(ክፍል ሀለት)
በክፍል አንድ መጣጥፌ ድሀና ኋላቀር የሆነው በምን ምክንያት እንደሆነ የሚነሱ ምን አልባቶችን፣ መላ ምቶችንና ተረኮችን ከዘረዘርሁ በኋላ በፈርጅ በፈርጅ ከፋፍዬ ለማሳየት የሞከርሁ ሲሆን በመጨረሻ ለኋላቀርነታችን ተጠቃሽ የሆነውን አብይ ምክንያት ገልጫለሁ ።
በዛሬው መጣጥፌ ደግሞ አካታች የፓለቲካ ስርዓትና አሳታፊ የኢኮኖሚ ልማት መጀመሪያ ለኢንዱስትሪ አብዮት በማስከተል ለሁለንተናዊ ብልጽግናና ዴሞክራሲያው ስርዓት ግንባታ ያለውን አስተዋጾ እንግሊዝንና ሰሜን አሜሪካን በአብነት በማሳየት አብራርቻለሁ ። ከዚህ በተቃራኒ ቆመው ከነበሩ ሀገራት ራሽያንና ኢትዮጵያን በዚህ መጣጥፌ ለማስቃኘት እሞክራለሁ ።
የፈረንሳይ አብዮት እንደ እንግሊዙ ግሎሪየስ አብዮት አነሳሱ ስር ነቀልና አደገኛ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ በአውሮፓ ለተለኮሰው የኢንዱስትሪ አብዮት አዎንታዊ አስተዋጾ ነበረው ። በሒደት ፓለቲካው አሳታፊ ፤ ኢኮኖሚው አካታች እየሆነ በመምጣቱ በእንግሊዝ ፣ በአውስትራሊያ ፣ በአሜሪካና በካናዳ ብልጽግና ማበብ ዴሞክራሲ መጎልበት ጀመረ ።
የግሎሪየስና የፈረንሳይ አብዮቶች ተንሰላስለው በምዕራብ አውሮፓ ሰማይ የዕድገት ጎህ እንዲቀድ አስቻሉ ። የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መሠረት ጣሉ። በእነዚህ ስኬታማ አብዮቶች የተነሳ አብዮት ሁሉ አጥፊና አፍራሽ ተደርጎ መታየቱ ቀረ ።
በተቃራኒው የለውጥ መነሻና መስፈንጠሪያ የሚሆንበት አጋጣሚ እንዳለ ምሳሌ ሆኑ ። አብዮቶች ፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ አገዛዝ የሚጎነቁሉ ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ተቋማት የሚጎለብቱበት እና የበለጸገ ሀገር መገንባት የሚችሉበት አጋጣሚም እንዳለ አብነት ሆኑ ።
በአንጻሩ አብዛኛዎቹ አብዮቶች የራሽያን የጥቅምት አብዮት ጨምሮ ሁሉም አካታች የኢኮኖሚና አሳታፊ የፓለቲካ ስርዓት ባለማቆማቸው ዛሬ ድረስ ባሉበት ይረግጣሉ ። የዛር ስረወ መንግስት (1547 _ 1917 ) በጥቅምቱ 1917 ዓም እኤአ በላቭ አደሩ ፣ በወታደሩ ፣ በገበሬው ፣ በተማሪው ፣ በከተማ ነዋሪው ፣ ወዘተረፈ የተባበረ ክንድ ሲገረሰስ ኃላፊነቱ የወደቀባቸው እነ ሌኒን ኢኮኖሚውን አካታች ፓለቲካውን አሳታፊ ከማድረግ ይልቅ የካርል ማርክስን የሶሻሊዝም ማኒፌስቶ እንዲመቻቸው አድርገው አጣመውና አዛብተው የ” ሶሻሊዝምን ” ስርዓት ተከሉ ። የዛሩን አምባገነናዊ አገዛዝ በሌላ ሶሻሊስት ፈላጭ ቆራ ተኩ ።
በሀሳብ የተለዩዋቸውንና በጋራ ከመሠረቱት የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ወጥተው ሜንሸቪክ ፓርቲን ያቋቋሙ ጓደኞቻቸውን ሳይቀር መግደል ፣ ማሳደድና ማሰር ቀጠሉ ። በምትኩ የእነ ሌኒኑ ቦለሸቪክ ፓርቲ በምድሯ ያለከልካይ አዛዥና ናዛዥ ሆኖ ወጣ ። ዛር ተቆጣጥሮት የነበረውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚና የተፈጥሮ ሀብት በመዳፋቸው አስገቡ ።
ጆሴፍ ስታሊን በቭላዲሚር ሌኒን ሲተካ የባሰ አረመኔና ጨፍጫፊ ሆነ ። በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ጨፈጨፈ ፣ አጋዘ ፣ አሰረ ። አብዮቱ ስርነቀላዊ ለውጥን ቢያገላግልም እንደ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ የእንግሊዝ ግሎሪየስ አብዮት ፓለቲካው አሳታፊ ኢኮኖሚው አካታች ባለመሆኑ ራሽያ ልትበለጽግና ዲሞክራሲያዊ ልትሆን አልቻለችም ።
ንጉሳዊውን አምባገነናዊ አገዛዝ በሌላ በኮሚኒስታዊ አገዛዝ ተክተው በዝባዥና ጨቋኝ በመሆናቸው ኢኮኖሚውንም ፓለቲካውንም በመዳፋቸው ስር በማድረጋቸው ዛሬ ድረስ በሩሲያ እንደ ምዕራባውያን ያለ ኢኮኖሚና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መከተል አልተቻለም።
የቀድሞው የሶቭየት ሕብረት የስለላ ድርጅት (ኬጂቪ )የበርሊን ወኪል ቭላዲሚሪ ፑቲን በመጀመሪያ እኤአ ከ1999 እስከ 2008 ድረስ በሁለት ተከታታይ “ምርጫዎች” በማሸነፍ በፕሬዘዳንትነት ሆኖ ካገለገለ በኋላ የሀገሪቱ ሕገ መንግስት ከሁለት ጊዜ በላይ ለፕሬዘዳንትነት መወዳደርን ስለማይፈቅድ ታማኝ አገልጋዩ እንደሆነ የሚነገርለትን ጠቅላይ ሚንስትር ዲሜትሪ ሜድቬዴቭን በፕሬዝዳንትነት አስመርጦ እሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ ። ለነገሩ የፕሬዝዳንትነቱ እውነተኛው መንበር እሱን ተከትሎ ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ተዛውሯል ።
ለስሙ ነው እንጂ ፕሬዝዳንቱ ያው ፑቲን ነው የነበረው ። ሜድቬዴቭ የአንድ ጊዜ አስመሳይ የስልጣን ጊዜውን ሲያጠናቅቅ ፑቲን ተመልሶ ለሶስተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆነ ። በቅርቡ ደግሞ በሕዝበ ውሳኔ ሕገ መንግስቱን በማሻሻል እስከ 2036 ዓም በፕሬዝዳንትነት የሚያቆየውን የስልጣን ኮርቻ አደላድሏል ።
ራሽያ ሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና አካታች የኢኮኖሚ ፓሊሲ ባለመትለሟ ከዚህ አዙሪት ሰብራ መውጣት ተስኗታል ። በተፈጥሮ ሀብት ፣ በነዳጅና በከበሩ ማዕድናት የበለጸገችዋ ራሽያ ዜጎቿን ሳይሆን ገዥዎቿንና የእነሱን ባለሟሎች ማበልጸጓን ዛሬ ድረስ ገፍታበታለች ። አንዳንድ የምዕራባውያን ሚዲያዎች የፑቲንን ሀብት 200 ቢሊዮን ዶላር ይገምቱታል ።
ይህ ረብጣ ሀብት ፑቲንን ምንአልባት በአለማችን ቁጥር አንዱ ቢሊየነር ሳያደርገው ይቀራል ። ራሽያ የፑቲን የግል ንብረት ተደርጋ የምትታየው ለዚህ ነው። ሰሞኑን የፑቲን ዋነኛ ተቃዋሚና የጸረ ሙስና ትግል ቀንዲል የሆነው ደማሙ/ካሪዝማቲክ ለማለት ነው ፤/ አሌክሲ ናቫልኒ ከስድስት ወራት በፊት በፑቲን አገዛዝ የስለላ ድርጅት ኤፍ ኤስ ቢ እንደተቀነባበረ በሚነገርሩርለት ኖርቪቾክ በተሰኘ መርዝ የግድያ ሙከራ ተደርጎበት በጀርመን ሀገር በተደረገለት ህክምና በተአምር ህይወቱ ተርፎ ትግሉን ካቆመበት ለመቀጠል በድፍረት ወደ አባት ሀገሩ ራሽያ ሲመለስ በአውሮፕላን ማረፊያው የቤተሰቦቹ ወይም የደጋፊዎቹ የእንኳን አተረፈህ እቅፍ አበባ ሳይሆን የጠበቀው የፓሊስ ካቴና ነበር ።
ተይዞ ወደ ዘብጥያ ወርዷል ። በበነጋው ግን ራሻውያንን ያስቆጣ አለምን ያነጋገረ እነ ፑቲንን ያሳጣ የሁለት ሰዓት ዘጋቢ ፊልም በናቫልኒ ድርጅት በዩቲውብ ተለቀቀ ። በመጀመሪያው ቀን ብቻ በአስር ማሊዮኖች የሚቆጠሩ ራሻውያን ተመለከቱት ። ተቀባበሉት ።
ናቫልኒ በሚተርክበት በዚህ ፊልም ፤ በ1 ነጥብ 35 ቢሊዮን ዶላር በጥቁር ባሕር ዳርቻ የተገነባ የፑቲንን እጅግ ቅንጡ ቤተ መንግስት በድሮን በታገዘ ቀረጻ በማሳየት በአገዛዙ ሙስና ምን ያህል እንደገነገነ ያሳያል ።
በዚህ ክፉኛ የተቆጡ ራሽያውያን ከተሞችን በተቃውሞ ሰልፍ አጥለቀለቋቸው ። ፑቲንና ጭፍራዎቹ የሚነሱባቸውን ተቃውሞዎች ሁሉ በኃይል ጸጥ እያደረጉ ፤ የሚነሳባቸውን ተቃውሞ ሁሉ የምዕራባውያን ሴራ ነው እያሉ ፤ የራሽያን ብሔርተኝነት እንደመሳሪያ እየተጠቀሙ እና ፑቲን ራሽያን ለመታደግ የመጣ መሲህ አርገው በመሳል እሱ ከሌለ ራሽያ የድህረ ሶሻሊዝም የእነ ቦሪስ የልሲን ዘመን ቀውስ እንደሚገጥማት በማስፈራራት የእድሜ ልክ ገዥ ፈጥረዋል ። ራሽያ ከዚህ አዙሪት መቼ እንደምትወጣ ማንም እርግጠኛ ሆኖ መናገር የማይቻለው ለዚህ ነው ።
አውዱና መልክዓው ለየቅል ቢሆንም የአጼ ኃይለስላሴን አገዛዝ በመፈንቅለ መንግስት የገረሰሰው ደርግ አሳታፊ የፓለቲካ ስርዓት እና አካታች የኢኮኖሚ ፈር ባለመቀየሱ አዲስ አይነት ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ አረፈው ።
ንጉሳዊው አገዛዞ በወታደራዊ አገዛዝ ተተካ ። ይሆን የታዘበው ሀገሬው ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም በማለት ለውጥ እንዳልመጣ ቅሬታውን ገለጸ ። ለውጡን ተከትሎ የተሰነቀው ተስፋ የማይጨበጥ ጉም ሆነ ።
በወታደራዊ ደርግ የተቀማው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ፣ ገበሬዎች ፣ ላቭ አደሮችና ከተሜዎች የ1966ዓም አብዮት በሀገራችን ታሪክ በወሳኝ መታጠፊያነት/critical juncture /ከሚጠቀሱ የታሪክ ገጾች ቀዳሚ ነው።
በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ማለትም ከአጼ ቴዎድሮስ ንግስና እስከ ደርግ መገርሰስ ባለው ጊዜ(1847 እስከ 1983ዓም) ከታላቁ የአድዋ አንጸባራቂ ድል ቀጥሉ የ66ቱን አብዮት ያህል የሀገራችንን ቀጣይ እጣ ፈንታ የበየነና የወሰነ ታሪካዊ ሁነት የለም ማለት ይቻላል ።
ዛሬ ሀገራችን ለምትገኝበት ሁለንተናዊ ስካርም ሆነ እራሷን ፈጥርቆ ለያዛት ሀንጎቨር የዳረጋት ጌሾው የበዛበት የ66ቱ ጥንስስ ነው ። አዎ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ለምትገኝበት ፓለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ወዘተረፈ ስካር ያ አላዋቂ የጠነሰሰው የዳጉሳ ጠላ ተወቃሽ ነው ።
ደርግ ይህን ታሪካዊ መታጠፊያ አሳታፊ ፓለቲካዊ ምህዳር እና አካታች ኢኮኖሚያዊ ማዕቀፍ በማዘጋጀት የሀገሪቱን መጻኢ እድል በአዎንታዊ መበየን ይችል ነበር። ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ሕዝባዊ የሽግግር መንግስት በማቋቋም በቀጣይ ነጻ ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ማካሄድ ይችል ነበር ። ደርግ ግን እንደነ ሌኒን ለስልጣኔ ያሰጉኛል ያላቸውን የአጼ ኃየለስላሴ ባለስልጣናትን እና የደርግ አባላት ሳይቀር መግደል ጀመረ ።
እነ አጥናፉ አባተንና ተፈሪ በንቲ በመንግስቱ የሚመራዊ የደርግ ክንፍ ገና በማለዳው በግፍ በመግደል ስልጣኑን ካደላደለ በኋላ መጀመሪያ ወደ ኢህአፓ በኋላ ፊቱን ወደ መኢሶን በማዞር መተኪያ የሌለውን የተማረ አንድ ትውልድ ጨረሰ ።
ለዛውም ባለብሩህ አእምሮ ሙህራንና በትምህርታቸው ጎበዝ የነበሩ ሀገር ተረካቢ ወጣቶችን ። በነገራችን ላይ በዛን ጊዜ የተፈጠረ ክፍተት ዛሬ ድረስ ሊሞላ ባለመቻሉ ዳፋው እንደ ጥላ ይከተለናል ።
የአጼውን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ገርሶሶ የባሰ አምባገነናዊ ሆኖ አረፈው። መሬት ለአራሹን አውጆ ብዙም ሳይቆይ የገበሬውን ምርት በርካሽ በኮታ መሰብሰብን ተያያዘው። መሬቱን በእጅ አዙር ተቆጣጠረው ። ንጉሳዊ አገዛዙ እንዳሻው ያዝዝበት የነበረውን ኢኮኖሚ በሶሻሊዝም ስም ተቆጣጠረው ። አፈናውን አባብሶ ቀጠለበት ።
የደርግን አዝማሚያ ገና በውል ሳያጤን ትህነግ/ህወሀት የሸዓብያን የትጥቅ ትግል መንገድ መከተል መረጠ ። እነዚህ ኃይሎች እየተጋገዙ በደርግ ላይ የሚሰነዝሩት ወታደራዊ ጥቃት እየተጠናከረ ሄደ ። ከአመት አመት እየተጠናከሩ ፤ የሚቆጣጠሩት ነጻ መሬት እየሰፋ ፤ ትግሉን የሚቀላቀል ወጣት ቁጥር እየጨመረ ፤ በጦር መሳሪያና በትጥቅ እየደረጁ መጡ ።
በመጨረሻም ትህነግ ከ17 አመታት የትጥቅ ትግል በኋላ በ1983 ዓም አዲስ አበባን ፤ ሸዓብያ ከ30 አመት የትጥቅ ትግል በኋላ በዚሁ አመት አስመራን ተቆጣጠሩ ። ትህነግም ሆነ ሸዓብያ እንደ ደርግ ሁሉ አሳታፊ የፓለቲካ ስርዓትና አካታች የኢኮኖሚ መንገድ በመትለም ከአዙሪቱ ሰብረው የመውጣት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸው የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀሩ ። የደርግ አሞባገነናው አገዛዝ በሌላ ለዛውም ሀገርን አምርሮ በሚጠላ ዘረኛ ፣ ከፋፋይና ዘራፊ አገዛዝ ተተካ ።
ባለፉት 30 አመታት በፌደራልና በኋላ በትግራይ አገዛዝ ላይ የነበረው “ነጻነትን የማያውቀው ነጻ አውጭ !” ትህነግ ለዜጎች ነጻነትና እኩልነት ታገልሁ ቢልም በተግባር ግን ከደርግ የባሰ አምባገነን ፣ ዘራፊና ቀውስ ቀፍቃፊ ሆነ ። እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፌደራል ስርዓት የማቆም እድል ቢያገኝም እሱ ግን አስመሳይ ዴሞክራሲን እንዲሁም ከፋፍሎ ለመግዛት የሚያመቸውን እና በዜጎች መካከል መጠራጠርን ፣ ልዩነትንና ጥላቻን የሚጎነቁል አገዛዝ ተከለ ።
የማንነትና የጥላቻ ፓለቲካ በተለይ ለ30 አመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ ሌት ተቀን በመሰበኩ ምክንያት ኢትዮጵያዊ ማንነት እየኮሰመነ አክራሪ ብሔርተኝነት እየገነገነ መጣ ። በዚህም የሀገር ህልውናና የግዛት አንድነት ፈተና ላይ ወደቀ ። በዜጎች መካከል ጥላቻ ፣ ልዩነትና መጠራጠር ሰፈነ ።
የአንድ ቡድን የበላይነት ገነነ ። ኢኮኖሚውን ከሽንኩርት ችርቻሮ እስከ ጅምላ ንግድ ተቆጣጠረው ። ፓለቲካዊ ስልጣኑን ጠቅልሎ በመዳፉ አስገባ ። የዜጎች ነጻነትና ዴሞክራሲ ባዶ ተስፋ ሆኖ ቀረ ። ደርግ በአዲስ አይነት ማፊያ ቡድን ተተካ ። ጭቆናው ከአመት አመት እየተባባሰ ሄደ።
ዘረፋ የአገዛዙ መለያ ሆነ ። የስብሀታዊ ስረወ መንግስት ሀገሪቱን በአጥንት አስቀራት ። ዜጎችን ሁለተኛ ዜጋ አደረጋቸው ። በዚህ የተማረረው ሕዝብ በተደጋጋሚ በተለያየ መንገድ ለውጥን ቢጠይቅም መልሱ ማብቂያ የሌለው ግድያ ፣ ስቃይ ፣ አፈናና እስር ሆነ ። በመጨረሻ ሕዝባዊ ተቃውሞው እየተጠናከር በትህነግ/ኢህአዴግ ውስጦ ያለው የለውጥ ኃይል ከሕዛዊ ተቃውሞው ጋር እየተናበበና እየተንሰላሰለ ከሶስት አመታት በፊት ለውጡ እውን ሊሆን ቻለ ።
ይህ ለውጥ ግን ከደርግም ሆነ ከትህነግ/ኢህአዴግ በመሠረቱ ፍጹም የተለየ ነው ማለት ይቻላል ። እንደ ቀደሙት አንድን አምባገነነ በሌላ የተካ ሳይሆን ምን አልባት የለውጥ ኃይሉ እንደ ሀገር እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት የመጨረሻው ዕድል እንደወጣለት በውል የተገነዘበና ወሳኝ መታጠፊያ እጁ ላይ እንደገባ በማጤን ፓለቲካውን አሳታፊ ፤ ኢኮኖሚውን አካታች ለማድረግ ተቋም መገንባት አሰራርን ማሻሻል የማይተካ ሚና እንዳላቸው በመረዳት ሶስት አመት ባልሞላ ጊዜ እንደ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚንስቴር ያለ አኩሪ ተቋም ገንብቶ ሀገርን በትህነግና በታሪካዊ ጠላቶቿ ተደግሶላት ከነበረ አደጋ መታደግ ቻለ ። እንደ ፈጣሪ ፈቃድ በቀጣዩና ሶስተኛ ክፍል መጣጥፌ የለውጥ ኃይሉ እየገነባቸው ስለአሉ ተቋማትና ይዘውት ስለመጡ ተስፋዎች አነሳለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
አዲስ ዘመን የካቲት 09/2013