(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
“የታሪክን ስህተት የሚደግሙ (በነፍስም በሥጋም) የተኮነኑ ናቸው”
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም
“ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት በጨለሙበት” በዚህ የቀን ክፉና በተከታታይ ቀናት የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪዎች የፈጸሙት የንፁሃን ዜጎች ጭፍጨፋ በዚህ ጸሐፊ የታዳጊነት የዕድሜ ዓመታት ይዘከር የነበረው በጥሞናና በአርምሞ ስሜት እየታሰበ ብቻ አልነበረም:: የስድስት ኪሎው የሰማዕታት ሐውልት ዙሪያ ገብ በተጠቀሰው እለት ይጥለቀለቅ የነበረው የሀዘን ማቅ የለበሱ ወይንም ነጠላቸውን ያዘቀዘቁ እናቶች የእዬዬያቸውን ድምጽ ከፍ አድረገው ሙሾ በማውረድ፤ አባቶችም የሀዘን ቆብ አጥልቀው ወይንም የጥቁር ቱቢት እራፊ ጨርቅ የሳሪያን ስፌት ኮታቸው ላይ ለጥፈው “እህህ!” በማለት በቆሙበት ቦታ እንባቸውን እያዘሩ እንደነበር ትዝታው ከውስጤ አልጠፋም::
ይህን መሰሉ የመታሰቢያ በዓል አከባበር ለምን ያህል ዓመታት እንደቀጠለ እርግጠኛ አይደለሁም:: በሬዲዮ ሞገድ ሲሰማ የሚውለው የሀዘን ማርሽም ለምን እንደተቋረጠ ምክንያቱን አላውቅም:: አብዛኞቹ ታሪኮቻችን “ዋጋ ቢስ” ተደርገው እንደተቆጠሩት ሁሉ ይሄኛውም ታላቅ ዝክር አሳቢና ተቆርቋሪ አጥቶ እየደበዘዘ የመጣ ይመስለኛል::
“ቅድመ አያትህ ባሻ የምሩ ብሩና ሌሎች በርካታ የአባትህ ወገኖችም በፋሽስት ጭፍጨፋ ወቅት በግፍ ተገድለዋል::” በማለት እናቴ በዚያ የጨቅላነት እድሜዬ ያጫወተችኝ የመታሰቢያ በዓሉን ለመዘከር ስድስት ኪሎ አደባባይ ድረስ ተከትያት በሄድኩበት አንድ አጋጣሚ ነበር::
እንዲያውም ወደ ሐውልቱ እየጠቆመች ከተደረደሩት ምስሎች መካከል አንዱ ሰማዕት ቅድመ አያቴ እንደነበሩ የነገረችኝን “ታሪክ” ሳስታውስ የዋህነቷና ቅንነቷ ትዝ እያለኝ እንባ በዓይኔ ይሞላል:: ያ በርህራሄ የተሞላውና በሀዘን ከተሰበረ ስሜት ይወጣ የነበረው ንግግሯ ከልቤ ውስጥ ተሰንቅሮ ስለቀረ ዛሬም ቢሆን በጉልምስና ዕድሜዬ በሐውልቱ አካባቢ ባለፍኩ ቁጥር በአካል የማላስታውሳቸው የቅድመ አያቴ “መንፈስ” ግዘፍ ነስቶ የሚንቀሳቀስ ስለሚመስለኝ ውስጤ በሀዘን መናወጡ አልቀረም::
በዚያው የታዳጊነት ዘመኔ በዓሉ በትምህርት ቀናት የሚውል ከሆነ ከወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር በሀዘን አንገታችንን እንዳቀረቀርን በመምህራኖቻችን መሪነት ከአራት ኪሎ ወወክማ ትምህርት ቤታችን እስከ ስድስት ኪሎ የመታሰቢያ ሐውልቱ ድረስ ተሰልፈን በመሄድ የበዓሉ አካል እንሆን እንደነበርም አልዘነጋሁም::
ያንን ወቅት ሳስታውስ በመንፈሴ የሚታወሰኝ በስድስት ኪሎ የሰማዕታት ሐውልት አካባቢና በመላው አዲስ አበባ በጨካኞቹ የፋሽስት ጭፍጨፋ የጎረፈው የንፁሐን ደም ብቻም ሳይሆን የሚሊዮኖች እምባም እንደ ዝናብ ተንዠቅዥቆ ምድሪቱን እንዳራሰጨ ጭምር ነው::
የታሪክ ምስክር፤
“… ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰላምና በፍቅር ከቤተ መንግሥቱ ግቢ [ዛሬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሆነው] ተሰበሰቡ:: ጥቂት ቆይቶ ግራዚያኒና መኳንንቱ ከተቀመጡበት ጠረጴዛ አጠገብ ቦምቦች ተወረወሩ:: ቦምቡ እንደተጣለ ግራዚያኒ ጠረጴዛው ስር ተደበቀ:: ሌሎቹ ኢጣሊያኖች ግን ከመሬት ተኙ:: ቦምቡን የጣለው በኢጣሊያኖች ዘንድ በአስተርጓሚነት የሚሰራ የኤርትራ ክፍለ ሀገር ተወላጅ ነው::
ለጥቂት ጊዜ ፀጥ አለ:: ኢጣሊያኖቹ ሌላ የሚወረወር ቦምብ እንደሌለ ካወቁ በኋላ ከተኙበት ተነሱ:: ወዲያው ካርቴሲ ወደ ኢትዮጵያውያን መኳንንት ሽጉጡን አነጣጥሮ የመጀመሪያዋን አንድ ጥይት ተኮሰ:: ካራቢኔሪዎችም ምሳሌውን ተከተሉ:: በጥቂት ጊዜ ውስጥም በዚያ ግቢ 300 ሬሳዎች ተከመሩ::… የካቲት 12 ቀን በተጀመረው ዕልቂት በሦስት ቀን ውስጥ 30,000 ሰዎች በአዲስ አበባ ብቻ ከተገደሉ በኋላ ሌላው እየታፈሰ ወደ በረሃ እሥር ቤቶች ተላከ::” (ጳውሎስ ኞኞ፤ የኢጣሊያ ጦርነት፤ ገጽ 158)::
የዕልቂቱ መንስዔ ምን ነበር? ጭፍጨፋውስ ለምን ሊፈጸም ቻለ? እነዚህ ሁለት ጥያቄዎች የአስከፊ ታሪኩ እትብቶች ስለሆኑ ምላሹን በጥቂት ዐረፍተ ነገሮች ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል:: የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪዎች በ1928 ዓ.ም ውቅያኖስ አቋርጠው ወረራ የፈጸሙበት ምክንያት ዝርዝሩ በርከት ቢልም መሠረታዊው ጉዳይ ግን ለዓለም ሕዝብ ሳይቀር ግልጽ ነበር::
የዘመኑ ኃያላን አውሮፓውያን ሀገራት (በዋነኛነትም እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂዬምና ጀርመን ወዘተ.) አፍሪካንና ሀብቷን ለመቀራመት በበርካታ የቃል ኪዳን ውሎች ተማምለው ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ገብተው ነበር::
በዚህም ምክንያት ሰበብ አስባብ ተፈልጎ እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያም በቅኝ ግዛት ሥር መውደቅና “መሰልጠን” እንደሚገባት በእብሪተኞቹ ኃያላን አውሮፓዊያን መንግሥታት ታምኖበታል:: በዋነኛነትም የአባይ ወንዛችን አትኩሮት የተሰጠው ማዕከላዊ ጉዳይ ነበር::
ከዚህን መሰሉ መሠሪ እቅድ ባልተናነሰ ሁኔታም የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት በ1888 ዓ.ም በአድዋ ላይ የተጎነጨው የሽንፈት ጽዋ የሮምን መንግሥት ለአርባ ዓመታት ያህል ሲያብከነክነውና ሲያቃዠው ስለኖረ ለወረራው ተግባራዊነት ያለ እረፍት ቀንና ሌሊት ይሠራ ነበር:: “ኢትዮጵያ የመስዋዕት በግ ተደርጋ ተቆጥራ ስለነበርም” ወረራውን በፈጸሙ ማግስት የሰብዓዊነትን ክብር ጥለው አውሬ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ይሄው የመነሻ ሰበብ ነበር::
ቤኒቶ አምሊካር፣ አንድሬ ሙሶሎኒ በጥቅምት ወር 1928 ዓ.ም ወረራውን አስመልክቶ ለሕዝቡ ያደረገው የእብሪትና የትዕቢት ዲስኩር ይህንኑ የሚያመለክት ነበር:: በድንፋታው ውስጥ የታጨቁት ቃላት እንደሚከተለው አጥረው ቀርበዋል፤ “የጣሊያን ሕዝብ ስማ! ለታሪክህ ክብርን፣ ለሕይወትህ ብልጽግናን ለማግኘት እንድትችል አስበን የጀመርነውን ጉዞ አናቋርጥም::
ከግባችንም ሳንደርስ አንቆምም:: ከአገራችን አራት ጊዜ እጥፍ የሆነ ስፋት ያላት ኢትዮጵያ የተባለችው በጭለማው ዓለም ውስጥ የምትገኝ የፌውዳሎች መከማቻ ሀገር በቅርቡ የጣሊያን ግዛት ትሆናለች:: እንደምታውቁት አድዋ በእጃችን ሆኖ ባንዲራችን ይውለበለብበታል::
ነገም በሌሎቹ የኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉ ጀግናው የኢጣሊያ ሠራዊት ድል እየመታ ይጓዝበታል::” (ዘውዴ ረታ፤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት፤ ገጽ 204):: ያሳፍራል! አድዋ በጣሊያን እጅ እንደሆነ ሙልጭ አድርጎ ሕዝቡን መዋሸቱም ለአምባገነንነት መገለጫ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል::
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የኔፕልስ ልዕልት መወለዷ እንደ ምክንያት ተቆጥሮ የፋሽስቶቹ ጄኔራል ግራዚያኒ ለአዲስ አበባ “ነዳያን” ምፅዋት ለመስጠት ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች ያንን አጋጣሚ እንደ እድል መቁጠር ብቻም ሳይሆን በውስጣቸው የነደደው የሀገር ፍቅር ቁጭት ተረጋግተው እንዲያስቡ ስላላስቻላቸው የወራሪውን ጠላት መሪ ግራዚያኒን ለመግደል ያቀዱት ዘዴ በመክሸፉ ያ ሁሉ እልቂት ሊፈጸም ችሏል::
በዚህም ምክንያት ነበር ንፁሐን ዜጎች በግፈኛው የፋሽስት ወራሪ ኃይል አንገታቸው ባካፋ፣ አካላቸው በዶማ እየተነደለ በራሳቸው ሀገርና ምድር “ለጨካኞቹ የፋሽስት አራዊቶች” የደም ጥማት ማርኪያ ሊሆኑ የቻሉት:: ይህ አሰቃቂ የወራሪው ትራዤዲ ከተፈጸመ እነሆ የሰማኒያ አራት ዓመቱ ዝክር ዛሬ በክብር ይታሰባል::
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር በ2008 ዓ.ም ሰባ አምስተኛውን የድል በዓል ባከበረበት ወቅት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያንን የከበረ መርሃ ግብር ለማስተባበር ዕድል አግኝቶ ስለነበር ከበርካታ ዝግጅቶች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ ፓስታ አገልግሎት ድርጅት ድጋፍ የወረራውን ወቅት ጀግኖች አርበኞች የሚወክሉ ባለውለታዎችን ምስል በቴምብር ማሳተም ነበር::
ከስድስቱ ቴምብሮች መካከልም አንዱ በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የተፈጸመውን ግፍ የሚወክል ታሪክ የተንጸባረቀበት ሲሆን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በዚህ ታሪካዊ ክንውን ውስጥ ያሳረፈውን መልካም አሻራ ባሰበ ቁጥር ከፍ ያለ የኅሊና እርካታ ይሰማዋል::
የዛሬው እህህታችን፤
ከዛሬ ሰማኒያ አራት ዓመት በፊት የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪዎች በንጹሐን ዜጎች ላይ የፈጸሙት ግፍ ከፋም ለማም በታሪካችን ጥቁር መዝገብ ውስጥ ሰፍሮ በዓሉ አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለ በየዓመቱ መዘከሩ አልቀርም:: ቢቻል የበዓሉ አከባበር የይድረስ ይድረስ መጋለብ በሚስተዋልበት ዝግጅት ባይዝረከረክ ይመረጣል::
የሚመለከተው ክፍልም በቂ ዝግጅት አድርጎ ታሪካዊ ፋይዳውን ከፍ በሚያደርግ ክብር ቢያደምቀው ለሀገራዊ ሞገስና ክብር ትልቅ ፋይዳ ሊያሳይ መቻሉ ብቻም ሳይሆን ለወጣቱ ትውልድም አይረሴ ትምህርት ሊሰጥ ይችላል::
ይህን ታሪክ (በተለይም ዛሬ) ስናስብ ግን ከኩራት ይልቅ አንገታችንን የሚያስደፉና ከፋሽስቱ ድርጊት የማይተናነሱ ክፉ ድርጊቶች በራሳችን ዜጎች እየተፈጸሙ እያስተዋልን ስለሆነ በምን ቋንቋ መግልጽ እንደሚቻል አንኳን የተቸገርንበት ወቅት ነው:: ባለፉት ወራት ውስጥ በበርካታ የሀገራችን አካባቢዎች የተፈጸሙት የንፁሐን ዜጎች ጭፍጨፋዎች ለመሆኑ ከፋሽስቱ ወራሪ ድርጊት በምን ሊለዩ ይችላሉ?
ወራሪው ጠላትስ ያንን መሰል ኢ ሰብዓዊ ድርጊት የፈጸመው በጠላትነት መንፈስ ሰክሮ ነው:: በአንድ ሀገር ዜጎች መካከል የወንድማማቾች ጭፍጨፋ ተፈጸመ የሚለውና በመላው ዓለም ሕዝብ ዘንድ መነጋገሪያ የሆነውን የማይካድራ የንጹሐን እልቂትን በምን ስም እንሰይመዋን? በየዕለቱ በራስ ወገን ተገደሉ፣ ቆሰሉ፣ ተዘረፉ፣ ተፈናቀሉ፣ ተሰደዱ ወዘተ. የሚለውን አሳዛኝ ዜናዎች መስማትስ እንዴት አይሰቀጥጥም? በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የተፈጸመው አሳፋሪ ድርጊትስ ምን ተብሎ በታሪክነቱ ለትውልድ ይተላለፋል? ዛሬ እየተዘከረ ያለው የሰማዕታት ታሪክ “ታሪክ ብቻ” ሳይሆን በእኛ ጀንበር ለተፈጸሙት የከፉ ድርጊቶችም ትምህርት ሊሆን ስለሚችል በድርብ ድርብርብ መታሰቢነቱ ቢዘከር መልካም ሊሆን እንደሚችል የዚህ ጸሐፊ የግል እምነት ነው:: ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2013