ዶ/ር ሄኖክ ዘውዱ፣ የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት
በመልካም ሥነምግባር የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ትውልዱን ከልጅነቱ ጀምሮ በተገቢው መንገድ ማሳደግ እንደሚገባ በርካታ ጸሐፍት መክረዋል ፣ዘክረዋል ። አብዛኛውን ጊዜ በወጣትነታቸውም ሆነ ጎልምሰው አልርቃቸው ያለውን የጥፋተኝነት እና ወንጀለኝነት አባዜ መተው ያልቻሉ ሰዎች የኋላ ታሪክ መመልከት ቢቻል ብልሹ የልጅነት አስተዳደግ አሻራ ያረፈባቸው ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል ።
ነጮቹ ልጆቻቸውን ሥነምግባር በማስተማር፣ የንባብ ልምድ እንዲያዳብሩ በማገዝ እና ፈጠራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በማገዝ ብዙ ጊዜያቸውን ይሰዋሉ ፣በርካታ ሃብትም ያፈሳሉ። እኛስ ብለን ብንጠይቅ ደግሞ ካለማወቅም ይሁን ከኢኮኖሚ ደካማነት የተነሳ ለህጻናት በጎ አስተዳደግ እምብዛም ትኩረት ሳንሰጥ መቆየታችንን እያንዳንዳችን እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል ።
ስንቶቻችን ልጆቻችን ማደግ ባለባቸው መንገድ እንዲያድጉ እድሉን አመቻቸተናል የሚለውን መጠየቅ ቢቻል መልሱ ለየቅል እንደሚሆን አያጠራጥርም ። በእርግጥ ህጻናትን ሳይንስም ሆነ ሃይማኖቶች በሚመክሩት መንገድ በጥንቃቄ ለማሳደግ ድካምና ጽናትን ይጠይቃል ። የኋላ ኋላ ግን ትርፍ የሚያስገኝ ድካም ነውና ቸል ሊባል ደግሞ አይገባውም ።
ውጤቱ ያማረ ፍሬ እንድናገኝ ደግሞ ችግኙን እየኮተኮቱ እና ተገቢውን የጸሐይና የውሃ መጠን እየለገሱ ማሳደጉ አስፈላጊ መሆኑ ሲታሰብ የህጻናትም እድገት ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል ። ለህጻናት ጤናማ የአዕምሮ እና አካላዊ እድገት ደግሞ የበጎ ወላጅነት አስተዋጽኦ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ።
በህይወታችን ፈታኝና አስቸጋሪ ከሚባሉት ልምዶች መከላከል ወላጅነት እና የወላጅነት ሚና አንዱ ነው ። ልጅ ወልዶ በአግባቡ አሳድጎ ለቁም ነገር ማብቃት የሁሉም ወላጅ ምኞት ነው ። ሆኖም አንዳንዶች ምኞታቸው ሲሳካ ሌሎቹ ደግሞ በምኞት ሲቀሩ ይታያሉ ።
የነገው የልጆቻችን ህይወት የተሳካ እንዲሆን መልካም የሆነና በሳይንስ የተደገፈ የልጅ አስተዳደግ ዘይቤዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው ። ልጃችንን በምናሳድግበት ወቅት እንደፈቀደ ይሁን የሚለውንም በመተው ፈላጭ ቆራጭ ሆነንም በዚህ ሂድ፣ በዚህ ግባ ሳንል፣ ገደብ ያለው ነፃነት በመስጠት ሲያጠፋ በማስተካከልና መንገዶችን በማሳየት መሆን አለበት ።
በልጆችና በወላጆች መካከል ቀና የሆነና በጎ ግንኙነት ካለ የልጆች የአዕምሮ፣ የቋንቋና ማህበራዊ ክህሎቶች በእጅጉ የዳበሩ ይሆናሉ ። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በቂ የሆኑና ጥራት ያላቸው ጊዜያቶችን ማሳለፍ አለባቸው ።
ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በጋራ የሚያሳትፉ የሚከተሉትን ተግባራት መሞከር ይቻላሉ፡-በጋራ ሆነው መዝሙሮችን መዘመር፣ በቴሌቪዥን ያዩዋቸውን ድራማዎችና ትዕይንቶች በቤት ውስጥ መሞከር፣ ተረትና ታሪክ መንገር፣ እነርሱም ያደመጡትን መልሰው እንዲነግሩን ማድረግ፣ ስዕል አብሮ መሳል፣ እርሳሶችን በመጠቀም የቀለም መፅሐፍት ላይ አብሮ መቀባት፣ አትክልቶችን አብሮ መትከልና መንከባከብ፣ በቤት ውስጥ ምግብ ሲዘጋጅና ገበታ ሲቀርብ በአቅማቸው ልክ አደጋን በማያስከትል መልኩ ማሳተፍ፣ የቤት ፅዳት በጋራ ማከናወን፣ ወደ ገበያ ስፍራ በጋራ መሄድ፣ ልብሶችን እንዲያለብሱን ማድረግ እና የእነሱንም ሲለብሱ አብሮ ማገዝ፣ አዝናኝ ጨዋታዎችን በጋራ መጫወት፣ መናፈሻ ስፍራዎች በጋራ ሄዶ መዝናናት፣ እና የመሳሰሉት በቂ የሆነ ቅርርብን ከሚፈጥሩ ተግባራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው ። እነዚህንም ተግባራት በጋራ ማከናወን በነገው የልጆቻችን ሁለንተናዊ እድገት ላይ ጥሩ የሆነ አሻራን ያሳርፋሉ ።
ልጆችን ኃላፊነትን ማለማመድና ለኃላፊነት ብቁ እንዲሆኑ ማስቻል የወላጆች በጎ ኃላፊነት ነው ። ለምሳሌ ቤቱን ዝብርቅርቅ እንዲል ያደረገ ልጅ “ለምን እንዲህ አደረግህ” ብለን ከመቆጣት ይልቅ “ይህን ነገር እዚህ ጋር ይሄን እንዲህ አድርገን ብናስተካክለው ቤታችን ያምራል” ብለን መምከርና ማሳየት ተገቢ ነው ።
የልጃችንን ባህሪ ለይቶ ማጥናት ያስፈልጋል ። ለምሳሌ “አንተ እንደዚህ ስላደረግህ መጥፎ ልጅ ነህ” ከማለት ይልቅ “እነዚህን መጥፎ ባህሪያት ብታስወግድ እኮ በጣም ጥሩ ልጅ ነህ” ብሎ መምከር ። ምንም ቢያደርግ ለልጃችን ያልተገደበ ፍቅር እንዳለን ሁልጊዜም ማሳየት ያስፈልጋል ።
ድርጊቶች ከቃላት በላይ ኃይል ስለሚኖራቸው የልጃችን ድርጊት ምን እንዳስከተለ ማሳየትና መምከር አለብን ። ለምሳሌ ዩኒፎርሙን ከትምህርት ቤት መልስ በአግባቡ መቀየርና ማስቀመጥ እንዳለበት ስንነግረው ችላ ያለን ልጅ በነጋታው ቆሻሻ ዩኒፎርሙን ለብሶ እንዲሄድ በማድረግ ለድርጊቱ በመጠኑም ቢሆን ዋጋ ማስከፈል አስፈላጊ ነው ።
ከልጆች ጋር ወላጆች በቂ የሆኑና ጥራት ያላቸውን ጊዜያት በማሳለፍ ግንኙነታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል ። ብዙ ጊዜ ወላጆች በስራ ተጠምደው ውለው ቤት ከመጡም በኋላ ስለስራቸው መብሰልሰልና ማውራት ይቀናቸዋል። ይህ አግባብ ባለመሆኑ የስራ ጣጣቸውን ቤታቸው ይዘው ባለማምጣት ለቤተሰባቸውና ለልጆቻቸው ሙሉ ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል ።
ልጆችን በቤት ውስጥ በሚደረጉ ነገሮች ውሳኔ ላይ ተሳታፊ ማድረግ የነሱን ሀሳብ መቀበልና ያሉት ተገቢ ከሆነ መተግበር፣ ካልሆነም የማይሆንበትን ምክንያት ማብራራት ተገቢ ነው ። ይህም ልጆቻችን አቅም እንዳላቸውና ብዙ ነገሮችን ማሳካት እንደሚችሉና የነሱም ሀሳብ ዋጋ እንዳለው ያሳያቸዋል ።
ለምሳሌ ቤተሰብ የሚገናኝበት መጠነኛ ስብሰባን በሳምንት ወይም በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በመደበኛነት መተግበር የበጎ ወላጅነት ተሞክሮ ነው ። ለልጆቻችን ሩህሩህና ደግ መሆን ነገር ግን ሁልጊዜ ቀጥተኛ አቋም እንዳለን ማሳወቅ አለብን ። ልጆቻችን ያልናቸውን ነገሮች ካላደረጉ ሁል ጊዜ ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰድም አስፈላጊ ነው ።
ለምሳሌ የጨዋታ ጊዜ ከ1 ሰዓት በላይ መሆን የለበትም ብለን ከነገርናቸው ሰዓት ዝንፍ ሳናደርግ ጨዋታቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ አለብን ። መለመንና ማባበል አያስፈልግም ። ወላጆች ለልጆቻቸው ላስቀመጡላቸው ገደቦች ተገዢ እንዲሆኑ ሁል ጊዜ ቁርጠኛና ቀጥተኛ መሆን አለባቸው ። ሁል ጊዜ ቁርጠኛ ሆነን ያልነውን ካደረግን ልጆቻችን አክብረውንና የኃይል ሚዛኑንም በኛ በኩል አስጠብቀን መቀጠል እንችላለን ።
እነዚህ ሁሉ የልጆች እንክብካቤ እና ክትትል ማድረጋችን አደግ ሲሉ በወጣትነታቸውም ሆነ በጎልማሳነታቸው ጊዜ ብቁ እና ለሀገር የሚተርፉ ዜጎች እንዲሆኑ ለማስቻል ነው ።
እኔም የበጎ ወላጅነትን ጠቃሚ ምክሮች እና ሳይንሳዊ ሃሳቦችን “ልጅ በእድሉ አይደግ” በተሰኘው መፅሐፌ ውስጥ በስፋት አስፍሬዋለሁ ። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቴ የማህበረሰብም ሆነ የሀገር ልማትና ለውጥ የሚገኘው ከህጻናት እንክብካቤ እና በወላጆች ቀና አስተዳደግ የሚመጣ መሆኑን ለማህበረሰባችን የእለት ተዕለት እርምጃ ውስጥ ለማስረጽ በመፈለጌ ነው።
የጤና ሚኒስቴርም ሆነ በርካታ ተቋማት ስለሕጻናት አስተዳደግ እና በጎ ወላጅነት ተግባራዊ ስራ ቢያከናውኑም እኛ የህክምና ሙያተኞች ደግሞ በዘርፋችን ማበርከት ያለብን ጉዳይ አለና ስለ በጎ ወላጅነት ዛሬም ነገም ቢሆን ሊነገርና ህብረተሰቡ ሊሰበክ ይገባል የሚል እምነት ማሳደር ያስፈልጋል ። ምክንያቱም በውጤቱ የእትብታችን መቀበሪያ የሆነችውን ሀገር ብልጽግና የማምጣት እድሉ ሰፊ ስለሆነ ነው።
ሀገር መሰረቷ ህጻናት ናቸው ሲባል ትውልዱ እየተገነባ ካልመጣ በአንድ ጊዜ ሊለወጥ እንደማይችል በማሰብ ጭምር ነው ። ለነገው የቤተሰብ እና የሀገር ግንባታ ማማር ደግሞ የህጻናት አስተዳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋልና በጎ ወላጅነትን እናበረታታ እናጎልብት የሚለውን መልዕክት ማስተላለፍ ያስፈልጋል ።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2013