ጌትነት ምህረቴ
”ከፊታችን ያለውን ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ታዓማኒ እንዲሆን መንግስት እንደ መንግስት እኛም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ሀላፊነታችንን በምን አግባብ ነው መወጣት ያለብን የሚለውን አስበንበትና ተጨንቀን መስራት ይኖርብናል።ህዝቡም በሰከነ መንፈስ ሚናውን መወጣት አለበት።የነገዋንና አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ኢትዮጵያን እያስብን መስራት ይገባናል።
ለዚህ ሁላችንም በዚህ ልክ የተቃኘ እሳቤ ይዘን መምጣት ይኖብናል።መጪው ጊዜ ጥሩ ነገር ይታየኛል።ምክንያቱም ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ላይ ትህነግ የለም።የትህነግ አለመኖር ለኢትዮጵያ አንዱ ትልቅ ተስፋ ነው‘ የሚሉት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ረዳት ፕፌሰር በለጠ ሞላ ናቸው።እኛም ከኚሁ ፖለቲከኛ ጋር በተለያዩ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገናል፤እነሆ።
አዲስ ዘመን፡- አብን እንዴት ወደ ፖለቲካው የትግል ሜዳ ሊመጣ ቻለ?
ረዳት ፕሮፊሰር በለጠ ፡-ወደ ፖለቲካው መድረክ አብን እንዲመጣ ዋናው ምክንያት የአማራ ህዝብ መገፋት ነው።የአማራ ህዝብ የተደራጀ ትግል እንዳያደርግ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መልኩ የህግና የመዋቅርም እግዶች ነበሩበት።በብሄር መደራጀት ላለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ ባህል ሆኖ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ሁሉም ብሄሮች በማንነታቸው ተደራጅተው ሲታገሉ ጠንካራ የሆነ የአማራ መደራጀት ዕውን እንዳይሆን አፈና ይፈጸም ነበር።ስለዚህ በከፍተኛ ጉዳት ውስጥ የወደቀ ህዝብ ስለነበር አማራ ራሱን አደራጅቶ ንቅናቄ ፈጥሮ ጠንካራ ትግል ማድረግ ነበረበት፤ ይህን ትግል ለማካሄድ አብን ፈጥረናል።
በእርግጥ ከዚህ በፊት የአማራ ልጆች የፖለቲካ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል።ትላንትም ተሳትፎ ነበራው፤ ዛሬም አላቸው።በተለይ በአንድነቱ የፖለቲካ ጎራ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ።ግን አጠቃላይ በኢትዮጵያ ላይ ገዥው ፖለቲካ የብሄር ፖለቲካ በመሆኑ ምክንያት የአንድነት ሀይሎች ጉልበት እንዳይኖራቸው ተደርጎ ቆይቷል። ስለዚህ በአንድነት ጎራ የነበራው ተሳትፎ የአማራ ልጆችን ዋጋ ያስከፈለ ነው።መስዋዕትነታቸውም ፍሬ አልነበረውም።
ምክንያቱም ስርዓቱ በአንድነት ሀይሎች ላይ ከፍተኛ አፈና ይፈጸም ስለነበር ተሳትፎ ቢያደርጉም ለአማራ ህዝብ ጠብ የሚል ነገር ይዘው አልመጡም።ስርዓቱ በራሱ ከጅምሩ አማራ ጠል ነበር ።ይህን ስለተረዳን የአማራው ህዝብ መደራጀት እንደነበረበት አምነን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄን ፈጥረናል።
አዲስ ዘመን፡- ስርዓቱ የአማራ ጠል ነው ለማለት ምን ምክንያት አላችሁ?
ረዳት ፕሮፊሰር በለጠ፡– ይህ ስርዓት የአማራን ህዝብ ታሪክ በጨቋኝነት የሚፈርጅ፣አማራ በሌሎች ህዝቦች በጥርጣሬና በጨቋኝነት እንዲታይ ያደረገ ነው። በአደባባይ ሲነገር የነበረ የሀሰት ትርክት ነበር። ትርክት ብቻ ሳይሆን ህገ መንግስቱም ከዚህ መንፈስ አንጻር የተቃኘ ነው።
ህግጋቶቹ፣ተቋማቱ በዚሁ መንፈስ ነው ይሰሩ የነበሩት።ይህ ሁኔታ አማራውን መገለል አድርሶበታል።በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ወሳኝ እንዳይሆን ተደርጓል።ይህ በመሆኑ ምክንያት የአማራው ህዝብ ጥቅሙን እንዳያረጋገጥ ተደርጓል።በዚህም የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ ሆኖ ቆይቷል።
አዲስ ዘመን፡- በፖለቲካው የትግል ሂደት ምን ምን ተግዳሮት አጋጠማችሁ?
ረዳት ፕሮፊሰር በለጠ፡– የአጋጠሙን ተግዳሮቶች በሁለት መልኩ የሚገለጹ ናቸው።አንደኛው አማራ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ኢትዮጵያ እንደ አገር በመመስረትና ነጻነቷን አስጠብቆ በማቆየት ሂደት ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነበር።በዚህ የተነሳ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍና እሳቤ ውስጥ የኖረ ህዝብ ነው።
ከዚህ መነሻነት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ተፈጥሮ ወደ ትግል ሜዳ ስንመጣ የመጀመሪያው ተግዳሮት የገጠመን ከአማራው ከራሱ ነው።አብዛኛው የአማራው ሊህቃን የእኛን በአማራነት መደራጀት ብዙም አላደነቀውም፣አልወደደውም ነበር።
የአማራ ልጆች መደራጀታቸውና ተደራጅተው መታገላቸው ዜናው ለብዙዎች አስደጋጭ ነበር።ከኢትዮጵያዊነት የመሸሽ ለብሄር ፖለቲካው እጅ መስጠት፤ ህወሓት በአሰመረው መስመር የመጓዝ አይነት ተደርጎ ተተርጉሟል።
ግን በተጨባጭ አገሪቱ ላይ ያለው ማደራጃ መርሁ የብሄር ፖለቲካ ነው።ይህን ባለመረዳት አብን መመስረቱን የኢትዮጵያዊነት የመሸሽ ስጋት አድርገው የተመለከቱት አሉ። ይህን ሀሳብ እኛም እንረዳዋለን።
ይህን አስተሳሰብ ለማሸነፍ ብዙ ስራ ይጠብቀን ነበር። ብዙ ህዝብን የማስገንዘብ ስራ ሰርተናል፤ ሰፊ ንቅናቄም ፈጥረናል።ከአገር ውስጥም ወደ ውጭም በመሄድ ሊህቃኑን ተደጋጋሚ የፖለቲካ ስራ በመስራት የተሻለ ግንዛቤ ስለእኛ ዓላማ እንዲረዳ በማድረግ አብዛኛውን ሰው ወደ እኛ መመለስ ችለናል።ዛሬ ላይ መደራጀታችን በእርግጥም አስፈላጊ እንደነበር ብዙ ሰው ያምናል። ድጋፉንም ይሰጣል።
ሁለተኛው በኢትዮጵያ አማራው እንዳይደራጅ የሚፈልግ ሀይል በርካታ ነው።በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተዋናይ የሆኑ ሀይሎች አማራው እንዲደራጅ አይፈልጉም ነበር።ለምሳሌ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም በጉባኤ አብንን ስንመሰረት አንዳንድ የትግራይ ሚዲያዎችና ድረ ገጾች ደርግ በአዳራሽ ተመሰረተ ብለዋል።ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የእኛን ስም የማጥፋትና የመታገል ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል።
ሌሎችም የብሄር አደረጃጃቶች አማራው እንዳይደራጅና የፖለቲካ ስራ እንዳይሰራ የሚፈልጉ ሀይሎች ከጅምሩ ጀምሮ እኛን በመፈረጅ ህዝቡ በእኛ ላይ እምነትና መተማመን እንዳይኖረው ሰፊ ስራ ሰርተዋል።
አንዳንድ የአንድነት ሀይሎችም አማራው በብሄር መደራጀቱ ችግር ይፈጥርብናል በሚል አብንን ጸንፈኛ፣ፋሽሽትና ከኢትዮጵያ ተገንጣይ ነው በሚል የተለያዩ ስሞችን በመስጠት ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ ሲነዙብን ቆይተዋል።ይህ ውጤት አልነበረውም አይባልም።
ቀላል የማይባለው የህዝብ ቁጥር በእርግጥም ጸንፈኛ ናቸው ብሎ ደምድሞ ነበር።እኛም ወደ ፖለቲካው ትግል ስንመጣ በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰው በደልና አፈና ትክክልና ተገቢ አይደለም ብለን ነው እንጂ በፖለቲካው ልምድ አልነበረንም። የካበተ ልምድም ስላልነበረንና ከተለያየ የስራ መስክ የመጣን ሰዎች ስለሆነ ስህተቶች ልንፈጸም እንችላለን።
ስለዚህ በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አንዳንድ በጽንፈኝነት ሊያስፈርጁን የሚችሉ ድምጸት ያላቸው ንግግሮችን አድርገን ሊሆን ይችላል።እንዲህ አይነት ነገሮች ተደምረው እውነተኛ ፍላጎታችን ሌላ ሆኖ እያለ ኢትዮጵያዊነታችን ፈጸሞ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ሳይሆን እነዚህ ፕሮፓጋንዳዎች በእኛ ላይ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ሌላ ስዕል እንዲይዙ አድርጓቸው ነበር።
እንደዚህ አይነት ተግዳሮቶች ነበሩ። ዛሬ ላይ ግን የመጣንበት የሁለት ዓመት ከመንፈቅ ጉዞ በእርግጥም ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ጊዜ ከፊት ቆመን ኢትዮጵያን የማዳን ስራዎችን እንደሰራን ማንም የሚገነዘበው ነው።
በዚህም ከመንግስት ጭምር ምስጋናን አግኝተናል። ወሳኝ በሆኑ ወቅቶች ላይ የወሰድናቸው የፖለቲካ አቋሞች በእግጥም ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ ሀይል እንደሆንን ማሳየት ስለቻልን ተግዳሮቶቹን አልፈናል ብዬ መናገር እችላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለውጡ እንዴት ትገልጹታላችሁ?
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ፡– የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመሰረታዊነት ለውጥ አለው አይባልም። በፊት የነበሩት መሪዎችና ዛሬ ላይ ያሉት መሪዎች የሚናገሩት ቃላት ልዩትነት አላቸው።በፊት ይህች አገር የሚሉ ከሆነ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያችን የሚል መሪ አለ።ይህ በራሱ በቀላል የሚታይ አይደለም።
ዛሬ ስለ አንድነት የሚናገርና አስፈላጊነቱን የሚተነትን መሪ አለን።ቀደም ሲል ልዩነቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይነገር ነበር።አገሪቱንም ኢትዮጵያችን ብሎ ለመናገር ሙሉ ልብ የሌላቸው መሪዎች ነበሩ።በዚህ ልክ ትርክቱ ተለውጦ ሊሆን ይችላል።
የአንድነትን አስፈላጊነት የሚናገሩና የሚያስገነዝቡ ንግግሮች በመሪዎች ደረጃ እንሰማለን፤ ግን መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ምንድነው ? የፖለቲካ ባህሉ ተለውጧል ወይ? ተቋማቶች ገለልተኛ እንዲሆኑ፤ ሙያተኞች እንዲመሩት ተደርጓል፤ ህግጋት ተለውጠዋል ወይ? ካልን በመሰረታዊነት ምንም የተለወጠ ነገር የለም።ትህነግን ጥለናል።
ግን ትህነጋዊነት ዛሬም ገዥ ሆኖ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ይታያል።ህገ መንግስቱም ትህነጋዊ ህገ መንግስት ነው። ዛሬም አገሪቱ የምትመራበት በእሱ ነው። የፌዴራል ስርዓቱ አጠቃላይ ትህነግ የሰራው የፖለቲካ ጉዞ ዛሬም ቀጥሏል።ስለዚህ በመሰረታዊነት ይህን ያህል የተለወጠ ነገር የለም።
በትርክት ደረጃ ግን የተለወጠ ነገር ይኖራል። ለምሳሌ የሴቶች ተሳትፎ አረጋግጫለሁ ለማለት ሴቶች ወደ ወንበር መጥተዋል።ይህ የሚበረታታ ነው።ግን ዘላቂ መሆን አለበት።ሌላው የመናገር፣ የመጻፍ መብትም ከሞላ ጎደል ከትናንቱ በተሻለ ሁኔታ ተለውጧል ።ግን በኢትዮጵያ መሰረታዊ የፖለቲካ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ተቋማዊ ለውጦች መምጣት አለባቸው።
ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት፤ ፌዴራል ስርዓቱ እንደገና መታየት አለበት፤ ህግጋቶቹና ተቋማቶቹ እንደገና መሰራት መቻል አለባቸው። ዲሞክራሲን ለመትከል አስቻይ ሁኔታ መፍጠር የሚችል መሆን አለበት።እንዲህ አይነት ሪፎርም አልተካሄደም።ለውጡ ከመጣ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የንጹሃን ዜጎች መፈናቅሎችና ግድያዎች ተከስተዋል።ይህ እንደ አገርም አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ከፖለቲካ ምህዳሩ አንጻር እንዴት አያችሁት?
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ፡– የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ እኛ በይፋ በምንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች አሉ። ምህዳሩን ከእዚህ አንጻር ካየነው ሰፍቷል እንላለን። የታችኛው የመንግስት መዋቅር በፈለግነው ልክ እንዳንንቀሳቀስ መሰናክል የሚፈጥር ቢሆንም በይፋ ፖለቲካ የምንሰራበትና ህዝብ የምናደራጅበት አካባቢዎች አሉ።
የማደራጀትና ንቅናቄን የመፍጠር ስራዎችን በነጻነት እንስራለን። እነዚህ አካባቢዎች አማራ ክልልና አዲስ አበባ ከተማ ናቸው። ስለዚህ በእነዚህ አካባቢዎች ምህዳሩ አስቻይ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት አለብን። ፍጹም አፋኝ የሆነና ከኦሮሞ ውጭ ያለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማስተናገድ ከባድ ችግር የሚታይበት ነው። ኦሮሚያ ክልል እኛ ብቻ ሳንሆን ሌላው የፖለቲካ ፓርቲ ፖለቲካ የሚሰራበት ክልል አይደለም።
ከፍተኛ አፈና ይፈጸምብናል።በክልሉ ቢሮዎች ከፍተን ነበር። ግን እንድንዘጋ ተገደናል። ቢሮዎቻችን በጥይት ተደብድበዋል። ባነሮቻችን ተቀደዋል። አባሎቻችን ማስፈራራትደርሶባቸዋል።ታስረዋል።ስለዚህ ቢሮዎቻችንን ለመዝጋት ተገደናል።እናም በክልሉ በይፋ የመንቀሳቀስ መብታችን እጅጉን ተገድቧል።
አሁንም ቢሆን መዋቅሮች አሉን፣ፖለቲካም እንሰራለን። ምህዳሩ ሰፊ ወይም ጠባብ ነው ለማለት ያስቸግራል። አጠቃላይ ፖለቲካውም እንደዚሁ ነው።ብዙ ነገሮቹ ምስቅልቅል ያሉ አንድ ወጥ መልክ የሌላቸው የተለያየ አገር አይነት የሚመስል አይነት የፖለቲካ ምህዳር ያላት አገር ናት።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ የአብን ተሳትፎና አስተዋጸኦ ምድነው ?
ረዳት ፕሮፌሰር፡– በለጠ፡-ለደጋፊዎቻችንና ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የተላላፉት መልዕክቶች በህዝቦች መካከል መጠራጠር እንዳይኖር የሚያደርጉ ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝቦች ዘላቂ ጥቅማቸው መረጋገጥ የሚችለውም ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ስንገነባ ብቻ ነው። ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት መንግስት ግንባር ቀደም ሚና እንዳለውና እኛም አጋዥ መሆናችንን በምንስራቸው የፖለቲካ ስራዎች ለማሳየት ጥረት አድርገናል።
በፖለቲካ ፓርቲዎችና በሊህቃን መካከል አገራዊ ምክክር መድረኮች እንዲኖሩ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል።
በእኛ በኩል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የተሻለ ጠንካራ እንዲሆን የፖለቲካው እንቅስቃሴ ከዛሬው በተሻለ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሚና እንደምንጫወት ይፋ አድርገናል።አባሎቻችንም በዚህ ልክ ለመቅረጸ ትምህርት ስንሰጥ ቆይተናል።
የአማራውም ህዝብ ዘላቂ ጥቅም መከበር የሚችለው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብረን መስራት እስከቻልን ድረስ ስለሆነ ይህን ለአባሎቻችን ለማስረጽ ከፍተኛ ስራ ስንሰራ ቆይተናል።የአማራ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚከበረው ከሌሎች ጋር ያበረ ፖለቲካ መስራት ሲችል ነው።
ለምሳሌ ከኦሮሞ ፓርቲዎች፣ከሌሎች የብሄር ብሄረሰቦች ፓርቲዎች ጋር በተቻለ መጠን ልዩነቱን አቻችሎ አንድ ሊያደርጉን የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች ስላሉን የጋራ ፖለቲካ የምንሰራ ከሆነ አገራችን ኢትዮጵያ ከዛሬው የተሻለ ልትሆን ትችላለች የሚል እምነት አለን።
ስለዚህ እኛ ከሌሎች ጋር አብረን ለመስራት ጥሪ ስናደርግ ቆይተናል።ለምሳሌ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ለነበሩት አቶ ለማ መገርሳ መልስ ባናገኝም ደብዳቤ ጽፈን ነበር ።ለአቶ ሽመልስ አብዲሳም እሳቸውን አግኝተን ምክክር ለማድረግ ደብዳቤ ጽፈናል፤ መልስ ግን አላገኘንም።
ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንም እንዲሁ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እኛም የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት እንደምንችል በመግለጽ ደብዳቤ ብንጽፍላቸውም መልስ አላገኘንም።
በዚህ ልክ እኛ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል።የአማራ ክልል መንግስትም ጋር አብሮ ለመስራት ጥረቶችን ስናደረግ ቆይተናል።ምንም እንኳን እነዚህ ጥረቶቻችን ይህን ያህል ፍሬ ባያፈሩም፤ በእኛ በኩል ግን ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥረት አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት በህወሓት ጁንታ ቡድን ላይ በወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ዙሪያ ምን አስተያየት አልዎት?
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ፡- ከሁለት ዓመት በፊት ህዳር ወር 2011 ዓ.ም ላይ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ አድርገን ውሳኔ አሳልፈናል።በአቋም መግለጫ ውሳኔ ያሳለፍነበት ጉዳይም ህወሓት አሸባሪ ድርጅት መሆኑን የሚገልጽ ነው። የህወሓትን የኋላ ታሪኩን በአጠቃላይ በደንብ ካየነው አሸባሪ ድርጅት ብሎ ለመፈረጅ አስቻይ ምክንያቶች ነበሩ።
ስለዚህ በወቅቱም መንግስት አሸባሪ ነው ብሎ እንዲፈርጀው ጥሪ አድርገናል።ይህ ብቻ ሳይሆን ህወሓት የሚያንቀሳቅሳቸው ድርጅቶች በሽብር ተግባር የተሰማሩ በመሆናቸው እንዲታገዱ ጥሪ አድርገናል።
ስለዚህ ዛሬ ላይ መንግስት የወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ አስፈላጊነቱ ጥያቄ የለውም።ግን ዘግይቷል። በመዘግየቱ አገሪቷ ዋጋ ከፍላለች።ለምን ዘገየ ለሚለው መንግስት ራሱን ማጠናከር ነበረበት።
በርግጥ ይህ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ ዋጋ አስከፍሏል። የመከላከያ ሰራዊት ጥቃት ደርሶበታል። ስለዚህ መንግስት የወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ ተገቢም፤ ግድ የሚልም ነው። እኛም ድጋፋችንንም አሳይተናል።
አዲስ ዘመን፡- ከህወሓት አስከፊ ውድቀት ሌሎች ፓርቲዎችና አመራሮች ምን ሊማሩ ይችላሉ ይላሉ?
ረዳት ፕሮፊሰር በለጠ፡– የምንማረው አንድ ቁም ነገር ይኖራል።ዛሬ ላይ ምን ያህል የጉልበተኛነት ስሜት ቢሰማን፤ ተቀባይነት ያለን ቢመስለንም፤የመንግስት ስልጣንን በህግ አግባብ እስካልተጠቀምን ድረስ ጭቆናን፣ አፈናንና ብዝበዛን ካሰፈንን መጨረሻችን ህወሓት ያጋጠመው አይነት አስከፊ ዕድል ነው። ይህን ከህወሓት ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ከታዩ ከሌሎች አንባገነኖች ውድቀት ጭምር መማር ያለብን ሀቅ ይህ ነው።
ህወሓቶች በቅርቡ ሊቢያ ሱዳን ግብፅ ላይ ከሆነው ትምህርት መውሰድ ባለመቻላቸው ለዚህ ውድቀት ተዳርገዋል። ኢትዮጵያን አዋርደው፣ በዝብዘውና ህዝቡን አንገቱን አስደፍተውት ውድቀቱን አፋጥነዋል። አሳፋሪ በታሪክ የሚታወስ ተግባር ነው የፈጸሙት። ሌላው ከዚህ መማር አለበት።
ዘላቂ የሆነ፣በታሪክ ፊት ስንቆም አንገታችንን ቀና ልናደርግ የምንችልበት ስራ ልንሰራ፣ በህግ ተገዥ ስንሆን፣ ለብዙሃን ፍላጎት ስናከብርና መስራት ስንችል እንዲሁም አገራችንን በዘላቂ ሰላምና ልማት ማሰለፍ የሚችል ስራ ሰርተን አስካልተገኘን ድረስ ታሪካችን በተመሳሳይ መልኩ የሚዘከር ይሆናል።
ዛሬ ጊዜ ስላገኘን የጉልበተኛነት ስሜት ስለተሰማን ሁሉንም ነገር ከህግ በላይ ሆነን እንፈፅማለን የሚል ፍላጎት ኖሮን የምንቀሳቀስ ከሆነ መጨረሻችን ውርደት ነው። መንግስትም ሆነ ሌሎቻችን ከእዚህ መማር አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሚጠቅመው በብሄር መደራጀት ሳይሆን በሀሳብ መሰባሰብ ሲቻል ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።በዚህ ጉዳይ ምን አስተያየት አልዎት?
ረዳት ፕሮፊሰር በለጠ፡– በሀሳብ የሚለው ዘርዘርና ግልጽ ተደርጎ መቀመጥ አለበት።እኛም ሀሳብ ያለን ፖለቲከኞች ነን።በብሄር የተደራጀ ፓርቲ ሀሳብ የለውም ማለት አይደለም።ከነባራዊ ሁኔታው መሸሽ ያለብን አይመስለኝም።ዛሬ ላይ በተጨባጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመደራጃ መርሁ የብሄር ፖለቲካ ነው።
ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የአንድን የብሄር ድርጅት ወክለው ነው አራት ኪሎ የተገኙት።ይህ ብዥታ ውስጥ የሚያስገባ ሳይሆን ግልጽ ነገር ነው። ትናንት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ወደ አራት ኪሎ የገቡት አንድን ብሄር የተደራጀ ድርጅትን ወክለው ነው። አቶ መለስ ዜናዊ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት የአንድን የብሄር ድርጅት ወክለው ነበር። ህገ መንግስቱም የብሄር ፖለቲካን ያሰፈነ ነው።
ስለዚህ ነባራዊ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በብሄር መደራጀት በተለይ ደግሞ በብሄር የተደራጁ ሀይሎች ጥቅሙን የጎዱበት ህዝብ በብሄር ሲደራጅ እንደነውር መታየቱ ስህተት ነው። ይህ የአማራውን ህዝብ ተደራጅቶ ጥቅሙን ማስከበር የሚደርስበትን በደል ለማስቀረት የሚያደርገው ጥረት ዋጋ አለመስጠት ነው። እንዲህ አይነት ጥያቄ ሌሎች ብሄሮች ተደራጅተው ፖለቲካ ሲሰሩ ጥያቄ ሆኖ አያውቅም።አማራው ሲደራጅ ነው ጥያቄው የተነሳው።
በአንድነት የተቃኘ ሀላፊነት የሚሰማው የፖለቲካ ሀይል ካልመጣ ፣የብሄር ፖለቲካ እስካለ ድረስ ሌሎች ጸረ አማራ ትርክትን የተላበሱ ሀይሎች ወደ መንበር እስከመጡ ድረስ ይህን ህዝብ ሰለባ ማድረጋቸው የሚቀር አይደለም።
ስለዚህ የአማራ ህዝብ በአንድነት ሀይሉ ተሰልፎ ሰፊ መስዋዕትነት ሲከፍል ቆይቷል።ግን የአንድነት ሀይሉ በብሄር ፖለቲካው ጉልበት ተሸንፎ ቀና እንዳይል ተደርጓል። መስዋዕትነቱም ፍሬ አልነበረውም።
አዲስ ዘመን፡- የአማራ ህዝብ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ስለሚኖር በብሄር መደራጀቱ ጥቅም አይኖረውም የሚሉ ወገኖች አሉ።በዚህ ሀሳብ ላይ ምን ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ፡– አማራ በሰፊዋ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች መኖሩ ብቻውን አማራው እንዳይደራጅ ምክንያት ሊሆን አይገባም።ለአማራው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሌላው ህዝብ ዘላቂ ጥቅም ጭምር ሲባል አማራ መደራጀት አለበት።ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለውን አማራ መብቶቹን ማስጠበቅ
ጥያቄዎቹን መመለስ ለአሮሞ ህዝብም ጥቅም ተገቢ እንደሆነ ለማስረዳት ጭምር እንደ አማራ መደራጀት አስፈላጊ ነው። በአንድነት ሀይል ተሰልፈን የብሄር ፖለቲካ የተደራጁ ሀይሎችን ማስረዳትና መግባባት አስቸጋሪ ነው።
ስለዚህ እንደ አማራ ተደራጅተን እንደ አማራ መሞገትና ማስረዳት አለብን።አቻ ሆነን መቆም አለብን።ይህ ማለት ግን ከኢትዮጵያዊነት መሸሽ አይደለም።ስንጀምርም ስንጨርስም በኢትዮጵያዊነት እሳቤ ነው።
አማራ በሚኖርበት ቦታ ሁሉ ዜጋ ሆኖ እንዲስተናገድ እኛ ትግል እናደርጋለን። አማራ የፖለቲካ ትግል ስላደረገ አይደለም ዋጋ እየከፈለ ያለው ትላንትም ሳይደራጅ ዋጋ ሲከፍል ቆይቷል። እና አመክንዮው ትክክል አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- አብን የሚያራምደው አመለካከት ምክንያት ጫና እየፈጠረብን ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ምላሽ አልዎት?
ረዳት ፕሮፊሰር በለጠ፡– ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች፣ሚዲያዎችና የመንግስት አመራሮችም ጭምር በእኛ ላይ ሰፊ ስም የማጠልሸት ፕሮፖጋዳ ስራ ሰርተውብን ነበር። አማራው እንዳይደራጅ የማይፈልጉ ሀይሎች ለእኛ ያልሆነ ስያሜ ሲሰጡን ቆይተዋል። እኛ መነሻችንንም መድረሻችንንም እናውቃለን።
መንገዳችንም ሰላማዊ ሲሆን ብቻ ነው የአማራውን ዘላቂ ጥቅም ማስከበር የሚቻለው ብለን እናምናለን።ከዚህ አካሄድ ፈንገጥ ካልን ለአማራው አማራጭ የፖለቲካ ድርጅት መሆን ስንችል እንዳንሆን ያደርገናል። በዚህ ላይ ብዥታ የለብንም።
ጥያቄችንም ግልጽ ነው። ትግል የምናደርገው በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም አካባቢ የሚኖር አማራ እንደ ሌሎቹ ህዝቦች በእኩልነት መስተናገድ የሚችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው።እኩል ሆኖ በቋንቋው እንዲጠቀም፣እንዲማር ፣እንዲዳኝ፣ ፍትህ እንዲከበርለትና በእኩልነት ዜጋ ሆኖ እንዲቆጠር ነው አንዱ ጥያቄያችን።
ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች አሉ።እነዚህ አብረው የሚታዩ ናቸው። ይህ በመሆኑ አማራው በመደራጀት ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ሲመጣ አማራው መደራጀትን የማይፈልጉ ሀይሎች እኛን እንደ ምክንያት በመውሰድ ህዝባችን ላይ ከፍተኛ ጥቃት ሲፈጸሙ ቆይተዋል። እኛ አዳማጭ ባይኖርም በህዝቦች መካከል ጥርጣሬ እንዳይኖር፣ አብሮነትን ለማጠናከር ያለሰለሰ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል።
ሌላው ዛሬ ላይ እኛ ስላለን የአማራውን ህዝብ መገፋት፣ስቃዩንና ህመም በአደባባይ እንዲጋለጥና እንዲወጣ እናደርጋለን። በደሉን፣ስቃዩንና የሚደርስበትን ግፍ የኢትዮጵያ ህዝብና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቅ እናደርጋለን።
ትናንት ላይ በአማራ ህዝብ ላይ ተመሳሳይ መከራና በደል ቢደርስበትም ሰዎች በዚህ ቦታ ተፈናቀሉ፣ ተጎዱ ይባላል እንጂ በግልጽ አማራ መጎዳቱ አይገለጽም ነበር።ምክንያቱም የሚያደምጠውና የሚያየው አካል አልነበረም።
ዛሬ ላይ የአማራ ድርጅት በመኖሩና አማራዊ ተቋማት ስላሉ አማራው በየትኛውም ቦታ የሚደርስበት ጥቃት እንዲታወቅ ይደረጋል። ስለዚህ አብን ወደ ፖለቲካው መድረክ ጋር ከመምጣቱ ጋር ሊያገናኙት ይችላል።
ሆኖም በተለያዩ አካባቢዎች በሚኖር አማራ ላይ ጫና እየፈጠረ ነው የሚለው ከአብን ጋር ማያያዝ ምክንያታዊ አይደለም። በአማራ ህዝብ ላይ መከራ የደረሰው አብን ስለመጣ ነው የሚለው አስተሳሰብ የሚስተዋለው የፖለቲካ ዓላማዎቻችን ካለመገንዘብ ነው።
ሌላው በማህበራዊ ሚዲያው የሚደመጡ ጫፍ የወጡ ድምጾች የአብን ተደርገው የሚፈረጁበት ሁኔታም አለ።ይህ አሳዛኝ ነው። እኛን የሚወክለን በድርጅታችን ድረ ገጽ የሚወጣ አቋም ነው።ከዚህ መለስ ያለው ባለቤቱ የማይታወቅና የሚጮህ ድምጽ ሁሉ የአብን ተደርጎ መወሰዱ ስህተት ነው። ትክክልም አይደለም።
ሆኖም እኛም እንደዛ እደምንፈረጅ ይሰማናል።ሆኖም ይህን አመለካከት ለማሸንፍ ከፍተኛ ስራ ስንሰራ ቆይተናል። ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያን ከአደጋ የተከላከልነበት ጊዜ አለ።
ለተጎዱ ህዝቦች አጋርነታችንን አሳይተናል።እኛ መገምገም ያለብን በዚህ ቁመናችን ነው። ኢትዮጵያዊነታችን ጥርጣሬ ውስጥ የሚወድቅ አይደለም። ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊ ነን ባንልም ከማንም ያነሰ ኢትዮጵያዊ እንዳልሆንን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ።
ግን ሌላ ስም ሲሰጠን ቆይቷል። ያልሆነውን እንደሆንን፤ ያልፈጸምነውን እንደፈጸምን ተደርጎ ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ ተነዝቶብናል።ያንን አሸንፈን ወደ ፊት መጥተናል።
አዲስ ዘመን፡- አብን በተለያዩ ጊዜ የሚያራምደው የብርተኝነት አቋም እንደ ስጋት የሚቆጥሩ ወገኖች እንዳሉ ይነገራል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ፡- አብን በህዝቦች ላይ ስጋት የሚፈጥር አቋም የለውም። ለምሳሌ ወሎ ላይ የሚኖር ኦሮሞ ወለዬ ነው። በዚህ ላይ ብዥታ ኖሮብን አያውቅም። ከሚሴ የሚኖር ኦሮሞ የሚቀርበው ለወሎ ህዝብ እንጂ አርሲና ወለጋ ላለው ኦሮሞ ህዝብ አይደለም።
አፋን ኦሮሞ ከመናገር ውጭ በባህሉ በስነ ልቦና የተሳሰረው ከወሎ አማራ ህዝብ ጋር ነው። ስለዚህ የከሚሴ ኦሮሞ ህዝባችን ነው።ራሱን በራሱን የማስተዳደር መብት ባይረጋግጥ ኖሮ እኛ ራሱን በራሱን እንዲያስተዳድር፣ ባህሉን እንዲያሳድግ፣ቋንቋውን እንዲጠቀም የምንታገልበት የፖለቲካ ጉዳይ ይሆን ነበር።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጋር ተያይዞም በህዝባችን ላይ ከፍተኛ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጸም ቆይቷል።ለዚህ ሁሉ ጥቃት ባለቤት አለው። አጥፊው ወደ ህግ ፊት መምጣት አለበት። በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች ጭምር በጥቃቱ ተሳትፈዋል።እነዚህን ሰዎች ለህግ አቅርቦ መቅጣት ሲገባ ጣት ወደ ሌላ መቀሰር ተገቢም፣ ምክንያታዊም አይደለም።
እንዲህ የሆነው አብን እንዲህ ስላለ ነው የሚለው ርካሽ የሆነ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች የሚያስወሩት ነው። ከዚህ ውጭ አብን በመመስረቱ ለሌላው ህዝብ ስጋት የሆነበት ሁኔታ የለም።
አዲስ ዘመን፡- በግልዎ አመለካከት የብሄር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ አዋጪ መንገድ ነው ብለው ያምናሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ፡– ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ባህል ቢሰፍን፤ተቋሞቻችን፤ህግጋቶቻችን ኢትዮጵያዊ መልክ ያላቸው ቢሆኑ ኖሮ የአንድነት ፖለቲካ ወደ ፊት መምጣት የሚችልበት እድል ይፈጠራል።
ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በእኩልነት የሚያስተናግድና በፍትህ የሚዳኝ ስርዓት ቢኖርና ሀቀኛ የሆነ የአንድነት ፖለቲካ ወደ መሪነቱ የሚመጣ አማራው ተጠቃሚ ነው የሚሆነው።በአሁኑ ጊዜ ግን እንዲህ ያለ ፖለቲካና ስርዓት የለም።
እንዳልኩህ ላለፉት 30 ዓመታት ሌሎች በብሄር ተደራጅተው የስልጣን መንበሩን ወስደው ህግ እያወጡ ህግ እያስፈጸሙ ያልተደራጀውን አማራውን በከፍተኛ ሁኔታ ጥቅሙን ሲጎዱ ቆይተዋል።ስለዚህ አማራው አለመደራጀቱ ነበር ነውር ሊባል የሚችለው።መደራጀቱ ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።ባለመደራጀቱ ብዙ ዋጋ ስለከፈለ መወቀስ ከነበረበት ባለመደራጀቱ ነው።ስለዚህ ዛሬ ላይ በብሄር ተደራጅተን ፖለቲካ ስንሰራ ለምን የሚለውን መረዳት ያለበት ሌላው ነው።
ሀቀኛ የሆነ የአንድነት ፖለቲካ ባለመኖሩና ቢኖርም እንኳን ጉልበት ሊኖረው አልቻለም።የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስርዓቱና ነበራዊ ሁኔታውም ይህንን የሚጋብዝም አይደለም።በዚህ ሁኔታ አማራው ወደ ራሱ ተመልሶ ራሱን አደራጅቶ ጥቅሞቹን ሊያስከብርለት የሚችል የፖለቲካ ስራ መስራት መጀመር ነበረበት።እንዲህ አይነት ጥያቄ የሚያነሳው መረዳት ነበረበት።
እኛ ብሶት የወለደን ነን።የአማራ ህዝብ የሚደርስበት መከራ እንድንመሰረት አድርጎናል።በድሎት ሳይሆን በብሶት ነው የመጣነው።አንድነት ሀይሉ ላይ ይደረግ የነበረው ተሳትፎችን አጓጉል መስዋዕትነት እንድንከፍል አደረገን እንጂ ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም።ስለዚህ ወደ ራሳችን መምጣትና ራሳችንን መሆን ነበረብን።ይህን መረዳት አለበት ሌላው።የአንድነት ፖለቲካ ቢኖር መንበሩን ቢወስድ አገሪቱ የምትመራው በዚህ ቢሆን አማራ ተጠቃሚ ስለሚሆን ነውር አልነበረውም።
አዲስ ዘመን፡- በመጪው ግንቦት መጨረሻ ላይ አገራዊ ምርጫ ይካሄዳል።በእናንተ በኩል ዝግጅታችሁ እንዴት ነው ?
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ፡– በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ የለም።አገሪቱ በውስጥ እዚህም እዚያ ባጋጠማት ውጥረት ምክንያት ምርጫ መካሄድ አስቸጋሪ ነው።ህዝቦች በብዛት በተፈናቀሉበ ጊዜና ህግና ስርዓት የማስከበሩ ዘመቻ ሙሉ ለሙሉ ያልተቋጨ በመሆኑና በብዙ አካባቢዎች ህዝቦች የመሰብሰብና የመናገር መብታቸው የታፈነ በመሆኑ ይህ ሁሉ መልክ ሳይዝ ወደ ምርጫ መግባት አስቻይ አልነበረም።ይህ ብቻ አይደለም ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገርም ወረራ ተፈጽሞባታል።ይህም ቀላል ጉዳይ አይደለም። ይህ ሁሉ እያለ ነው ወደ ምርጫ የተገባው።ስለዚህ አስቻይ ጊዜ አይደለም።
ግን ደግሞ ምርጫ የሚካሄድ በመሆኑ ለዚህ ዝግጅት ማድረግ ስላለብን ሰፊ ዝግጅት እያደረግን ነው።እጩዎችን እየመለመልን ነው። ስልጠናዎችን እየሰጠን ነው።በምርጫ ቦርድ ሰሌዳ መሰረት ስራዎቻችንን ለመከወን ሰፊ ዝግጅት እያደረግን ነው።ፖሊሲዎችን አርቅቀናል።በቀጣይ የምናስተች ይሆናል። ለህዝባችን አማራጭ ሀሳቦቻችንን ይዘን እንቀርባለን።
ስለዚህ ምርጫውን ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ ባይኖርም ወደ ምርጫ እስከገባን ድረስ ህዝብ ድምጹን ሰጥቶ ቅቡልነት ያለው መንግስት መመስረት ስላለበት ያን ለማድረግ ዕድል ስለሚፈጥር ወደ ምርጫው እንገባለን።ጠንካራ ተወዳዳሪ ሁነን ለመገኘት የምንችለውን ድምጽ ለማግኘት ሰፊ ዝግጅት አድርናል።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫው ፍትሀዊና በህዝብ ታማኔ እንዲሆን ከመንግስትና ከእናንተ ምን ይጠበቃል?
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ፡- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል መሰረታዊ ለውጥ አላሳየም። እናም ትናንትና ምርጫ ወቅት የነበረው መዋቅራዊ አፈና መታየቱ አይቀርም የሚል ስጋት አለን። ፍጹም ሰላማዊ ተዓማኒ የሆነ ምርጫ እንዲካሄድ ፍላጎት ቢኖረንም ይካሄዳል ብለን መናገር አስቸጋሪ ነው።
ምክንያቱም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል አልተለወጠም። ተቋማቶቹ፣ ህግጋቶቹ ብዙም አልተለወጡም። ዛሬ ላይ ያለው መንግስትም ህወሓት ይመራው ከነበረ ኢህአዴግ የሚባል መንግስታዊ ስርዓት አካል ነው። እርግጥ ነው ከዚህ የተቀነሰ ሀይል ቢኖርም ከዚህ የቀጠለውም ብዙ ነው።መንፈሱንም ፍላጎቱንም ይዞ ነው የሚቀጥለው። እናም ሰፊ ተግዳሮት ይሆንብናል።
ሌላው ምርጫው ዕድልም አለው።ዛሬ የነቃና ራሱን በማንነቱ ያደራጀ ፣ድምጼ ለስልጣን ያበቃኛል ብሎ የሚያምን ህዝብ አለ።ይህ አብን ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ ስለፈጠረ አንዱ ዕድል ነው።እኛ በበኩላችን መጫወት ያለብንን ሚና እንወጣለን።ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አባሎቻችንን ፣እናስተምራለን።የምርጫ ቦርድ የምርጫ ማስፈጸሚያ ደንቦችን አክብረን ለመስራት ለአባሎቻችን ስልጠና እንሰጣለን።
አዲስ ዘመን፡- መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ ስጋት ወይንስ ዕድል ይዞ ይመጣል ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ፡- ኢትዮጵያ የተሻለች አገር የመሆን ዕድል አላት። ህዝብ የሚፈልገውን መንግስት የመምረጥ ዕድሉን ይዞ የሚመጣ ምርጫ ከፊቷ ይጠብቃታል።ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ መልካም ዕድሎችም ስጋቶችም ከፊቷ አሉ።የኢትዮጵያ ህዝቦች በመሰረታዊነት ጥያቄዎቻቸው ሊታረቁ የሚችሉ አይደሉም።
ሊህቃኑ ሆደ ሰፊ ሆኖ አንዱ ሌላውን ለማዳመጥ፤ ለመገንዘብና ህመሙን ራሱን በሌላው ጫማ ውስጥ አድርጎ ማስቀመጥ መመካር ካለ ምንም እንኳን ልዩነቶች ሊኖሩ ቢችሉም አንድ ሊያደርጉን የሚችሉ በርካታ ነገር መኖራቸው መታወቅ አለባቸው።
አንድ ሊያደርጉን በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ ፖለቲካ መስራት እንችላለን። አንዳንድ አቋሞቻችን ላይ አስታርቀን የጋራ ሚዛናዊ ሁኔታ ላይ ደርስን ኢትዮጵያን በጋር መስራት የምንችልበት ዕድል አለ። በዚህ አኳያ ተስፋ አለ። ነገ ምርጫ ሲካሄድ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ ድምጹን ሰጥቶ ህዝብ የመረጠው ወደ ስልጣን ከመጣ የኢትዮጵያ ተስፋ የለመለመ ነው የሚሆነው።
ስለዚህ የበጎ ሀይሎች ጥምረት ወደ ፊት ከመጣ በጊዜ ሂደት ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የተሻለች ትሆናለች። መንግስት ይህን የምርጫ ዕድል አፈኖ ኢህአዴግ በመጣበት መንገድ እሄዳለው የሚል ከሆነ አሁንም የታመመች፣ በብዙ መንገድ መንፈሷ የተሰበረ ኢትዮጵያ ሆና መቀጠሏ አይቀርም።
ይህን ዕድል በአግባቡ መጠቀም የሁላችንም ሀላፊነት ነው። ከፊታችን ያለውን ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ታዓማኒ እንዲሆን መንግስት እንደ መንግስት እኛም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ሀላፊነታችንን በምን አግባብ ነው መወጣት ያለብን የሚለውን አስበንበትና ተጨንቀን መስራት ይኖርብናል። ህዝቡም በሰከነ መንፈስ ሚናውን መወጣት አለበት። የነገዋንና አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ኢትዮጵያን እያሰብን መስራት ይገባናል።
ለዚህ ሁላችንም በዚህ ልክ የተቃኘ እሳቤ ይዘን መምጣት ይኖርብናል። መጪው ጊዜ ጥሩ ነገር ይታየኛል።ምክንያቱም ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ላይ ትህነግ የለም።የትህነግ አለመኖር ለኢትዮጵያ አንዱ ትልቅ ተስፋ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2013