እፀገነት አክሊሉ
የካቲት 11 ቀን 1967 ዓም የደርግን ስርዓት ትጥቅ ትግል መፋለም የተጀመረበት ነው። ይህ ትግል ሲነሳ ሰንቆት የነበረው አላማም ኢትዮጵያን ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር ማድረግ። ህዝቧንም ካለበት ጭቆና አላቆ ሰብዓዊ መብቱ እንዲከበር ማስቻል እንደነበር የትግሉ መስራቾች በተለያየ ጊዜ ነግረውናል። ሆኖም በጊዜ ሂደት ውስጥ ትግሉን በአግባቡ የሚገራው አጥቶ አቅጣጫውን ስቶ ሀግርና ህዝብን ከፍ ያለ ዋጋ አስከፍሏል።
ማሕበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ (ማገብት) ምስረታ ጀምሮ በኋላም ህወሓትን ከመሰረቱት ጥቂት ሰዎች መካከል ዶክተር አረጋዊ በርሄ አንዱ ናቸው። በወቅቱ የትግሉ መስራችና ከፍተኛ አመራር ይሁኑ እንጂ ከድርጅቱ በልዩነት ተሰናብተዋል። ዶክተር አረጋዊ በርሄ ከረጅም ዓመት የስደት ህይወት በኋላ ለውጡን ተከትሎ ወደአገር በመግባት የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲን መስርተው በሊቀመንበርነት እየሰሩ ነው።
አሁን ላይም የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር በመሆን መንግስት የሰጣቸውን ሃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛሉ። እኛም የካቲት 11 ቀን 1967 ዓም በተመሰረተው ህወሓት የትግል ጅማሪ፣ ሂደት እና መጨረሻ / አሁናዊ ሁኔታ /በተመለከተ አነጋግረናቸው ፣እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን ፦ ደርግ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት ተራማጅ በሆኑ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች አማካይነት ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ (ማገብት) የሚል ማህበርን በመመስረት ከዛም ህወሃት እውን እዲሆን በማድረግ ነውና የትግል ጉዞዎን የጀመሩት ፤ በወቅቱ ትግሉ ሲጀመር የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
ዶክተር አረጋዊ ፦ የትግሉ አጀማማር በተደጋጋሚ ጊዜ እንደገለጽኩት “የህወሓት የፖለቲካ ታሪክ” በሚል በመፅሃፌም እንዳሰፈርኩት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ኖራ የብሔሮች እኩልነት እንዲረጋገጥ ህዝቡ አጥቶት የነበረው ፍትህ እንዲሰፍን በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ማስቻል የሚል እላማ ይዘን ነበር የተነሳነው፣ ድርጅቱም የተመሰረተው።
ይህንን ዓላማችንን ደግሞ ገና ከአዲስ አበባ ሳንወጣም ጀምሮ በጽሁፍ አስቀምጠው ነው ትግላችንን የቀጠልነው። ትግሉ እንደተጀመረም ፍጹም የቆመለትን አላማ ከግብ ለማድረስ የጣረ በታጋዮች መካከልም መተማመንና መደማመጥ ሀሳብን በነጻነት መግለጽን ያሳየ በጠቅላላው የትግሉን አካሄድ በሚገባ ያወቀ ነበር።
ሁኔታዎች ዋል አደር እያሉ ሲመጡ መልካቸውን እየቀየሩ እንዲያውም በውስጡ አክራሪና ጽንፈኛ ሰዎች እያቆጠቆጡ በመምጣታቸው የመገንጠል አላማን ሁሉ አነገቡ፤ በዚህም ውስጥ ውስጡን የበላይነት ለመያዝ ቻሉ። ከዚህም አልፈው ይህንን አስተሳሰባቸውን በማኒፌስቶ ደረጃም አስከማውጣት ደርሰው ነበር።
ነገር ግን ትግሉ አላማውን በፍጹም ሊስት አይገባውም በማለትና በመታገል ወደተነሳበት አላማ ለመመለስ ቻልን፤ ነገር ግን ለይስሙላ የእኛን ሃሳብ የተቀበሉ ቢመስሉም በአስተሳሰብ ደረጃ የተለወጡ ስላልነበሩ ውስጥ ወስጡን እየሰሩ ድርጅቱ ላይ ብዙ ችግር እንዲፈጠር አልፎም እኛ ከመሰረትነው ድርጅትና ካነሳሳነው ትግል እንድንገለል ሆነ።
እኛን ከትግሉ ካባረሩ በኋላም ብዙ ሽኩቻዎች ያስተናገዱ ቢሆንም ድል ቀንቷቸው የደርግን ስርዓት መገርሰስ ቻሉና ስልጣን ያዙ። ይህንን መጥፎ አስተሳሰባቸውንም በህገ መንግስት ደረጃ ሳይቀር አስፍረው በመላው አገሪቱ ዛሬ እስከደረስንበት ደረጃ ድረስ ያሉ በርካታ ችግሮችን ለመፍጠር ችለዋል።
አዲስ ዘመን ፦ ትግሉ ሲጀመር አንግቧቸው የተነሳቸውን የዴሞክራሲም ይሁን የህዝቦች እኩልነት እንዲሁም የፍትህ ጥያቄ ከትጥቅ ትግል ውጪ ባሉ አማራጮች ማቅረብ አልቻላችሁም ነበር ወይስ መፍትሔው ይኸው ብቻ ነው ብላችሁ አስባችሁ ነው?
ዶክተር አረጋዊ ፦ በወቅቱ ምንም አማራጭ አልነበረም። ምክንያቱም የተማሪውን እንቅስቃሴ በሀይል ነጥቆ ስልጣን የያዘው ወታደራዊ ሀይል ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን የተከተለም አልነበረም።
በመሆኑም ደርግ ስልጣን ሲይዝ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የ መፈክርን ይዞ ነው የተነሳው ፤ ከዚህ አንጻር ደግሞ የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብት መጠበቅ ጉዳዩም አልነበረም፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን የሚያነሱ ቡድኖችን ወይም ግለሰቦችንም ከመጀመሪያው ጀምሮ በሀይል የመደፍጠጥ ተግባር ሲፈጸም ነበር፤ ከዚህ አንጻር በሰላማዊ ትግል ደርግን መፋለም የማይቻል በመሆኑ እንዲሁም በርካታ የአፍሪካ ወታደራዊ አመራሮች ምን ሲያደርጉ እንደነበርም ጥናቶችን በማድረጋችን ይህንን ሀይል በታጠቀ ህዝባዊ ሀይል ብቻ ነው መገርሰስ የሚቻለው የሚል አቋምን ይዘን ነበር የወጣነው።
ሌሎች አማራጮች አልነበሩም ወይ ላልሽው በሀሳብ ደረጃ ማየት ይቻላል ነገር ግን መሬት ላይ ወረድ አድርገን በተግባር ካየነው የማይቻል በመሆኑ ነው ከተማሪው ንቅናቄ ጋር በማያያዝ የርእዮት አለም ጉዳይ ተዳምሮበት ወደ ትግል የገባነው።
አዲስ ዘመን፦ ህወሓት ሲመሰረት በመልካም ሀሳብ በታጋዮቹ መከካልም ፍጹም ዴሞክራሲያዊ በሆነና በመተማመን መመስረቱ ተደጋግሞ ይነሳል ፤ ነገር ግን ውስጥ ውስጡን እየሄዱ ደግሞ ሴራ የሚሸርቡ አካላት እንደነበሩም ጠቀስ አድርገዋልና ይህ ግን ሳታውቁት ወይም እያወቃችሁት በመካከላችሁ የተፈጠረ ችግር ነው ?
ዶክተር አረጋዊ ፦ በጠቅላላው ሲታይ በትግሉ ውስጥ ለግል ጥቅሙ ስልጣንን አብዝቶ የሚፈለግ እና ለህዝብ ጥቅም የወገነ ነበር። ይህ ደግሞ ችግሩን ፈጥሯል። የዛን ጊዜ የስልጣን ጥማቸው ሰላሳ አመት እንኳን በስልጣን ላይ ቆይተው በቃን እንዳይሉ እያደረጋቸው መሆኑን እየታዘብን መጥተናል።
እነዚህ አሁን ላይ ራሳቸውን ወደ ጁንታነት የቀየሩት አባላትም ያን ጊዜም ቢሆን ህልማቸው ሁሉ ስልጣን ብቻ ነበር፤ የህዝብን ህይወት ማስተካካልና መለወጥ ለእነሱ እንደ ትርፍ ነገር የሚታይ ነበር። ይህ ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት በተግባር ያሳዩት ሀቅ ነው። በጽሁፍም ቢሆን መጀመሪያ ቻርተር ብለው ያዋቀሩት ቀጥሎም ወደህገ መንግስት የቀየሩትን ማየት በቂ ይመስለኛል።
በመሆኑም ይህ የስልጣን ጥማታቸው በመካከላችን የተወሰኑ ልዩነቶች እንዲፈጠሩ አድርጎ ነበር፤ በዚህም ደግሞ እኔን ጨምሮ የተወሰኑ ሰዎችን ለመምታት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ሴራን የሚሸርቡ አካላትም ነበሩ።
አዲስ ዘመን ፦ ህወሓት ሲመሰረት መስራች በኋላም አመራር ነበሩ፤ በመካከል ግን በተፈጠሩ ልዩነቶች ምክንያት ከድርጅቱ ተሰናብተዋል፤ በወቅቱ ይህ ሁኔታ ምን ፈጠረብዎት?
ዶክተር አረጋዊ፦ ብዙ አቅደሽ ብዙ ዋጋ ከፍለሽ ነገ ደግሞ ለህዝቤ አዲስ ቀን አወጣለሁ ብለሽ ከጀመርሽው ትግል መውጣት በጣም ደስ የማይል ስሜትን ይፈጥራል፤ ነገር ግን ሰዎቹ እያወቁ ወደ ጥፋት መንገድ እየሄዱ ዝም ማለት ደግሞ እንደ አንድ ዜጋ የህዝብ አደራ እንዳለበት ግለሰብ በጠቅላላው ህሊና እንዳለው ሰው ዝም ማለቱ እጅግ በጣም ከባድ ስህተት ነው።
እኔ በበኩሌ ትግሉንም የተቀላቀልኩት የህዝቡን የዘመናት ችግር ወይም ጥያቄ በተቻለኝ አቅም ራሴን ሰውቼ ለመፍታት ስለነበር እነሱ ከዚህ መስመር ሲያፈነግጡ አቅጣጫው አሳይቼ ለመቀጠል ጥረት አድርጌያለሁ፤ ግን ደግሞ የማይሆን ሲሆን ትግሉን አቋርጬ መውጣት ነበረብኝ። እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ በጣም ከባድ ነበር።
አዲስ ዘመን ፦ በወቅቱ ልዩነቱን በመነጋገር መፍታት አይቻልም ነበር?
ዶክተር አረጋዊ፦ አልነበረም። በእኔ በኩል ብዙ ሙከራዎችን አድርጌያለሁ። እንዲያውም ከድርጅቱ ካባረሩኝ በኋላ ሁሉ ሁለት ዓመት አብሬያቸው ቆይቻለሁ።
ይህንን ያደረኩበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ምናልባት ሃሳባቸውን መቀየር ችለው በንግግርም ተግባብተን ወደትግሉ እመለስ ይሆናል የሚልም ተስፋ ስለነበረኝ ነበር ፤ ነገር ግን የእነሱ የስልጣን ስስት ስግብግብነት አስተሳሰባቸውን ሁሉ ጨምድዶ ይዟቸው ስለነበር ሊለወጡ አልቻሉም፤ እንዲያውም እኔን እንደጠላት አንድ ቀን አደጋ እንደሚያደርስባቸው አካል በማሰብ ከበባው ፣ውክቢያው፣ መከታተሉ እና ትንኮሳው ስለበዛ እኔም ወጣሁ።
ህወሓቶች ሲፈጠሩ ጀምሮ በውይይት የሚያምኑ አልነበሩም፣ ያን ጊዜም በውስጥም በውጪም እንደመፈክር ይዘውት የነበረው ነገር ቶሎ ብሎ የስልጣን ማማውን መያዝ የሚል ነበር፤ ይህንንም በተግባር አሳይተውናል። ላለፉት 30 ዓመታት የአንድ ፓርቲ ሀያልነት አንግሰው ቆይተዋል። ይህም አልበቃ ብሏቸው የ40 እና 50 ዓመት እቅድ ሲያዘጋጁም ነበር፤ ከዚህ አንጻር ከእነሱ ጋር ተወያይቶ ልዩነትን አጥቦ በጋራ መስራት ለእኔ በጣም ከባድ ነበር።
አዲስ ዘመን ፦ ከድርጅቱ ከወጡ በኋላ ግን አካሄዳቸውን ሲያዩ ምን ይሰማዎት ነበር? ይህ ቀን እንደሚመጣስ አስበው ያውቃሉ?
ዶክተር አረጋዊ ፦ አዎ ! የጊዜ ጉዳይ እንጂ አካሄዳቸው ወደገደል እንደሚከታቸው ህዝቡም ነቅቶ እንደሚነሳና እንደሚያምጽባቸው ይታየኝ ነበር። ለዚህም ነው ያለእረፍት እታገላቸው የነበረው።
የታየኝ ነገር ደግሞ መሬት ጠብ ያለማለቱን የምታይው በስልጣን ጥማት ምክንያት ያገለሉን የትግሉ ጠንሳሾች እዚህ ደርሰን እነሱ ደግሞ እንዳይሆን ሆነው ወድቀው ማየታችን ነው። ስለዚህም ነው ከተፈጠረው አዲስ ለውጥ ጋር ተያይዘን ሃሳባችንን መግለጽ የራሳችንን አስተዋጽዖ ማበርከት የቻልነው።
“ከስስታም አንድ ያንቀው አንድ ይወድቀው” ይባላል፤ ምክንያቱም የስልጣንም ይሁን የቁስ ስስት ምን ግዜም ጠልፎ ይጥላል። ስስታም ሁሌም ቢሆን ትኩረቱ የሚሰስተው ነገር ላይ በመሆኑና አካባቢውን ዙሪያ ገባውን ማየት ስለሚሳነው ስለማያገናዝብና ስለማይገነዘብ አወዳደቁ ቅርብ ነው ፤ ለዚህ ማሳያው ደግሞ የጁንታ ቡድን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ዘንድሮ 46 ዓመት ስለሆነው የትጥቅ ትግል ምን ይላሉ?
ዶክተር አረጋዊ ፦ የካቲት 11 ን ስናስታውስ ትግሉን የጀመርንበት ብቻ ሳይሆን ትግሉን በድል አጠናቅቀን የሀገራችንን ህዝቦች ዘላቂ ጥቅም የምናይበት በህዝቦች መካካል አንድነትን እና ትብብርን የምንፈጥርበት የብሔሮች እኩልነት ከምን ጊዜውም በላይ የሚረጋገጥበትን መንገድ ለማመቻቸት ያሰብነውን ሃሳብ ሁሉ ነው።
በሌላ በኩልም የካቲት 11 ብለን ጫካ ስንገባ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንደ ስትራቴጂ ያስቀመጠ በክልሎች ላይ ያለው የብሔር ጥያቄንም መፈታት እንዳለበት እንደ አጀንዳ የተያዘ ነበር ። ይህ በጣም ትዝ የሚለኝ እውነታ ነው ። በሂደት ግን በአንዳንድ ስልጣን ወዳዶችና ስገብግቦች የታጠፈ የትግል መስመር ሆኖ ቀረ።
አዲስ ዘመን ፦ የካቲት 11 ከተነሳበት አላማ አንጻር ዛሬ ላይ ሆነው ውጤቱን ያስገኛቸውን ነገሮች እንዴት ይገልጿቸዋል?
ዶክተር አረጋዊ ፦ የካቲት 11 እንደዛ በጠንካራ ወኔ በህዝብ ፍቅርና በነጻነት ጥማት ለትግል የተወጣበት ቀን ቢሆንም ኋላ ላይ በተፈጠሩ ሁኔታዎች ምክንያት ግቡን ሳይመታ ቀርቷል። ይህ ደግሞ በግልጽ የሚታይ ሀቅ ነው።
ግን እንዲያው ግቡ ምንድን ነው ካልን ዋናው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መመስረት በዚህ ውስጥ ደግሞ የህዝቦችን ነጻነት፣ የብሔሮችን እኩልነት ማስፈን ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማስቆምና ሁሉም ዜጋ በአገሩ መሬት ላይ ተንቀሳቅሶ መስራት በሰላም የመኖር መብቱን ማረጋገጥ ነበር። ነገር ግን እነዚህ ሁኔታዎች ያን ጊዜ አላማ አድርገናቸው እንነሳ እንጂ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ በቅጡ የተከበሩ ካለመሆናቸው የተነሳ የየካቲት 11 ትግል ግቡን ሳይመታ ቀርቷል።
በነገራችን ላይ የካቲት 11 ትጥቅ ትግል ሲጀመር በኋላ ዋና ግብ የሆነው ስልጣን መያዝን አናስበውም ነበር ፣የትግሉ ግብም እሱ አልነበረም ፤ በእርግጥ ሂደቶቹ ተመችተው ስልጣኑንም ለመያዝ ችለዋል፤ ይህንንም ለትግሉ ግብ አድርገው የሚወስዱ አሉ፤ በተለይም ጁንታዎቹ አፋቸውን ሞልተው ድል አድርገናል ይላሉ።
ለእኔ ግን እርሱ ድል አይደለም ፤ ድል ማለት ከላይ ያስቀመጥናቸውን ዴሞክራሲያዊት አገር መመስረት የህዝቦችን እኩልነትና ነጻነት ማክበር ነበር። ከዚህ አንጻር መዝኜው ትግሉ ግቡን አልመታም እላለሁ።
አዲስ ዘመን ፦ ከዚህ ተነስተን አሁን ላይ የካቲት11 ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ የድል ቀኑ ነው ወይም በዓሉ ነው ማለት እንችላለን?
ዶክተር አረጋዊ ፦ በዓላቸው ልንለው አንችልም ፤ በእርግጥ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓም የተጠነሰሰው ትግል አፋኙን ደርግን ከምድረ ገጽ አጥፍቷል ፤ ይህ እንግዲህ አንድ ወታደራዊ ድል ነው። ነገር ግን በከተማ የነበረው ደርግ ከጫካ በመጣው ደርግ ነው የተቀየረው።
ከዚህ አንጻር የተገኘው ድልም የስርዓት ልውውጥ ሳይሆን አንድ አይነት ባህርይ ያላቸው አገዛዞች መንበር መቀያየር ከመሆኑም በላይ ከአፋኝ ስርዓት ወደ ሌላ አፋኝ ስርዓት ሽግግር የተደረገበት ድል የተጠነሰሰበት ነው። ከዚህ አንጻር ትግሉ በአገሪቱ ላይ እንዲሁም በህዝቦች አንድነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ብሎም የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ መሰረታዊ ለውጥን ያመጣ ነው ብዬ ለመውሰድ እቸገራለሁ።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ ደግሞ የጁንታው ርዝራዦች እንዲሁም ደጋፊዎች በየካቲት 11 ሌላ የትግል አቅጣጫ ቀይሰንና ተሰባስበን ዳግም ወደ አገር ማስተዳደር እንመለሳለን በሚል የሚያወሩት ነገር አለና በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ዶክተር አረጋዊ፦ አዎ ዳግም የአገር መሪ እንሆናለን እንመለሳለን የሚሉ ብዙ አሉ። ይህ ከአባባል በዘለለ ግን ምን ዓይነት ተስፋ ቢኖራቸው ምንስ አድርገው ወይስ የትግራይ ህዝብ ለእነሱ አሁንም ድጋፍ አድርጎ ነው የሚመለሱት ? ብለሽ ስታስቢ አርቆ ማሰቢያቸውን የተነጠቁ በቀቢጸ ተስፋ የሚኖሩ መሆናቸው ግልጽ ሆኖ ይታያል።
እነዚህ ሰዎች እኮ ከህግ ማስከበር ዘመቻው በፊትም መስከረም 30 ቀን ወደ ስልጣን እንመጣለን እያሉ ሲፎክሩ የነበሩ ናቸው ፣ያም አልሆነም። እንዲያውም ዛቻና ጉራቸው ለራሳቸው መቀበሪያ ሆኖ በአይናችን አየን። እዚህ ላይ ግን እነዚህ ሰዎች ያለፉትን 30 ዓመታት ህዝቡ ውስጥ የዘሩት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ህዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያምናቸው ያደረገ በመሆኑ እነሱ የማይሳካላቸውን ነገር ባወሩ ቁጥር የሚሸወድላቸው ብዙ ነው፤ ይህ ደግሞ ከባድ ነገር ቢሆንም ዋል አደር እያለ ህዝቡም ከጥቅማቸው ጉዳታቸውን እየተገነዘበ ስለሚሄድ ተሰሚነታቸውን ቀስ በቀስ አጥተው ብቻቸውን እንደ ቁራ እንደሚጮሁ ምንም ጥርጥር የለውም።
አሁን እንኳን በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት እነሱ ራሳቸውን ለማዳን እየፈረጠጡ ለህዝቡ ግን “አሀዳዊ መንግስትን “ ልንደመስስ እየሄድን ነው በማለት ከመቀሌ እየጮሁና ህዝቡንም እያስጮሁ ሲወጡ አይተናል፤ ይህ ደግሞ ህዝቡን የማታለል ስትራቴጂያቸው ነው። በዙሪያቸው ያሉና እነሱ የፈጠሯቸው ሚዲያዎችም ሴራቸውን ስለሚያርገበግቡላቸው ውሸቱን እውነት ብለው ለማሳመን አይቸገሩም።
የሚገርመው ነገር አሁንም መቀመጫቸውን አሜሪካን አገር አድርገው የሚተላለፉ የእነሱ ሚዲያዎች ይህንኑ እያራገቡ ነው፤ እነሱ ይህንን የሚያደርጉት እውነታውን አጥተውት ሳይሆን ባለፉት 30 ዓመታት ሀብት እንዲያካብቱ የተሰራላቸውን ውለታ ለመመለስም ጭምር ነው።
ነገር ግን ቆመንለታል አሁንም ወደ ስልጣን እንመጣለታለን የሚሉትና በአፋቸው ህዝባችን የሚሉት ትግራዋይ ቁልቁል ነው የሄደው። በእነሱ አገዛዝ ዘመንም በእርዳታ የሚኖር፣ በቂ የመጠጥ ውሃ ማግኘት የማይችል፣ ልጆቹ በተለያዩ ዓለማት የተበተነና በባህር እየሄዱ የሚሞቱበት ነው።
አሁን ህዝባችን ይበሉ እንጂ በስልጣን በነበሩበት ዓመታት አንድም ቀን አስታውሰውት ይህ ይደረግለት ብለው አያውቁም፤ ሚዲያዎቹም ቢሆኑ ህዝቡ ተቸግሯል ውሃ፣ ትምህርት ቤት፣ የጤና ኬላ ያስፈልገዋል ብለው አያውቁም ፤ይልቁንም ስለ ጌቶቻቸው ብቻ ነበር ቀን ከሌሊት የሚያወሩት፤ አሁንም ይህንኑ ነው እያደረጉ ያሉት።
አሁን ደግሞ የካቲት 11 ቀንን ምክንያት በማድረግ ከበሯቸውን እየደለቁ ነው ፤ ህዝቡ ግን አሁንም እነሱ በፈጠሩበት ችግር መከራውን እያየ የለጋሽና የመንግስትን እጅ እየጠበቀ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።
እውነት ለህዝቡ የሚያስቡ ስልጣንን የሚፈልጉትም በሀቅ ህዝባቸውን ለማገልገል ከሆነ አሁን ስለወደሙት መሪዎቻቸው ማላዘን ትተው ከህዝቡ ጎን በመቆም ከዚህ ሰብዓዊ ችግር የሚወጣበትን መንገድ በጋራ መፈለጉ ላይ ማተኮር ይገባቸዋል።
አሁንም የካቲት 11 ቀንን ዳግም ወደስልጣን መመለሻ መንገድ ሊያደርጉት ማሰባቸው የአእምሯቸውን መደንዘዝ የሚያመላክት ነው።
ምክንያቱም የትግራይ ህዝቡም ይሁን መላው ኢትዮጵያዊ ለውጥ ነበር የሚፈልገው የፈለገውለውጥ ደግሞ መጥቷል፣ ይህንን ወደፊት ለማስቀጠል መስራት ነው የሚያስፈልገው።
በተለይም በአሁኑ ወቅት የትግራይ ህዝብ መልሶ እንዲቋቋም ከገባበት ችግር እንዲወጣ የመሰረተ ልማት ችግሩ የረሀቡ የውሃ ጥሙ ሁሉ እንዲፈታለት ነው የሚያስፈልገው። ይህ እንዲሆን ደግሞ መንግስትም ሆነ መላው የአገሪቱ ህዝብ ከፍተኛ የሆነ ርብርብን እያደረጉ ነው። በቅርቡ እንኳን 75 ዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ እርዳታ አድራጊዎች ወደአገር እንዲገቡ ፈቅዶ እርዳታው እየተሰጠ ነው።
ለህዝብ መቆም ማለት ይህ ነው “እኔ ካልበላሁት ጭሬ ላፍሰው “ በማለት ብቻ ያለፈን እንዲመጣ መናፈቁ ለማንም አይጠቅምምና እውነት የካቲት 11 ቀንን ከልባቸው የሚፈልጓት ከሆነ ህዝባቸውን የሚጠቅም ከችግር የሚያወጣው ስራ በመስራት አጋርነታቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የዛሬ 46 ዓመት የካቲት 11 ቀን ወደ ትጥቅ ትግል ሲገባ እኮ እንኳን የትግራይ ህዝብ መላው ኢትዮጵያዊ ትግሉን በገሃድም በድብቅም የሚደግፍ ነበር። ነገር ግን ከድል በኋላ ለዚህ ህዝብ ውለታ የተከፈለው አፈና፣ ረሃብ፣ ጭቆና በስሙ መነገድ ብቻ ነው። አሁን ላይ ደግሞ ይህ ሁኔታ ህዝቡ በጣም ገብቶታል ለእነሱ ጥቅም የእነሱን የስልጣን እድሜ ለማራዘም የሚከፍለው መስዋዕትነት እንደሌለ የሚገብረው ልጅም እንደሌለው አሳይቷቸዋል፤ ህዝቡ ሁሉም ነገር ገብቶታል አንዳንድ የጁንታው ርዝራዦች ግን ይህ ነገር የገባቸው አይመስልም። በመሆኑም ሙከራቸው ተስፋ ያጣ የቀን ቅዠት ነው ።
አዲስ ዘመን ፦ የካቲት 11 በትግራይ እናቶች ወጣቶች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነበር፤ አሁን ላይ ደግሞ የትግሉ ሁኔታ መልኩን ቀይሯልና ከዚህ አንጻር እርስዎ ለህዝቡ ለወጣቱ የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድን ነው?
ዶክተር አረጋዊ፦ ጥሩ ነው! የትግራይ ህዝብ ከችግሬ እላቀቃለሁ እለወጣለሁ እድገት ይመጣል ብሎም ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል፤ ልጆቹን፣ ንብረቱ ብቻ ምን አለፋሽ መልከዓ ምድሩን ሳይቀር ገብሯል። ከዚህ አንጻር ቀኑን ለጥሩ አላማ የተነሳሳበት አድርጎ ማስታወሱ ምንም ስህተት የለውም፤ ነገር ግን እነዛ አላማዎች አልተሳኩም፤ ስላልተሳኩ ዛሬ ላይ ቆም ብሎ እንደ አዲስ ማየት ምን ተሰርቶ ነው ስኬት ያልመጣው ወድቀቱ ከማን የመጣ ነው ፤ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። እዚህ ላይ ግን ይህ ውድቀት የህወሓት አመራሮች ነው በውስጡ ግን ህዝቡንም ይዘውት
ወድቀዋል። በመሆኑም ይህንን አላማውን እንደገና ከልሶና አይቶ ለሰላምና ዴሞክራሲ በአንድነት መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን በጁንታው ቡድን ላይ የህግ ማስከበር ዘመቻ ተካሂዶ ፍጻሜውን አግኝቷል፤ይህንን እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር አረጋዊ ፦ ለውጡ መሰረት እንዲይዝ ቀጣይ እንዲሆንና ጁንታው በሀሰት ፕሮፖጋንዳ የትግራይን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ለመነጠል የሚያደርገው ጥረት አንድ ቦታ መገታት የነበረበት በመሆኑ በጣም አስፈላጊ ነበር፤ እኔም በዚህ ህግ ማስከበር ዘመቻ እንደዛ ለያዥ ለገላጋይ አስቸግረው የነበሩ አካላት በዚህ መልኩ ወድቀው ሳያቸው ከፍተኛ የሆነ እርካታ ነው የሚሰማኝ።
እነዚህ ሰዎች እኮ በስሙ ለሚነግዱበት ህዝብ እንኳን መታመን ያልቻሉ አገርን ቁልቁል ወደገደል እየመሩ የነበሩ በጠቅላላው አስፈላጊ ያልሆኑ ነበሩ ፣ በዚህ መልኩ ተወግደው ህዝቡም ከሌላው የአገሩ ዜጋ ጋር እኩል ታይቶና ተጠቃሚ እንዲሆን የተጀመሩ ስራዎችን ጥሩ ናቸው።
አዲስ ዘመን ፦ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ነዎትና በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎ ምን እየሰራ ነው?
ዶክተር አረጋዊ፦ ማህበራዊ መሰረታችን ትግራይ ላይ እንደመሆኑና የአካባቢው ሰው ደግሞ በጣም ስለተጎዳ የህዝቡን ወቅታዊ ችግር በመፍታት ላይ ነው እየተረባረብን ያለነው። ለዚህም ስራ ይረዳ ዘንድ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ተቀናጅተን አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ሁሉ እየተጋገዝን፣ እየተረዳዳንና እየተመካከርን እየሰራን ነው።
እንደ የትግራይ ህዝብ እጅግ የተጎዳ የለም፤ ይህንን ምናልባት አብዛኛው ሰው ላይገነዘበው ይችላል ፤ ነገር ግን ህዝቡ ከጦርነት ወደ ጦርነት፣ ከችግር ወደችግር፣ ከረሃብ ወደ ረሃን፣ ከአፈና ወደ አፈና እየሄደ የነበረ ከመሆኑ አንጻር ችግሩ እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ አይደለም። የችግሩ ስር መስደድ የሚያሳየው ደግሞ በአንድ ወር ጦርነት መላው ክልል ረሃብ በረሃብ ሲሆን ነው ፤ ስለዚህ ይህንን ችግር ተባብረን የመፍታት ስራን ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥተን እየተንቀሳቀስን ነው።
የፖለቲካው ስራም ተትቷል ማለት ሳይሆን እኛ ማህበራዊ መሰረታችን የሆነው ትግራይ መልሶ ሳይቋቋም የምንቀሳቀሰው ነገር ስለማይኖር ለጊዜው እሱን አቁመነዋል፤ ምርጫ ቦርድም በትግራይ ክልል የሚደረገው ምርጫ እንዲራዘም ስላደረገ ይህ ለእኛ ጥሩ አጋጣሚ ከመሆኑም በላይ በመልሶ ማቋቋም ስራው ላይ ሙሉ ጊዜያችንን እንድናደርግ አግዞናል።
አዲስ ዘመን፦ ትዴፓ የጽህፈት ቤት ሃላፊው ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ለመስራት ወደአካባቢው አቅንተው አንደውም የውሃ ቢሮ ሃላፊም ሆነው ነበር፤ አሁን ደግሞ ተመልሰው እንደመጡ ይነገራልና ይህ ለምን ሆነ?
ዶክተር አረጋዊ፦ አዎ ወደ አካባቢው ሄደው በማገዝ ላይ ነበሩ ግን በስራ ላይ አንዳንድ አለመግባባቶች ስለተፈጠሩ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። ነገር ግን በቅርቡ ስብሰባ በማድረግ እንወያያለን ከዛ በኋላ ችግሮቹ ተፈተው ወደ ስራው ይመለሳል ፣ጊዜያዊ አስተዳደሩንም ያግዛል።
አዲስ ዘመን ፦ እንግዲህ የትግራይ ህዝብ በተለያዩ ጊዜያት በሚነሱ ጦርነቶች የተጎዳ አካባቢ ነው ከዛም በኋላ የጁንታው ቡድን በስሙ ሲነግድበት የኖረ ህዝብም ነውና እንደው ይህ ህዝብ በተለይም አሁን ካጋጠመው ሰብዓዊ ቀውስ በቶሎ ያገግም ዘንድ ዘላቂ መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር አረጋዊ፦ አዎ ህዝቡ በጣም ተጎድቷል አሁን ላይ ደግሞ በተለይም የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ሰልችቶታል። ከዚህ ችግር ሊወጣ የሚችለው ደግሞ በተለይም አሁን ላይ መንግስት በጀመረው ልክ የእርዳታ አሰጣጥ ሂደቱን ተደራሽ ሲያደርግ አገር በቀልም ይሁኑ የውጭ አገር ለጋሽ አካላት ወደ ክልሉ ገብተው እውነተኛ የሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያደርጉ ከምንም በላይ ደግሞ የፈረሱ መሰረተ ልማቶች ተጠግነው ዳግም ወደ ስራ ሲገቡ ነው።
በዘላቂነት ግን ከችግር ሊወጣ የሚችለው እንደከዚህ ቀደሙ አንድ ፓርቲ ችግሬን ይፈታልኛል ብሎ መቀመጥ ሳይሆን ተደራጅቶ ሃሳቡን መግለጽ የሚያስፈልጉት ነገሮች እንዲሟሉለት ግፊት ማድረግ ሲችል ብቻ ነው። አሁን እያሳለፈ ያለው ከባድ ጊዜ ያመጣበት ችግሩንም ስራውንም ለአንድ ፓርቲ ሰጥቶ ሳይደራጅ ቁጭ ማለቱ ነው፤ በመሆኑም ከዚህ በኋላ ባስፈለገው መልኩ ለራሱ ጥቅም ተደራጅቶ ጥቅሙን ማስጠበቅ መቻል አለበት ፤ ዘላቂ መፍትሔውም ይኸው ነው።
እስከዛሬ አውቅልሃለሁ በሚሉት አካላት የተሰጠው መፍትሔ የትም አላደረሰውም እናም አሁንም ከእነሱ መፍትሔ የሚጠብቅ ከሆነ ከዚህም የባሰ ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል። መፍትሔም ሊሆን አይችልም።
በዚህ መልኩ መብቱን በእጁ ካስገባ ደግሞ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ይጠቅመኛል ይሰራልኛል የሚለውን በካርዱ ይመርጣል ፤ እንዳሰበው ሆኖ ካላገኘው ደግሞ ማስወገድ መቻል አለበት።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር አረጋዊ፦ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2013