አስናቀ ፀጋዬ
ኢትዮጵያ የበርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት መሆኗ ቢነገርም ሃብቱን በሚገባ ሳትጠቀምበት ዘመናት ተቆጥረዋል ።የተፈጥሮ ደኖቿ፣ ወንዞቿ፣ ሃይቆቿና ልዩ ልዩ የከበሩ ማዕድን ሃብቶቿ በተለያዩ የኪነጥበብ ስራዎች ቢቃኙም በሚፈለገው ልክ ለምተው ለህዝቦቿ ጥቅም አልሰጡም።
የማዕድን ሃብቷን ጥቅም ላይ በማዋል ኢኮኖሚዋን ለማሳደግና የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተደረጉ ቀደምት ጥረቶችም ቢኖሩ ያን ያህል አርኪ ሆነው አልተገኙም ።ለዚህም እንደሌሎቹ ዘርፎች ሁሉ የተፈጥሮና የማዕድን ሃብቱ በቂ ትኩረት አለማግኘቱ በምክንያትነት እንደሚጠቀስ የዘርፉ ባለሞያዎች ይስማማሉ ።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ በተለይ ለማዕድን ዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ቢሆንም ሀገሪቱ ካላት ሰፊ የማዕድን ሃብት አንፃር ስራው ገና ጅምር ስለመሆኑም ባለሞያዎቹ አስረግጠው ይናገራሉ ።
የማዕድን ሃብቱ ገና በስፋት ጥቅም ላይ ካልዋለባቸው የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አንዱ መሆኑ የሚጠቀስ ሲሆን በተለይ በወላይታ ዞን ኦፓልና ሌሎች የጌጣጌጥ ማዕድናት በስፋት የሚገኙ ቢሆንም በልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት ከሃብቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳልተቻለም ከክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ ።
የወላይታ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ ተመስገን አለማየሁ እንደሚሉት እስካሁን ድረስ በዞኑ በጥናት ተረጋግጠው ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት ማእድናት በአብዛኛው ለኮንስትራክሽን ግብአት የሚውሉ ናቸው።
እነዚህ ማዕድናትም በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ይገኛሉ ።በተለይ ደግሞ ለግንባታ ግብአት በስፋት የሚውሉ ባዛልትና የድንጋይ ጠጠር በሃምቦና ዲጉና ፋንጎ ወረዳዎች ውስጥ ይገኛሉ ።
በከፊል ከከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት መካከል ደግሞ ኦፓል ዲጉና ፋንጎና አንካ ዳሞት ወረዳ ፋንኮ ቪዦ በሚባሉ ቀበሌዎች ላይ እንደሚገኝ በጥናት ታውቋል።ማዕድኑ ከሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ጋር በቅንጅት ከተጠና በኋላ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተውበት ወደ ማምረት ስራ ተሸጋግረዋል ።
ከኢንዱስትሪ ማዕድናት ውስጥም የድንጋይ ከሰል በኬንዶ ዲዳይ ወረዳ ሼላ መበራ፣ ሼላ ሰዴና ቦሳ ቦርታ ቀበሌዎች በስፋት እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን አንድ ኩባንያ ማዕድኑ በሚገኝበት በሼላ ሰዴ ቀበሌ ፍቃድ አግኝቶ ወደ ማምረት ስራ ገብቷል ።ማዕድኑ በስፋት ይገኝባቸዋል ተብለው በሚታሰቡ ሌሎች ቀበሌዎች ላይ ደግሞ አምስት የሚሆኑ ባለፍቃዶች ጥናት እያካሄዱ ይገኛሉ ።
እንደ ሃላፊው ገለፃ በዞኑ ምን ያህል የማዕድን ሃብት እንዳለ እስካሁን በተጠናው ጥናት ሁሉንም አካባቢዎች ያካለለ ባይሆንም በዲጉና ፋንጎ ወረዳ ላይ በሁለት ቀበሌዎች ከ1 ነጥብ 2 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ በላይ የሚሸፍን የኦፓል ማዕድን እንዳለ ተጠንቷል ።በአመላካች ደረጃ ሌሎች ማዕድናትም በዚሁ አካባቢ እንደሚገኙ ታውቋል።
በኬንዶ ዲዳይ ወረዳም የድንጋይ ከሰል እንዳለ በጥናት የተረጋገጠ ቢሆንም ጥናቱ ግን ጥቅል አይደለም።ጥናቱ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑና የሚያጠናውም አካል ባለመኖሩ የተሟላና ዘመናዊ አይደለም ።
ከኮንስትራክሽን ማዕድናት አንፃር በዋናነት አሸዋና ድንጋይ በዞኑ በስፋት የሚመረቱ ሲሆን የኮብል ስቶን ድንጋይ፣ የአርማታ ጠጠርና ለመንገድ ስራ የሚውል ገረጋንቲም ይመረታል ።
ስራ አጥ ወጣቶች በማህበራት ተደራጅተው በተለያዩ ሳይቶች ላይ በመግባት ማዕድናቱን እያመረቱም ይገኛሉ። ያመረቷቸውን ምርቶችም ለፈላጊዎች በማቅረብና ገቢ በማግኝት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ።
ሆኖም ከከበሩ ማዕድናት መካከል አንዱ የሆነው የኦፓል ምርት እንዴት እንደሚመረትና የንግድ ስርዓቱ እንዴት እንደሚመራ የወጣ የቁጥጥር ህግ ባለመኖሩና አዲስ ከመሆኑ አኳያ በስፋት ወደማምረት ስራ አልተገባበትም ።ለጊዜውም አስር ወጣቶች በአንድ ማህበር ውስጥ ተደራጅተው የምርት ስራ ጀምረዋል።
ሃላፊው እንደሚገልፁት በቅርቡ የኦፓል ማዕድን ምርቱ ደረጃ ይወጣለታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ደረጃው ከታወቀ በኋላ በስፋት ምርቱን የማስተዋወቅና ከዚህ በፊት ገብተው ለመስራት ፍላጎት ያሳዩ እንዳሉ ሆነው ሌሎች አቅም ያላቸው ባለሃብቶችም ገብተው እንዲሰሩበት ይደረጋል ።
የኦፓል ማዕድን በተጠናበት የዞኑ አካባቢ ተጨማሪ ጥናት የሚካሄድ ከሆነም ቀደም ሲል በዚሁ አካባቢ ታንታለም የተሰኘ ማዕድን ግኝት ፍቃድ በፌዴራል ደረጃ በመሰጠቱ ማዕድኑን አውጥቶ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል።
ይሁን እንጂ ቀጣይነት ያለው ጥናት ማድረግ ይፈልጋል ። በዚሁ አካባቢ ላይ በተጨማሪነት ቤዝ ሜታልና ማንጋኒዝ የተሰኙ ማዕድናት እንደሚገኙም የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ጥናቶች አሳይተዋል። ዩኒቨርስቲዎች ከሚያከናውኗቸው ጥናቶች በተጨማሪ ግን ከፌዴራል መንግስትም እገዛ ይፈልጋል ።
ከዞኑ የኮንስትራክሽን ማዕድናት ጋር በተገናኘ ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ አንዱ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ሲሆን የሚፈለገውን የቁጥጥር ስርዓት ተክሎ ለመሄድ በርካታ ባለድርሻ አካላትን፣ የፀጥታ፣ የገቢዎችና የማዕድን መዋቅር ቅንጅትን የሚፈልግ በመሆኑ የተለያዩ መድረኮች ተዘጋጅተው ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ ።
በዋናነት ግን ከጌጣጌጥና ኢንዱስትሪ ማእድናት ጋር በተያያዘና ሌሎች የዞኑን አቅም ባካተተ መልኩ በቂ ጥናት ባለመደረጉ ሀብቱን በስፋት መጠቀም አልተቻለም ።ይህንኑ ችግር ለመቅረፍም ከወላይታ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን በተለይ በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ የአጌትና ኦፓል ማዕድናት እንዳሉ አመላካች ፍንጮች በመገኘታቸው ጥናቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ ።
በቀጣይም የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይና ሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች በአካባቢው ያለውን የማዕድን ሃብት አጥንተው ለዞኑ ቢሰጡ ለወጣቶች ስራ ዕድል ፈጣራ የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ይላል ።
ማዕድን በሚመረትባቸው አካባቢዎች ላይ የሚደርሱ የመንገድ ችግሮችም የሚታዩ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ ገጠር መንገድ ሶዶ ዲስትሪክት ጋር በመቀናጀትና ወጣቶችን በማስተባበር መንገዶቹ እንዲሰሩ ጥረት ተደርጓል ።ማእድን አምራች ወጣቶች በስፋት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ግን በቀጣይ የመንገድ ስራ ድጋፎች ያስፈልጋሉ ።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2013