(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ እየተዋወቀ ያለ አንድ ልማድ ወደ ሀገራዊ “የባህል” ደረጃ ከፍ ብሎ ሊያድግ ድክ ድክ ሲል እያስተዋልን ነው፡፡ ከነብሂሉስ “ልማድ ውሎ ሲያድር ባህል ይሆናል” ይባል የለ፡፡
ይህ ልማድ በሰሞነኞቹ ሠርገኞች ሠፈር አዘውትሮ የሚስተዋል ይሁን እንጂ ቀድመን ጎጆ ያዋቀርነው ጎምቱዎች ለዚህን መሰሉ አቅመ ወግ ባለመታደላችን ብንፀፀትም በልጆቻችን ደስታ ላይ ግን በስፋት እየተስተዋለ ስለሆነ መጽናናታችን አልቀረም፡፡
ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ በሠርግ በዓል ላይ እድምተኞች የሚፈርሙበት ከኩርማን ጋሻ ትንሽ መለስ የሚል ስፋት ያለው የሙሽሮች ፎቶግራፍ በምግብና በመጠጥ መስተንግዶ መሃል እየቀረበልን የመልካም ምኞታችንን ጥቂት ቃላትና ፊርማችንን በሰሌዳው ላይ እንድናሳርፍ ሳንጠየቅ የቀረን ሰዎች ካለን ምናልባትም በዝንጋኤ ካልሆነ በስተቀር አሻራችንን የማኖሩ ጉዳይ ወደፊት ግዴታ ሳይሆን እንደማይቀር በሚያሳዩ ምልክቶች ካረጋገጥን ውለን አድረናል፡፡
ለፊርማ የሚቀርበው የፎቶግራፍ ሰሌዳ በጥንቁቅ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች የካሜራና የእጅ ሥራ ጥበብ የተዋበ ስለሚሆን እንኳንስ ባለጉዳዮቹን ቀርቶ እድምተኛውን ሳይቀር ማማለሉ እርግጥ ነው፡፡
እንዲያውም አንዳንዴ የሙሽሮቹ ተፈጥሯዊ መልክ በእጅ ሥራው ጥበብ (Retouch) ረቅቆና ተመንጥቆ ስለሚዋብ እነ ሊዮናርዶ ዳቪንቼና ሚካኤል አንጂሎ ከሳሏቸው ከመላዕክቶች ሥዕል ጋር ወደመቀራረብ ደረጃ ሲደርስም ያስተዋልንባቸው አጋጣሚዎች ጥቂቶች አይደሉም፡፡
በዚህን መሰል ዝግጅት በተዋበው የሙሽሮቹ የፎቶግራፍ ሰሌዳ ላይ የሚጻፉት የእድምተኞች መልዕክቶች መልካም ትዳርን፣ ፍቅርን፣ አድናቆትንና ወገናዊነትን የሚገልጹ እንጂ የሙሽሪትን አፍንጫ ጎማዳነት ወይንም የሙሽራውን ድንክነት የሚያሳብቁ አይደሉም፡፡
እርግጥ ነው የርዕሰ የጉዳዩን ጨዋታና ትንተና ለመንደርደሪያ ያህል ተራቀቅንበት እንጂ ልማዱ ሥር ሰዶ ወደ ባህል ደረጃ ቢመነጠቅም ክፋት የለበትም፡፡ ለሙሽሮቻችን የደስታና የታሪክ ምንጭ መሆኑ ከታመነበት ደጋግመን በፎቶግራፋቸው ላይ አሻራችንን ብናሰፍር ምን ችግር ይኖረዋል? ምንም፡፡
ፊርማው እኮ የሚዘልቀው እስከ ምጽዓት ቀን ድረስ ነው፡፡ አይደለዝ ወይ አይሰረዝ፡፡ ዓመታት ቢነጉዱና ሙሽሮቹም ለሁለት ፀጉር ቢታደሉ እንኳን ትዝታው ስለማያረጅ ጠቀሜታ አልባ ነው ተብሎ አይወረወርም ወይንም አይሰረዝም፡፡
ፊርማው ለሙሽሮቹ ብቻም ሳይሆን ፈራሚው ራሱ ከአጸደ ሥጋ ቢለይ እንኳን ማስታወሻው “ህያው” ሆኖ ስለሚኖር ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ እንደየደረጃው በትምህርት ማጠናቀቂያ የምረቃ መርሃ ግብርና በልደት በዓል አከባበር ላይም ይሄው ፎቶግራፌ ላይ ፈርሙልኝ ልማድ አድማሱን እያሰፋ በመሄድ ላይ መሆኑም እየተስተዋለ ነው። ለማንኛውም ቀድሞ የተጀመረው በሠርግ ላይ ስለሆነ ቢያንስ ለየካቲት 13 ቀን ተጋቢዎች መልካም ትዳርን፣ በሙሽሮቹ ፎቶግራፍ ላይ ለመፈረም ዕጣው ለሚደረሳቸው እድለኛ እድምተኞችም “ታድላችሁ!” በማለት አድናቆታችንን ገልጸን ለማዋዣነት የመረጥነውን የመንደርደሪያ ወጋችንን እዚህ ላይ ገታ አድርገን ኮስተር ወዳለው ሀገራዊ ጉዳያችን እናዘግማለን፡፡
«ሀገር እንደ ፎቶግራፍ ሰሌዳ»
ኢትዮጵያ ሀገሬን አዘውትሬ የምመስላት የየዘመኑ ትውልድ ምስሉን ቀርጾ እንዳሳረፈባት ሰሌዳ ነው። ይህ ዘይቤያዊ ገለፃ የሀገርን ክብር ያሳንሳል ተብሎ ለሙግት እንደማይዳርግ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ልክ እንደ ሙሽሮቹ ፎቶግራፍ በሀገር መልክ ላይም እንዲሁ ትውልድ ፊርማውንና አሻረውን አሳርፎ ማለፉ እውነት ነው፡፡
ከልደት እትብትና ከሕይወት ፍፃሜ በድን ማሳረፊያነት እጅግ የላቀ ምሥጢር ያላት ይህቺ ኢትዮጵያ ይሏት ረቂቅና ምጡቅ ሀገር ከ እስከ ከ ተብሎ ተዘርዝሮ የማያልቅ መገለጫዎች ያሏት ተዓምረኛ ምድር ሆና የምትታየኝ በብዙ ምክንያትና ማስረጃነት ነው፡፡ ዝርዝሩን ለወደፊቱ እየቆነጣጠርኩ ለአንባቢዎቼ ለማቃመስ እሞክራለሁ፡፡
እንዲያው ለመንደርደሪያ ያህል አንድ አጠቃላይ እውነታ ለማስታወስ ልሞክር፡፡ በብዙ የሀገር ልጆች የጥበብ ሥራዎች ውስጥ ሲገለጥና ሲመሳጠር የኖረው ይኼው አንኳር የምሥጢራዊነቷ ጭብጥ ነው፡፡
ሠዓሊው በኅብረ ቀለማት፣ ቀራፂው ከቁስ ውስጥ ፈልቅቆ በሚያወጣው ጥበብ፣ ደራሲው የብዕር ቀለሙን አናጥቦ በሚያስነብበው ታሪክ፣ ሙዚቀኛው ከመሣሪያዎቹ ጋር አዋህዶ በሚያፈልቀው ጥዑም ዜማ ሲቀዳና ሲመነዘር የኖረው ይኼው ሀገራዊ ምስላችን ነው/ነበርም፡፡
እርግጥ ነው በሙሽሮች የፎቶግራፍ ሰሌዳ ላይ ታዳሚዎች በሙሉ እንደሚያሰፍሩት አድናቆት ሁሉም ዜጎች አሻራቸውን በሀገር ሰሌዳ ላይ የሚያኖሩት “አወዳሽና አድናቂ” ወይንም በጎና መልካሙን ብቻም ላይሆን ይችላል፡፡ ለእንዳንዱ ዜጋ ሀገር የገነት ተምሳሌት፣ የመንግሥተ ሰማያት ክፋይ ተደርጋ ስለምትቆጠር ይህን መሰሉ ዜጋ አሻራውን የሚያሳርፈው “በወርቅ ብዕር” በተጻፉ ደማቅ የቃላት መርገፍ ሊሆን ይችላል፡፡
እንደነዚህ ዓይነቶችን “በድሃ ምድር ያበቡ የግፍ ባለጠጋ ዜጎችን” ፈልገን የምናገኘው በአብዛኛው “ከተራ ዜጎች መንደር” ውስጥ አይደለም። የእነርሱ ቦታ ተራ ሠፈር ያለመሆኑ ብቻም ሳይሆን “ተራ ሠፈርተኞችም” አይደሉም፡፡
ይህ ማለት ግን የግል ጥረታቸው፣ የላብና ወዝ ስኬታቸው ከማማ ላይ የሰቀላቸው ጥቂቶች ይጠፋሉ ማለት አይደለም፡፡ የሕይወትን ውጣ ውረድ በአሸናፊነት ተወጥተው በትምህርት ወጤታቸው አንቱ ተብለው የተከበሩ፣ በንግድ ወይንም በፈጠራ ብቃታቸው ተጨብጭቦላቸው በሀብትና በዝና የገነኑትንም ማስቀየማችን አይደለም፡፡ ለማለት የተፈለገው ሀገራችን በእስከ ዛሬው የእርጅና ዕድሜዋ ዜጎቿን ስታንበሸብሽ የኖረችው በእኩልነትና በፍትሕ ያለመሆኑን ለማመልከት ብቻ ነው ፡፡
በደሃዋ ሀገሬ መልክ ላይ ጥቂቶች በሕገ ወጥነትና በግፍ ሲዋቡና በጉስቁልናዋ፣ በመከራዋና በአሳሯ ላይ “ዋንጫ ኖር!” እያሉ በመፋነን መሬት ሲጠባቸው ሳስተውል ግራ እጋባለሁ፡፡ “ራስ ገዝ ኢሰብዓዊያነታቸውም” በአደባባይ ተገልጦ ስመለከት ስሜቴ እየተሳከረ ለቅጽበታዊ ወፈፌነት ይዳርገኛል፡፡
በተለይም ፈጣሪ በቸርነቱ አድልዎ ሳያደርግ ያደለንን የተፈጥሮ ፀጋ ማዕድ እኩል መቋደስ ተስኖን በአጋባሽነት መንፈስ ታውረን እርስ በእርስ ስንነካከስና ስንጠላለፍ ኖረን መሞታችን እንቆቅልሽ/ህ ብቻ ሳይሆን “በድፍን እንቁላል” የሚመሰል ሀገራዊ ምሥጢራችን ጭምር ነው፡፡
ገጣሚ አያልነህ ሙላቱ በአንድ የግጥም ሥራው ውስጥ እንደገለጠው (ጽጌሬዳ ብዕር፤ ገጽ 24) ይህ ጸሐፊም የሚሰማው ተመሳሳይ እውነት ነው፤
«ካገሬ ትዝታ የሚታየኝ ጎልቶ፣
ትዝ የሚለኝ ለእኔ፣
ድንቁርና ስቃይ ፍርድ እልቦ አረመኔ፡፡
ይህ የሦስት ስንኞች ገለፃ ከእኔ የሺህ ቃላት ትንተና የተሻለ አቅም እንዳለው የመልዕክቱ ክብደት ምስክር ነው፡፡
በተራ ዜጎች ስም የሚምሉ በርካታ ፖለቲከኞችና በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ጠግበውና ረክተው በማግሳት በአረግራጊ ስፖንጅ ላይ ሲንፈላሰሱ አድረው ማለዳ ላይ በሚዲያ መስታወት ፊት ቀርበው “በሕዝባቸው” ሲያላግጡ ማስተዋል ነፍስን፣ ሥጋንና መንፈስን ማወክ ብቻም ሳይሆን ለቁጣ ጭምር የሚያነሳሳ ነው፡፡
ኑሮ ባጎሳቆለው የድሃ ትከሻ ላይ ፊጥ ብለው በሀገር ውስጥና በባዕዳን ድንቅ ዲዛይኖች በተፈበረኩ አልባሳት ተሞሽረው በንግግር ሲራቀቁ፣ በማይጨበጥ ተስፋ ቃዥተው ሲያስቃዡን መመልከትን የተለማመድነው ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከጥንት ቅድመ አያቶቻችን ጀምሮ ነው፡፡ የዛሬው መጠን ግን ገደቡን የጣሰና ምን ይሉኝን የደፈጠጠ ስለሆነ በባህርይው በብዙ ይለያል፡፡
በዚህ ጸሐፊ እምነት አሁን (በዚህ ጊዜ) በተዘረጋልን የኢትዮጵያ ሰሌዳ ላይ የምናሳርፈው የየግላችን ፊርማና አሻራ ምን ተብሎ እንደሚነበብ ግራ ተጋብተን ለመገመት የተቸገርንበት ወቅት ይመስለኛል፡፡ ሙሽሮች በሚዜዎቻቸው አማካይነት የፎቶግራፋቸው ሰሌዳ ላይ አሻራችንን እንድናሳርፍ የሚጋብዙን የተለየ ብዕር አዘጋጅተው ነው፡፡ ሰሌዳው ተራ ብዕር ለመቀበል አልተዘጋጀም፡፡
ቢሞከር እንኳን ፍሬሙንና ፎቶግራፉን ጭሮ ያበላሽ ካልሆነ በስተቀር ከልባችን የሚፈልቀውን አድናቆትና መልካም ምኞት ለማስፈር ምቹ አይሆንም፡፡ ዛሬ ዛሬ በተዘረጋው የኢትዮጵያ ፎቶግራፍ ሰሌዳ ላይ በርካታ ዜጎች እየጻፍን ያለነው ዕንባ በተቀላቀለበት ብዕርና ደም በሚተፋ መጻፊያ ስለሆነ ሰሌዳው የተጨመላለቀ ይመስለኛል፡፡
ግን ለምን? የፖለቲካው መልክ በሴራ ጨቅይቶ በእድፍ ስለተጨማለቀ ምን ተብሎና እንዴት ተደረጎ በሰሌዳው ላይ መልካም የተስፋ አሻራ ማስፈር ይቻላል? “ከመሪነት ሐዲድ ላይ አንዳች ኃይል አያዛንፈንም” እያሉ ሌት ተቀን የሚፎልሉና ድንጋይ በሚሰብር ቅል የሚመሰሉ “የጊዜ ጀግኖች” ሳይቀሩ ከማቀራረብ ይልቅ ሲያቋስሉን፣ ከማጠጋጋት ይልቅ ሲያናቁሩን እያስተዋልን እንዴት በዜግነታችን ክብር ተማምነን በሀገራችን ሁለንተናዊ የፎቶግራፍ ሰሌዳ ላይ የከበረ አሻራችንን ለማኖር አቅም ይኖረናል?
እንደ የጅብ ጥላ [በእንጉዳይ እንዳንመስላቸው የሞራል ብቃት የሌላቸው] የፖለቲካውን ማሳ የወረሩ ቡድኖችም ሀገርን ሊመሩ ቀርቶ እርስ በእርሳቸው እየተዘነጣጠሉ እንደ አሜባ ሲጠፋፉ እያስተዋልን ምን ብለን ተስፋ ጥለንባቸው የሀገሬን ሰሌዳ አቅርባችሁ አሻራችንን እንድናሳርፍ አግዙን ብለን ተስፋ እንጥልባቸዋለን፡፡ እንዴትስ አምነን እንዲመሩን ራሳችንን እናነጥፍላቸዋለን!?
በጸሐፊው የግል ጠንካራ እምነት እኛን ብዙኃን ምስኪን ዜጎች የኮቪድ ወረርሽኝ ተኮራምተን ቤት እንድንውል እንዳስገደደን ሁሉ ኢትዮጵያንም እንዲሁ የሙስና፣ የሥልጣን እብደት፣ የደቦ ዘረፋ፣ የተረኝነትና የባለ ጊዜነት የልብ እብጠትና የማን አለብኝ ጀብደኝነት የወረራ ጥቃት እየፈጸሙባት አቁስለው የሚያስለቅሷት እየመሰለኝ ከዓይኔ እምባ፤ ከብዕሬ የጠቆረ ቀለም እያፈለቅሁ የማላቅሳት ይመስለኛል፡፡
የብዕር ብቻም ሳይሆን የዕድሜና የሙያ ታላቃችን ነፍሰ ሄር ማሞ ውድነህ የሀገርን ውስጣዊ መከራና የባዕዳንን ድርብርብ ጥቃቶች በተመለከተ በአንድ የግጥም ሥራቸው ውስጥ እንዲህ ቆዝመው ነበር፤
«ሰበብና ምክንያት እኛ ስንደረድር፣
እንዳትፋረደን ይህቺ ሀገር ይህቺ ምድር።»
እውነት ነው የምክንያታችን ሰበቡና ትርጉሙ እጅግ የተራቀቀ ስለሆነ የእንቆቅልሻችን ፍቺው ዛሬም እንደ ትናንቱ “ምን ዕንቁላል ድፍን፤ ያየህ እንደሆነ እምዬ ማርያም አይንህን ድፍን” የሚለው የሕጻናት የእርግማን ጨዋታ የምር ሆኖብን እነሆ ሀገርም ሆነች እኛ ዜጎች በፅኑ ታመን እህህ የዕለት ቀለባችን ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
ምናልባትም ልጆቿ ጠላቶቿ፣ ባዕዳንም አጥቂዎቿ ሆነው ፈተና ላይ የወደቀ ሀገር ከእኛ ውጭ ይገኝ ስለመሆኑ ቢያንስ በዚህ ወቅት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የጓዳችን ማጀት ግማት፣ የጠላቶቻችን የዕብሪት ክርፋት ክፉኛ እያስነጠሰን እንዳለ ማን ይክዳል? በቀስተ ዳመና ኅብረ ቀለማት ሊመሰል የሚችለው የሀገራችን መከራና አሣር ቁጥሩን ብቻም ሳይሆን ዓይነቱንም ዘርዝሮ ለመጨረስ በእጅጉ ያዳግታል፡፡
በጎ ባህሎቻችንና እሴቶቻችን ጠውልገው የወየቡ ይመስላል፡፡ የሃይማኖትና የእምነት አቋማችን ጠይሞ ተጎሳቁሏል፡፡ የፖለቲካውን ፊት ክፉ ማዲያት እንደወረሰው ቀደም ሲል ጠቅሻለሁ፡፡ እየተከባበሩ መደማመጥ ወደ ጨረባ ተስካርነት ካመራ ሰነባብቷል፡፡ የኤኮኖሚው ሀገራዊ “መቅኒ” እየተመጠጠ በዕለት ኑሯችን ላይ ጫናው በርትቶብናል፡፡ የውስጣዊው ጫና ብርታት ሰላማችን እንዳይረጋጋ “የሱናሚ ማዕበል” ሆኖ አስጨንቆናል፡፡
የዘረዘርነው በሙሉ እውነት መሆኑ ባይካድም ሀገራዊ ህልውናችን ሞቶ ይቀበራል ማለት ግን በፍጹም አይደለም፤ አይሆንምም፡፡ ሀገር አንገቷን ቀልሳ ብታነባም መከራዋን በአሸናፊነት ተወጥታ ወደ ከፍታ እንደምትሸጋገር እሙን ነው፡፡ የዘጽአቷ ቀንም ሩቅ አይሆንም፡፡ ትውልድ ይመጣል፤ ትውልድ ይሄዳል፡፡
የሀገር ምሰሶ ለጊዜው የተነቃነቀ ይምሰል እንጂ ፈርሶ ይናዳል ግን ማለት አይደለም። ስለዚህም ለየግላችን ተተምኖ በተሰጠን የአሻራ ማኖሪያ ሰሌዳ ላይ በእጃችን ላይ ያለውን ዘር በበጎነት ዘርተን እንለፍ፡፡ ይህንን ማሳረጊያና የተስፋ ቃል የማጎለብተው በተወዳጁ መምህሬ በደበበ ሰይፉ አንድ ግጥም ይሆናል፡፡
በትን ያሻራህን ዘር+
በጓጥ በስርጓጉጡ፣
በማጥ በድጡ፤
እንደተንጋለልክ – እንደ ዘመምክ፣
ትንፋሽህን እንደቋጠርክ፤
ልል ቀበቶህን እንዳጠበክ፤
የተልዕኮህን አባዜ፣
የሕይወትህን ቃል – ኑዛዜ
ወርውር!
የእጅህን ዘገር፡፡
በትን!
ያሻራህን ዘር፡፡
ይዘኸው እንዳትቀበር፡፡
አሜን ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2013