ጌትነት ተስፋማርያም
የህወሓት ጁንታ ቡድን እራሱ በፈጠረው ግጭት እና የጦርነት ጉሰማ እንዳያንሰራራ ሆኖ ከስልጣኑ ተወግዷል። ከጁንታው ቡድን አመራሮች መካከል ገሚሱ በህግ ቁጥጥር ስር ሲውሉ ከፊሉም ህይወታቸው አልፏል፤ የተቀሩትም በየስርቻው ተደብቀው ይገኛሉ።
ይህንን ተከትሎም አጥፊ ቡድኑን ለሰራው ስራና ላጠፋው ውድመት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎችም እስከ አሁን ድረስ ተጠናክረው ቀጥለዋል። በዚህ ረገድ የጁንታውን የጥፋት አካሄድ ከመነሻውም ሲቃወሙ የነበሩ እና ሲታገሉ የቆዩ የትግራይ ሰዎች መኖራቸው ግልጽ ነው።
የጁንታው ቡድን ለትግራይ ህዝብ እንደማይጠቅም በግልጽ በመናገር ሲታገሉ ከቆዩ የፖለቲካ ሰዎች መካከል ደግሞ በመምህርነት ሙያ ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል አንዱ ናቸው። ህወሓት ያካሄደውን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ የሆነ ምርጫ በመቃወም ህዝብ እንዳይቀበለው ጥረት ሲያደርጉ ነበር።
በኋላም የህወሓት አመራሮች ባስነሱት ግጭት መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እንዲደርስ ሲያደርጉ በጽኑ በመቃወም ሃሳባቸውን በተደጋጋሚ ሰጥተዋል። የጁንታው አመራሮች መያዝ በትግራይ ውስጥ ተስፋ ማንገሱን ከማብሰር ባለፈ በክልሉ የተቋቋመው አዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጭምር የገለጹ ሰው ናቸው።
በትግራይ ክልል የተቋቋመውን የብልጽግና ፓርቲ ከመሰረቱ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል ህወሓት የተመሰረተበትንና በየዓመቱ ሲከበር የቆየውን የካቲት 11 ቀን በማስመልከት አጠቃላይ ስለትግሉ አጀማመርና አካሄድ እንዲሁም ትግሉ የተጠለፈበትን መንገድ አስመልክቶ የታዘቡትን እንዲያካፍሉን ጠይቀናቸዋል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን:- የትግራይ ህዝብ የትግል መስዋዕትነት በህወሓት ቡድን ተጠልፏል የሚል ሃሳብ በተለያዩ ሰዎች ሲነሳ ይደመጣል፤ ይህ ምን ማለት ነው? በምን መልኩ ነው የትግራይን ህዝብ ትግል ህወሓት ጠልፎታል የሚያስብለው?
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:- እውነት ነው፤ የትግራይ ህዝብ ክቡር መስዋእትነት በህወሓት ጥቂት አመራሮች ተጠልፎ ቆይቷል። የትግራይ ህዝብ መስዋእትነት ብቻም ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ትግልም ጭምር በዚህ የክህደትና የጥፋት ቡድን እኩይ ተግባር ተጠልፏል።
ይህ የክህደት ታሪክ መፈጠር የጀመረው ከትጥቅ ትግሉ ጅማሬ ወቅት አንስቶ መሆኑ ደግሞ የክህደት ቡድኑ ስር ሰዶ እንዲቆይና የጥፋት ተግባሩን ለመፈፀም ሰፊ እድል እንዲያገኝ አድርጓል። ጉዳዩን ከስር መሰረቱ ግልጽ ለማድረግ፤ የትግራይ ህዝብና ሃቀኛ የአብራክ ክፋይ ልጆቹ የታገሉት ለሶስት አላማዎች ነበር።
የትግራይ ልጆች በዋነኛነት ለእኩልነት፣ ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያና ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ነበር የታገሉት። እነዚህ ትላልቅ አላማዎች የህዝቡና የሃቀኛ ጀግኖች ልጆቹ የታሪክ መሻቶችና የትግል አላማዎች ሆኖ ትግሉ ሲፋፋም በቂም በቀልና በማንነት ቀውስ የሚሰቃዩ ጥቂት አመራሮች የትግራይ ህዝብና የሰፊውን ታጋይ እውነተኛ አላማ ጠምዝዘውታል።
ጠምዝዘውም የትግራይን ህዝብ እንዲሁም የመላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክና ስነ-ልቦና በመካድ በቁንፅል እና በባእዳዊ የማርክሳዊ-ሌኒናዊ ስነ-ሃሳብ ተነድተዋል። በዚህም የትግራይ ህዝብ ትግልና መስዋእት የታለመለት ህዝባዊ ፍሬ እንዳያፈራ አድርገውታል።
ይህ የክህደት ታሪክ ቢያንስ በሶስት ቀደምት ምዕራፎች ተስተውሏል፤ በአንደኛው ምዕራፍ ትግሉ ከተጀመረ ከሶስት አመታት በኋላ “ሕንፍሽፍሽ” ተብሎ በሚታወቅ ወቅት ላይ የድርጅቱ ዴሞክራሲያዊነት ላይ ጥያቄ ያነሱ ታጋዮች በአካባቢያዊ ማንነታቸው በመፈረጅ የተፈፀመባቸውን የክህደት እርምጃ እናገኛለን።
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የክህደቱ ምዕራፍ በ1977 ዓ.ም የተፈፀመ ነበር፤ ይህም ማርክስ ሌኒን ሊግ ትግራይ (ማሌሊት) የተባለ በህወሓት ውስጥ ሌላ ፓርቲ በመመስረት የክህደት ሃይሉ የበላይነት የተቆናጠጠበትና የህዝባዊ አላማው አቀንቃኞች በከፍተኛ ደረጃ የተገፉበት ምዕራፍ ነበር።
በሶስተኛ ምዕራፍ ደግሞ ከድል በኋላ ለድል ያበቋቸውን ታጋዮች እንደጠላት ታይተው የተገፉበትና ከድርጅቱ በግፍ እንዲባረሩ የተደረገበት የክህደት ምዕራፍ ይገኛል።
ህወሓት እንዲህ እንዲህ እያለ ህዝባዊ አላማውን እየተወ የጥቂት ቡድን አባላት መፈንጫ እየሆነ በመቀጠል መጨረሻ ላይ እራሱንም ጭምር ለዘመናት በተበተበው የሴራና የክህደት ፖለቲካ ጠልፎ ክፉኛ በመውደቅ ህዝብና ሃገርን ለአደጋ ጥሎ አልፏል።
በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ የትግራይ ህዝብ ትግልና ክቡር መስዋእትነት ተጠልፏል የምንለው፤ ህዝባችን ከባድ መስዋእትነት የከፈለለትን የእኩልነት፣ የዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት አላማዎች ተጨናግፈው በሚያሳዝን ሁኔታ አሁንም በተመሳሳይ የአላማና የትግል አዙሪት ውስጥ ለመገኘት ተገዷል።
አዲስ ዘመን:- ህወሓት የተመሰረተበት የካቲት 11 ቀን በየዓመቱ ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበት ሲከበር ቆይቷል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች በሴፍቲኔት መርሀ ግብር በችግር ቀናትን ይገፉ ነበር፤ ይህንን እውነታ እንዴት ያዩታል?
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:– በመጀመሪያ ስለየካቲት 11 የተወሰነ መሰረታዊ ጉዳይ እናንሳ። የካቲት 11 በትግራይ ክልላዊ ህገ-መንግስት ውስጥ ከተደነገጉ ህዝባዊ በዓላት አንዱ ነው፤ ይህ በዓል ለትግራይ ህዝብና በጥቂቶች ለሚዘወረው የህወሓት ቡድን የተለያየ ስሜት ነበረው።
በህዝቡ ዘንድ የቆራጥ ልጆቹ ጀግንነት ማስታወሻና ከአግላይ ስርዓቶች ለመላቀቅ ብሎ ትግል የጀመረበት ቀን ሆኖ ሲከበር፤ በህወሓት ቡድን ዘንድ ደግሞ የየካቲት 11 ቀን በዓል እንደልዩነት መፍጠሪያ፣ ጠብ መጫሪያና መፎከሪያ በዓል ብቻ ተደርጎ በቁንጽልነት ሲከበር ቆይቷል።
በሌላ መልኩ በክልላዊ ህገ-መንግስቱ እንደተቀመጠውና በህዝብ ዘንድ እንደሚታወቀው በዓሉ የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል የጀመረበት ቀን ተብሎ እየተከበረ ሲቆይ በጎላ መልኩ ግን በከሃዲው ቡድን አማካኝነት የህወሓት የልደት ቀን ተደርጎ፤ ህዝባዊነቱ ሳይሆን ድርጅታዊ በዓልነቱ ገኖ እንዲከበር ሲደረግ ቆይቷል።
ከዚህ በከፋም በጁንታው ቡድን አማካኝነት የትግራይ ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በ17ቱ ዓመት የትጥቅ ትግል ወቅት ብቻ መታገል እንደጀመረና ድል እንደተቀዳጀ ተደርጎ በማቅረብ የሶስት ሺህ ዓመት የትግራይ ህዝብ ደማቅ ታሪክ ችላ እንዲባል በዓሉ መሳሪያ ሆኖ ሲያገለግል ነበር።
የካቲት 11 ልክ እንደድርጅቱ አጠቃላይ አሰራር ከህዝባዊነቱ ይልቅ ድርጅታዊነቱና ታሪክ አዛቢነቱ ጎልቶ እስካሁን ድረስ እየተከበረ ቆይቷል።
ከዚህ በተጨማሪም ለበዓሉ ማክበሪያ ከመንግስትና ከህዝብ በግድ የሚሰበሰብ በርካታ ገንዘብ ወጪ ሲደረግበት ተስተውሏል። ይህ ደግሞ የመረበ-ደህንነት (ሴፍቲኔት) እና ሌሎች መሰረታዊ እርዳታዎች ጥገኛ የተደረገው ቁጥሩ የማይናቅ ህዝባችን የኑሮ ሁኔታ ያላገናዘበ የሴረኞች ተግባር የፈጠረው ሁኔታ ነበር።
ከዚህ በኋላ የየካቲት 11 በዓል መከበሩ ቢቀጥል ችግር የለውም፤ ነገር ግን በዓሉ የትግራይ ህዝብን የትግልና የክቡር መስዋዕት አላማዎቹ ባገናዘበ መልኩ እንዲሁም ደማቅና ረጅም ምልአተ-ታሪኩንና አገራዊ አንድነቱ በሚያከብር መልኩ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን:- የጁንታው ቡድን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን በውጭ ሀገራት በሚገኙ ባንኮች አስቀምጦ ለምስረታ በዓሉ ሲባል ግን ከትግራይ ገበሬዎች ላይ ጭምር መዋጮ እንዲያደርጉ የሚያስገድዱበት ሁኔታ ነበር ይባላል፤ከዚህ ጉዳይ በስተጀርባ ያለው ገፊ ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:– ህወሓት በዝባዥና የጥቂቶች ስርዓት ነበር፤ ይህ ስርዓት እንኳን ሰበብ አግኝቶ ይቅርና እንዲሁም የህዝብ መቀነትና ኪስ በርብሮ ሃብት ለማካበትና ህዝብ ድሃ ሆኖ እንዲገዛለት ከማድረግ የቦዘነበት ግዜ አልነበረም።
በህወሓት ታሪክ ትግራይ ውስጥ ህዝብ እንዲያዋጣ ያልተገደደበት የልማት ስራና ክብረ-በዓል እምብዛም አይገኝም። ይህ ብዝበዛ የሚፈጸመው ደግሞ የህወሓት ቡድን ከድሃውና ከጭቁኑ ህዝብ የበዘበዘው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት በየካዝናው ሸሽጎና ወደውጭ ሀገራት ባንኮች አሽሽቶ ሳለ ነው።
ይህ ተግባሩም የብዝበዛ ፍላጎቱ ምን ያክል መረን የለቀቀ መሆኑን በግልፅ ያሳያል። ቡድኑ ለትግራይ ህዝብም ጭምር ትልቅ ጠላት እስከመሆን የደረሰ እና ከየት-መጣሽ የሚያስብል አሊያም ልክ እንደ ኤሌየን (alien) የማይታወቁ ፍጠራን የሚያስቆጥረው እንደነበር የፈፀመው ግፍ ህያው ምስክር ነው።
አዲስ ዘመን:- የዛሬ ዓመት መቀሌ ላይ የህወሓት ምስረታ በዓል ሲከበር የነበረው ስሜት እና ድባብ ምን ይመስል ነበር፤ በወቅቱ ምን ታዘቡ?
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:– የካቲት 11 በነበረው የህወሓት የምስረታ በዓል ነው ወይስ የትግራይ ህዝብ የ17ቱ የትጥቅ ትግል መጀመሪያ ዕለት የሚለው ጥያቄ ውስጥ አስገብተን አምና የነበረው አከባባር ስንመለከት፤ አምና በዓሉ ሲከበር እጅግ ደመቅ ብሎ በመቀሌ እና በተለያዩ ከተሞች ተከበሮ እንደነበር ሁላችንም እናስታውሰዋለን፤ ለዚህም ዋና ምክንያቱ የ45ኛ ዓመቱ መከበር ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ለበዓሉ ደመቅ ብሎ መከበር ሁለት ምክንያቶችም ነበሩ፤ አንደኛው ምክንያት በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረው ተጨባጭ የስጋት ስሜት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ህወሓት በህዝቡ ዘንድ ይበልጥ ለመሸሸግ የሚያስችለውን እድል ለመፍጠር አልሞ በመንቀሳቀሱ ነበር።
ከበዓሉ በኋላ ህወሓት በህዝቡ ዘንድ ይበልጥ ተሸሽጌያለሁ ብሎ በማመን ህገ-ወጥ ምርጫ እስከማካሄድና ጦርነት እስከመክፈት ያደረሰው እብደታዊ ተግባር ውስጥ ገብቶ ታይቷል። ነገር ግን ህዝቡ በዛ ደረጃ በነቂስ ወጥቶ በዓሉን ያከበረው በህወሓት የመሪነት ውድቀት ምክንያት የተሰማውን ስጋት ዞር ለማድረግ እንዲሁም እንደህዝብ በማይደራደርባቸው ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም ለመግለጽ ነበር።
ይሁንና የትግራይ ህዝብ ያምናውን በዓል ወጥቶ ሲያከብር ህወሓትን ለማጀብና ተስፋ እንዳለው ለመግለጽ ፈልጎ አልነበረም። ይህ መሆኑም ህግ የማስከበር እርምጃው ሲካሄድ ህዝቡ ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም በማሳየቱ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ለየቅል መሆናቸው በገሃድ ታይቷል።
አዲስ ዘመን:- ህወሓቶች ከሌሎች ትላልቅ ሃገራዊ ክብረበዓላት ይልቅ የካቲት 11 ቀን ልዩ ትኩረት ይሰጡ ነበር። ይህ አካሄዳቸው ፓርቲውን ከሃገር በላይ አድርገው የመቁጠር ዝንባሌ እንደነበረባቸው በተጨባጭ ያሳያል የሚሉ አሉ፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው ብለው ያስባሉ?
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:- በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቀናት በዓላት ተደርገው ይከበሩ ቢባል በርካታ በዓል መሆን የሚችል ቀናት ማግኘት የሚቻል ይመስለኛል። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ የተሰራባቸው ቀናት ታሪክ ካልተሰራባቸው ቀናት ጋር ቢነፃፀሩ ከጥንት ጀምሮ ታሪክ የተሰራባቸውና በዓል መሆን የሚችሉት ቀናት በእጅጉ ስለሚበዙ ነው።
የየካቲት 11ድን በዓል ከሌላ ቀን ጋር አወዳድሮ የትኛውን ማክበር ይሻላል የሚል ምርጫ ውስጥ ግን መግባትም እምብዛም አስፈላጊ አይመስልኝም እንደእኔ። ነገር ግን የህወሓት ቡድን ለረጅሙና ለደማቁ የኢትዮጵያ ታሪክ ክብር ያልነበረው ስብስብ መሆኑ ሊሰመረበት ይገባል።
ቅድምም ለመግለጽ እንደሞከርኩት የህወሓት ቡድን የትግራይን የመላ የኢትዮጵያ ህዝብን ስነ-ልቦናና ታሪክ በቅጡ የማያውቅ አይደለም። ካወቀም ከራሱ ስልጣንና ዝና አንፃር ብቻ በማየት የህዝብና የአገር ታሪክ የሚያንኳስስ ቡድን ነው፤ ከቻለም ታሪኩን ለማጥፋት የሚጥር ኃይል ነበር።
ይህ አስተሳሰቡና ተግባሩም ለራሱም ሳይበጀው ቀርቶ በስተመጨረሻ የእራሱ ታሪክ፣ ዝናና እድል ለአደጋና ለኪሳራ ጥሎ ጠፍቷል። ከዚህ ውድቀት ሁላችንም የምንማረው አንድ ወሳኝ ነገር ቢኖር… ታሪካችን በምልአት እና በተገቢው አውድ ማወቅና ማክበር እንደሚጠበቅብን ነው። እንደዛ ስናደርግ ብቻ ነው እውነተኛ ማንነታችንን መረዳት የምችለው።
ይህንን ስናደርግ ነው እንዴት ወደ ፊት መጓዝ እንዳለብን የምናውቀው፤ እንደዛ ስናደርግ ነው መጪውን የብልጽግና ዘመን ብርሃናማ ማድረግ የምንችለው የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን:- ከዚህም በላይ ህወሓቶች ለታሪክ ከበሬታ እንደሌላቸው ይነገራል፤ በተለይ የትግራይ ህዝብም ሆነ ከህዝብ ለወጡ በታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ግለሰቦች ጭምር ለመቀበል እንደሚከብዳቸው ይነገራል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:- ልክ ነው፤ ህወሓቶች ለታሪክ ከበሬታ የላቸውም ብቻ ሳይሆን ታሪክን እንደጠላትም ጭምር ነበር የሚያዩት። ይህ ማለት ደግሞ በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ ታሪክ ለነሱ ለመረዳትና ለማድነቅ ከአቅማቸው በላይ ነበር።
ለሴራ ፖለቲካቸው የማይመች ሆኖ ስለሚያገኙትም ታሪክን እንደጠላት ያዩታል። በተለይ በትግራይም ሆነ በኢትዮጵያ የነበሩ የስመጥር ሰዎችና መሪዎች ታሪክ እና ዝና እጅግ ያስፈራቸዋል።
አይደለም የሩቅ ዘመን ታሪካችን ውስጥ የተፈጠሩ ስመጥር ሰዎችና መሪዎች በትጥቅ ትግሉ ጊዜ የነበሩና እንዲሁም በየጊዜው ድርጅቱን ለቀው ይወጡ የነበሩ ስመጥር ታጋዮች ስም ሳይቀር ያስፈሯቸዋል። ከዚህ የተነሳም ለታጋዮቹም ጭምር የሚገባቸውን ክብር እንዳያገኙ ያደርጉ ነበር።
ከዚህ በባሰ መልኩም አማራጭ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎችም ጭምር የማሸማቀቅና የማንገላታት ደባዎች ይፈጸምባቸው ነበር። ስለዚህ የህወሓት ቡድን አባላት ለታሪክ፣ ለስመጥር ሰዎችና መሪዎች ብቻ ሳይሆን በሃሳብ ለተለያቸውና በብቃት ለበለጣቸው ሰው ሁሉ የክፋት ወጥመዳቸውን ሲያጠምዱ የኖሩ ሴረኞች ነበሩ።
አዲስ ዘመን:- ምንም እንኳን የብልጽግና ፓርቲ አመራር ቢሆኑም የዘንድሮው የየካቲት 11 ህወሓት ምስረታ ቀን እንዴት ባለ መልኩ ያልፋል ብለው ያስባሉ?
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:– እንደ ብልጽግና ፓርቲ አመራርም እንደ አንድ ትግራዋይ ኢትዮጵያዊም ሃሳብ መስጠት ይቻላል፤ ብልጽግና አቃፊ ነው ስንል በተግባር በሚገለጽ እውነታ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
በዓሉ በክልል ህገ-መንግስት ስለተደነገገ እንዲሁም ከህዝብ ጋር በእጅጉ ስለሚያያዝ መከበሩ ይደገፋል። ምክንያቱም ለህጎችና ለህዝባዊ አጀንዳዎች ክብር ስላለን፤ ነገር ግን ቅድምም ለመግለጽ እንደሞኮርኩት በዓሉ ህዝባዊነትና አገራዊ አንድነት በሚያከብር መልኩ ቢያልፍ እና ቢያንስ የህዝብን የአንድነት ስሜት በማይነካ መልኩ መከበር አለበት የሚል እምነት አለኝ በግሌ።
ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲና ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚከፈል መስዋእትነትም በሁሉም ዘንድ የሚከበርና የሚደገፍ ይመስለኛል። ከዚህ በተጨማሪም በዓሉ ወጪ ቆጣቢና ጊዜውን በሚመጥን መልኩና እውነተኛ አላማዎቹ ላይ አተኩሮ ቢከበር መልካም ነው።
አዲስ ዘመን:- በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ከየካቲት 11 ቀን ጋር ተያይዞ የተለየ የሚያደርገው ጉዳይ ይኖር ይሆን?
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:– ጨቋኙና በዝባዡ የህወሓት ቡድን ከስልጣን ከመወገዱ ጋር ተያይዞ የዘንድሮ የካቲት 11 ቅድም ያነሳናቸው ነጥቦች በሚያሟላ መልኩ የሚከበርበት እድሉ ሰፊ ነው። ማለትም ህወሓት ከመወገዱ ጋር ተያይዞ በዓሉ ህዝባዊነትና አገራዊ አንድነት በሚያከብር መልኩ እንዲያልፍ የማድረግ እድሉ ሰፊ ነው።
በሌላ መልኩ ደግሞ የስርዓቱ ቅሪቶች ቀኑን ሰበብ አድርገው ህወሓት ተመልሳ ትመጣለች የሚል ከንቱ ወሬ በመንዛት ህዝቡ ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር ሊሞክሩ ይችሉ ይሆናል። በተለያየ መንገድ ስለዚህ አሉታዊ ሃሳብ ሊሰብኩ ይችላሉ።
ነገር ግን ህዝቡ ስለህወሓት እና ስለወቅታዊው የትግራይ ሁኔታ ትክክለኛ ግንዛቤ እየጨበጠ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ብዙ ውጤት አይኖረውም። የሚነዛው ወሬ ውጤት እንዳይኖረውም ህዝብም ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ እና እውነታውን በበለጠ እንዲረዳ እየተደረገ ነው፤ በዚህ ረገድ በተለያዩ አማራጮች ስራዎች እየተሰሩ ነው።
አዲስ ዘመን:- ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ያሉ ሰዎች ህወሓት ተመልሶ ወደስልጣን ይመጣል በሚል በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ጭምር የተለያየ ነገር ሲያወሩ ይደመጣል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሃሳብ አለዎት?
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:– ህወሓት ተመልሶ ይመጣል የሚል ወሬ ከፍተኛ ጭንቅና ተስፋ መቁረጥ የወለደው የጥቂቶች ከቡድኑ ጋር የቆረቡ ሰዎች ፕሮፖጋንዳ ነው። ከዚህ በኋላ ህወሓት ወደስልጣን ተመልሶ የሚመጣበት አንዳችም እድል የለውም።
የህወሓት ቡድን ሞት እና የአመራሮቹ ህልፈት ተፈጥሯዊ ሞት ነው፤ ያንን የሚቀናቀን እና ሊቀይር የሚችል አንዳች ምድራዊ ሃይልም ሆነ እድል የለም። በአካልም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን እንደታየው የህወሓት አመራሮች አንዳንዶቹ በህግ ቁጥጥር ስር ናቸው፤ ሊሎቹ በህይወት የሉም። ስለዚህ ህወሓት ተመልሶ ይመጣል ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን:- በትግሉ ወቅት በቅንነት ዋጋ ለከፈሉ የህወሓት የቀድሞ አባላት እና ደጋፊዎች አስመልክተው የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎ፤
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:- በጣም ጥሩ ነጥብ ነው! በትጥቅ ትግሉ ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ አያሌ የህዝብ ልጆች ቅድም ለጠቀስናቸው ህዝባዊ አላማዎች ሲሉ በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግር መስዋእትነት ከፍለዋል።
ህይወታቸውን ያጡ፤ አካላቸውን ያጎደሉ እና የተለያየ ችግር የደረሰባቸው እነዚያ ሃቀኛ የህዝብ ልጆች ለከፈሉት መስዋዕትነት እና ላደረጉት ትግል ምስጋናና ክብር ይገባቸዋል። የካቲት 11 መከበር ያለበትም እነዚህ ሃቀኛ የህዝብ ልጆችና የትግሉ ህዝባዊ አላማዎች በሚያስታውስና በሚያከብር መሆን አለበት።
በዚህ አጋጣሚም እንኳን ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያና ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሲባል የትግራይ ህዝብ ከብዙ ኢትዮጵያዊ ወንድም ህዝቦች ጋር በጋራ በመሆን ህዝባዊ ትግል የጀመረበት ቀን አደረሳቹ ለማለት እወዳለሁ!
አዲስ ዘመን:- መጨመር የሚፈልጉት ሃሳብ ካለ እድሉ ክፍት ነው።
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:- በስተመጨረሻ የምለው ነገር ቢኖር… የህዝቦች ጥያቄ በአግባቡ አለመመለስ ወደ ባሰ ነገር እንድንገባ ስለሚያደርገን ህዝባዊነትና ህዝብ አገልጋይነት ሁሌም መታወስና መተግበር ያለባቸው ነገሮች መሆናቸውን ማስመር እፈልጋለሁ።
በተለይ አሁን በደረስንበት የለውጥ ምዕራፍ ላይ የህዝብን ፍላጎት ማስቀደምና ህዝብ ማገልገል ቀዳሚ ስራችንና ግባችን መሆን አለበት። ይህን ሳናደርግ ከቀረን የታሪክ አዙሪትና ንትርክ ውስጥ ለመቆየት ወስነናል ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ ለማንም የሚጠቅም ጉዳይ አይደለም።
በመሆኑም የምንኮራባቸው የጋራ እና የተናጠል ታሪኮቻችንን በጋራ እየጠበቅን እና እየተጠቀምን ያጋጠሙ ክፍተቶች ደግሞ እንዳይደገሙ በማድረግ መጪው ጊዜ የብርሃን፣ የተስፋና የብልጽግና ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ ሃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን:- ለሰጡን ጊዜ እና ሃሳብ ከልብ እናመሰግናለን
አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል:- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2013