ለምለም መንግሥቱ
ህንፃ እንደዛፍ መብቀል ጀመረ እስኪባል ድረስ አንዱ ከሌላው በቅርጽና በይዘት የተለያየ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ከተሞች ወደላይ የህንፃ ግንባታ በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛል። ህንፃ ወደላይ የሚገነባው ለመሬት ቁጠባ ሲባል ብቻ አይደለም።የዘመናዊ ከተማ መገለጫ ተደርጎም ይወሰዳል።
በመሆኑም ለአካባቢ፣ ለከተማ ጥሩ ገጽታና ለመሬት ቁጠባም አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብለው የሚገነቡ ህንፃዎች የህንፃ አዋጁን ተከትለው መከናወን ይኖርባቸዋል።በህንፃ አዋጁ መሠረት አንድ ህንፃ የግንባታ ሥራው ከመጀመሩ በፊት ከመሬት አስተዳደር መሬት ማግኘነት አለበት።መሬቱ ለሚገነባው የህንፃ አይነት ተስማሚ መሆኑና ሌሎችም አስፈላጊ መሥፈርቶች መማላታቸው በህንፃ ሹም ከተረጋገጠ በኃላ ነው ወደ ሥራ የሚገባው።
ይሁን እንጂ ለመኖሪያም ሆነ ለተለያየ አገልግሎት መሥጫ የሚሆኑ ህንፃዎች ተገንብተው እንዳለቁ ብዙም ሳይቆይ ከፊት ለፊታቸውና በላስቲክና በሸራ በተወጠሩ እንዲሁም በአነስተኛ ግንባታዎች ውበታቸው ደብዝዞ ይታያሉ።በነዚህ በአነስተኛ ግንባታዎች ውስጥ የሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶች ደግሞ የበለጠ ገጽታውን ያበላሹታል።
እርምጃ ወስዶ የሚያስተካክል አካል ባለመኖሩ ክፍተቱ ቀጥሏል።ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው፤እንደ ትምህርትቤት፣ጤና ተቋማትና ሌሎችም ለህዝብ አገልግሎት መሥጫ ለሚውሉ የሚገነባው ከግለሰብ ወይንም አነስተኛ አገልግሎት ካላቸው ጋር የግንባታ ደረጃው እንደሚለያይ ይነገራል። ለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎችና የሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል በተነሱት ጉዳዮች ላይ ምን ይላሉ?ችግሩንና መፍትሄውን ጠይቀን እንደሚከተለው አቅርበናል።
በቅድሚያም በፌዴራል ኮንሥራትክሽን ሥራዎች ቁጥጥር ባለሥልጣን የህንፃ ቁጥጥር ዳይሬክቶረት ዳይሬክተር አቶ በረከት ተዘራ እንዲህ በማለት ያስረዳሉ፤ ወደላይ የሚገነቡ ህንፃዎች በዓለም አቀፍም በሀገር አቀፍም የወጡ የህንፃ ደረጃዎችን ማዕክል ባደረገና በተጣጣመ መለኩ መከናወን ይኖርባቸዋል። በዚሁ መሠረትም የአንድ ህንፃ ከፍታ በወጣው ደረጃ ይወሰናል።
በኢትዮጵያ አማካዩና የሚመከረው የህንፃ ከፍታ ሶስት ሜትር ሲሆን፣እንደ አካባቢው የሙቀትና የቅዝቃዜ ሁኔታ ግን ግንባታው ሊለያይ ይችላል።ግን አማካኙን ማስቀመጥ ግድ ነው።የአንድ ቤት በርና መሥኮት እንዲኖረው ሲፈለግ እንኳን በዘፈቀደ በርም ሆነ መስኮት አይወጣም።
ለሆቴል፣ለሆስፒታል፣ለትምህርትቤቶች እየተባለ ተለይቶ ነው የሚገነባው።በተለይ እንደ ትምህርት ቤት፣ ጤና ተቋማት ያሉ ለህዝብ መገልገያ የሚውሉ ህንፃዎች ከደረጃ መወጣጫቸው ጀምሮ ተገልጋዩን ታሳቢ ያደረጉ መሆን ይኖርባቸዋል።ለዚህም በህንፃ አዋጁ ላይ መሥፈርቶች ተቀምጠዋል።
በህንፃ አዋጁ ላይ በግልጽ የተቀመጡ መሥፈርቶች ቢኖሩም ደረጃቸውን ያልጠበቁ የህንፃ ግንባታዎች ፈቃድ የሚሰጥበት የአሰራር ክፍተቶች በግንባታ እንዱስትሪው ውስጥ መኖራቸውን አቶ በረከት አልሸሸጉም።
ከህንፃዎቹ ፊትለፊት ገጽታን የሚያበላሹ አነስተኛ ግንባታዎችን አስመልክቶ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች ጋር የሚቀርቡ ምክንያቶች አሳማኝ አንዳልሆኑም ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ማንኛውም ሥራ መከናወን ያለበት በዘፈቀደ ሳይሆን አስፈላጊነቱና አካባቢን የማይረብሽ መሆኑ በጥናት ተለይቶ መሰራት ይኖርበታል።ከህንፃ ሹም የግንባታ ፈቃድ ማግኘት አለበት።
ፍቃድ ሳይኖር የሚከናወን ማንኛውም ግንባታ ህገወጥ ነው።ህገወጥነትን ለመከላከል የተቋቋመው ደንብ ማስከበር ተቋም ዋና ተግባሩ ህግ ማስከበር በመሆኑ ሊከላከል ይገባል።እስከዛሬ ባለው ተሞክሮ አብዛኞቹ ቀድመው ከተገነቡ በኃላ ነው ፍቃድ የሚጠየቅባቸው።
እንዲህ ያለው አካሄድ ለህገወጥነት መሥፋፋት መንገድ ይከፍታል።በዚህ ረገድ የወረዳና የቀበሌ የህንፃ ሹሞች ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።ሌላው ቢቀር ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሲሆን የግንባታ ተረፈበምርት በሥፍራው መኖር የለበትም።አሁን እየታየ ያለው ግን በአብዛኛው ተቋራጩ አጽድቶ አይወጣም።
በተጨማሪም ተቋራጮች ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ፣ በጊዜና በጥራት የግንባታ ሥራውን ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል።ባለሥልጣኑ እነዚህን ለማጣራት ባከናወነው ሥራም የተቀመጡት መስፈርቶች ተሟልተው አላገኛቸውም።
በኮትራክ ተሮች የሚስተዋለው የአቅም ማነስ፣ ሙስና እና ሌሎችም ምክንያቶች በዘርፉ የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልተደረሰም።ባለሥልጣኑ በመንግሥትም ሆነ በግል የሚከናወኑ ግንባታዎች ወይንም የግባታ ኢንደስትሪው በህንፃ አዋጁ መሠረት እንዲተገበር ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በክትትልና ቁጥጥር እንዲታረም እየሰራ ይገኛል።
ግንባታዎች በዘፈቀደ እንዳይከናወኑ እየተከናወነ ሥላለው ተግባርም አቶበረከት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በየክፍለከተሞች የሚገኙ የመሬት አስተዳደር ተቋማት ለኢንደስትሪ፣ ለመኖሪያ፣ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉትን ለይተው ፈቃድ ይሰጣሉ። ተጠሪነቱ ለከተማዋ ከንቲባ የሆነው የህንፃ ሹም ግንባታውን ለሚያከናውነው አካል የተሰጠው መሬት ትክክል መሆኑን የማረጋገጥ፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት።
ባለሥልጣኑም በፌዴራል የሚከናወኑ ግንባታዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳና የተቀመጠውን የጥራት መስፈረት አሟልተው መከናወናቸውን ይቆጣጠራል። ክፍተት ካለም ለሚመለከተው አካል ያሳውቃል።
እስካሁንም ባከናወነው ሥራ በህንፃ ዘርፍ 63 የመንግሥት ፕሮጀክቶችን፣ በመንገድ ዘርፍ ደግሞ በ39 ፕሮጀክቶች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ያከናወነ ሲሆን፣ ለፕሮጀክቶቹ አቅጣጫ በመሥጠትና በተሰጠው አቅጣጫም እንዲከናወን ኃላፊነቱን ተወጥቷል።
ይህንንም ለፈዴራል ገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት አድርጓል። ግልባጩም ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲደርስ ሆኗል።ከጊዜው ዕድገት ጋር የሚሄድ የህንፃ አዋጅ እንዲኖርም በየጊዜው ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አቶ በረከት የህንፃ አዋጁን የማሻሻል ሥራውም ለሶስተኛ ጊዜ መከናወኑንና የመጨረሻውም በሂደት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከተሞችን ታሳቢ ያደረገ የግንባታ ሥራ እየተከናወነ እንዳልሆነ እምነት እንደሌላቸው የነገሩን ሌላው አስተያየት ሰጪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ግንባታና ከተማ ልማት ተቋም መምህር ኢንጂነር ዶክተር ረዳት ፕሮፌሰር ጥበቡ አሰፋ ፤ የግንባታ ዘርፉ በምርምር መታገዝ እንዳለበትና በዘርፉ ትምህርት ከሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የተጠናከረ ግንኙነት ሊኖር ይገባል ይላሉ።በዚህ በኩል በሀገር ደረጃ ያለው ተሞክሮ ደካማ እንደሆነ ይናገራሉ።የግንባታ ኢንደስትሪው ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ሳይሆን፣ንግድ መር እንደሆነም ይጠቅሳሉ።
እርሳቸው እንዳሉት በአንድ አካባቢ የኢኮኖሚ ምጣኔ ሀብት ጥቅም ይገኝበታል ተብሎ ከታሰበ ህንፃ ይገነባል።ማንኛውም ያዋጣኛል ብሎ ያለ ሁሉ ለንግድ ይጠቀምበታል።በህንፃው ፊትለፊት ላይም ያለከልካይ የፈለገውን ያደርጋል። አስፈጻሚው አካል ስለከተማ ገጽታ ሳይሆን፣ ስለሸጠው መሬትና፣ከሽያጩ ስለሚገኘው ገቢና ህንፃው ስለመከራየቱ ነው የሚጨነቀው።
ህንፃዎች እንደ ሰው ፊት ገጽታ ሁሉ በሰዎች ውበታቸው ይደነቃል፡ ይነቀፋል። ግንባታ ከአካባቢው ጋር መጣጥም ይኖርበታል።ሌላው ቀርቶ አንድ ህንጻ ካለው ስም በተጨማሪ የድርጅቶች ስም እና ማስታወቂያ በህንፃው ላይ ሊታይ አይገባም። ህንፃው የታወቀውና የሚጠራ በራሱ ስያሜ ብቻ ነው።
ከፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ የከተማ ዲዛይን የሚባል አዲስ ሙያ መኖሩንና ከ1970ዎቹ ጀምሮ ሲተገበር መቆየቱን የጠቆሙት ኢንጂነር ጥበቡ፤ነገር ግን በአግባቡ ባለመተግበሩ አሁን የሚነሱ ክፍተቶች ሊፈጠሩ ችለዋል። የማዘጋጃ ሹሙ የህንፃውን ከፍታና ርቀትን ከመወሰን ባለፈ በህንፃው ፊትለፊት ስለሚኖሩና ህንፃው ምን አይነት ቀለም ሊኖረው እንደሚገባ ታሳቢ አይደረግም።
ልክ አንድ ቤተሰብ በባህሪና በመልክ እንደሚመሳሰል ሁሉ ህንፃዎችም የዚህን ያህል መሆን ይኖርባቸዋል። በአጠቃላይ የሚነበብ ከተማ መፍጠር ያልተቻለው የተዘበራረቀ የማስፈጸሚያ መመሪያ መተግበሩ ነው። ይህን ለመተግበር ደግሞ የህንፃ ዲዛይንን ጠንቅቆ ማወቅ ይጠይቃል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በዘርፉ ባለሙያዎችን አፍርቷል። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነቡ ህንፃዎችንም ዲዛይን በማድረግ አስተዋጽኦ አደርጓል።ግን በግብአትነት ለመጠቀም ያለው ጥረት ደካማ በመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም።
በአሁኑ ጊዜም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ በሁለተና ዲግሪ መቀሌ፣አዳማ አርባምንጭ ዩኒቨርስቲዎች በከተማ ዲዛይን በማሰልጠን ሚናቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ። የሰለጠነውን የሰው ሀብት በአግባቡ በመጠቀም የግንባታ ዘርፉን ክፍተቶች ማረም ይገባል።የከተማ ዲዛይን በማሰራት ስለእያንዳንዱ ግንባታ መቆጣጠር ከቻሉ ሀገሮች ኪጋሊን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢንጂነር ዶክተር ጥበቡ እንደገለጹት የዘርፉ ባለሙያዎች በተለይም የዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ የከተማ ዲዛይን ማህበር ለማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ማህበሩም እውን ሲሆን፣ ለዘርፉ በተቀናጀ ሙያዊ ዕገዛ በማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። በተለይም በከተማ ፕላንና አርክቴክቸር አማካኝነት በሚከናወን መካከል ያለውን ከፍተት በመሙላት በከተሞች የሚገነቡ ህንፃዎች መልክ ለማስያዝ ያግዛል።
በዘርፉ ለሚሰማሩም ግንዛቤ በመፍጠርም ኃላፊነቱን ይወጣል። እንዲህ ያለውን እገዛ ለማድረግ ማህበር ለማቋቋም ፍላጎቱ ቀድሞም ቢኖርም በገንዘብ አቅም ማነስና የሚያበረታታ አካል ባለመኖሩና በተለያየ ምክንያት ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል።ነገር ግን አሁን ተነሳሽነቱን በመውሰድ ለማቋቋም እንቅስቃሴው ተጀምሯል።
የምጣኔ ሀብትና የፖሊሲ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኽተስፋ፤ በመኪና ለማለፍ አስቸጋሪ የሆኑ ተጣብቀው የተገነቡ ህንፃዎች በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ አካባቢዎች መታዘባቸውን ይናገራሉ።ቦሌ ክፍለከተማ ከአትላስ ቦሌ መድኃኒያለም ቤተክርስቲያን የሚወስደውን መንገድ ለአብነት ይጠቅሳሉ።
ይሄ የከተማው ማስተርፕላን በዘፈቀደ የሚከናወን መሆኑን ያሳያል። በአንዳንድ ቦታ ለተለያየ ተግባር ሲፈለግ በከፊልና በተወሰነ ደረጃ መፍረስ የሚያጋጥመውም በማስተር ፕላን ባለመከናወኑ ነው።ይሄ ደግሞ በግለሰብም በሀገርም የኢኮኖሚ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።
አንዳንዶቹም ከነችግራቸው የሚተውት ኢኮኖሚ ጉዳቱ ታሳቢ በመደረጉ ነው።የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያጋጥም የሚተር ህንፃዎች ጉዳይም ዶክተር ቆስጠንሲኖስን ያሳስባቸዋል።በእርሳቸው ባላቸው ዕውቀት የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያጋጥም ለችግሩ ተጋላጭ አይሆኑም ተብለው የሚታሰቡት የሼራተን ሆቴልና የናኒ ህንፃ ናቸው።
እንደ ፖሊሲ ባለሙያው ማብራሪያ፤ የከተማ አስተዳዳሪዎች በየጊዜው በከተማዋ ለሚገነቡ ህንፃዎች ደረጃቸውን አለመጠበቅና የህንፃ አዋጁም በአግባቡ እንዳይተበር የራሱ ተጽእኖ አሳድሯል።
ማስተርፕላን ከከተሞች እድገት ጋር መለዋወጥ እንዳለባቸው ቢታመንም በጥናትና በዕውቀት አለመሰራቱ ከተሞች ሰፍተው ያስከተሉትን ችግሮች አዲስ አበባ ከተማን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በተለይም የእርሻ መሬትን ለከተማ በማዋል የፖለቲካ ቀውስ አስከትሏል።
የተፈጠረው የከተማው መስፋፋት እንደ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ውሃና፤ ሌሎችንም መሰረተ ልማት ለማሟላት አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጥማል።አሁንም እየታየ ነው። የግንባታ ኢንደስትሪው በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ በማድረግ ለችግሩ መፍትሄ መሥጠት ይገባል። ከከተማው ዕድገት ጋር የሚመጥን ግንባታ ባለመከናወኑ የእግረኛ የሚስተዋለው ለህዝብ አገልግሎት ተብለው የተሰሩ መንገዶች እንኳን ለታለመላቸው ዓላማ እየዋሉ ሳይሆን ለመኪና ማቆሚያ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
አንዳንድ ሀገሮች ከህንፃዎች ሥርና ለመኪና ማቆሚያ በማዘጋጀትና ለመኪና ማቆሚያ ብቻ የሚሆን በመገንባት እንዲህ ያሉ ችግሮችን ማቃለል ችለዋል። በኢትዮጵያም በተመሳሳይ በመተግበር ችግሩን ማቃለል እንደሚያስፈልግ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።
ወጥነት የሌለው የከተማ ህንፃ ግንባታ በዘርፈ ብዙ ችግሮችና ክፍተቶች ውስጥ እንደሆነ ከዘርፉ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ከሙያው ውጭ ያለውም ቢሆን የሚታዘበው በመሆኑ ችግሩ ከማንም የተደበቀ አይደለም። ከሁለት አመት በፊት ወደ ሥራ የገባው የፌዴራል ኮንስትራክሽን ሥራዎች ቁጥጥር ባለሥልጣን የጀመረውን የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በማጠናከር ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም፣አስፈጻሚው አካልም በዘርፉ ውስጥ ያሉትን በማስተባበርና በማቀናጀት ለተሻለ ውጤት መትጋት ይጠበቅበታል።የዘርፉ ባለሙያም ቢሆን ሙያዊ ግዴታውን በመወጣት አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል። ይህ ሲሆን የተናበበ ከተማ መፍጠር ይቻላል። ባለሙያዎቹም ይህንኑ ያጠናክራሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 09/2013