ፍቅሬ አለምነው
ኢትዮጵያውያንን ኢትዮጵያንም በባእድ ወራሪ ለመግዛት የተሞከሩ ሙከራዎች በብዙ ውርደትና ሽንፈት ተደምድመዋል:: የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ነጻነትና በክብሩ ከመጡበት ለማንም ለምንም እንደማይንበረከክ በተደጋጋሚ በየጦር ሜዳው አስመስክሮአል:: ለሀገሩ ! ለነጻነቱ ! ለክብሩ !ያለውን ቀናኢነት በየዘመኑ ተጨባጭ በሆኑ የተጋድሎ ድሎች አስመስክሯል። ይህም ለኢትዮጵያውያን መለያ መታወቂያና አርማ ሆኗል::
የኢትዮጵያ ሕዝብ መደፈርን መጠቃትን አሜን ብሎ የማይቀበል ለባርነት ያልገበረ የማይገብር ኩሩና አትንኩኝ ባይ ነው:: ሞት ለምኔ ባይ በሀገሩ ሕልውናና ነጻነት የማይደራደር ይልቁንም ሞቱን የሚመርጥ ጀግና ህዝብ ነው ::
ሩዶልፎ ግራዚያኒ በአዲስ አበባ ከተማ የካቲት 12 ቀን 1928 ዓ.ም ኢትዮጵያውያንን በአረመኔነት የጨፈጨፈበት ቀን ነው:: ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በአዲስ አበባው ቤተመንግሥት ሕዝብን ሰብስቦ ዲስኩር ሲያደርግ በነበረበት ሰአት የቦምብ ጥቃት ፈጽመው ስላቆሰሉት ለዚህ ጥቃት የወሰደው የአጸፋ እርምጃ አሰቃቂ በሆነ ጭፍጨፋና ደም መፍሰስ ተቋጭቷል::
በዚሁ እለት የአዲስ አበባ ነዋሪ በግፍ በጭካኔ በአረመኔነት ተጨፍጭፏል:: ከተማዋ በደም የጨቀየችበት፤ የታጠበችበት ዜጎቻችን በወጡበት የቀሩበት የከፋ የሐዘን ቀን ስለሆነ በብሔራዊ ደረጃ አስበነው እንውላለን::
ፋሽስት ወራሪዎች በወገኖቻችን ላይ የፈጸሙትን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ታሪክና ትውልድ እየዘከረ ያስታውሰዋል እንጂ መቼም አይረሳውም:: ይቅርታም የለውም:: ይልቁንም ለነጻነታችን የተከፈለ ታላቅ የደም ዋጋ በመሆኑ ዝንተ አለም ሲታወስ ሲዘከር ይኖራል::
የካቲት 12 ቀን 1928 ዓ.ም ማለዳ በዛሬው እለት የስድስት ኪሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በያኔው ቤተመንግሥት ገብቶ የሰፈረው የፋሽስቱ ሹም ሩዶልፎ ግራዚያኒ ባዘጋጀው በዓል ላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዲገኙ ባስተላለፈው ጥሪ መሰረት እልፍ የመዲናችን ነዋሪዎች ዲስኩሩን ለማዳመጥ ተሰብስበዋል::
በሀገር ፍቅር የነደዱት ወጣት ኢትዮጵያውያን ቀደም ብለው እንዴት በነዚህ የፋሽስት አለቆች ላይ እርምጃ ወስደው መግደል እንዳለባቸው ሲመክሩበት ሰንብተዋል:: ከእነሱ ጋር በምስጢር የውስጥ አርበኞችም እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ ::
አብርሀም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ወጣቶች ተሽሎክሉከው ግራዚያኒ ወዳለበት መድረክ አካባቢ ይቀርባሉ:: የታጠቁትን የእጅ ቦምብ ነቅለው ወደ ግራዚያኒ ወረወሩ :: ፍንዳታው አካባቢውን ሲያናውጠው እሪታ ጩሀትና ትርምስ ነገሰ::
ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ የግራዝያኒ ወታደሮች አለቃቸውን አፋፍሰው ወደ ሆስፒታል ወሰዱ:: በጥቃቱ ከግራዝያኒ ውጪ የሠራዊት አዛዥ ጄኔራሎችና መኮንኖች ቆስለዋል::ሞተዋል::
ግራዚያኒን በአዲስ አበባ ከተማ ነፍስ ያለው የሚንቀሳቀሰውን ሁሉ እንዲፈጅ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት የፋሽስት ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ሠራዊት የአዲስ አበባን ነዋሪ ባገኘበት ሁሉ ጨፈጨፉ :: አዲስ አበባ በቦምብ በጥይት በሚነዱ ቤቶች ጭስ ታፈነች:: ሞት በአዲስ አበባ ሰማይና ምድር ላይ ሰለጠነ:: ነገሰ::
በሺዎች በየቦታው በግፍ ስለተገደሉ ሬሳ አንሺ፤ ቀባሪ ፤አፈር አልባሽ ጠፋ::ቤት ያለአባወራና እማወራ፤ ሕጻናት ያለአሳዳጊ፤ እናትና አባት ያለልጅ ቀሩ:: ለግጦሽ የወጡ ከብቶች ሰዓቱን ጠብቆ ወደ በረታቸው የሚመልሳቸው አባወራና ኮበሌ አልነበረም:: በየመንገዱ የወደቀውን ሬሳ የሚሰበስብ አልተገኘም::
አዲስ አበባ በወደቀው የሰው ሬሳ ክፉ ሽታ ተናወጠች:: ቀዳሽም አራሽም ሴት ወይዘሮም ጠፉ:: ከእንጦጦ በላይ፤ ጉለሌን ይዞ እስከ ሰላሌ አልፎ እስከ ጀማ ወንዝና አባይ ዥረት ድረስ የኢትዮጵያ አርበኞች እየተቅበጠበጡ ይሸልሉ ነበር::
ሰላቶ ገዳይ—ባንዳ ገዳይ
ጀማ ከወንዙ— ከአባይ ዥረት ላይ !!
ከወዲህ መስፍን—- ከወዲያ በላይ
ውቂያ ይዘዋል——በሰላቶ ላይ !! እያሉ ከአዲስ አበባ ለአሰሳ የሚወጣውን የጠላት ጦር በየቦታው እያደፈጡ ይገጥሙት ነበር::
መሬቷ እሳት—- ልጆቿ– ቋያ
ማነው ሚደፍርሽ እምዬ ኢትዮጵያ !!
የሚለው ስንኝ የጀግንነታቸው መለያ የሞት አይፈሬነታቸው መገለጫ ነበር:: ጣሊያን አዲስ አበባ ቢገባም ኢትዮጵያን አልገዛም:: አርበኞቻችን እያሳደዱ ፈለጉን እየተከተሉ መቆሚያ መቀመጫ አሳጥተውታል ::የዛሬውን የሰማዕታት ቀን የካቲት 12ን የዛሬው ትውልድ እንደዘከረው ሁሉ መጪውም ትውልድ ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበለ ይዘክረዋል::
የኢጣሊያ ሠራዊት በታላላቅ ጦርነቶች ውስጥ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ተደቁሶ ተመቷል:: አከርካሪው ተሰብሮ የሽንፈት ጽዋ ተጎንጭቶ የወረራ ታሪኩ በውርደት ተደምድሞአል::በአባቶቹና እናቶቹ ላይ የተፈጸመውን በደል የሚረሳ የኢትዮጵያ ትውልድ አይፈጠርም:: ይህ ቀን ስለነጻነታችን የከፈልነው ታላቅ ዋጋ መገለጫ ጭምር ነው።
ይህን ዕለት ስናስብ ሌላው ሀገር በቀል ፋሽስት የህወሓት ጁንታ የባንዳ ውላጅና የጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ተላላኪ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ከመቀሌ ጀምሮ በተለያዩ ቀጠናዎች በነበረው የሰሜን እዝ ሠራዊታችን ላይ በውስጥ ተላላኪዎቹ አማካኝነት ያካሄደውን መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋና ግድያ እያስታወስን ነው ::
ሀገር ሰላም ብለው በአልጋቸው ላይ ያሸለቡ ጁንታው በጫረው እሳት ስጋት ውስጥ የነበረውን የትግራይ ሕዝብ ሊጠብቁ ለዓመታት በቀበሮ ጉድጓድ የነበሩ የሰራዊቱ አባላትን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፣ በገደላቸው የሠራዊቱ አባላት አስከሬን ላይ ጨፍሯል:: ሜዳ ላይ አስጥቶ እንዳይቀበሩ አድርጎአል::
ጁንታው ፋሽስቱ ሩዶልፎ ግራዚያኒ በአዲስ አበባ ካደረገው አረመኔያዊ ግፍና ጭፍጨፋ በላይ በእጥፍ የከፋ አረመኔያው የወንጀል ድርጊት በወገኖቻችን ላይ ፈጽሟል:: የሀገር ሀብት የዘረፈ በዜጎች ደም የታጠበ ወንጀለኛና ፋሽስት ቡድን ነው ::
ያደረገው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት ሁሉ ተበጣጥሶና ተደምስሶ የሰበሰበው ወታደራዊ ቀላልና ከባድ መሳሪያ ወድሞበት፤ ብዙዎች ቁልፍ አመራሮቹ በቁጥጥር ስር ውለው ጄኔራሎቹ ተደምስሰው ዛሬ በነበር የሚጠቀስ ግን ደግሞ ምላሱ ያልሞተ ተራ ወሬኛና ወሻካች ሆኗል::
የኢጣሊያው ፋሽስት ግራዚያኒና የህወሓት ጁንታ ጨፍጫፊዎች ያደረሱብንን ግፍና በአረመኔነት የተሞላ ግድያ፤ ሴቶችን መድፈር፤ በጀምላ በዜጎች ላይ ያደረሱትን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ከትውልድ ትውልድ ይተላለፋል::
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የህወሓት ጁንታ በሰሜን ዕዝ ሠራዊታችን ላይ ያደረሰውም ጭፍጨፋ የሰማዕታት ቀን በሚል ወደፊት ልናከብረው ይገባል :: የጥቁር ታሪካችን አካል ነው።የግራዚያኒ ፋሽስት ወታደሮች የአዲስ አበባን ነዋሪ ሕጻን፤ ሽማግሌ፤ አሮጊት፤ ወጣት፤ ቄስ መነኩሴ፤ ሼህ ሳይሉ በየመንገዱ በጥይት በአካፋ በዶማ ጨፍጭፈዋል::
እናቶች ተገድለው ሕጻናት የእናቶቻቸውን ጡት ከአስከሬኑ ላይ እየጠቡ ተገኝተዋል:: በዛን ዘመን ከተማዋ በብዛት ጎጆ ቤት ነበራት:: ዜጎች በየቤታቸው ባሉበት የኢጣሊያን ወታደሮች በከተማዋ ውስጥ እየዞሩ አንድም ቤት ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር ውስጡ ካሉት ሰዎች ጭምር እሳት እየለኮሱ አጋይተውታል::
በተለይ ስድስት ኪሎ፤ ሽሮ ሜዳ፤አፍንጮበር፤ ቤተመንግሥቱና አራት ኪሎ አካባቢ በወቅቱ ከእልቂቱ የተረፉት አዛውንቶች እንደሚናገሩት በደም አበላ ታጥበዋል:: የሰው ልጅ ደም እንደ ጎርፍ በየሜዳው ፈሷል:: የተፈጸመብንን ግፍ በደልና ጭፍጨፋ መቼም አንረሳም !! ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለአለም ትኑር !!
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2013