አስመረት ብስራት
አስቸጋሪ ልጅ የለም፤ የተቸገረ ልጅ እንጂ የሚለው ግንዛቤ ውስጣችን እስካልገባ ድረስ የሚማቱ፣ የሚጮሁ፣ እቃ የሚሰብሩ ልጆችን መርዳት እንችልም። ለዚህም ነው በዚህ መነሻ ልጆችን መርዳት የሚገባን መሆኑን ለማመልከት የተነሳነው።
እንደዚህ ዓይነት ልጆችን ከመርዳታችን በፊት አመለካከታችን «አስቸጋሪ ልጅ የለም የተቸገረ ልጅ ግን አለ» በሚል ግንዛቤ መዋጥ አለበት። ያኔ ነው የልጆችን ጭንቀት በተገቢው ልክ መረዳት የምንችለው።
በመጀመሪያ አስቸጋሪ ወይም ረባሽ ወይም ከይሲ የሚለውን ታርጋ ከልጆች ላይ እናንሳ! ልጆቹ ማንንም ለማናደድ ብለው ምንም ስለማያደርጉ እንደዚህ ዓይነት ስያሜዎች አይገባቸውም።
ቀጥሎ ምንድን ነው የተቸገረው? ምንድን ነው የሚሰማው? ከባህሪው ጀርባ ያለውን ችግሮች በማግኘት ወደ መፍትሄ እንድንሄድ ይረዳናል። መፍትሄው ቀላልም ከባድም ሊሆን ይችላል። ከባድ የሚሆነው ማናችንም ተምረን ተመርቀን አይደለም ወላጅ የሆንነው ሲቀጥል ድርጊቱ ሲከስት የወላጅም ስሜት እኩል ስለሚፈተን እና ግራ ስለሚያጋባ ነው።
ለምሳሌ ለሌላ ሰው ትንሽ የሚመስል ነገር እንደዚህ የተቸገሩ ልጆች ትልቅ እሳት ውስጣቸው ይጭርና ድንገት እንደመብረቅ የሆነ ነገር ሊያደርጉ ስለሚችሉ ወደ መጥፎ ተግባር ይገባሉ። ይህ በሆነ ሰዓት ወላጅም እኩል ከቁጥጥር ውጪ ይሆናል። ቀላል የሚሆነው ደግሞ መፍትሄው ቀላል ስለሆነ ነው!
ቢቻል ዝም ብሎ ማረጋጋት ምክንያቱም «ብልጭ» ባለባቸው ሰዓት ምንም መልስ ወይም ጩኸት ስለማይሰሙ ነገሩን ያባብሰዋል፣ በሌላ ቋንቋ «አእምሯቸው» ይቆለፋል።
ወላጅ መጀመሪያ እራሱን አረጋግቶ አጠገባቸው መሆን፣ ሁኔታውም እሚፈቅድ ከሆነ አቅፎ ወይም ይዞ ማረጋጋት። በአንዳንድ ትምህርት ቤት እና በመዋእለ ሕፃናት የማረጋጊያ ክፍል ተዘጋጅቶ እንደ ልጆቹ ፍላጎት፣ ለሰለስ ያለ ሙዚቃ፣ ዳንስ፣ ሻማ፣ ፊኛ ወይም የቦክስ ዕቃ ይቀመጥላቸዋል። ለየት ያለ ክፍል በመውሰድ ያረጓጓቸዋል። «አእምሯቸው ስለሚቆለፍ» የስሜት ህዋሳታቸውን በደንብ በሌላ በመጠቀም አቅጣጫን ማስቀየር አንዱ ዘዴ ነው።
ብዙውን ጊዜ ሆደ ባሻነት (የተሰበረ ልብ / የውስጥ ስብራት) ስለሚኖራችው ብዙ ፍቅር እና ጤናማ እንክብካቤ ፍቱህ መድኃኒት ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2013