በአክበረት ታደሰ (ሄዋን)
እኔ ገጣሚ አይደለሁም፤ አልያም ደግሞ ደራሲ፤ ሥነ-ግጥም ላይ ሂስ ለመስጠት የሚበቃ በቂ እውቀትም የለኝም። ቅኝቴ የሚሆነው እንደ አንድ የሙዚቃ አድማጭ ብቻ ነው። ስለዚህም አንባቢዎቼ ትዝብቴን በዚህ መልኩ እንድትረዱልኝ እፈልጋለሁ። ሙዚቃ ስሜት ናት፣ ሙዚቃ ስሌት ናት፣ የሕይወት ቀመርም።
በሙዚቃ ውስጥ ሕይወትን ከነብቁ ገጾች ማየት እንችላለን። ሙዚቃ ባለ ብቁ ቋንቋና ባለ ብዙ ስሜትም ናት። ካዘነው ጋር ስታዝን፣ ከተደሰተው ጋር ስትደሰት፣ ተስፋ ከቆረጠው ጋር ተስፋዋ ሲሟጠጥ፣ ከተስፈኛው ጋር ነገን ስትናፍቅ፣ ከጀግናው ጋር ስትሸልል ከፈራው ጋር ሃሞቷ ሲፈስ፣ ከአፍቃሪው ጋር ስታፈቅር ብቻ ምኑ ተገልጾ ያልቃል በሁሉም አውድ ውስጥ መገኘት ትችላለች።
ለዚህም ነው ጽሑፌ መጀመሪያ ላይ ሙዚቃ ሕይወት ናት ያልኩት። በሁሉም የሥራ ባህርያት ውስጥ ስለምታልፍና ስለምትኖር ነው ይህችን በሰው ልጆች ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የምትችል ምትሃት ለመስራት እጅግ የበዛ ጥንቃቄ እና የጠለቀ እውቀት ያስፈልጋል የምለው። በተለይም በግጥም ዜማና በሙዚቃ መሣሪያዎች ተቀናብሮ የሚሰራውን ሙዚቃ (ዘፈን) የሚሰሩ ሰዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብዬ አስባለሁ።
ምክንያቱም ደግሞ ሙዚቃ ጥበብ ናት፣ ጥበብ ደግሞ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነች። ስለዚህ በዓለማችን ላይ ያሉ የተለያዩ የሕይወት ገጾችን መንካት፣ መዳሰስና የሰውን ልብ መኮርኮር ይኖርባታል። የሰውን ልብ ማግኘት የሚቻለው ደግሞ ኑሮውን፣ የዕለት ዕለት ተግባሩንና በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን እውነትና የሕይወቱን ክፍል በጥበብ አስውቦ በማቅረብ ነው።
ስለዚህ በሙዚቃ ውስጥ ሙዚቃውን የሚሰራው ሰው የመጣበትን የሚኖርበትን ወይም ተደራሽ የሚደረገውን ማህበረሰብ ባህል፣ ወግ፣ አኗኗር፣ ልማድ ጠብቆ አካባቢውን የሚገልጽና ኅብረተሰቡ ሊቀበለው የሚችል መልዕክት ማስተላለፍ አለበት።
ይህን እንደመግቢያ አድርጌ ልዳሰሰው ወደፈለግኩት ወደ እኔ ዘመን ሙዚቃ ልግባ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ባለሙያዎች (የሙዚቃ) ጊዜውን እንደገለጹት ከ2000 ዓ.ም ወዲህ ያለውን የሀገራችንን ሙዚቃ ከብዙ በጥቂቱ እንመልከት። የዘፈኖቹ ዓላማ ጭፈራ ብቻ ነው። ይህም ማለት ከሙዚቃ መልዕክት ይልቅ ለሙዚቃው ምት ትኩረት የተሰጠበት ሁኔታ ነው ያለው። ጭፈራ ቤትን አላማ አድርገው የሚሰሩ ሙዚቃዎች በዝተዋል። የሙዚቃ ምቱ ለእንቅስቃሴ ስለሚጋብዝ ብቻ በቪዲዮ ክሊፕ ይታገዝና ዘፈን ተብሎ ይወጣል።
ሌላውን ሌላ ጊዜ ልመለስበትና አሁን በዚህ ጽሑፍ ግን ዘፈኖችን ብቻ እዳስሳለሁ። የቪዲዮ ክሊፖቻችንን ጉዳይ በሌላ ጽሑፍ የምመለከተው ይሆናል። ቅኝቴን ልቀጥል እናም የእኔ ትውልድ የሙዚቃ ግጥምን ምንነት ረስቶታል ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ነገር ግን ይሄን ስል ስለ ግጥሙ መልዕክት ተጨንቀው ለሱ የሚስማማ ዜማ ፈልገው ለጉሮሮ የሚጣፍጥ ዘፈን የሚሰሩ ባለሙያዎች የሉም ማለቴ አይደለም። ለነሱ ያለኝ አክብሮትም ሰፋ ያለ ነው። ነገር ግን አብዛኛው በሚባል መልኩ በአሁኑ ሰዓት እየወጡ ያሉ ዘፈኖች ዓላማቸው ናይት ክለብ ብቻ ሆኗል። በጣም የሚገርመው ደግሞ ለናይት ክለብ እየተባለ የሚሰራ ሥራ መኖሩ ነው።
እንዲያውም ለጭፈራ ቤት የሚሆን ዘፈን የሚሰራ አቀናባሪ፣ ዘፋኝ ዜማ ግጥም ደራሲ ሁሉ አለ። ዓላማው ዳንኪራ ብቻ የሆነ ማለት ነው። ይህ የእውነት ለሀገራችን ሙዚቃ ማሽቆልቆል ትልቅ ምክንያት ነው። በሚገርም መልኩ ምንም መልዕክት የሌላቸው ዘፈኖችና መልዕክት ቀርቶ የረባ ግጥም እንኳን ሳይኖራቸው ሙዚቃ ተብለው ያወጡና በጣም ዝነኛ ዘፋኝ ይሆናሉ።
ተወዳጅነታቸው ከምን የመጣ ነው ቢባል መልሱ የሙዚቃው ምት ለዳንስ ስለሚመች ብቻ በወጣቱ ዘንድ ተወዳጅ ስለሚሆኑ ነው። አብዛኞቹ ሊባል በሚችል መልኩ የዘፋኙ ድምጽ በኮምፒዩተር ታግዞ ሳይሆን ኮምፒዩተር በዘፋኙ ድምጽ ታግዞ የሚዘፍን እስኪመስል ድረስ አርቲፊሻል የሆነ በኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃዎች ጫጫታ የተሞላ ለሆይ ሆይታ ብቻ የሚመች ዘፈን ይወጣል።
አብዛኛውን ጊዜ በዕድሜ ከፍ ያሉ ሰዎች አንድ ነገር ሲነሳ እሱማ በእኛ ጊዜ ቀረ ማለትን ያዘወትራሉ። ለእኔ ደግሞ ሁላችንም የራሳችንን ዘመን እንወዳለንና ለእኛም ያለንበት ጊዜ ጥሩ ነው ብዬ ስለማምን በእኛ ዘመን ብዙ ጥሩ ነገሮች መጥተዋል እል ነበር። በአንድ ነገር ግን ከእነሱ ጋር እስማማለሁ ከተወሰኑ ዘፋኞች ሙዚቀኞች በቀር እነሱን ከዚህ ማጠቃለያ በማውጣት፣ ሙዚቃ ድሮ ቀረ፣ ግጥም ድሮ ቀረ፣ ቅኔ ድሮ ቀረ፣ ዜማ ድሮ ቀረ በሚለው። ምክንያቱም የቀደመውን ትውልድ ሙዚቃ ስንመለከት የግጥሞቹ ብስለት በጣም አስገራሚ ከመሆኑም በላይ በእርግጥም የማይዳሰሱት የሕይወት ክፍል አልነበረም።
ስለሁሉም ነገር ዘፍነዋል፤ የሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ፍቅር እንኳን ሲገልጹት በተመረጠ ቋንቋና ቅኔን ባዘለ የግጥም ጥልቀት ባለው አገላለጽ ነው። ስለ ጾታዊ ፍቅር በሚዘፈንበት ጊዜ እንኳን የፍቅርን ርቀት ከልብ በማይጠፋ ውብ ቃላት ነው የሚገልጹት። ስለ ልብ መተሳሰር ስለመንፈስ አንድነት ነው በሚያስደንቅ ሁኔታ የሚያቀነቅኑት።
የእኔ ትውልድስ ስለ ፍቅር ከሆነ ዘፈኑ ቁመናው፣ አረማመዱ፣ ሰውነቷ፣ ዓይኗ እንጂ ስለ ማንነት፣ ስለባህሪና ውስጣዊ ውበት የሚሉት ነገር የላቸውም። ስለ ውስጣዊ ውበት የሚገልጽ ሙዚቃ ለማግኘት ብዙ ፍለጋ ማድረግን ይጠይቃል። እንዲህ ተፈልጎም ከተገኘ መታደል ነው።
በመሆኑም ትውልዱ ፍቅርን ከአካላዊ መሳሳብ ጋር ብቻ እንዲያያይዘው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ (ተፅዕኖ) ቀላል የሚባል አይደለም። በእኔ እምነት ፍቅር የመንፈስ መተሳሰር እንደሆነ የተዘነጋ ይመስለኛል።
በቀደመው ትውልድ የሴት ልጅን ውበት የሚገልጽ ዘፈን ሲሰራ አግባብ የሆነ ጨዋ ቋንቋዎችን በመጠቀም ነበር። ሌላው በዚህ ትውልድ ዘፈኖች ላይ የታዘብኩትም የሴትን ክብር የማይገልጽ ብሎም የሚነካ አግባብ የሌላቸው ግጥሞችን መጠቀም ነው። አንዳንድ ሙዚቃዎች እንዲያውም ሴት ልጅን ከወሲብ መገልገያነት ያለፈ ጥቅም እንደሌላት አድርገው ሁሉ ያቀርባሉ። ከዚህ ባለፈ ማሰብ እንደማይቻል የሚሰብኩም ናቸው።
ጽሑፌ የቀደመውን ትውልድና የእኔን ዘመን በማነጻጸር በሀገራችን ሙዚቃ ላይ አደጋ ላይ ያለውን የዘፈን ግጥም መመልከት ነውና ለማነጻጸሪያነት ከቀደመውም ከዚህም ትውልድ አንዳንድ ዘፈኞችን በመውሰድ መልዕክታቸውን ለማየት እሞክራለሁ።
«ኧረ ነጋ ነያ ነያ»
በይ አብረሽኝ ዋያ ነያ (2 ጊዜ)
ነጋ ነይልኝ ዓለም ነይልኝ (ይሁኔ በላይ የቀደመው ዘመን ማሳያ) ኧረ ነጋ ነያ እያለ ግጥሙ ሲወርድ ጨዋታውን፣ ማንነቷን፣ ከሷ ጋር የሚያሳልፈውን ጊዜ እንደሚናፍቅ ይገልጻል። ነግቷል ነይ አብረን እንዋል ሲል ከሷ ጋር ማደር ስለማይፈልግ አይደለም። ሁሉም ሰው ከሚወደው ሰው ጋር እንደዚያ ዓይነት ጊዜ ማሳለፍ እንደሚፈልግ ነጋሪ የማያስፈልገው ሃቅ ነው። ነገር ግን ይሄ የሁለቱ ጥንዶች የግል ጉዳይ እንጂ በአደባባይ የሚወጣ ነገር አይደለም። በሌላ አነጋገር በሁለቱ መካከል የሚቀር ጉዳይ ብቻ ነው። ሌላው የቀደመውን ዘመን ዘፈኖች ስመለከት ውበትን የሚገልጹበት መንገድ ይማርከኛል።
ውበትን ሲገልጹ ከፀሐይ፣ ከጨረቃ፣ ከከዋክብት ጋር ለማመሳሰል ግርማ ሞገስን ሲገልጹ ከሰማይ ጋር በማነጻጸር ነበር። ይህ የቀደመው ዘመን መለያ ነው።
ወደዚህኛው ዘመን ደግሞ እንምጣ «ላግኝሽ ማታ ማታ፣ ነይ ማታ ማታ ደስ የምትይኝ አንቺ በማታ» ሁሉም ነገር በማታ ሆነ ጨለማ ተገን ተደርጎ ማለት ነው። በጨለማ የሚደረግ ነገር ደግሞ ስህተት አለው። በሌላ አገላለጽ ስርቆት ነው ማለት ነው። ለምንድነው ስለማታ ብቻ የሚያወሩት ብለን መጠየቅም እንችላለን። ይሄ ገጣሚ ሴቷን የሚፈልጋት ለመዝናናት እንጂ ለቁምነገር አይደለም ብለንም እኮ መውሰድ እንችላለን። ቀን አይፈልጋትም፤ ቀን ለእሱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሌሎች ነገሮች አሉ። ማታ ላይ ግን እሷን ማግኘት ይፈልጋል። ምክንያቱ ደግሞ ለመዝናናት።
ይህም ሴትን ለወሲብ መገልገያነት ከማሰብ ጋር የተያያዘ ካልሆነ በስተቀር ለማውራት ለመጫወትና ለሌሎች ነገሮች የግድ መምሸት አይኖርበትም። ሴቷን ጭፈራ ቤት ለመውሰድና መጠጥ በማጠጣት የሚፈልጉትን ለማድረግ ምሽተን መጠበቅ ሊያስፈልግ ይችል ይሆናል። በነገራችን ላይ ይህን የምለው ለማለት ያህል ብቻ አይደለም። በተጨባጭ ያለው ነገር ከንክኖኝ እንጂ። ምክንያቱም ዘፈኑን በሚገልጽ ቪዲዮ ክሊፕ ወቅት አሁን ያልኳቸውን ነገሮች ነው በምስል አስደግፈው የሚያሳዩን። የተራቆተ አለባበስ የለበሱ ሴቶች ከወንዶቹ ጋር የሚኖራቸው አቀራረብ እና እንቅስቃሴም ከላይ የገለጹኩትን የሚመስል ነው።
ጽሑፎች በተለይ ደግሞ የዘፈን ግጥሞች ጨለምተኛ መሆን የለባቸውም። ጨለማ የአደጋ፣ የመጥፎ ነገር ሲምቦል ስለሆነ በተቻለ መጠን መልካም ነገርን የሚመኙ፣ የሚያንፀባርቁና ተስፋን የሚያሳዩ ነው መሆን ያለባቸው። ስለዚህ ማታ በጨለማ ለምን? ከማታ የተሻለ እኮ ቀን ደስ የሚል የፍቅር ጊዜን ማሳለፍ ይቻላል። ፍቅርን በብርሃን የሚያሳይ ብዙ የሕይወት ክፍልም አለ። በሚያስቅ ሁኔታ አንዳንድ ዘፈኖች ግጥም የሚባል ነገር አይኖራቸውም፣ ለራሳቸውም የማይሰማ የሆነ ነገር የሚሉ ይመስለኛል። ከዚያ ውጪ ምንም የለም። ኧረ እንዲያውም አንዳንዶቹ የቋንቋ እጥረት ያለብን ይመስል የራሴ ቋንቋ ብለው ማንም ሊረዳው የማይችል ነገር ይዘባርቃሉ።
ለራሳቸውም ትርጉም የሚሰጣቸው አይመስለኝም፣ እኔ ቋንቋ የሚለውን ቃል ስረዳው ሰዎች ከሰዎች ጋር እንዲግባቡበት የተፈጠረ ነው። እነዚህ የራሱ ቋንቋ እያሉ የሚያላዝኑት ግን ለራሳቸው ትርጉም ሰጣቸው ብንል እንኳን የሚሰሩትን ሙዚቃ ራሳቸው እንዲያዳምጡት ነው እንዴ የሚሰራው? ሰው ካላዳመጠው አዳምጦ መልዕክቱን ካላስረዳው ዘፈን መስራት ምን ያደርግለታል። የሙዚቃ መሣሪያዎች ቅንብር ድምጽ ስለያዘ ብቻ ሙዚቃ ብሎ ሰው እንዲሰማው ይሆን? ይሄ ደግሞ ትርጉም አይሰጥም።
ሌላው የዚህ ዘመን ዘፈኖች ላይ የሚታየው ችግር መልዕክት ማስተላለፍ ላይ ነው። ነገሩ የረባ
ግጥም በሌለበት መልዕክቱ ከየት ይመጣል? በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ሀገራችን የቋንቋ ሀብታም ሆና እያለ ሌላ የባዕድ ሀገር ቋንቋ በየመሃሉ መቀላቀሉ ነው። my baby my love signorita የሚሉ የባዕድ ቋንቋዎችን በየመሃሉ መጠቀምም እየተለመደ መጥቷል። በቀናነት ከሚዘፍኑት ቋንቋ ውጪ ቋንቋ መቀላቀል ፈልገውም ከሆነ ዘፈኑ አማርኛ ከሆነ ኦሮምኛ መቀላቀል ይቻላል። ወይም ደግሞ ዘፈኑ ትግርኛ ከሆነ ጉራጊኛ ቢቀላቀልበት የራሳችን ቋንቋ ውህደት ውበት ይሰጠዋል። ይሁንና እጥረት ያለብን ይመስል ወደ ነጮቹ መሄድ ለምን እንደሚቀናቸው አይገባኝም።
እንደዘመናዊነት ተቆጥሮም ከሆነ ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ እንዲሆኑ ሙሉውን በውጭ ቋንቋ ጋር ቢዘፍኑ መልካም ነው። ቋንቋችንን ከባዕድ ቋንቋ ጋር ሲደባለቁት በጣም ከመናደዴም በላይ ማለት የሚፈልጉትን ለመግለጽ ቋንቋዎችን አልበቃ ብሏቸው ነው ብዬም እጠይቃለሁ። ይሄ ደግሞ ምንም መልካም ጎን የለውም ብዬ ነው የማስበው። ሙዚቃችንን ለማስተዋወቅ አስበው ከሆነ መታወቅ ያለበት በራሳችን ቋንቋ እና ባህል እንጂ በሌላ ቋንቋ መሆን የለበትም። እነሱ የሚሉትን ከደገምንማ ምኑን ልዩ ሆንን ታድያ? በተለያዩ የአፍሪካም ሆነ ኢንተርናሽናል አዋርዶች ላይ ታጭተው የነበሩ ሙዚቃዎቻችን ብንመለከት የተመረጡት ፍጹም ባህልና ቋንቋችንን በመጠቀማቸው ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጹ ዘፈኖች መሆናቸው መዘንጋት የለበትም።
በመሆኑም ይህ ትርጉም የማይሰጥ ነገር ልብ ቢባል መልካም ነው። በቋንቋችን መቼ ሰርተን፤ መቼስ አልቆብንነው የሰው ማየት የጀመርነውስ? ይህ ለእኔ የራስን ነገር አለማክበር ነው። በነጮች ፍቅር መለከፍ ብሎም ፈቃዳዊ ባርነትና የሉላዊነት ተጽእኖ ነው። ገና ስንት ያልፈታናቸው ቅኔዎች፤ ያልተጠቀምንባቸው ቋንቋዎችና የተቀኘናቸው ዜማዎች እያሉ። ሲጀመር ኢትዮጵያዊነት ቢቀዱት መች ያልቅና ነው ሌላ የሚያስማትረን?
ሌላው የዚህ ዘመን ሙዚቃ (ዘፈን) መገለጫ እየሆነ የመጣው ነገር ከማህበረሰቡ ባህልና ወግ ማፈንገጥ ነው። ይሄ ከላይ ከገለጽኩት ከዘመናዊነት አባዜ ጋር የተያያዘ ነው። ፍጹም እኛን የማይገልጹ ዘፈኖች እየተሰሩ ነው ያሉት። ትልልቅ ሰዎች ዘፈኖቹን በሚሰሙበት ጊዜ የሚሸማቀቁባቸው፣ ባህላችንን የማይወክሉ፣ ማንነታችንን የማይገልጹ በሚያሳዝን ሁኔታ በእኛ በኢትዮጵያውያን ሲባሉ ደስ የማይሉ ነገሮች ናቸው በሙዚቃዎቻችን እየተላለፉ ያሉት። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን እኮ አሁን ይሄ ትውልድ የዘነጋው (እየዘነጋው ያለው ነገር ቢሆንም) የተለየ እሴት ባህልና ወግ ያለን ሕዝቦች ነን። ሴት ልጅ የምትከበርበት ማህበረሰብ ነው እኛን ያመጣን። የሴት ልጅ ውበት ሲገለጽ እንኳን ክብሯን በማይነካ መልኩ ነው።
በቃ የእኛ ማህበረሰብ ይሄ ነው። ሴት ልጅ ተገላልጣ ራቁቷን ሊባል በሚችል መልኩ መሄዷን የማይደግፍ፤ የሴት ልጅን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ነገሮችን የሚነቅፍ ነው። በፓንትና በጡት መያዣ መታየት (በአደባባይ)፣ (በሚዲያ) በሌላው ዓለም ትክክል ሊሆን ይችላል የእኛ ማህበረሰብ ግን ይሄን አይፈቅድም። እውነታው ይሄ ነው። በቅርብ ቀን ነው ቲቪ ላይ አንድ ዘፈን እያየሁ ሲሆን ዘፋኟ ደግሞ ሴት ናት። ግጥሙ «ግባልኝ ግባ ወደሜዳው፣ ውረድ ወደ ሜዳው፣ አጨዋወትህማ» በሚሉ ግጥሞች የተሞላ ነው። ቪዲዮ ክሊፑ ደግሞ ልጅቷ አልጋ ላይ ሆና ነው የሚታየው። ሰውነቷን ተገላልጣ የምታሳየው እንቅስቃሴ ግጥሙን የሚገልጽ ነው። ይህ ደግሞ በጣም ያሳፍራል።
በአጠቃላይ እንደዚህ ዓይነት ዘፈን ለእኛ ማህበረሰብ የሚመጥን አይደለም። ስንት ያልተዘፈነባቸው ያልተዳሰሱ ሃሳቦች እያሉ ለምን እንደዚህ ወደወረደ ዓይነት አዘፋፈን መምጣት እንደተፈለገ አይገባኝም። ተከታይ ለማግኘት ትኩረት ለመሳብ ይሁን ወይም እንደዚያ ዓይነት ሁኔታ ትክክል ነው ብለው አስበው ይሆንን? ለእኔ ግን ዓላማው ግልጽ አይደለም። በእኔ እምነት ግን ይህ ነገር ማህበረሰቡና ትውልዱ ላይ ሊፈጥረው የሚችለው የማንነት ቀውስ ትኩረት ተሰጥቶት እንደዚህ ዓይነት ሙዚቃዎች በሚዲያዎቻችን እንዳይተላለፉ ሳንሱር ሊደረግ ይገባል። ትውልዱን ወደ ትልቅ ማንነትን ማጣትና አዘቅት እየከተቱት ነውና ደግመን ደጋግመን ልናስብበት ይገባል በማለት ሙዚቃዎቻችን ላይ ከብዙ በጥቂቱ ያደረግኩትን ቅኝቴን እዚህ ላይ አበቃሁ። ሻሎም!
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2013