ውብሸት ሰንደቁ
በህይወትዎ “ተወዷል” እያሉ አንድ ኪሎ ቡና የገዙበትን ዋጋ ያስታውሱታል? ስንት ነበር? እምዬ ኢትዮጵያ አምና ለዚያውም የትየለሌ ሀገራት በጨረታ ተሻምተው አንድ ኪሎ ቡና 407 ዶላር እንደሸጠች ሰምተዋል?
አዎ! ይህ ክስተት ነበር ተብሎ የሚቀር እውነት አይደለም፤ ዘንድሮም የጥራት ውድድሩን አሸናፊው ቡና ከዚህ በላይ በሆነ ዋጋ እንደሚሸጥ እየተጠበቀ ነው:: ቡና በኢትዮጵያ ብዙም ግንዛቤው በሌላቸው አልሚዎች እየለማ ባለበት ወቅት ይህን ያህል ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘቱ ያስገርማል:: ቢሠራበት ደግሞ ምን ሊሆን እንደሚችል ለብልህ አይነግሩም… እንደሚባለው ተረት ነው::
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅና የዘንድሮው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ አስተባባሪ አቶ ግዛት ወርቁ እንደነገሩኝ በያዝነው ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያ 92 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ልካ 304 ሚሊየን ዶላር አግኝታለች:: ከባለፈው ዓመት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር ወደውጭ ተልኮ የተሸጠው ሲሶ ያህል ቢሆንም በሁሉም ዓመታት የመጀመሪያው ስድስት ወር የሚላክ ቡና ላይ አነስተኛ አፈፃፀም ነው የሚመዘገበው::
ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ ቡና የምርት ጊዜ የሚጀምረው ከጥር አካባቢ ጀምሮ ስለሆነ ሽያጩ ከፍ ማለት የሚጀምረው ከዚሁ ወር ጀምሮ ነው:: በዚህም በሚቀጥሉት ወራት ከፍ ያለ የቡና መጠን እንደሚላክ ይጠበቃል:: በእርግጥ ባለፉት ስድስት ወራት የተላከው የቡና መጠን ዝቅ ያለ ቢሆንም ከአለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ግን የተሻለ ዋጋ የተሸጠበት ነው::
ከኢትዮጵያ ቡና ከፍተኛ ግዢ የምታካሂደው ከዚህ በፊት ጀርመን የነበረች ሲሆን በዚህ ዓመት ከፍተኛ ግዢ የፈፀመችው ሳዑዲ አረቢያ ሆናለች:: በዚህ ስድስት ወር ውስጥ ወደውጪ ከተላከው የኢትዮጵያ ቡና 21 ሺህ ቶን የገዛችው ሳዑዲ አረቢያ፣ 12 ሺህ ቶን ጀርመን ቀሪውን ደግሞ ሌሎች ሀገራት ግዢ ፈፅመዋል::
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ብዙ ነገሮችን እንዳወሳሰበው ሁሉ በቡና ገዢዎች ላይም ተፅዕኖውን አሳርፏል:: ሳዑዲ፣ ጀርመን፣ ቤልጅየም፣ ጃፓን የኢትዮጵያ ቡና ተቀባይ ሀገራት ናቸው::
ከዚህ ቀደም አሜሪካ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ገዢ ብትሆንም በዚህ ዓመት ኮቪድ 19 ባደረሰባት ቀውስ ዝግ ስለነበረች የኢትዮጵያን ቡና በቀዳሚነት ከሚገዙት ተርታ መሰለፍ አልቻለችም:: በተለይ የኢትዮጵያን ስፔሻሊቲ ቡና ገዢ ሀገራት የመቀነስ አዝማሚያ ታይቷል::
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ቡና አምራቾች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አበክሮ እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ግዛት ናቸው:: ቡና አምራቾች የዓለም አቀፉንና የአገር አቀፉን ዋጋ ባገናዘበና የቡናውን ጥራት ከግምት ውስጥ በአካተተ መልኩ ሚዛናዊ በሆነ ዋጋ መሸጥ እንዲችሉ ጥረት ይደረጋል::
የቡና አምራች ገበሬዎችን የቡና ጥራት ለማስጠበቅ የኢትዮጵ ቡና ላኪዎች ማህበር ቡና ጉንደላን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይም ይሳተፋል:: ገበሬዎቹ በጥራት ቡና እንዲያመርቱ የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ትልቁን ሚና እየተጫወተ ያለው የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ነው::
ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ በኢትዮጵያ ቡና ምርት ላይ ጥራት ያሻሽላል:: ምርቱ ጥራቱ ከተሻሻለ በተሻለ ዋጋ ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ስለሚሸጥ ለጥራት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል:: የኢትዮጵያ ስፔሻሊቲ ቡና ወይም ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና ሆኖ የመሸጥ አቅሙ ከፍ ያለ ነው:: ለዚህም የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጠው የስፔሻሊቲ ቡናን ለመሸጥ ነው::
ምክንያቱም የኢትዮጵያ ቡና ጥራቱ በገዢዎች ዘንድ የተወደደ እና ጥራቱም ጥሩ ነው ተብሎ ይታመናል:: ስለዚህ የኢትዮጵያ አብዛኛው የቡና ሽያጭ የስፔሻሊቲ ቡና እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው::
ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ እንደተለመደው ዘንድሮም የሚካሄድ ሲሆን ናሙና የመቀበል ሂደቱ ባለፈው ሳምንት ተጠናቋል:: ከጥር 24 እስከ የካቲት 03 2013 ዓ.ም የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ተወዳዳሪዎች ናሙና ቅበላ ሲካሄድ ነበር::
በዚህ ሂደትም ከ1800 በላይ ናሙናዎች ተሰብስበዋል:: ያለፈው ዓመት በፊት ከነበሩት የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ናሙና ቅበላዎች የተሻለ ሆኖ የተመዘገበ ቢሆንም የዘንድሮው ክብረ ወሰን የሰበረ የናሙና ብዛት ቅበላ ተደርጓል ::
ባለፈው ዓመት የገባው የቡና ናሙና 1ሺ402 ሲሆን በጊዜው ይህ ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነበር:: ዘንድሮም ለውድድር የቀረበው የቡና ናሙና ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፤ ማንቃት ላይ በተለያየ መንገድ የተሠራው ሥራ እና ገበሬው ጥራት ያለው ቡና ይዞ በማምረትና ለማቅረብ ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው:: ይህ በድምሩ የሀገሪቱን የቡና ጥራት ከፍ ያደርጋል፤ በተሻለ ዋጋ ለመሸጥም ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው::
አዲስ አበባ፣ ድሬደዋ፣ ሀዋሳና ጅማ የቡና ጥራት ውድድር (ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ) የናሙና መቀበያ ጣቢያዎች አሉ:: በዘንድሮው ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ናሙና በማቅረብ ከጅማ እና ከሀዋሳ የተሳተፉት ከፍተኛውን ቁጥር ይዘዋል::
የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ አሸናፊዎች ቡናቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄድ ጨረታ በውድ ዋጋ ይሸጥላቸዋል:: ባለፈው ዓመት የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ አሸናፊ የሆነው ቡና አንድ ኪሎ ቡና 407 ዶላር ሒሳብ ነው የተሸጠው::
በዚህ የተወሰኑ ገበሬዎች ይጠቀማሉ፤ ብዙ ቡና አምራቾች ደግሞ በበለጠ ጥራት ለማምረት ይነሳሳሉ፤ ይበረታታሉ:: እንደ ሀገር እና እንደ ቡና ላኪ ማህበር ሲታሰብ ግን ዋናው ጉዳይ የጥቂት ገበሬዎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አይደለም፤ አብዛኞቹ ገበሬዎች የቡና ጥራትን ለማሻሻል እንዲተጉ ያሥፈልጋል::
ቡና አምራቾች ጥራት ያለው ምርት ከተመረተ በጥሩ ዋጋ ሊመረት እንደሚችል ግንዛቤ ወስደው ለወደፊቱ የሚያደርጉት ማሻሻል ነው:: ይህ ነው እንደአጠቃላይ የኢትዮጵያን ቡና ጥራት ከፍ የሚያደርገው::
ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ላይ የቡናውን ዋጋ ከፍ ከሚደርገው አንዱ ቡናው በመመዘኛ መስፈርቶች መሰረት ያስመዘገበው ነጥብ ነው:: ባለፈው ዓመት በመመዘኛ መስፈርቱ 91 ነጥብ ያመጣው ቡና ነው አንድ ኪሎ 407 ዶላር የተሸጠው::
ይህ ቡና ይህን ያህል ነጥብ ባመጣበት ባለፈው ዓመት 168 በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ቡና ገዢዎች ናቸው በጨረታው የተሳተፉት:: በእርግጥ በአንዳንድ ሀገራት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሰው እንደልቡ ካፌዎች ጋር ሄዶ ቡና እንዳይጠቀም ከልክሎታል::
እነዚህ የተመረጡ ስፔሻሊቲ ቡናዎች ካፌ ውስጥ ይሸጣሉ እንጂ በኪሎ ተገዝተው በግለሰብ ቤት የሚቀመጡና ለአገልግሎት የሚውሉ አይደሉም:: ስለዚህ የዘንድሮ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ቡና አሸናፊ ላይ የዋጋ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል::
ኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ጫና ያመጣ ቢሆንም በቡና ኤክስፖርት ላይ ተፅዕኖው እንዳይበረታ ማህበሩ የተለያዩ የገበያ ቴክኒኮችን ተጠቅሟል:: ከገዢዎች ጋር በመግባባት ናሙና መላክና ማስቀመስን ጨምሮ በይነ መረብ ስብሰባዎችን በመጠቀም በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል::
በስድሰት ወራት ውስጥ እስራኤል፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አልጀሪያና ቻይና በመሳሰሉ ሀገራት በየኤምባሲዎቻቸው በኩል የሚፈጠሩ ዕድሎች በመጠቀም የኢትዮጵያን ቡና ጥራትን እና ያለውን ጥቅም ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል::
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ያለው ቀውስ አሜሪካ ያስገባችው ቡና ዝቅተኛ ነው:: ከዚህ በፊት ብዙ ስፔሻሊቲ ቡና በመግዛት የምትታወቀው ሀገር አሜሪካ ብትሆንም በስድስት ወሩ በኢትዮጵያ በመግዛት ደረጃዋ ወደ አምሥተኛ ልትወርድ ችላለች:: እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ቢኖሩም እንኳን በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ የስፔሻሊቲ ቡና ዋጋ የተሻለ እንደሚሆን ይገመታል::
ይህ የሚሆነው ባለፈው ዓመት ጥሩ ፉክክር በመኖሩ ምክንያት ቡና የሚያመርተው አርሶ አደር ጥሩ ቡና አምርቶ አንድ ኪሎ ቡና ስንት እንደሸጠ በደንብ ስለታየ በአርሶ አደሮች መካከል ከፍተኛ የጥራት ውድድር ስለሚኖር ጥሩ የቡና ጥራትና ዋጋ ይጠበቃል:: የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውጤት የሚታወቀው ሚያዚያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ነው::
የኢትዮጵያ ቡና ጥራት ስንል አብዛኛው ቡና በጥራት እንደማይመረት ይታወቃል ያሉት ሥራ አስኪያጁ ለዚህም እንዲህ በማለት አስረጂ ያቀርባሉ:: ለአብነት እንኳን ብናነሳ እስካሁን መሬት ላይ አስጥቶ ማድረቅ ያልቆመበት ነው::
ይህ የቡናን ጥራት ያጓድላል:: እነዚህን የመሳሰሉ ከግንዛቤ ማነስ የሚመነጩና በኋላ ቀር መንገድ የሚከናወኑ ነገሮች ጥራት የሚያጓድሉ ነገሮች ናቸው:: ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ይህንን ዓይነት ጥራት አጓዳይ ተግባራትን ለመቅረፍ በተዘዋዋሪም ቢሆን እየሠራ ነው::
በእርግጥ ቡና በፀሐይ መድረቁ ላይ ችግር የለበትም፤ ሲደርቅ ግን ከመሬት ሊኖረው የሚገባ ከፍታ አለ:: ቡና በፀሐይ መድረቅ ያለበት ከመሬት 70 እና 80 ሴንቲ ሜትር ከፍ ተብሎ በተሠራ አልጋ ላይ መሆን ይኖርበታል::
ይህ የሚሆንበት የራሱ ምክንያት አለው:: ቡና ከሌላ ያገኘውን ማንኛውም ሽታ መውሰድ ስለሚችልና አፈር ከነካ አፈር አፈር የማለት ባሕርይ ስላለው ነው:: ከአፈር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሽታ ከሚያስተላልፉ ነገሮችም መራቅ ይኖርበታል::
ስለዚህም ነው ቡና በክምችት ጊዜ በጥሩ ሁኔታ በተሠራ መጋዝን መቀመጥ አለበት የሚባለው:: በተመሳሳይ ሲጓጓዝም ንፅህናውን በሚጠብቅ መልኩ መጓጓዝ አለበት:: የቡና ጥራት ሊያጓድሉ የሚችሉ ነገሮች እነዚህን የመሳሳሉ ሌሎች በርካታ ነገሮች ናቸው:: ቡና በለቀማ ጊዜም እንኳን ከዛፉ ላይ መለቀም ይኖርበታል፤ ለዚያውም ቀይ ቀዩ ብቻ ተመርጦ ነው መለቀም የሚኖርበት::
እነዚህ ሁሉ የቡና ጥራትን የሚያጓድሉ ነገሮች ናቸውና ይህንን ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች መሠራት ይኖርበታል:: በእርግጥ ጥራት የማስጠበቁ ጉዳይ በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሂደት የሚቀየር ነው:: ለዚህም ነው ጥሩ ጥራት ያለው ቡና ያመረተ ጥሩ ገቢ እያገኘ ሲሄድ ሁሉም እየተሻሻለ ይመጣል በሚል የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር እየተካሄደ ያለው::
ቡናና ሻይም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ጥራት ማሻሻያ ትምህርት እየሰጠ መሆኑና ወደ መሥክ በመውጣት የቡና ጉንደላ እያካሄዱ መሆኑ ጥሩ ነው:: ይህ ምርታማነትን ለመጨመርና ጥራትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ቢኖረውም ግን ለወደፊት ብዙ ቀሪ ሥራዎች አሉን:: በቡና ምርትና ጥራት ማሻሻል ረገድ ከክልሎች ጋር ያለው ግንኙነት ጥርት ያለ ሊሆን ይገባዋል::
በማጠቃለያቸው አቶ ግዛት እንዲህ ብለዋል፤ ሀገሪቱ ሰላም ብታገኝ ከዚህ በላይ መራመድ ይቻላል:: አንዳንዴ ቡና የሚለቅም ሰው ሁሉ ችግር የሚገጥመበት ሁኔታ አለ:: ኢትዮጵያ በቡና ጥራት የምትወዳደረው ከታወቁት እነብራዚል፣ ኮሎምቢያና ኢንዶኔዢያ ከመሳሰሉ ቡና አምራች ሀገራት ነው::
ስለዚህ ክልሎች በተቀናጀ ሁኔታ ሠርተው አቅማችንን አጠናክረን ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ ቡና ይዘን እንድንቀርብ ልናመቻች ይገባል:: ክልሎች ከሌላ ልምድ ካለው ሀገር ጋር እንደሚወዳደሩ ተገንዝበው ቡና ላይ ትኩረት ሰጥተው ቢሠሩበት ጥሩ ነው እላለሁ::
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2013