፊያ /መቆጣጠሪያ/ ማማ፣ የግድብ ውሀ ማስተንፈሻ ፣ የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦ ሥራን ያጠቃልላል፡፡ግድቡ 77 ነጥብ አንድ ሜትር ከፍታና 890 ሜትር ደግሞ እርዝመት ሲኖረው 187 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም አለው፡፡ግድቡ ከሚይዘው ውሃ 30 በመቶው ለጎንደር ከተማ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት የሚውል ሲሆን 17ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 45ሺህ አባወራ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ይገመታል፡፡
በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሥራ ተቋራጭነት በ2006 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ግድቡ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከታቀደለት የመጠናቀቂያ ጊዜ ዘግይቷል።ፕሮጀክቱን በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ ቢገባም በግንባታ ሂደት ተጨማሪ ስራዎች በማጋጠማቸው ግንባታው ሰባት አመት አስቆጥሯል፡፡
ተቋራጩ በቂ ግብዓት ይዞ ወደስራ አለመግባቱ፣ በማሽነሪ እቃዎች ዋጋ መናርና፣ ለአርሶ አደሮች የሚከፈለው ካሳ አፈጻጸም መዘግየት ለግድቡ ግንባታ ሂደት መጓተት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ የግድቡ ግንባታ መዘግየት ብቻም ሳይሆን ተጨማሪ ወጪንም ጠይቋል፡፡አሁን ላይ ስድስት ቢሊየን ብር ደርሷል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብም ለከፍተኛ ምሬት መንግሥትንም ለተጨማሪ ወጪ የዳረገው ይሕ ፕሮጀክት፣ በአሁን ወቅት ካቀረቀረበት ቀና ያለ ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል በግንባታ ምዕራፉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሩን ለመፍታትም የአካባቢው አስተዳደር እና የፌደራል መንግስት በሰጡት ትኩረት የመፍትሄ እርምጃዎች ተወስደው ግንባታው አሁን ላይ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ስድስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የተመደበለትን የግድብ ግንባታ እንቅስቃሴም በፌደራል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር እና የኮርፖሬሽኑ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ እና ሌሎች አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ተጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ኢንጂነር አይሻ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉት ፕሮጀክቶች መካከል መንግስት ከህዳሴ ግድብ እና ከኮይሻ ፕሮጀክቶች በመቀጠል የመገጭ ግድብ ሥራ ፕሮጀክትን በሶስተኛ ደረጃ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተለው ፕሮጀክት እንደሆነም ጠቁመው፣ግድብ በዚህ አመት መጨረሻ የመጀመሪያ ዙር ውኃ ለመያዝ በሚያስችል ሁኔታ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡፡
ኮርፖሬሽኑ የሪፎርም ሥራ ከጀመረ በኋላ ከፍተኛ ለውጥ ካመጡት የኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቶች መካከል የመገጭ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ የስራ ፍጥነቱ ከቀጠለ በያዝነው ዓመት መጨረሻ ላይ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት ሥራ ማከናወን እንደሚቻል ጠቁመው፣ሆኖም ግን ይህን ስራ የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስፈልጉ የግንባታ ግብዓቶችን በማሟላት በሳምንት ሰባት ቀን እና በየቀኑ 24 ሰዓት በአግባቡ መስራት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
እንደ መረጃው ከሆነም የግንባታው ሂደት ሳይስተጓጎል በተጀመረው ፍጥነት እንዲጓዝም እንደ ሲሚንቶና ብረት ያሉ ግብዓቶችን እጥረት በመፍታት በኩል ቦርዱ በቅርብ እየተከታተለ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል ።
የወሰን ማስከበር ስራዎች በተሻለ ፍጥነት እየተጠናቀቀ ስራውን የማሳለጡ ተግባር መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።ፕሮጀክቱ ምንም እንኳ በተሻለ አፈፃፀም ላይ ቢገኝም በቀጣይ ይበልጥ እንዲራመድ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመው፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደርም እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
በዚህ ወቅትም የመገጭ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፀጋዬ መኮንን፣ባለፉት ዓመታት የግንባታ ግብዓት የሚመረትበትን ቦታ ከካሳ ክፍያ በወቅቱ ነፃ ባለማድረጉ፣ በግድቡ የግንባታ ስራ ላይ የዲዛይን ለውጥ መደረጋቸው፣ በተደጋጋሚ ሲከሰቱ የነበሩት የሲሚንቶ፣ የብረት፣ የነዳጅ፣ ኮንስትራክሽን መሳሪያዎች እና የሌሎች የግንባታ ግብዓቶች እና ባለሙያዎች እጥረት፣ የግድብ ደህንነት ማስጠበቂያ መሳሪያዎች ግዢ ለፕሮጀክቱ መዘግየት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአሰራር ስርዓት ለውጥ በማድረግ በመሰራቱ፣ የተለያዩ የግድቡ ስራዎችን ከ11 በላይ ንዑስ ተቋራጮችን በማስገባትና ከፋፍሎ ማሰራት በመቻሉ እንዲሁም በየቀኑ በሁለት ፈረቃ ለ24 ሰዓት መስራት በመጀመሩ የፕሮጀክቱ ሥራ እየተፋጠነ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የግድቡ ግንባታ 69 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ለፕሮጀክቱ መጓተት ትልቅ ችግር የነበረው ተቋራጭ ይሰራ የነበረው የግድቡ የውኃ መቆጣጠሪያ ማማ ግንባታ ስራ እንደነበር የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ በአሁኑ ወቅት የውኃ መቆጣጠሪያ ማማ ግንባታ ስራው በኮርፖሬሽኑ እየተሰራ በመሆኑ ችግሩ መቃለሉን ይናገራሉ።
ሆኖም ግን ከውኃ መቆጣጠሪያ ማማ ግንባታ ስራዎች የኤሌክትሮሜካኒካል ስራው ብቃቱ ባላቸው ንዑስ ተቋራጮች እንዲሰራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ እንዲሁም ሌሎች ለግድብ ደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች በፍጥነት ተገዝተው መቅረብ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ ሥራ አማካሪ የሆነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን እና ቁጥጥር ሥራዎች ኮርፖሬሽን የመገጭ ግድብ ተጠሪ መሐንዲስ አቶ ይርጋ አበባዬ በበኩላቸው፤ ይህ ፕሮጀክት በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚገነቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት በጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ንዑስ ተቋራጮችን ወደ መገጭ ግድብ ፕሮጀክት በማስገባት በተለያዩ የፕሮጀክቱ ስራዎች እንዲሳተፉ ማድረግ መቻሉ ኮንትራክተሩ የነበረበትን እጥረቶች በማሟላት አቅሙን እንዳሳደጉለት፣ የፕሮጀክቱን ግንባታ ስራም እስካሁን ድረስ ከነበረው የአሰራር ፍጥነትና ብቃት በተለየ ሁኔታ አፈፃፀሙን እንዳሳደጉት አብራርተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ስራ እየተፋጠነ ቢሆንም የውኃ መቆጣጠሪያ ማማ ግንባታ እና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች መዘግየት፣ የግድብ ደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች በፍጥነት እየቀረቡ አለመሆናቸው እንዲሁም የግንባታ መሳሪያዎችና ሌሎች ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ አለመሟላታቸው በግንባታ ሒደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው፣የመገጭ ግድብ ለጎንደር ከተማ እና አካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ እንዲሁም የግድቡ 30 በመቶ ውኃ ለመጠጥ ውኃ አገልግሎት በማዋል የረዥም ጊዜ የጎንደር ከተማን የንፁህ መጠጥ ውኃ ፍላጎት የሚመልስ በመሆኑ የከተማው መስተዳድር በትኩረት እየተከታተለው መሆኑን ነው የተናገሩት ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2013