ፍቅሬ አለምነው
የሕወሃት ቡድን የተሰጠውን ሰፊ የሰላም እድል በንቀትና በእብሪት ሳይጠቀምበት ቀርቶ ራሱ በቆሰቆሰው ጦርነት ጠፍቶአል። በስልጣን ዘመኑ የዘረጋውን ምስጢራዊ መዋቅርና አባላቱን በመጠቀም ግለሰቦችንም በመግዛት እጅግ የከፉ ሀገር አፍራሽ ሴራዎችን በመላው ኢትዮጵያ ሲያዛምት ቆይቶአል።
በሀገራችን አራቱም ማእዘናት ነግሶ የነበረውን የሰላምና መረጋጋት እጦት ከጀርባ ሁኖ የሚመራው የሚያደራጀው የሚያስተባብረው በገንዘብ የሚረዳው ትህነግ ነበር። በሴራ ፖለቲካ ጥርሱን ነቅሎ ያደገው ይህው ቡድን ለታዋቂ ግለሰቦች ሞት፤ለዜጎች የእርስ በእርስ ግጭት፤ ለተለያዩ ከተሞች በሁከትና በረብሻ መውደም ዋናው መሪ ተዋናይ ነበር።
ታዋቂ ግለሰቦችን በመግደል በማስገደል ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት፤ ለአመጽ ማነሳሳት ረብሻና ሁከት እንዲነግስ ስርአተ አልበኝነት እንዲሰፍን ሁሉም ነገር ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ለማድረግ በስርአቱ አቅዶ ብዙ ሰርቶአል።ግን ደግሞ ሁሉም ሴራዎቹ መክነውበታል።
እኔ ስልጣን ከለቀቀኩ ኢትዮጵያ በእርስ በእርስ ጦርነት መታመስ ፤ በእልቂት መናጥ ፤ በደም መታጠብ ፤ብትንትኗ መውጣት አለባት በሚል ረዥም ርቀት ሄዶ ከጸረ ኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ጭምር በማበርና በመሰለፍ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ብዙ ሰርቶአል። አልሆነለትም።
በትግራይ ቴሌቪዥን ሲተላለፉ የነበሩትን የወያኔ ወታደራዊ ሰልፎችና ትርኢቶች አሮጊትና ሽማግሌዎችን ጭምር መሳሪያ እያስያዘ ሲፎክርና ሲሸልል ቁጭ ብድግ ሲሉ ድንፋታና ቀረርቶ ሲያሰሙ ላየና ለተመለከተ መልእክቱ ግልጽ ነበር።
ትግራይም ሆነ አዲስ አበባ ላይ ትኩረት አድርገው የሰሩት መከላከያ ሰራዊቱን እርስ በእርስ ለማባላት ለማፋጀት እንችላለን ብለው በሰፊው በምስጢር ተዘጋጅተው ነበር። ፕሮፓጋንዳ በመርጨት መከፋፈል ለመፍጠር ብዙ ርቀት ሄደው ሞክረዋል። በመከላከያ በሪፎርሙ ውስጥ የሰራው ድንቅ ስራ ሴራቸውን አምክኖታል።
ትግራይ መሬት የመጣ ይረግፋል፤ መቀበሪያው ይሆናል እስከማለት ደርሰው ነበር። ቅጥ ያጣ እብሪትና መዳፈር የነገሰበት ሁኔታም ነበር። ሕዝብም በግርምት ቢያስተዋልም ቀጣዩ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ቀላል ነበር። አሮጌዎቹ የህወሓት ኮሚኒስቶች የወቅቱ የአለም ፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ ከስረ መሰረቱ መለወጡን ማስተዋል አልቻሉም።
በነበሩበት ጥንታዊ እሳቤ ተቸንክረው ቀርተዋል። በእብሪት ድንፋታና ዛቻ ተሞልተው ሕሊናቸው ተጋርዶ ምስጢራዊ እቅዳቸውን ተማምነው ያዘጋጁትን ወታደራዊ ኃይል በመተማመን ያወጡት ወታደራዊ እቅድ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ብለው አስበውም ነበር።
ድል እናደርጋለን በጦርነት አሸንፍን በ3 ወር ግዜ ውስጥ አዲስ አበባ አራት ኪሎ ቤተመንግስት ተመልሰን እንገባለን ብለው ደምድመው ነበር። ግብዝነትና እብሪት የውድቀት በር ከፋች ናቸው።
የመንግስትን ሆደ ሰፊነትና ትእግስት ከፍርሀትና ከአቅም ማነስ የመነጨ አድርጎ የወሰደው ህወሓት በቀደመው ዘመን የነበሩ የኮሚኒስት ወታደራዊ ስልቶችን ተጠቅሞአል።
የቻይናውን ስመ ጥር ወታደራዊ ስትራቴጂስትና ፈላስፋ የሳንትዙንና የቪየትናም ጦርነት መሪዎችን የነጀነራል ጂያፕን በጠላት ላይ በአልተጠበቀ፤ በአልታሰበ፤ በአልተገመተ ሁኔታ በተመሳሳይ ሰአት፤ በብዙ አቅጣጫዎች ድንገተኛና መብረቃዊ ወይም የአውሎ ነፋስ ነጎድጓዳዊ ምትና ማጥቃት በመሰንዘር የድል ባለቤት መሆን እንችላለን ብለው ደምድመዋል።
እጅግ የከፋ ጭካኔና አረመኔነት በተመላበት መንገድ ተግባራዊ ማድረግ በአንድ ግዜ ለድል ያበቃናል ነበር እሳቤያቸው ይሄንን ፋሽታዊ እርምጃ ከመቀሌ ከተማ ጀምሮ በመላው ትግራይ ሰፍሮ በነበረው የሰሜን እዝ ሠራዊት ላይ ተግባራዊ አድርገዋል። አስገራሚው ነገር ከይሆናል እቅዳቸው ውጭ ባይሆንስ ባይሳካስ የሚለውን ተለዋጭ ሁኔታ ማስቀመጥ አልቻሉም። የገጠማቸውም ያላሰቡትም ችግር ይሄ ነው።
የጥፋት እቅዳቸውን ስለተማመኑ አልፈው ተርፈው መንግስትን ናና ግጠመን ፈሪ ነህ እስከማለት አብጠው ነበር። ለዚህም የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ጦርነት እንዲከፈት መወሰኑን ጭምር በይፋ ባይሆንም በቴሌቪዥን ለትግራይ ሕዝብ ያስተላለፉት የተዋጋ ጥሪ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው።
ከዚህ ቀደም ብሎ በነበረው የ2 አመት ግዜ ለረዥም አመታት ለመዋጋት የሚያስችላቸውን ደረቅ ቀለብ፤ የቀላልና ከባድ መሳሪያ ጥይቶች፤ መድኃኒቶች፤ ብዙ ሺህ ሊትር ነዳጅ ዘይት፤ የሳተላይት ኮሙዩኒኬሸን የሚያደርጉባቸውን መሳሪያዎች፤ ቀላልና ከባድ ተሸከርካሪዎች፤ በዘመናዊ መሐንዲሶች በመላው ትግራይ የተገነቡ የተለያዩ ኮንክሪት የመከላከያ ምሽጎችን፤ማዘዣ ጣቢያዎችን፤ የውስጥ ለውስጥ ዋሻዎችን፤ በመቀሌ ከተማና በገጠር እጅግ ከፍተኛ ወታደራዊ መሬቶች በሚባሉ ተራራዎችና በረሀዎች ውስጥ ሁሉ በምስጢር ገንብተውም ነበር። መገንባቱ ብቻ ሳይሆን አመራሮቹ ቀጠና ተከፋፍለው ከከተማ ወጥተው በየተራራው ገብተዋል።
ከዚያ በኋላ ነበር ወያኔ ድንገተኛና መብረቃዊ ማጥቃት ያለውን በሰሜን እዝ ሠራዊት ላይ የሰነዘረው። ከውስጥ ባሉ የትግራይ ተወላጅ በሆኑ መኮንኖችና የበታች ሹም በሆኑ ወታደሮች አማካኝነት በሰራዊታችን ላይ ድንገተኛ ማጥቃት ሰንዝረው እንደተኙ በእሩምታ ተኩስ ፈጇቸው።
ልብሳቸውንና ጫማቸውን አስወልቀው ለሕዝብ መሳቂያና መሳለቂያ እንዲሆኑ በመቀሌ ከተማ በባዶ እግራቸው እየተሰደቡ እየተተፋባቸው እንዲሄዱ ነው ወያኔ ያደረገው።
ያገታቸውን አገተ።የገደለውን ገደለ። ቀላልና ከባድ መሳሪዎችን መድፍና ታንኮችን ሚሳኤሎችን ያገኘውን ያህል እጁ አስገባ።እምቢ ለወያኔ እጅ አንሰጥም ያሉት ጀግና አዛዦችና ሠራዊታቸው በተለያየ አቅጣጫ እየተዋጉ መረብን ተሻግረው ኤርትራ ገቡ።
እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንሰሳ እኔ ካልገዛሁ ካልኖርኩበት ይውደም ብሎ በስንትና ስንት ሀገራዊ ሀብት የተገነቡትን የመንግስት ተቋማት፤ መንገዶች፤ ቢሮዎች፤ አየር ማረፊያዎች፤ ድልድዮች፤ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ንብረቶችን አበላሽቶ የትግራይን መሰረተ ልማት እንዳልነበረ አውድሞ በየበረሀውና በየተራራው ሸሽቶ የተደብቀው ይኸው ቡድን የራሱ ሕዝብ የለየለት ጠላት መሆኑን በገሀድ አስመስክሮአል። መቼም እውነተኛ የሕዝቡ ልጅ መሆን አይችልም።
በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ጉራውና እብሪቱ ተንፍሶ እየተደመሰሰ እየታደነ ትላልቅ ሹሞቼ የሚላቸው ጀነራሎቹ ሁሉ ሞተዋል። ተማርከዋል።በአሳፋሪ ሞተዋል፤ ውርደትም ተከናንበዋል። ህወሓት የትግራይ ሕጻናትን ለጦርነት አዘጋጅቶ መሳሪያ አስታጥቆ እሳት ውስጥ ማግዶ አስጨርሶአል።
በትግራይ የሚገኘውን የሰሜን እዝ እንዲበተን አድርጎ ድንበሩን ያለጠባቂና ያለተከላካይ ክፍት እንዲሆን ያደረገው ህወሓት፤ በጭካኔና በአረመኔነቱ ከናዚ በላይ ፋሽስት የሆነው ህወሓት፤ በምን መስፈርት ነው ስለትግራይ ሕዝብ ተቆርቋሪ ነኝ፤ ሴቶች ተደፈሩ፤ ንብረታቸው ተዘረፈ፤ ሰው አለቀ፡ ረሀብ ገባ ፤ የዘር ማጥፋት ተካሄደ ወዘተ ብሎ ሊያወራ ሊናገር የሚደፍረውስ?
ማነው የትግራይን ሕዝብ አሁን ለሚነገረው መከራ ችግር ረሀብ ጥፋት በአደባባይ አጋልጦ የሰጠው? ራሱ ህወሓት ነው። ዛሬ በውጭ የሚገኙት የትግራይ ተወላጅ ዲያስፖራዎች ለውጭ መንግስታትና አለም አቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያን መንግስት በመወንጀል የሚያቀርቡት ክስ ሁሉ ተቀባይነት የለውም። ውድቅ ነው።
በአውሮፓ ሰልፍ መውጣት ሜዳ ላይ መንከባለል የህወሓትን ናዚነት ፋሽስትነት አይሸፍነውም። አይለውጠውም። ዛሬ ነገሮች ሁሉ ተለውጠዋል። ትሕነግ ራሷ በቆሰቆሰችው ጦርነት ተደምስሳ አፈር ግጣ ወደ መቃብር ወርዳለች;።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2013