ውብሸት ሰንደቁ
ጣና ፋይበር ግላስ ማኑፋክቸሪንግ የአበባ ማስቀመጫዎችን በተለያየ መልኩ የሚያዘጋጅ አምራች ድርጅት ነው ።የምርት ግብዓቶቹ ከውጭ መጥተው እዚሁ በሀገር ልጅ ዲዛይን ተደርገው የሚሠሩ ዘመን ዘለቅና ዓይነ ግቡ ምርቶች ናቸው ።በእርግጥ ምርቶቹ ውድና የቅንጦት ዕቃዎች የሚመስሉ ናቸው ።
እነዚህ ምርቶች ጣና ፋይበር ግላስ ማምረቻ ውስጥ ሲመረቱ ሀገር ሀገር የሚሸት ዲዛይን አላቸው ።እንዲያውም ብዙዎቹ በውበት ያጌጡና ቅንጡ ሆነው መነሻ ሃሳባቸው የኛኑ ዋንጫ፣ ዋርማና ማሰሮ ይመሳስላሉ ።በፋይበር ግላስ ግብዓትነት ተመርተው ሲያበቁ የሚቀቡት ቀለም ደግሞ እጅግ ዘመናዊና የቅርብ ጊዜ ምርት የሆነ የመኪና ቀለም ነው ።
ግብዓታቸው ውድ ስለሆነና ዋጋዎቻቸውም በዚሁ የተነሳ ወደድ ስለሚሉ ቢዝነስ ፕላን ሲዘጋጅ የገበያው ነገር አስፈሪ እንደነበርና አቶ ኤርምያስ በድፍረት የገባበት ዘርፍ እንደሆነ ነግሮኛል፤ በዚያ ላይ የፈጠራ ሥራ ያስደስተኛል ይላል ።ሥራው ከተጀመረ በኋላ በየድርጅቶችና በየቢሮዎች በመንከራተት ማስታወቂያ መሥራትም ግድ ሆኖ ነበር ።በርግጥ ዕቃዎቹን ለማስተዋወቅ ፌስቡክ፣ ቴሌግራምና ኢንስታግራም የመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎችም ከጅምሩ አብረው የተጀመሩ ሥራዎች ነበሩ ።
ምርቶቹ ከተለመዱ በኋላ ሰው መጥቶ የሚያጣው ዓይነት ዲዛይን ባለመኖሩ ገበያው ጥሩ እየሆነ መጥቷል፤ ከ30 በላይ የሚሆኑ ዲዛይኖች አሉት። በከተማው ውስጥ አብዛኛው የእኛ ምርት ነው ያለው ሲል በልበ ሙሉነት ይናገራል ።አሁን ሌሎችም ተመሳሳይ ምርት አምራቾች የእኛን በማየት እየተነቃቁ ነው ።
አቶ ኤርምያስ መላኩ የድርጅቱ ባለቤት ነው ።ምዕራብ ጎጃም ዞን ሽንዲ ወረዳ ነው ተወልዶ ያደገው ። ከልጅነት ጀምሮ የፈጠራ ሥራ ያስደስተኛል የሚለው አቶ ኤርሚያስ ሕይወት መንገዷ ራሳችን ከምንፈልገውና ከምንጠብቀው ለየቅል የሚሆንበት ጊዜ አለና በቀጥታ ወደሚፈልገው ዘርፍ አልተቀላቀለም ።
እናም ሕይወት አሃዱ የተባለችው በእህል ንግድ ነው ።እንደ ባቄላ፣ ሽንብራ፣ ስንዴ፣ በቆሎና በርበሬ የመሳሰሉትን ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ አምጥቶ በመሸጥ የተጀመረው ንግድ እስከ በሬ ንግድ አስሷል ።በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ሄድ መለስ ሲልባት የነበረችውን አዲስ አበባን በ2001 ዓ.ም ኑሮ ጀመረባት ።በወጣ ገባ የሚያውቃትን አዲስ አበባን መኖሪያው አድርጎ የኮንስትራክሽን ዕቃዎችን ማቅረብ ቢጀምርም ሥራው አስደሳች ሊሆንለት አልቻለም ።
በተለያዩ ኢግዚቢሽኖች ተዟዙሮ የፈጠራ ጥሙን ያረካ የነበረው አቶ ኤርሚያስ ወደ ፋይበር ግላስ ቴክኖሎጂ ሲማትር አምራቾቹ ጥቂት ሆነው አገኛቸው ።ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የፋይበር ቴክኖሎጂን በሙሉ ልብ ማጥናት ጀመረ ።በርግጥ በፋይበር ቴክኖሎጂ ላይ ተሰማርተው ያገኛቸው ጥቂት የተባሉት አምራቾችም እንኳን ማምረት የጀመሩት
የውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖችን እንጂ በሌላ መልኩ አዘምነው ሲጠቀሙበት አላየም ።በዘርፉ ከጎግልና ከዩቱዩብ በቂ ሥልጠና ወሰደና በ2007 ዓ.ም አካባቢ እንደሌሎቹ መሰል የፋይበር አምራቾች የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከር በማምረት ሥራውን ጀመረ ።በወቅቱ ከሌለ ገንዘቡ ላይ ለዩቲዩብ ወጪ በማውጣት የተለያዩ በዘርፉ የተሠሩ ሥራዎችን እና አሠራራቸውን በተመለከተ ሥልጠና ወስዶ ከፋይበር ቴክኖሎጂ በርካታ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ማምረት እንደሚቻልና ፈጠራ የታከለበት ሥራም በውስጡ መሥራት እንደሚቻል ተገንዝቧል ።
በፋይበር ግላስ ምርት በሀገር ውስጥ ያየውን እሱ ከተረዳው ጋር ሲያወዳድረውም ዘርፉ ያልተነካ እንደሆነ ተረዳ ።በወቅቱ እነዚህን ዲዛይኖች የሚረዳና የሚሠራ የሰው ኃይል ባለማግኘቱም የፋይበር ቴክኖሎጅን የተቀላቀለው በተለመደው መልኩ የውኃ ታንከሮችን በማምረት ነው ።በርግጥም የውኃ ታንከር ምርቱን የጀመረው ጥሬ ዕቃውን ከውጭ አስመጥተው ከሚያመርቱ ድርጅቶች ገዝቶ ስለነበር በዋጋ ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር ተወዳድሮ ገበያ ላይ መቆየት የማይሞከር ነገር ነበር ።
ከዚያም የጂፕሰም (ቅርፅ ማውጫዎች) ሞልዶችን በማዘጋጀት የጂፕሰም ምርቶችን በመሸጥ በወቅቱ በገበያ ተወዳዳሪ መሆን አለመቻል ምክንያት አሽቆልቁሎ የነበረውን ኢኮኖሚውን በማረጋጋት በፋይበር ግላስ ቴክኖሎጂ አበባ መትከያዎችን ከዩቲዩብ በሠለጠነው መሰረት በመሥራትና የራሱን ፈጠራ በማከል ለገበያ መቅረብ ጀመረ ።
በዚህም መንገድ ቢሆንም የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት እጅግ አስቸጋሪዎች ነበሩ ።ሥራውን እንደጀመርኩ የገንዘብ ችግር ነበረብኝ፤ እንዲያውም ማራኪ ዲዛይኖችን ለማግኘት ስጣጣር ስለነበር አብዛኛው ወጪዬ ኢንተርኔት ሆኖብኝ እማረር ነበረ ይላል ።በድርጅቱ ውስጥ ሠራተኞች ኤርምያስ ያገኘውንና የራሱን ፈጠራ ያከለበትን ዲዛይን ወስዶ ካስረዳቸው በኋላ ሞልድ ተሠርቶ ምርቱመመረት ይጀምራል ።
የማህበራዊ ሚዲያው ሥራ ከድርጅቱ መመሥረት ጋር አብሮ የተመሰረተ በመሆኑ አሁን ላይ ምርቶችን በኦንላይን ገበያ ለመሸጥ አግዟቸዋል ።የኦን ላይን ገበያው ሁኔታም በአካል መጥተው ከሚገበዩት በልጦ 90 በመቶ ደርሷል ።
ለሽያጭ በኦንላይን የቀረቡት ዕቃዎች ለገዢዎች እንዲመች ለየዲዛይኖች የኮድ ቁጥር ተሰጥቷል ።እነዚህን ኮዶች በመጥቀስ ደንበኞች ዋጋው ስንት እንደሆነ ማወቅ ይችላሉ ።ምርቱም ባለው ጥራትና ዲዛይን በሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
ጣና ፋይበር ግላስ ማኑፋክቸሪንግ የማምረቻ ቦታው ኮተቤ አካባቢ ነው ።ሰሃሊተ ምህረት አካባቢ ደግሞ የመሸጫ ቦታ አለው ።ከሾፌርና ቢሮ ከሚሠሩ ሠራተኞች ውጪ በቀጥታ ከሥራው ጋር ግንኙነት ኖሯቸው የሚሠሩ 24 ቋሚ ሠራተኞች አሉ ።ሥራውን ሲጀምር በመነሻ ካፒታልነት አስመዝግቦ ወደሥራ የገባው 2000 ብር ሲሆን አሁን ድርጅቱ ለምርት ማድረሻ የሚሆኑ መኪኖቹንና ሌሎች ሀብቶችን እንዲሁም በባንክ ያለ ተቀማጭ ገንዘቡን ጨምሮ ካፒታሉ ወደ 3ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት ሆኗል ።
አቶ ኤርሚያስ እንዲህ ይላል፡- በግሌ የጊዜን ዋጋ የተረዳሁት አሁን በመሆኑ ያለፈው ጊዜ በጣም ይቆጨኛል ።ሰዎችን ጊዜያቸውን እንዲጠቀሙበት እመክራለሁ ።ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ለወሰነ ሰው ሥራ አይጠፋም ብዬ አምናለሁ ።ሥራ ተገኝቶም ውጣ ውረዶቹ ብዙ ናቸው ።ሰዎች ሙሉ ሰው የሚሆኑት ያጋጠሙዋቸውን ፈተናዎች በድል መወጣት ሲችሉ እንደሆነ ካሳለፍኩት ህይወት ተምሪያለሁ ።ስለዚህም ወደሥራ የሚገቡ ሰዎች በቀላሉ የማይበገሩ ሊሆኑ ይገባል ።ዋጋ ለመክፈል በሙሉ ልቡ ያልተነሳ ሰው ስኬታማ ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2013