መላኩ ኤሮሴ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር ወለድ ምጣኔ ዋጋ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ሰሞኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል:: በዚህም መሰረት የኮርፖሬት የብድር ወለድ ምጣኔ ከስምንት በመቶ ወደ ዘጠኝ በመቶ ከፍ ብሏል።ለቤቶች ልማት የሚሰጥ ብድር ወለድ ደግሞ ከ9 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 10 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ እንዲል ተወስኗል::
ባንኩ በብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ካደረገው ማሻሻያ በተጨማሪ፤ በዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎቶች ላይም የዋጋ ማሻሻያ አድርጓል:: በዚህ መሰረት በውጭ ምንዛሪ አገልግሎቶች ላይም የአገልግሎት ዋጋ ማሻሻያ ተደርጓል:: ለውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ለዘጠና ቀናት ለሚሰሩ አገልግሎት ይከፈል የነበረው የ5 ነጥብ 5 በመቶ ክፍያ ወደ 9 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ ማለቱን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል::
በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለሚሰጥ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት አንዳንድ ምርቶች ላይ ዝቅ ባለ የአገልግሎት ዋጋ ይስተናገዳሉ:: በዝቅተኛ በ4 ነጥብ 5 በመቶ የአገልግሎት ዋጋ ይስተናገዳሉ የተባሉ የምርት ዓይነቶች ውስጥ መድሃኒት፣ ዘይት፣ ስኳር እና ማዳበሪያ ተጠቃሽ ናቸው:: ለእነዚህ ምርቶች ይጠየቅ የነበረው የውጭ ምንዛሪ የአገልግሎት ዋጋ 4 ነጥብ 5 በመቶ መሆኑ ተገልጿል::
በባንኩ መረጃ መሰረት በአብዛኞቹ የባንኩ አገልግሎቶች ላይ ከአንድ በመቶ ያልበለጠ የዋጋ ጭማሪ የተደረገ ሲሆን፣ በብድር ወለድ ምጣኔው ላይ ግን እንደየብድር ዓይነቶቹ ተከፋፍሎ የብድር ወለድ ምጣኔ ቀድሞ ከነበረበት ከፍ ማለቱ ታውቋል:: አብዛኞቹ አገልግሎቶች ወቅታዊውን የገበያ ሁኔታ ያላገናዘበ የአገልግሎት ዋጋ ይዞ በመዝለቁ በባንኩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ በመምጣቱ የማሻሻያ ውሳኔው መተላለፉን የባንኩ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል::
በብድር ወለድ ምጣኔ ዋጋ ላይ ማሻሻያ እና የባንክ አገልግሎቶች የዋጋ ማሻሻያ መደረጉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የራሱ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የተለያዩ አስተያያት ሰጪዎች ሲገልጹ ይደመጣሉ:: በተለይም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የምጣኔ ሀብት ምሁራን ያብራራሉ::
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ እንደሚሉት፤ የባንኩ የብድር ወለድ ምጣኔ ዋጋ ማሻሻያ እና የባንክ አገልግሎቶች የዋጋ ማሻሻያዎች የዋጋ ንረት ላይ የራሱ አሉታዊ ሚና ይኖረዋል::
እንደ አቶ ዋሲሁን ማብራሪያ፤ የንግድ ባንክ በርካታ የመንግስት ፕሮጀክቶችን የሚይዝ ፣ ለመንግስት ትልቅ አበዳሪ፣ በርካታ ደንበኞች ያሉት እና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለደንበኞቹ የሚያበድር ተቋም በመሆኑ ባንኩ በብድር ወለድ ላይ ያደረገው ማሻሻያ ብዙ ነገሮችን የመንካት እድሉ በጣም ሰፊ ነው::
በተለይም እጅግ ጠቃሚ የሆኑ መድሃኒቶችን ለሚያስገቡት የሚቀርብ የብድር ወለድ ምጣኔ አራት ነጥብ አምስት በመቶ ተመን የሚስተናገድበት ሁኔታ መመቻቸቱ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እገዛ ይኖረዋል:: ስኳር ፣ማዳበሪያ፣ ዘይት እና መድሃኒት በሀገሪቱ ውስጥ በብዛት ተፈላጊ ናቸው::
እነዚህ ምርቶች የብድር ወለድ ምጣኔ ከዚህ ቀደም ከሌሎች የቅንጦት እቃዎች ጋር ተመሳሳይ ነበር:: የቅንጦት እቃዎችን ከሚያስገቡት እኩል የብድር ወለድ የሚከፍሉበት ሁኔታ ነበር::
ይሄ መሰረታዊ እቃ አቅራቢዎችን ሞራል የሚነካ ከመሆኑም ባሻገር የመሰረታዊ እቃዎች ዋጋ ከፍ እንዲል አንዱ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል:: አሁን ማሻሻያ መደረጉ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል:: መንግስት የወሰደው እርምጃ የሚበረታታ መሆኑን ይናገራሉ::
ማሻሻያው በአንድ በኩል ዋጋ ለማረጋጋት ቢጠቅምም በሌላ በኩል ለቤቶች ልማት የሚሰጥ ብድር ላይ የተደረገው ማሻሻያ የዋጋ ንረትን የማባባስ እድል እንደሚኖረው ይገልጻሉ።ይህም ለኮንዶሚኒየም ቤት ይቆጥቡ የነበሩ ሰዎች ይከፍሉ የነበረው የወለድ ምጣኔ ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል አብራርተዋል::
የብድር ወለድ ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር የዋጋ ንረቱ እንዲባባስ የማድረግ እና ገበያውን የበለጠ የማናጋት እድል ሊኖረው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይጠቅሳሉ:: ገበያ ላይ ከፍተኛ የቤቶች እጥረት ባለበት ሁኔታ ውሳኔው መተላለፉ ችግር ሊያስከትል ይችላል የሚል ሀሳብ ያነሳሉ። በመሆኑም በቤቶች ብድር ወለድ ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ ዳግም ቢያጤነው ሲሉ ይናገራሉ::
በዋቸሞ ዩንቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህሩ አቶ ከአብነህ ሳሙኤል እንደሚሉት የወለድ ምጣኔው ዝቅ እንዲል የተደረጉ ዘርፎች ባለሃብቶች በዘርፎቹ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማበረታታ ነው:: እነዚህ ዘርፎች ከዚህ ቀደም ተገቢው ማበረታቻ ስላልቀረበላቸው አሁን ዘርፉን በማነቃቃት ዘርፉን ለመለወጥ ካለው ፍላጎት የመነጨ ነው::
በዚሁ መሰረት መድሃኒት፣ ዘይት፣ ስኳር እና ማዳበሪያ የመሳሰሉት የፍጆታ እቃዎች በዝቅተኛ የብድር ወለድ የሚስተናገዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ለእነዚህ ዘርፎች የሚቀርብ የብድር ወለድ ምጣኔ ዝቅ መደረጉ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና ስለሚኖረው ውሳኔው ይበል የሚያሰኝ ነው በማለት የአቶ ዋሲሁንን ሀሳብ ያጠናክራሉ::
በሌላ በኩል መንግስት የወለድ ምጣኔ ከፍ እንዲል ያደረጋቸው ዘርፎች ከዚህ ቀደም ችግር የነበረባቸው እና ምቹ ሁኔታዎች ቢፈጠሩም እንኳ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ያልቻሉ ችግር ያለባቸው እና ችግሮቻቸውን ፈትተው በሙሉ ሀይላቸው እንዲንቀሳቀሱ የብድር ወለድ ምጣኔውን ከፍ ማድረግ ተገቢ እርምጃ ነው ይላሉ::
ለአብነት ያነሱትም፤ ከዚህ ቀደም ለቤቶች ልማት በርካታ ማበረታቻዎች የቀረቡ ቢሆንም በቀረቡት ማበረታቻዎች ልክ የሀገሪቱ የቤቶች ችግር አልተቀረፈም:: ይህ ሊሆን የቻለው ሪል ስቴት አልሚዎች የሚቀርብላቸውን ማበረታቻዎች ተጠቅመው ሪል ስቴቶችን ከማልማት ይልቅ በሌሎች ዘርፎች ላይ በማዋላቸው ነው:: የወለድ ምጣኔ ከፍ ሲል አልሚዎቹ ብዙ ወለድ መክፈል ስለማይፈልጉ ቤቶችን ቶሎ ቶሎ በማልማት ለደንበኞቻቸው ለማስተላለፍ ይገደዳሉ::
አቶ ከአባነህ በቤቶች ዘርፍ የብድር ወለድ ምጣኔ ዝቅ ሊል ይገባል የሚለውን የአቶ ዋሲሁንን ሀሳብ ይቃወማሉ:: የቤቶች ዘርፍ የብድር ወለድ ምጣኔ ከፍ ማለቱ ምንም እንኳ አዳዲስ ቤቶች ግንባታ እንዲጀመር ባያበረታታም የተጀመሩ ቤቶች ቶሎ እንዲጠናቀቁ አንዱ ገፊ ምክንያት በመሆኑ እርምጃው ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ::
ከዚህ ባሻገር የባንኩ ውሳኔ ከዚህ ቀደም በመላ ሀገሪቱ የተጀመሩ ቤቶች ግንባታ እንዲጠናቀቅ ስለሚያደርግ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ሲሉ ያክላሉ::
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2013