መርድ ክፍሉ
ፋሺሰት ጣሊያን ከ40 ዓመት በኋላ የአድዋን ድል ለመበቀል ኢትዮጵያን ወሮ፤ በንጉሡ ፊት አውራሪነት የተመራውን ጦር በአቅም ማነስና በአንዳንድ ባንዳዎች በመታገዝ በማይጨው ጦርነት በሽንፈት ቢጠናቀቅም ፋሺስቱ በወረራ በቆየባቸው አምስት ዓመታት አንድም ቀን ኢትዮጵያን በሰላም አልገዛም::
ጣሊያን ወትሮም ፋሺስት ወራሪ ኃይል ነው እና በኢትዮጵያውያን የተቃጣበትን የቦምብ አደጋ ለመበቀል የፋሺስት ወታደሮች በዕለቱ በእንግድነት የተሰበሰቡት ኢትዮጵያውያንን፤ ድሃዎችንና አካል ጉዳኞችን ጨምሮ የአዲስ አበባን ሕዝብ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ጨፍጭፏል::
የታሪክ ድርሳናት እንደሚያመለክቱት በዚህ ጭፍጨፋ ሰላሳ ሺህ ኢትዮጵያውያን ተጨፍጭፈዋል:: ሕፃናት ሴቶች ሳይቀር የተገደሉ ሲሆን የፋሺሰት ወታደሮች የኢትዮጵያውያንን ጎጆዎች በማቀጠል፤ ከእሳት ለማምለጥ የሚሞክረውን እንደ አዳኝ ግዳይ ጥለዋል::
አብረሀም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በግራዚያኒ ላይ የጣሉት ቦምብ የማቁሰል አደጋ አድርሷል:: ግራዚያኒ ከታቀደለት ሞት ቢያመልጥም፤ መጠነኛ ጉዳት ደርሶበት ነበር። በመትረፉም ምክንያት፣ የነሱ የጀግንነት ተግባር፣ አዲስ አበባ ሕዝብ ላይ የሰላሳ ሺህ ሰው ሕይወት በ3 ቀን እንዲጨፈጨፍ ምክንያት ሆኗል።
በደብረሊባኖስ ገዳም የሚኖሩት መነኮሳትና የሃይማኖት አባቶች ደብቀዋቸዋል በማለት እልቂት ደርሶባቸው ነበር። አብረሀም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም እስከዘላለሙም ቢሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በጀግንነታቸው እየታወሱ ይኖራሉ።
የካቲት 12 ቀን ሲነሳ ስምዖን አደፍርስ፣ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም የተባሉ ወጣቶች ሁልጊዜም ይታወሳሉ:: ወጣቶቹ በኢትዮጵያ የተቃጣውን የቅኝ ግዛት ወረራ በቻሉት አቅም ለመቃወም ሞክረዋል:: በዚህም የቦምብ አደጋ ጥለዋል::
እነሱ በፈጠሩት ግርግር ብዙ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ቢያጡም የኢትዮጵያን አይበገሬና በቅኝ ላለመገዛት ፍላጎት በትንሹም ቢሆን ማሳየት ችለዋል:: በዛሬው ቀን 84ኛ ዓመቱ የሰማዕታት ቀን እየተከበረ ይገኛል:: በዚሁ ቀን ሦስቱን ወጣቶች ማስታወስ ወደድን::
ስምኦን አደፍርስ
አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒ ላይ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ቦምብ ሲወረውሩ ስምኦን አደፍርስ የተባበራቸው ጀግና ነበር። በታክሲው ይዟቸው የተሰወረ ልበ ደፋር ሰው ነው። በኢትዮጵያ የታሪክ ዓለም ውስጥ ስለ እሱ ብዙ አልተባለለትም። በ1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ስምንት ታክሲዎች ብቻ ነበሩ።
ከነዚህ የስምንቱ ታክሲዎች አንደኛው ባለቤት ስምኦን አደፍርስ ይባላል። የያኔው ዘመናዊ ሰው መኪና ሲነዳ እንደ ብርቅ እና ተአምር የሚታይም ነበር። ከተለያዩ የታሪክ መዛግብት የተገኙ የዚህን ጀግና ኢትዮጵያዊ ታሪክ በአጭሩ እንመልከት::
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ስለዚሁ ስምኦን ስለሚባለው አስገራሚ ኢትዮጵያዊ ሰፋ አድርገው ከጻፉ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። ስምኦን ከአባቱ ከአቶ አደፍርስ አድጎ አይቸውና ከእናቱ ከወይዘሮ ሙሉ ብርሃን መሸሻ በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በሐብሮ አውራጃ በአንጫር ወረዳ ልዩ ስሙ ጉባ ላፍቶ በሚባለው ሥፍራ በ1905 ዓ.ም ተወለደ።
ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ በመጀመሪያ እዚያው ላፍቶ በሚገኘው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ደብር ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በሕፃንነቱ በመምጣት በልደታ ማርያም ካቴድራልና በአሊያንስ ፍራንሴዝ ትምህርቱን በሚገባ አጠናቀቀ። ከዚያም በታክሲ ነጂነት ወደ ግል ሥራ ተሠማርቶ ይኖር ነበር።
ጠላት በማይጨው ጊዜያዊ ድል አግኝቶ አዲሰ አበባ ሲገባ ስምኦን ገና ወጣት እና ብቻውንም የሚኖር ነበር። ጣሊያንን በጣም ስለሚጠላ ለአገሩም በጣም ተቆርቋሪና ታማኝ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ስላወቁ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ባልንጀራቸው እንዲሆን አደረጉት። ብዙም ከተቀራረቡ በኋላ የሆዳቸውን ምሥጢር ገለፁለት። እሱም ሀሳባቸውን ሀሳቡ በማድረግ አብረው እቅድ ያወጡ ጀመር።
በመጀመሪያ ለማንም ሳይናገሩ በመኪናው ሆነው ወደ ዝቋላ ሔዱ። እዚያም ለ15 ቀናት ያህል ተቀምጠው በግራዚያኒ ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስዱና ከወሰዱም በኋላ ምን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲያወጡና ሲያወርዱ ከረሙ። በተለይም የቦምብ መጣል ልምምድ ሲያደርጉ ሰነበቱ። የቦምብ ቁልፍ አፈታትና አወራወርን ያጠኑት ዝቋላ ነበር። ያስተማራቸውም የደጃዝማች ፍቅረ ማርያም መትረየስ ተኳሽ የነበረ ሰው ነው።
ብዙም ሳይቆዩ የካቲት 12 ቀን 1929 ደረሰ። የአዲስ አበባ ሕዝብ ቤተ መንግሥት እንዲገኝ ታዘዘ። ግቢው ዙሪያውን መትረየስ ተጠምዶበት ይጠበቅ ነበር። ግራዚያንም ለድሆች ምፅዋት እሰጣለሁ ስላለ ብዙ ሰው ወደ ግቢው አመራ። አብርሃና ሞገስም ‹‹መኪናህን ቤንዚን ሞልተህ ያው እንደተባባልነው መኪናዋን አዙረህ ፊት በር በደንብ ጠብቀን›› ብለው ስምኦንን ቀጠሩት። እነርሱ አስተርጓሚዎች ስለነበሩ ግቢ ገቡ። ስምኦንም መኪናዋን አዘጋጅቶ በተባባሉበት ቦታ ይጠብቃቸው ነበር።
ወደ አምስት ሰዓት ገደማ ግራዚያኒ ሕዝብ ሰብስቦ ይደነፋል። የአርበኞቻችንን ስም እየጠራ ያንኳስሳል። የሁሉንም አንገት ቆርጬ ሮማ እልካለሁ ይላል። እነ አብርሃም ቦምብ ጣሉበት። እርሱንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ጀኔራሎቸ አቆሰሉ። የአውሮፕላን አብራሪዎች ጀኔራል ሞተ።
ከዚያም በተፈጠረው ረብሻ መትረየስና ጠመንጃ ሲተኮስ እነርሱ በፊት በር በኩል ሹልክ ብለው ወጥተው በተዘጋጀችው የስምኦን መኪና ወደፍቼ ተነሥተው ሔዱ። ስምኦንም እነርሱን እዚያ አድርሶ ወደ አዲሰ አበባ ተመለሰ።
የካቲት 19 ቀን በሳምንቱ ጣሊያኖች በጥቆማ መጥተው ስምኦንና የቤት ሠራተኛውን ያዙ። ለብቻ አሠሯቸው። እንዲህ እንዲህ ያሉ ሰዎች ይመጡ ነበር ወይ እያሉ ሠራተኛውን ጠየቁት። እሱም ያየውን ሁሉ ነገራቸው። ፈትተው ለቀቁት። ሠራተኛው ባደረገው ጥቆማ ብዙ የስምኦን ጓደኞች ታደኑ።
ታሥረውም ተገደሉ። የስምኦን ታናሽ ወንድም ሱራፌል አደፍርስም ሲታደን ከርሞ ሊያዝ ሲል ሌሊት አምልጦ በእግሩ ከአዲስ አበባ ወደትውልድ ስፍራው ወደ ሐረርጌ ተመለሰ።
ስምኦን የመጀመሪያው የጭካኔ ቅጣት ከደረሰበት በኋላ ደጃች ውቤ ሰፈር አጠገብ በነበረው ወህኒ ቤት አሠሩት። ምርመራው በጥብቅ ቀጠለ። በመግረፍ፣ ጠጉሩን በመንጨት፣ የጣቶቹን ጥፍሮች በመንቀል የሥቃይ ውርጅብኝ ቢያወርዱበትም ስምኦን ከዓላማው ፍንክች አላለም። ምስጢር አላወጣም። አሠቃዮቹም ከእርሱ ምንም ማግኘት ስላልተቻላቸው ሚያዝያ 29 ቀን 1929 ገደሉት።
አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም
አብርሃ ደቦጭ የኤርትራ ክፍለ ሀገር ተወላጅ ነው። የፋሺስት ወረራ በኢትዮጵያ ላይ በተነሳበት ጊዜ አብርሃ ደቦጭ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ይማር ነበር። አብርሃ ደቦጭ ጣልያንኛ ተምሮ ስለነበር አዲስ አበባ ውስጥ ኢጣልያ ሌጋሲዮን የሚሰሩትን ዘመዶቹን ለመጠየቅ እየሄደ በዚያ ካሉ ጣልያኖች ጋር ተዋውቋል።
ወደ ጣልያን ሌጋሲዮን መመላለሱና ከኢጣልያኖች ጋር መተዋወቁ አስጠርጥሮት አብርሃ ደቦጭ ተይዞ ታሰረ። የታሰረው አፈ ንጉስ ከልካይ ቤት ውስጥ ነበር። ኢጣልያ አዲስ አበባን በያዘ ጊዜ አብርሃ ደቦጭ ተፈታ። ከዚያም በኋላ የግራዝማች አበራ ግዛውን ዘመድ በሚስትነት አግብቶ መኖር ጀመረ።
አብርሃ ደቦጭ ጣልያንኛ ተምሮ ስለነበር አዲስ አበባ ባለው በፋሺስት ፖለቲካ ቢሮ ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራ ጀመር። በዚህ ጊዜ፣ ከሞገስ አስገዶም ጋርም ጓደኛ ሆኑ:: ሞገስ አስገዶም የሚኖረው ስብሃት ከሚባል ጓደኛው ጋር ሲሆን ስብሃት ደግሞ የሚሰራው ከጀርመን ኮንሱላር ሚሲዮን ውስጥ ነበር::
አብርሃ ደቦጭ የጣልያኖችን የግፍ አሠራር እና ትእዛዝ እያየ ለጓደኞቹ ያጫውት ነበር። እንዲህ ዓይነቱን ጨዋታ ብዙ ጊዜ የሚጫወቱት ስብሃት ከሚሰራበት ከጀርመን ኮንሱላር ሚሽን ውስጥ ነው። ጀርመን፣ የጣልያን መንግሥት ደጋፊና ወዳጅ ስለነበር በእነ አብርሃም ደቦጭ መሰብሰብ ተጠራጣሪ ነበር።
ይህም ብቻ ሳይሆን አብርሃ በጣልያን ፖለቲካ ቢሮ ውስጥ የሚሰራ ሰው ስለነበር ከውጭ ያለው ሰው በክፉ ዓይን እያየው ስለሚጠላው የሚያጫውተው ቀርቶ የሚያስጠጋውም አልነበረም። ይህን የመሳሰለው ነገር ሁሉ አብርሃን ያስቆጨዋል። ጣልያኖችን ለመበቀልም ቆረጠ። ጫማ አውልቆ በባዶ እግሩ መሄድ ጀመረ። ጫማ ማድረግ የተወበት ሁለት ምክንያቶች ነበሩት። አንደኛው፣ እግሩን ለማጠንከር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ያን የተቀደደበትን ጫማ መለወጫ በማጣቱ ነበር።
‹‹ኒው ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያ ኒውስ›› ይባል በነበረው ጋዜጣ ላይ አልአዛር ተስፋ ሚካኤል እንደፃፈለት «አብርሃ ደቦጭ ጫማ በሌለው እግሩ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ አስር እና አስራአምስት ኪሎ ሜትር እየራቀ መሄድ ጀመረ። በሄደበትም ጫካ ውስጥ ድንጋይ እየወረወረ ስለቦምብ አጣጣል ማጥናትና ክንዱን ማጠንከር ጀመረ።» ብሎለታል። አብርሃ ደቦጭ ጥናቱን ጨርሶ በራሱ መተማመን ሲጀምር የቤት ዕቃዎቹን በሙሉ ሸጠ። ሚስቱንም ደብረሊባኖስ ወስዶ አስቀመጠ።
የጣልያን ልዑል ልጅ ስለወለደ በአዲስ አበባ በቤተ መንግሥቱ ለልጅቱ መወለድ ምክንያት የደስታ ሥጦታ ለማድረግ መወሰኑን ሰማ። በዚያም ቦታ በግራዚያኒና በተከታዮቹ ላይ ቦምብ ለመጣል ወሰነ። ይህንኑ ውሳኔውንም ለሚያውቃቸው ኢትዮጵያውያን ነገረ።
ለበጅሮንድ ለጥይበሉ ገብሬ፣ ለብላታ ዳዲ፣ ለቀኛዝማች ወልደዮሐንስ፣ ለደጃዝማች ወልደ አማኑዔልና ለሌሎቹም ጉዳዩን ነግሮ ጥሪው ከተደረገበት ቦታ እንዳይወጡ አስጠነቀቃቸው። እነዚያ ከአብርሃ ደቦጭ ማስጠንቀቂያ የተነገራቸው ሰዎች አብርሃ ደቦጭን እንደሰላይ ቆጥረው «ዞር በል ወዲያ» አሉት እንጂ ሃሳቡን አልተቀበሉትም።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም በዓሉ ከሚደረግበት ቦታ ቀደም ብለው ደረሱ። ከበዓሉ ቦታ ከመሄዳቸው በፊት አብርሃ ደቦጭ ቤት ውስጥ ሳንቃው ወለል ላይ የጣልያን ባንዲራ አንጥፈው ዙሪያውን በሚስማር መትተው ነበር።
ሁለቱም በኪሶቻቸው ቦምብ ይዘዋል። ማርሻል ግራዚያኒ ለተሰበሰበው የአዲስ አበባ ሕዝብ ንግግር ሲያደርግ የያዙትን ቦምብ ወረወሩበት። አምልጠውም ከግቢው ውስጥ ወጡ። አምልጠው ከወጡ በኋላ ከአርበኛው ከራስ አበበ አረጋይ ዘንድ ሄደው ተደባለቁ። ለራስ አበበም ምን አድርገው እንደመጡ አጫወቷቸው። ጥቂት ጊዜ ከራስ አበበ ዘንድ ቆይተው ወደ ሱዳን ለመሻገር መፈለጋቸውን ነግረው አስፈቀዱ።
ከራስ አበበ አረጋይ ጦር ጋር የተወሰነ ከቆዩ በኋላ ወደ ካርቱም ለመጓዝ ሲንቀሳቀሱ በድንበር አካባቢ ማህበረ ሥላሴ ገዳም በታች ማጠቢያ የሚባል ቦታ ላይ በጥቆማ በጠላት ጦር ተከበቡና ተይዘው ሕይወታቸውን ለራሳቸው እና ለሀገራቸው ሲሉ በስቅላት መልክ ሰጡ:: ከድል በኋላ ንጉሰ ነገስቱ የሁለቱ ጀግና አርበኛ ኢትዮጵያውያን አጥም ከወደቀበት እንዲመጣ አስደርገው በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ፍታት ተደርጎላቸው እንዲያርፉ አስደርገዋል። ምንጭ: የኢትዮጵያ እና የኢጣልያ ጦርነት በጳውሎስ ኞኞ::
በኢትዮጵያ የአርበኞች ትግል ፋሽስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ለቅቃ ስትወጣ ኢትዮጵያ የተዋደቀችለትን ነፃነቷን አስከበረች። አርበኞች ልጆቿም ከየምሽጋቸው ወጡ። የወደቁላትንም ጀግኖች ልጆቿን ጀብዱም ለማውራት በቁ። ሆኖም ብዙ ባንዳዎች የነበሩ አስከፊና አፀያፊ የሆነው ለማውራት ሥራቸውን ለመደበቅና ለመሸፈን እንዲያውም እራሳቸውን አርበኞች አስመስለው ለመቅረብ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያላስወሩት የሐሰት የጀብድ ወሬ የለም።
እነዚህ የወገን ከሀዲዎች በግል ጥቅም የሰከሩ ስለነበሩ የዘረፉት እንዳይታወቅባቸው ሐቀኛ የአርበኛና የትግል ሕይወት ተሸሽጎና ተቀብሮ እንዲኖር አድርገው ነበር። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ትግል እንደገና ነፃነቷን አስከብራ መኖር ስትጀምር እነዚያ የትናንት ባንዳዎች አርበኞች ተብለው መታየታቸው ነበር።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2013