በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
ከሀዲው ትህነግ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ትውልድም ሀገርም የማይረሳውና ይቅር የማይለው ዘግናኝ ጥቃት በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ሲፈጸም ሀገር ተገዳ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጫና ሕልውናን የማስቀጠል ዘመቻ ውስጥ ገባች ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በሰጡት ብልህ አመራር ፤ በጀግናው ሰራዊት ተጋድሎና በመላው ኢትዮጵያውያን ደጀንነት በ15 ቀን ለዛውም ሁለቱ የተኩስ አቁሞች ሲቀነሱ በዘጠኝ ቀን ጦርነት ከ200ሺህ በላይ የሆነውን ሚሊሻ ፣ ልዩ ኃይልና ከዳተኛ የቀድሞ የመከላከያ አባል ደምስሶና በትኖ ሕዳር 19 ቀን 2013 ዓም መቐሌን ተቆጣጠረ ።
ትህነግ ከጸሐይ በታች የሚገዳደረኝ ኃይል የለም ፤ መቀሌና ትግራይ የጠላቶቿ መቀበሪያ ትሆናለች እያለ በእብሪት ሲሸልልና ሲፎክር ከርሞ እግሬ አውጭኝ ብሎ ፈረጠጠ ። ያልቻለው በወሳንሳና በቃሬዛ ሆኖ ዋሻ ገባ ። ሽንፈት ፣ ውርደትና እውነት በቃኝ ብሎ “መነነ”። የትህነግ የውንብድና ፣ የሽፍትነት ፣ የመንግሥትነትና የክልል አስተዳዳሪነት ታሪክ በአሳፋሪ ሁኔታ ተደመደመ ።
ተቋጨ ። ደማሙ ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ “ኦሮማይ” እንዲል ። የጨለማው መጋረጃ ትህነግ ተቀዶ አዲስ ጎህ ቀደደ ። ተስፋ ለመለመ ። ስለሆነም ዛሬ የምስረታውን 46ኛ ወይም አገዛዝ ላይ የቆየባቸውን 30ኛ ዓመት በሀገርና በሕዝብ ላይ የፈጸመውን ህልቆ መሳፍርት የሌለውን ግፍ እያስታወስን በመብሰክሰክ መቆዘምን ሳይሆን ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እኩይ አሻራውን /legacy /ለማንሳት ፣ ሰንበሩን ለማሻርና ቁስሉን ለማጠገግ ያለ ልዩነት እጅ ለእጅ ተያይዘን ለመስራት ተማምለንና ቃል ኪዳን ገብተን ሙት ዓመቱን እንድናስታውሰው መረጥሁ ።
ስለዚህ ከየካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሀገርም ሆነ በክልል ገዥነት የቆየባቸውን 30 የድቅድቅ ጨለማ ዓመታት እና ትቷቸው የሄዳቸውን አሻራዎች ባነሳንና ባጸዳን ቁጥር የኋልዮሽ እያሰላን ወይም የቀረንን እየቀነስን እንሄዳለን ።
በዚህ መሠረት ዘንድሮ ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ ከወደቀ በኋላ “የሚታወሰው “ የመጀመሪያ የካቲት 11 የሀገርና የሕዝብ ምርኮ መመለስ አሀዱ የተባለበትና ሰንኮፉ ጥላቻ መነቀል የተጀመረበት ስለሆነ ከ30 አንድ ቀንሰን የቀረንን ስንቆጥር 29 ይሆናል ።
የትህነጋውያንና ስብሀታውያን ርዝራዦች ግን በተቃራኒው የምስረታውን 46ኛ ዓመት በዋሻቸውና በተሰደዱበት በፈጠራ ትርክትና በማይጨበጥ ገድል ያከብሩታል። እኛም አሻራውን አንድ በአንድ እያራገፍን ታላቋን ኢትዮጵያን እየተመለከትን በተስፋ እናከብረዋለን። የነገዋን ኢትዮጵያ እያሰብን አሻራውን እናነሳለን። እኩይ አሻራው ተለቃቅሞ የሚያበቃበትን ቀን በጉጉትና በናፍቆት እንጠብቃለን ።
የቀረንን ቆጠራው የእፉኝቱን ትህነግ እኩይ አሻራ የማንሳትና የማጥፋት ተምሳሌትና ወካይ ነው ። እኔ ቆጠራውን በዓመት አድርጌዋለሁ ። ለ30 ዓመታት ያህል መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ የተሰራበትን የኢ-ዴሞክራሲያዊነት፣ ኢ-ፍትሀዊነት፣ አምባገነናዊነት፣ አሻጥረኝነት፣ ሸፍጠኝነት ፣ ጥላቻ ፣ ልዩነት ፣ ዘረኝነት ፣ ጎሰኝነት ፣ ጨለምተኝነት ፣ አክራሪነት ፣ ጽንፈኝነት ፣ በቀለኛነት ፣ ቂመኝነት ፣ መጠላለፍ ፣ መጠፋፋት ፣ ምቀኝነት ፣ ሙሰኝነት ፣ ሴራ ፣ ሟርት ፣ ውሸት ፣ የፈጠራ ትርክት ፣ ፖለቲካዊ ነውረኝነት ፣ በአቋራጭ መበልጸግ ፣ ስርቆት ፣ ግለኝነት ፣ መንጋነት፣ ተረኝነትና አድመኝነት በአጠቃላይ እነዚህን 30 እኩይ አሻራዎች ሳይታክቱ አንድ በአንድ በማንሳት የቀረንን ቆጠራ ማሳካት ።
በሌላ አነጋገር ዜሮ ማድረስ። በግሌ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የትህነግን ማንነት በማጋለጥና አሻራዎቹን ለማስወገድ የሚያግዙ በሺዎቹ የሚቆጠሩ መልዕክቶችን ለማጋራት ጥረት አድርጌያለሁ ። ቅድመም ሆነ ድህረ ለውጥ እንደ ሪፖርተር ላሉ ጋዜጦች ጥቆማ በመስጠት በመጻፍ አቅሜ የፈቀደውን ጥሬያለሁ ። ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ደግሞ በተለይ ለዚሁ ጋዜጣ ስለ ትህነግ እኩይ ማንነትና አሻራውን ስለማስወገድ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጣጥፎችን አስነብቤያለሁ ።
ከጥቅምት 24 ወዲህ እንኳን ደርዘን ያህል ትህነግን ብቻ የተመለከቱ መጣጥፎችን ጫጭሬያለሁ ። አገዛዝ ላይ በነበረበት ዓመታትም በየመድረኩ በድፍረት ማንነቱን አጋልጫለሁ ። የተሳሳተ መንገዱን ሞግቻለሁ ። ከዩኒቨርሲቲ እንደ ወጣሁ ስራ በጀመርሁበት በዋግ ኽምራ ዞን ሰቆጣ በ1989/90 ዓ.ም የዞኑ ሰራተኞች ለ”ሰማዕታት” ሀውልት ማሰሪያ የወር ደመወዛቸውን ለመስጠት በፖለቲካዊ ግፊት ሲስማሙ ብቻየን በልዩነት በመውጣት ከደመወዜ ላይ አስር ሳንቲም ብትቀነስ ፍርድ ቤት እሔዳለሁ ብዬ ለማላምንበትና ለማልጋራው ዓላማ ለተከፈለ ዋጋ እውቅና አልሰጥም በሚል ተከራክሬያለሁ።
ያ ሐውልት ባለፈው ባህርዳር ላይ ሲፈርስ ስመለከት ለራሴ “አይ መሰንበት ደጉ፤”እያልሁ ነበር ። እውነት ለመናገር ዛሬ ላይ ስንት ወጣቶች በፈጠራ የማታገያ ፕሮፖጋንዳ ተታለው ዋጋ እንደከፈሉ ላስተዋለ እንደ እግር እሳት በጸጸት ይለበልባል። የቀረንን ቆጠራ አበክሬ የጀመርሁት ቢሆንም በትህነግ መቃብር ላይ ግን አብረን እንደገና አሀዱ እንደምንል ለማስታወስ ነው ። የትህነግን እኩይ አሻራ ማንሳት ገና ብዙ ስራ ይጠይቃልና።
የቀረንን ቆጠራ ከትህነግ ጭፍራዎች በተቃራኒ አቅጣጫ ጉዞ ለመጀመራችን ተጨማሪ ተምሳሌት ነው ። እነሱ በእኩይ አሻራዎች ላይ ተጨማሪ የጥፋት አሻራ እያኖሩ እየደረቱ ነው ። ከአፈርሁ አይመልሰኝ ብለዋል ።
በአውሮፓና በአሜሪካ ከሀገር በተዘረፈ ሀብት እየተንደላቀቁ የትግራይን ሕዝብ ለ3ኛ ዙር ጦርነት እየቀሰቀሱት ነው ። ለትግራይ ሕዝብ የተሰበሰበን እርዳታ ለጦርነት ለማዋል እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ መረጃ እየወጣ ነው ። ዘመኑንም ትውልዱን በማይመጥን ስራ ተጠምደዋል ።
ትህነግ ላለፉት 46 ዓመታት ይከተለው በነበረ የተሳሳተ ርዕዮተ ዓለምና ፖሊሲ እንዲሁም የገነገነ ዘረፋ የተነሳ ከተረጅነት መላቀቅ ባለመቻሉ የሕግ የበላይነትን በማስከበርና በህልውና ዘመቻ በተፈጠረ ክፍተት ሚሊዮኖች ተርበዋል ። ትህነግ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በስሙ መነገዱ ሳያንስ ዛሬም የቡድኑ ጭፍራ ዲያስፖራ በስሙ እየነገዱበት ነው። በስሙ እርዳታ እያሰባሰቡ በረሀቡና በእርዛቱ እየሸቀጡ ነው ።
ትህነግ ሕዝቡን በድህነት ቀይዶ ለመግዛት እንዲመቸው ከድህነት እንዳይወጣ ሌት ተቀን ሲያሻጥር ኖሯል ። ከዚህ ባርነት ነጻ ከወጣ በኋላም መልሰው የጭቆና ቀንበር ሊጭኑበት አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆነው ብቅ ብለዋል ። ለዚህ አኩይ አላማዎች ደግሞ በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያ የሀገሪቱን ስም እያጠለሹ እና ሕዝብን በፈጠራና በሀሰተኛ መረጃ ውዥንብር ውስጥ ለመክተት እየባዘኑ ከመሆኑ ባሻገር ከታሪካዊ ጠላቶቻችን እና ከውስጥ ተላላኪዎች ጋር ግንባር በመፍጠር ሀገሪቱን ለማተራመስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ። የሀገራችንና የለውጥ ኃይሉን ገጽታ እያጠለሹት ነው ።
በዚህም በተወሰነ ደረጃ ምዕራባውያንና አለማቀፍ ማህበረሰቡን ማደናገር ችለዋል ። የሚያሳዝነው ይህ እንደሚሆን አውቅ ስለነበር መቐሌ ነጻ እንደወጣች ቀጣዩ ስራ የብዙኃን መገናኛ እና የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ እንዲቀጥል በዚሁ ጋዜጣ አሳስቤ ነበር ።
መንግስት ጥቆማውን ወስዶ በአግባቡ ባለመስራቱ በትህነግ የተቀነባበረ የሀሰተኛ መረጃ ዘመቻ ስማችን በክፉ እንዲነሳ ሆኗል ። በክህደት ላይ ክህደትን ፣ በሽብር ላይ ሽብርን ፣ በወንጀል ላይ ወንጀልን መደራረቡን ሙያ አድርገውታል። ጨለማን በጨለማ ፣ ጥላቻን በጥላቻ ለማሸነፍ ስሁት መንገዳቸውን ገፍተውበታል።
እኛ ጨለማን በብርሀን፣ ጥላቻን በፍቅር ለመርታት የትህነግን አሻራዎች እንደ ፈጣን ሎተሪ መፋቅ ፣ ማንሳትና መጥረግ ጀምረናል። እኛ ኢትዮጵያውያን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ነገዋ የተስፋ ምድር ኢትዮጵያ ለመድረስ በጉጉትና በናፍቆት የቀረንን ቆጠራ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንጀምራለን። እያንዳንዱ ቆጠራ አንድ የትህነግን እኩይ አሻራ ማንሳትን ይወክላልና ከፍ ብዬ በሁለተኛው አንቀጽ ላይ ከዘረዘርኋቸው 30 እኩይ አሻራዎች የየድርሻችንን በማንሳት የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን ።
ከፍ ብሎ መፋቅ አለባቸው ብዬ ከዘረዘርኋቸው እኩይ አሻራዎች ዋና ዋናዎቹ 1 .ጥላቻ 2 .የፈጠራ ትርክት 3. ሴራ 4 . ልዩነት 5.ኢ-ዴሞክራሲያዊነት 6 .ኢ-ፍትሀዊነት 7 .አምባገነናዊነት ናቸው ። የእነ ዚህ ሁሉ መሠረት ፣ ዋልታና ማጠንጠኛ ነው ብዬ የማምነውን ጥላቻን አጠር አድርገን እንመልከት።
ጥላቻ ፦ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው ትህነግ ከምስረ ታው ጀምሮ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ጥላቻን የመታገያ ስትራቴጂክ ስልቱ አድርጎ ቀን ከሌት ሰርቷል ። ሳሙኤል ሀንቲገን ፣”THE CLASH OF CIVILIZATIONS AND THE REMAKING OF WORLD ORDER “ ማለፊያ መጽሐፉ ፤”የራስህን ማንነት ለመውደድ የሌላውን ማንነት አንቅረህ መትፋት መጥላት አለብህ ፤” እንዳለው ትህነግ ራሱን ከወርቅ ሕዝብ የተፈጠርሁ እያለ ሌላን ማንነት ግን ሲያንቋሽሽና ሲያናንቅ ከመኖሩ በሻገር በፈጠራ ትርክት ጥላቻን በሜካናይዝድ እርሻ ሲዘራ ኖሯል ።
በ1968 ዓም ይፋ ባደረገው ከካርል ማርክስ በተኮረጀ ማኒፌስቶው የለወጠው ነገር ጠላትን መፈረጅ ላይ ነው ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና አማራ የትግራይ ሕዝብ ጠላቶች ናቸው በሚል የተሳሳተ ትንታኔና መደምደሚያ ላይ የቆመው ርዕዮት አለም ትግራዋይ በእነዚህ ማህበረሰቦች ላይ ብዥታ በተወሰነ ደረጃም የመረረ ጥላቻ እንዲኖራቸው አድርጓል ።
የትህነግ ቡድን ስልጣን ላይ ከተቆናጠጠ በኋላ ደግሞ መዋቅራዊና ተቋማዊ አድርጎ ከመስራቱ ባሻገር በኢትዮጵያውያን መካከል በነዛው የፈጠራ ትርክት የተነሳ በመሀላቸው ጥላቻና መጠራጠር እንዲፈጠር አድርጓል ። እንደ ቅኝ ገዥ ከፋፍሎ ለመግዛት ሲል ሕዝብን እሳትና ጭድ ብሎ በመከፋፈል በአንድነት እንዳይቆሙ ከማድረጉ ባሻገር ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ እንዲፈጸም አሲሯል ።
ባለፉት 30 አመታት በአማራ ሕዝብና በቤተ ክርስቲያኗ የተፈጸሙ ግፎች ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው ። ኦሮሞ አማራን ፣ አማራ ኦሮሞን ፣ ትግራዋይ አማራን ፣ አማራ ትግራዋይን ፣ ጉሙዝ አማራን ፣ ሲዳማ ወላይታን ፣ ወላይታ ሲዳማን ፣ ጉጂ ጌዲዎን ፣ ጌዲዎ ጉጂን ፣ ኦሮሞ ሱማሌን ፣ ሱማሌ ኦሮሞን ፣ ወዘተረፈ በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲያይ አድርጓል ። በዚህም ጥላቻ ነግሷል ። ልዩነት ሰፍቷል ።
አንድነት እርቋል ። የቀውሶቻችን መፈልፈያም ይኸው የሰየጠነ ስብከት ነው ። የጭፍጨፋ ፣ የጥላቻ ፣ የማፈናቀል ፣ የመንጋ ጥቃት ፣ ወዘተረፈ መነሻ ለዓመታት ሲሰበክ የኖረው ጥላቻ ነው ። ጨለማ በጨለማ ሳይሆን በብርሀን እንደሚሸነፈው ሁሉ ጥላቻም በሌላ ጥላቻ አይረታምና በፍቅር ልናንበረክከው ይገባል ። ከዚህ በኋላ እዳው ገብስ ነው ። የጥላቻን አሻራ ስላነሳነው ሌሎች እኩይ አሻራዎችን ለማስወገድ ቀላል ይሆናል ። ጥላቻን በፍቅር እንሻገር።
እንደ መውጫ የቀረንን መቁጠር በአንድ በኩል የጓጓንለትን ሁነት እስኪ ደርስ መናፈቅን ሲያመለክት፤ በሌላ በኩል አንድ ነገር ሊጀመር ወይም ሊጠናቀቅ የቀረውን ዓመት ፣ ወር ፣ ሳምንት ፣ ቀን እየተከታተለ በማሳወቅ ለድርጊት ለውሳኔ የሚያነቃና የሚያነሳሳ ስልት ነው ። ኢትዮጵያውያንን በፍቅርና በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንደ ማየት የሚናፍቅና የሚያጓጓ ምን አለ ።
ፍቅርን ለመገላገል ደግሞ በጥላቻ ምትክ ፍቅርን መጸነስ ይጠይቃል ። ፍቅርን ለመጸነስ ደግሞ የጥላቻን እኩይ አሻራ ማንሳት ይቀድማል ። የተዘራብንን የጥላቻ ሰንኮፍ መንቀል ይጠበቅብናል ። የሀገራችን ሁሉም ቀውሶች የሚቀፈቀፉት በጥላቻ እቅፍ በሚያገኙት ሙቀት ነው ። ልዩነት ፣ በጥርጣሬ መተያየት ፣ የፈጠራ ትርክት ፣ የሴራ ፖለቲካ ፣ የውሸት ናዳ ፣ ማንነትን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ፣ ማፈናቀሎች ፣ ማንነትን ለይቶ ሀብት ማውደም ፣ የመንጋ ፍርድ ፣ የቀውስ ፣ የግጭት ፣ ወዘተረፈ እንቁላሎች የሚፈለፈሉት በጥላቻ ክንፍና እግር መሀል በሚያገኙት ምቹ ሙቀት ነው ።
ስለሆነም ከትህነግ አሻራዎች አንዱንና ዋናውን ጥላቻን በማንሳት የቀረውን አሀዱ ብለን መቁጠር ስንጀምር የቀረን 29 ይሆናል ። የኋልዮሽ እየቆጠርን ዜሮ ላይ ለመድረስ የትህነግን እኩይ አሻራዎች ሙሉ በሙሉ አንስቶ ለመጨረስ ቀጣይነት ያለው የተቀናጀ ርብርብ የሚጠይቅ ከባድ ስራ ከፊታችን ይጠብቀናል ።
ፍቅር ያሸንፋል !!!
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2013