ሶሎሞን በየነ
ቀደም ሲል ምንም እንኳን መንግሥት የዲያስፖራ ፖሊሲ በማውጣት ዲያስፖራው በአገሩ ልማት እንዲሳተፍ፣ ኢንቨስት እንዲያደርግ፣ ለቤተሰቡ የሚልከውን ገንዘብም በህጋዊ መንገድ እንዲልክና የአገሩ ዲፕሎማት እንዲሆን ለማድረግ ያላሰለሱ ጥረቶች ሲደረግ ቢቆይም የተመዘገበው ውጤት አመርቂ አልነበረም።
ይህ ሊሆን የቻለባቸው የተለያዩ ተጨባጭ ምክንያቶች ቢኖሩም ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚጠቀሰው ግን በአገሪቱ ግላዊና ፖለቲካዊ ነፃነት አለመኖር፣ የመንግሥት ፖሊሲዎችና አመለካከቶችም ለዳያስፖራውና ለግሉ ዘርፍ አመቺ አይደሉም የሚል አመለካከት መስፈኑ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ፣ እርግጡን ለመናገር ዳያስፖራው መንግሥትን እንደ ጠላት ሲያየው ነው የኖረው፡፡
ነገር ግን በአገሪቱ የመጣውን ፓለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በመንግሥት ላይ የነበረውን የጠላትነት አመለካከት በመቀየር ፊታቸውን ወደ አገራቸው እንዲመልሱና ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ የሚቻልበት ልዩ ዕድል የተፈጠረበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል፡፡
በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎም መንግስት በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ባመቻቸው እድል መሰረት በርካታ ዳያስፖራዎች በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በቱሪዝም ዘርፎች በመሰማራት ራሳቸውንናአገራቸውን በመጥቀም ላይ ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን ዳያስፖራ አንድ ዓይነት ባህሪና መገለጫ ያለው አንድ የተወሰነ ቡድን አይደለም፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያን ዳያስፖራ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በግርድፉ ብናየው፣ 90 በመቶው ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ በካሸርነት፣ በታክሲ ሾፌርነት፣ በመስተንግዶና በመሳሰሉ የአገልግሎት ዘርፎች ዝቅተኛ የሥራ ቦታዎች ላይ ተቀጥሮ የሚሠራ ነው፡፡
የተቀረው አሥር በመቶ ዳያስፖራ አብዛኞቹ ደግሞ ሬስቶራንቶች፣ ካፌዎች፣ ሱቆችና ጥቃቅን የአገልግሎት ዘርፍ ኩባንያዎችን የመሳሰሉ የአነስተኛ ንግድ ድርጅቶች ባለቤቶችና ሕክምና፣ ሕግና ምህንድስናን በመሳሰሉ የተለያዩ የሙያ መስኮች የሚሠሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ ከአጠቃላዩ የዳያስፖራ ቁጥር አንፃር ሲታይ ገንዘብ፣ ዕውቀትና ልምድ ያካበቱ እንዲሁም ወደ አገራቸው ተመልሰው እሴት የሚጨምሩ፣ መጠነ ሰፊ የንግድ ተቋማትን የማቋቋም ፍላጎቱ ኖሯቸው ኢንቨስተር ሊሆኑ የሚችሉ ዳያስፖራዎች ቁጥር እጅግ አናሳ ነው፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያዊው ዳያስፖራ የሚገኝበትን አጠቃላይ ተጨባጭ ሁኔታ በቅጡ መገንዘብ፣ በየደረጃው ለሚገኘው የዳያስፖራ ቡድን የሚመጥን የዳያስፖራ ፖሊሲና የማበረታቻ ማዕቀፍ ለመቅረፅ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያዊው ዳያስፖራ የሚገኝበትን አጠቃላይ ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ኤጀንሲ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ከውጭ ተመላሽ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ሊሳተፉባቸው በሚችሉ የንግድና ኢንቨስትመንት ፓኬጆች (አማራጮች) ማዘጋጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ከሰሞኑ ምክክር አድርጓል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንደገለጹት፤ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዳያስፖራዎች በተለይ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን ያላቸው አስተዋጽኦ የተገደበ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።
ለዚህም ዳያስፖራዎቹ ያላቸው አቅም ውስን መሆኑና እነሱን ሊያስተናግዱ የሚችሉ በቂ ፓኬጆች አለመኖራቸውን በምክንያትነት የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ እነዚህ ዜጎች ረጅም ጊዜ በስደት ኖረው ሲመለሱ ማረፊያ የሚያጡ አብዛኛዎቹ የዲስፖራ አባላት እንዳሉ ገልጸው የኢንቨሰትመንት ፓኬጅ ቢዘጋጅ ራሳቸዉ የሚሰሩትና ለአካባባያቸዉ የስራ እድል የሚፈጥሩበት አዲስ የሆነ እሳቤ ይዞ ይመጣል ብለዋል፡፡
ለእነዚህ ዜጎች ምቹ ሁኔታን መፍጠር ከተቻለ ከስደት መልስ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መውጫ መንገድ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ እንደሚቻል ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
የኤጀንሲዉ ምክትል ዳሬክተር ዶ/ር መሃመድ ኢንድሪስ በበኩላቸው፤ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዲያስፖራዎች የሚሳተፉባቸው የቢዝነስና የኢንቨስትመንት አማራጭ እና እድሎች መፍጠር ዋነኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ህገ ወጥ መንገዶችን ተጠቅመው የሚላኩ ገንዘቦችን በህጋዊ መንገድ እንዲላክ ለማድረግም ያስችላል ብለዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የነበረው የፖሊሲና እና የአተገባበር ክፍተቶች አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ዲያስፖራዎች በኢንቨስትመንቱ እንዳይሳተፉ እድርጓቸዋል ያሉት ዶክተር መሃመድ፤ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዲያስፖራዎች አብዛኛዎቹ ቋሚ ገቢ አላቸው። ነገር ግን የቁጠባ ባህሉ ዝቅተኛ ነው።
ያለውንም ገቢም ወደ ኢንቨስትመንቱ የመቀየር እድሉ የለም፡፡ ስለዚህ ቋሚ ገቢውን ወደ አገር በማስገባት ለዲያስፖራው፣ ለቤተሰቡ አጠቃላይ ለአገር ሊፈጥር የሚችለውን የፋይናንስ ጥቅም ለማሳደግ በጋራ ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራት ያስፈላጋል ብለዋል፡፡
አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን ዲያስፖራዎች በተለያዩ መድረኮች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን (ዶክተር) ጭምር በኢንቨስትመንቱ ለመሳተፍ ቢጠይቁም፤ እነርሱን ሊያሳትፍ የሚችል ፓኬጅ ባለመኖሩ በልማት ፕሮጀክቶች ላይ የራሳቸውን አበርክቶ እንዳያደርጉ እንቅፋት ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ ስለዚህ የዚህ ፓኬጅ ቀረጻ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው የዲያስፖራው ማህበረሰብ የዘመናት ጥያቄ መልስም ጭምር ነው ብለዋል ዶክተሩ።
በሌላ በኩል ከተለያዩ ባንኮች የመጡ ባለድርሻ አካላትም አጋርነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉና አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዲያስፖራዎች ለሃገራቸዉ ኢኮኖሚ የበኩላቸዉን አስዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዚህ የምክክር መድረክ ማጠቃለያ ላይ በውጭ አገር የሚኖሩ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በትውልድ አገራቸው በንግድና በኢንቨስትመንት ሊያሳትፍ የሚችል ልዩ የኢንቨሰትመንት አማራጭ በፓኬጅ መልክ በሚዘጋጅበት ሁኔታ ላይ ውይይት በማድረግ የጋራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2013