ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
‹እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ፣ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተባልታችሁ ካላለቃችሁ በስተቀር ኢትዮጵያ ሀገራችንን ለሌላ ባዕድ አትሰጧትም፣ ክፉ ነገርም ሀገራችንን አያገኛትም› ።ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ከተናገሩት የተወሰደ ነው፡፡
‹ስንደመርና በፍቅር ስንመላለስ አለም ያከብረናል፣ ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፣ ኢትዮጵያ አንድ ሆና ትቀጥላለች፣ ኢትዮጵያን ማንም አያስቆማትም›። ያሉት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያን ያክል ታሪክ ያለው ሀገርና ህዝብ አለም ላይ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። እርግጥ ነው ለማናውቃት ይሄ ቀልድ እንደሆነ እገምታለሁ።ብዙ ሀገራት ከእኛ በተሻለ ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያውቃሉ። አንዳንድ ጊዜ እንዳውም ተወልደን ስላደግንባት ሀገር እኛ የማናውቀውን ከሌሎች የምንሰማበት ብዙ አጋጣሚ አለ ።
ስለ ባህልና ወጋችን ስለታሪካችንም ‹‹ይሄም አለ እንዴ?›› እስክንል ድረስ የሚነግሩን ብዙ የውጪ ዜጎች አሉ ።ይሄ በጣም ያሳፍራል ።ስልጣኔ ራስን ከማወቅ የሚጀምር ነው።
ስለ ራሳችን፣ ስለሀገራችን፣ ስለታሪካችን ሳናውቅ የሚኖረን እውቀትና ጥበብ ወንዝ አያሻግረንም።ሀገር ማንነት ናት…ከማንም ከምንም በፊት ልናውቃት ልንረዳት የሚገባን ።ሀገር እኔና እናንተ አስተሳሰባችንም ጭምር ናት ።
ሀገራችንን ሳናውቅና ሳንረዳ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለቱ ከስም የዘለለ ፋይዳ የለውም ። ሀገር ጥበባችን ናት..ታላቅነታችን በርሷ ውስጥ ተሸሽጓል ።ያለ ቅድመ ሁኔታ እናፈቅራት ዘንድ የውዴታ ግዴታ ተጥሎብናል።
የአውሮፓን ጓዳ ጎድጓዳ ስንበረብር ስለራሳችን ማወቅ እንዴት ያቅተናል? ዛሬ ላይ ዘመናዊው አለም በምርምርና በጥናት አገኘሁት የሚለውን ስልጣኔ ቀደምት አባቶቻችን የደረሱበት ስለመሆኑ በርካታ ማረጋገጫዎች እየወጡ ነው ።ስለጸሀይና ጨረቃ፣ ስለፍጥረተ ክዋክብት፣ ስለነፋሳት፣ ስለ ተቀረው አለም ሁሉ ጥልቅ ግንዛቤን ያዳበሩ የድንቅ አእምሮ ባለቤቶች ነበሩ ።
በተለያየ ጊዜ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ትርጉሙን እንዲነግሩኝ በርካታ ወጣቶችን የጠየኩ ቢሆንም ፈረንጅ አምላኪው ትውልድ ግን ሀገሩን አያውቃትም ።አንዳንዶች ለባዕድ አስተሳሰብ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ የራሳቸው የሆነ ምንም የሌላቸው ሲሆኑ የተቀሩት ወዴት እንደሚሄዱ የማያውቁ በተሳሳተ መንገድ ላይ የቆሙ ሆነው አግኝቻቸዋለው፡፡
ኢትዮጵያ ማለት ነጮቹ እንደሚሉት የተቃጠለ ፊት ያላቸው ህዝቦች የሚኖሩባት ማለት ሳይሆን የራሷ የሆነ የከበረና የተወደደ ታሪካዊ ስያሜ ያላት ገናና ሀገር ናት ።የአሁኑ መጠሪያዋንም ያገኘችው የወቅቱ ንጉስ ከሆነው ንጉስ ኢትዮጵ ነው ።ኢት ማለት ስጦታ ማለት ሲሆን ዮጵ ደግሞ ቢጫ ወርቅ ወይም ደግሞ እንቁ ማለት ነው ከዚህ ታሪካዊ እውነት በመነሳት ኢትዮጵያ ማለት የቢጫ ወርቅ ስጦታ ማለት ነው ።
ታሪክ የማያውቁ አንዳንዶች ግን ከየትም የቃረሙትን መሰረተ ቢስ የፈረንጅ እውቀት ይዘው ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ነው ሲሉ ታሪክ ያበላሻሉ።ከዚህም በተጨማሪ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ እውቅ ጸሀፍት ስሟ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነሳ ቆይቷል ።ከነዚህም ውስጥ የግሪክ ጸሀፍቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ ።
ጥቂቶቹን ብነግራችሁ እንኳን ሆሜር የተባለው ደራሲ ከክ.ል.በፊት ኦዲሴ በተባለው ድርሰቱ ላይ ስለ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ሲናገር እንዲህ ነበር ያለው ‹በኢትዮጵያ የሚኖሩ ህዝቦች እጅግ የተራቀቁ፣ እጅግም ሀያላን የሚያማምሩና የተከበሩ ህዝቦች ናቸው ሲል አወድሷል ።ፈላስፋው ፕሮክለስ ደግሞ ‹ይቺ ፍጹማዊት ሀገር በልቦለድ የተፈጠረች ሳትሆን በእውነት የነበረች የልባሞች ሀገር ናት ሲል አቆላምጦናል ።
ታላቁ እስክንድር ደግሞ ‹እነሆሜር የመላዕክት መቀመጫ ያሏትን ታላቅ ሀገር በምርኮ መያዝ እንደምን ይቻለኛል? ሲል ተናግሯል። ነብዩ መሀመድም ‹ኢትዮጵያ የእውነት ሀገር ናት፣ በውስጧም ሰውን የማይበድል እርሱም የማይበደል ንጉስ አለ ወደዛው ሂዱ›› ሲሉ ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንደላኩ ታሪክ ይነግረናል ።
ኢትዮጵያዊነት ከስሞች ሁሉ የተለየ የብዙ ታሪክ የብዙ እውነት ባለቤትነት ነው ።በኢትዮጵያዊነቱ ያልኮራ በሌላ በምንም ሊኮራ አይችልም ።ሀገራችን እንኮራባት ዘንድ የተሰጠችን ብቸኛ ጌጣችን ናት ። ይሄ ታላቅነታችን ዛሬ ላይ በህዝቦቿ ፍቅር ማጣት እየደበዘዘ መጥቷል ።ጥንት የገነት ህዝቦች መኖሪያ የተባለችው ሀገር ዛሬ አንድነት ባጡ ፍቅር በተራቡ ነፍሶች ተሞልታለች ።
በአንድ ሀገር ላይ አንድ ልብ ግን ደግሞ የተለያየ አስተሳሰብ ያስፈልጋል ።አንድ ልብ የአንድነት የአብሮነት ማሳያ ሲሆን የተለያየ አስተሳሰብ ደግሞ ከመልካም ልብ የሚፈልቅ ሀገር ገንቢ እሳቤ ነው ።
አሁን ላይ አንድነት ከራቀው ከተከፋፈለ ልብ የሚወጣ የተከፋፈለ ሀሳብ የምናራምድ ሆነናል። በልባችን ውስጥ ሀገር የሚገነባ ትርፋማ ሀሳብ ጠፍቷል። በታሪክ በባህል በብዙ ነገር ተሳስረን ተቃቅፈን ተጋምደንና ተፋትለን እየኖርን ተለያይተናል።አብረን ቆመን ተራርቀናል ።
በአባቶቻችን አጥንት ደም..በአያቶቻችን እንባ ቀለም ላንለያይ ተጽፈን ለመውደቅ እንጋፋለን ።እኔ በአንተ ውስጥ አንተ በእኔ ውስጥ እየኖርን እንዴት ግን ተለያይቶ መኖር ተቻለን? ተጋብቶና ተዋልዶ በአንድ የኖረ ሰውነት እንዴት መለያየት ይቻለዋል? አብሮነትን ተጸይፈን አንድነትን አኮስሰን እንዴት ነው ወደ ፊት መራመድ የምንችለው? እንዴት ነው ከፍ የምንለው፣ እንዴት ነው ከፊታችን ያለውን የኋላቀርነት ገደል የምንሻገረው?እርስ በርስ እየተበላላን እርስ በርስ እየተነቃቀፍን እንዴት ነው ጸንተን የምንቆመው? ማነው ባህር የሚያሻግረን? እኛው ለእኛ ካልሆንን..ካልተሳሰብን ማነው የሚመጣልን? እኔ ግን ነገን ፈራሁ..በመቻቻል የምትደነቅ ሀገር ናፈቀችኝ ።
ቴዎድሮስ የሞተላት አብዲሳ አጋ የተዋደቀላት..ዘርዐይ ደረስ ደሙን ያፈሰሰላት ኢትዮጵያ ወዴት አለች? እሷን እሻለው..እርሷን እላለው ።አንድ ሀገር ከሉዐላዊነት ባሻገር ህዝቦቿ በፍቅር፣ በአንድነትና በመቻቻል የሚኖሩባት የጋራ ቤታቸው ልትሆን ይገባል ።ስልጣኔን ለአለም ያስተዋወቀች ሀገር ዛሬ አንድነት ርቋት ስትንገዳገድ ማየት በእውነት ያማል ።
ከምድር ርቀው ከጨረቃ መጥቀው በጸሀይና በግዛቷ ላይ አሻራቸውን ያሳረፉ አባቶቻችን የፈጠሯት ታላቅ ሀገር በእኛ ልትፈረስ ሲዳዳት ያሳዝናል ።እኛ ወንድማማቾች ነን..ከዚህ ሌላ ታሪክም እውነትም የለንም ።
ያለፈውን ትተን በአዲስነት ዛሬን እንኑር ። ከማናውቀው ትላንት ይልቅ የምናውቀው ዛሬ ዋጋ አለውና የማናውቀውን ያልኖርንበትን ትላንት ረስተን ላሁናችን ክብር እንስጥ ።መኖራችን ያለው ዛሬ ላይ ነው ዛሬ የለውጥ የተዐምራቶች መገኛ ነው…ዛሬን እንኑር። የሚያዋጣን እንደ አንድ እናት ልጆች መዋደድና መከባበር ነው ።
የሚያዋጣን ለሁላችንም የምትሆንን ሰላማዊ ሀገር መገንባት ነው ።የሚያዋጣን በፍቅር መኖር ነው ።ሌላው ሁሉ የሚጥለን ነው፣ ሌላው ሁሉ የማይበጀን ነው ።ዳር ቆሞ ለሚያየን ጎረቤት መሳቂያ መሳለቂያ ከመሆን ውጪ መለያየታችን የሚፈይድልን አንዳች ነገር የለም ።
ካለፈው እንማር..ከፊታችን ያላየንው ብዙ መልካም ነገር አለ ፡፡ተዐምር በመስሪያችን ሀይላችንን ለማይሆን ነገር አናባክን ።በመሸነፍ ውስጥ እውነተኛ ማሸነፍ አለ…ግን መሸነፍን አንወድም ።ሁሌም አሸናፊ መሆንን ነው የምንፈልገው..ሁሌም የበላይ ሆነን ለመታየት ነው የምንጥረው ።ሁሌም ከፊት ሆነን ለመቆም ነው የምንሞክረው ።እውነተኛ ማሸነፍ በመሸነፍ ውስጥ ነው ያለው ።
ፍቅር በመሸነፍ ውስጥ የሚያሸንፍ ነው ።ፍቅር ተሸንፎ ማሸነፍ ነው። ወንድሞቻችሁን በማሸነፍ ታላቅነታችሁን ለማሳየት አትሞክሩ ።በወንድማማቾች መካከል ህብረት እንጂ አሸናፊነት የለም ።አንድነት እንጂ መለያየት የለም። ይቅርታ እንጂ ቂም የለም ።ፍቅር እንጂ ጥላቻ የለም።
ወንድሙን አፈናቅሎ ወንድሙን ገሎ ወንድሙን አሳዝኖ ሰው እንዴት አሸናፊ ሊባል ይችላል? አበው ሲተርቱ ‹ወንድሙን ታግሎ የጣለ ጀግና አይባልም ይላሉ። ብጥልህ ብትጥለኝ..ብጎዳህ ብትጎዳኝ በእኔና በአንተ መካከል አሸናፊ የለም ።ህመምህ የሚያመኝ ህመሜ የሚያምህ ከአንድ ባህር የተቀዳን አንድ አይነት መልኮች ሰበዝና አለላ ነን ።
በእኛ ሀገር ሁሉም ነገር ፉክክር ነው..እኔነትን አስቀድመን የምንሮጥ በራስ ወዳድነት የምንኖር እንዲህም ነን..የእስካሁኑ ሩጫችን ሀገራችንን ሰላምና ብልጽግና ከማሳጣት ባለፈ አልጠቀማትም ።
ከእኔነት እንውጣ…ከወንድሞቻችን ጋር ሳይሆን ከአለም ጋር እንወዳደር ።በበለጸገ እንጂ በከሰረ አስተሳሰብ ያደገ ሀገርና ህዝብ የለም። አለም ላይ ሁሉም ሀገራት የተለያየ ግለሰባዊ ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ አመለካከቶችን የሚያራምዱ ናቸው በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ግን አንድ ናቸው ።
እኛ ከሌላው ሀገር የምንለየው የአመለካከት ልዩነታችንን ሀገራዊ ማድረጋችን ነው ።ሌላው ሀገር የአመለካከት ልዩነቱን ለሀገር አንድነት ለህዝቦች ብልጽግና ለልማትና ለፈጠራ ሲጠቀምበት እኛ ግን ለእኩይ ድርጊት እንጠቀምበታለን ።
የትኛውም ሀገርና ህዝብ የአመለካከት ልዩነት ይኖረዋል እንዳውም በአንድ ሀገር ላይ የተለያዩ አመለካከቶች መኖራቸው የተለያዩ መፍትሄዎችን ለማምጣት እንደ ምክንያት ስለሚወሰዱ ከጉዳታቸው ይልቅ ጥቅማቸው የጎላ ነው ወደእኛ ሀገር ሲመጣ ግን የትኛውም የግለሰብም ሆነ የማህበረሰብ የአስተሳሰብ ልዩነት ከጉዳት ውጪ ጥሩ ነገር ሲያመጣ አላየንም ።
ምንም አይነት ልዩነት ይኑረን በሀገራችን ጉዳይ ግን አንድ መሆን ግዴታችን ነው ።አባቶቻችን እንጂ እኛ በሀገር ጉዳይ ተግባብተን አናውቅም።ከአፍራሽ አመለካከት ወጥተን ወደ ሰለጠነ ዘመናዊ እሳቤ መሸጋገር ይኖርብናል። በውይይት የሚያምን የበለጸገ አስተሳሰብ ያስፈልገናል ።ያለዛ ተያይዘን ከመውደቅ ባለፈ እድል የለንም ።የበለጸገ አስተሳሰብ እኔነት አያውቅም።
የበለጸገ አስተሳሰብ ነገን አሻግሮ የሚያይ ነው። የበለጸገ አስተሳሰብ ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚሆን ብዙ እውነት አለው። የበለጸገ አስተሳሰብ መፍትሄ እንጂ ችግር ሆኖ አያቅም።አንድ ሰው ራሱን ሲሆንና ሀገር ሲሆን ወይም እንደ ራሱ ሲያስብና እንደ ሀገር ሲያስብ አንድ አይነት አይደለም ።
እንደ ራሳችን ስናስብ በራሳችን እውነት በራሳችን የህይወት ምህዋር ውስጥ ራስ ተኮር ሆነን ነው..የፈለግነውን ልናስብ የፈለግነውን ልናደርግ እንችላለን ።ሀገር ሆነን እንደ ሀገር ስናስብ ግን የፈለግነውን አናስብም፤የፈለግነውንም አናደርግም ከሀሳባችን መካከል ምርጡን መርጠን ነው የምናስበው፤ምክንያቱም ሀገር ማለት የምርጥ ሀሳቦች ውጤት ስለሆነች ።
ምክንያቱም ሀገር ከሌለች እኔና ህልሜ በእኔ በኩል የሚመጣውም ትውልድ የለምና።ምክንያቱም ሀገር ማለት ሰው ስለሆነ።ስናስብ በሀላፊነት ስሜት ተሞልተን ይሁን ስንኖር ከራሳችን አልፈን ለሌላውም በመትረፍ ይሁን፡፡
ስንኖር ተረዳድተን፣ ተደጋግፈን ይሁን። በሀሳባችን የሚጎዱ፣ በመኖራችን የሚያዝኑ እንዳይኖሩ መጠንቀቅ አለበን ።የነጠረና የተፈተሸ ሁሉን አቃፊ ዘመናዊ እሳቤን እናዳብር ።በአንድ ሀገር ላይ ጨዋና የበለጸገ አስተሳሰብ የለም ማለት እድገትም ስልጣኔም የለም ማለት ነው ።ጭራሽ ያቺ ሀገር ሀገር ሆና ስለመቀጠሏ ማረጋገጫ የላትም ።አስተሳሰብ ስልጡን ሲሆን ብልጽግና ነው ።
ኋላ ቀር ሲሆን ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ነው ።ግለሰባዊ አስተሳሰብ አድጎ ነው ሀገራዊ የሚሆነው አስተሳሰባችንን መግራት ካልቻልን ለእኛም ለሌላውም አደጋ ነው የምንሆነው። በአሁኑ ሰዐት አገራችንን እያመሳት ያለው የግለሰቦች ፍሬ አልባ ወሬ ነው ።በተለያየ የማህበራዊ ሚዲያዎች ሀገር የሚያፈርሱ ህዝብ የሚያጫርሱ ብዙ የውሸት ወሬዎችን እናያለን እንሰማለን ።
ብዙዎቻችን ስሜታዊ ነን ቆም ብሎ ማሰብ አናውቅም ፡፡በሰማነው የተሳሳተ ወሬ ብዙ ጥፋት አድርሰን እናውቃለን ።የበለጸገ አስተሳሰብ ያለው ግለሰብ ሆነ ማህበረሰብ ለድርጊት አይቸኩልም፤ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ ነገሮችን ያያል እንጂ ።ነገሩ እውነት ሆኖ ቢገኝ እንኳን ወደ ጥፋት ከመሄድ ይልቅ ወደ መፍትሄ የሚያተኩር ነው።ለራሳችንም ለሀገራችንም ከማይጠቅም አንቆ ከያዘን እኩይ አስተሳሰብ መላቀቅ አለብን ።ሀገራችንን ለመካስ ትክክለኛ ጊዜ ላይ ነን..ለሀገራችን እናስፈልጋታለን ።
አሁን ላለችው ወደፊት ለምትኖረውም ኢትዮጵያ እናስፈልጋታለን።ተለያይቶ መቆም ትርፉ መውደቅ ነው ።አሁን በያዝነው የተሳሳተ አመለካከት ልክ የሆነ ነገር አናገኝም።ተቀያይሞና ተኮራርፎ የቆመ ማህበረሰብ ወደ ኋላ እንጂ ወደ ፊት ሊያስኬደው የሚችል ሀይል አይኖረውም ።በአብሮነት እንቁም…..የአንዱን ህመም ታጋሪ ሆነን ።ቸር ሰንብቱ ።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2013