ጌቴሴማኒ ዘ-ማርያም
ኮቪድ19 በሀገራችን ከተከሰተ ወራት አልፈው ዓመቱ እየተያዘ ነው። ቀደም ሲል በህክምና ተቋማት ቅጥር ጊቢብቻ ወረድ ሲልም በአንዳንድ በትንፋሽ አማካኝነት የሚተላለፉ በሽታዎች ሕክምና መስጫ ክፍሎች ጭምር አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የአፍና አፍንጫ ጭንብልም ወደ አደባባይ ወጥቶ መላውን ሕዝቡን ከኮቪድ ለመታደግ መዋል ከጀመረ እንዲሁ ዓመት እየሆነው ነው። በዚሁ አንደኛ ዓመቱን ለመድፈን በተቃረበ ዕድሜ ውስጥ የአፍና አፍንጫ ጭንብል በሀገራችን በዋነኛነት ኮቪድ 19ን ለመከላከል ሲውል ቢታይም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት።
እነዚህን ጥቅሞቹን የህክምና ባለሙያዎቹ ከእኛ ከደቀ መዛሙርቶቻቸው ቀድመውና አሣምረው እንደሚያውቋቸው ለመግለፅ የሚያስችሉ ብዙ ማሳያዎች አሉ። እነዚሁ ባለሙያዎች እያንዳንዱ የህክምና አገልግሎት በሚሰጥበት ክፍል ሁሉ የአፍና አፍንጫ ጭንብሉን በማድረግ ጥቅሙን ሲተገብሩ መመልከቱ ጭንብሉን ማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የተረዱ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው።
እኔ እንዳስተዋልኩት ከነዚሁ ባለሙያዎች ያልተናነሰ የአፍና አፍንጫ ጭንብልን ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያውቁ አያሌ ተጠቃሚዎችም አሉ።እኔ እንዳስተዋልኩት አንድ ዓመቱን ሊይዝ በተቃረበው የአፍና አፍንጫ ጭንብል አገልግሎት ዕድሜ ውስጥ ጥሩ ልምድ ተገኝቷል። ከጤና ባለሙያዎች ባልተናነሰ ሁኔታ የአፍና አፍንጫ ጭንብልን ዘርፈ ብዙ ጥቅም የተረዱ አያሌ ተጠቃሚዎችን ማፍራትም ተችሏል።
ይሄ ደስ የሚያሰኝና እሰየው! የሚያስብል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እዚህ ጋር ተጠቃሚዎች የምንላቸው ያለውን ዋጋ ተረድተው በአግባቡ የሚገለገሉበት ብቻ ናቸው። ምክንያቱም ይሄን ማለታችን በአግባቡ ካልተገለገሉበት ጥቅሙን ማወቅ ብቻ አላዋቂ ከመባል የማያድንና ትርጉም የለውምና ነው።
የተጠቃሚዎቹ ግንዛቤና አተገባበር እጅግ የሚበረታታ ነው። ቢሆንም ብዙዎቻችን ጭንብሎቹ ከኮቪድ ባሻገር ሌሎች በሽታዎችን እንደሚከላከሉልን ግንዛቤ ያለን አይመስለኝም። ቢኖረንም አናሳ ነው ባይ ነኝ። ወይም ደግሞ በተለይ ጭንብሎቹን አዘውትረን ስንጠቀም አለመታየታችን አውቀን እንዳላዋቂ የሆንን ያስመስልብናል።
ግን ደግሞ አውቀን እንዳላዋቂ በመሆናችን እራሳችን እንጂ ኮቪድ አይጎዳም።በመሆኑም ጭንብሉ ያለ ዕድሜያችን ሊቀጥፉን ከሚችሉ ከብዙ በሽታዎች እንደሚታደገን የግድ ማወቅ አለብን።አውቀን መተግበርም ይጠበቅብናል።
ዕድሜ ለጭንብል! ብዙ የአፍና አፍንጫ ጭንብል ተጠቃሚዎች አሁን ላይ እራሳቸውን ከኮቪድ ቫይረስ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ በሽታዎች እየተከላከሉ ይገኛሉ።በመከላከሉ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እያገኙበት መሆኑንም ከራሳቸው አንደበት እያደመጥን ነው። ማንኛውም መጥፎ ጠረን ከሚያስከትለው የጉንፋን ኢንፉሌንዛ ቀላል ቫይረስ ጀምሮ ከቲቢና ከሌሎች
በትንፋሽ አማካኝነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ራሳቸውን መጠበቅ ችለዋል። በዚህም ከራሳቸው አልፈው ተርፈው ሌላውን የሕብረተሰብ ክፍልም ከነዚሁ በትንፋሽ አማካኝነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ሲከላከሉ እየታዩ ነው። እንደነዚህ የአፍና አፍንጫ ጭንብል ተጠቃሚዎች ጭንብል ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በኮቪድ ምክንያት በስፋት እንደውም ሁሉም ዜጋ በሚባል ደረጃ የአፍና አፍንጫ ጭንብል ማድረግ ከጀመረ በኋላ ጉንፋን ጨርሶ ባይጠፋም በመጠን እየቀነሰ መጥቷል። እጅግ ኃይለኛ ሳል የሚስል፣የሚያስነጥስ ዜጋ ቁጥሩ ቀንሷል። ይሄ የሚበረታታ ነው! ለአፍና አፍንጫ ጭንብልም የላቀ ምስጋና ያስቸረዋል።
በጭንብል ተጠቅሞ ከኮቪድ መጠንቀቁንና መከላከሉንም ያስቀጥልና ብዙ ዜጎችም የጭንብሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያነሳሳል፤ ያበረታታል። ይሄን ተሞክሮ ከፋይዳው አንፃር ቀምሮ ማስፋትም ተገቢ ነው።
በተለይ ያለማሰለስ ስትስሉና ስታስነጥሱ አፍና አፍንጫችሁን በክርናችሁ ሸፍኑ እየተባለ በሚነገርበትና አንዱ ወገን ለሌላኛው ወገን ብርቱ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በሚመከርበት ዛሬ ድረስ የባህርይ ለውጥ ማምጣት ያልቻሉ ግለሰቦችን እዛው በፀበላችሁ ብሎ የሚይዝልን ገደብም ነው ጭንብል።
ጎበዝ! እውነት ለመናገር እኮ እነዚህ ዓይነቶቹ በሥራ ገበታም ሆነ መንገድ በመጋራትና በተለያየ አጋጣሚ የምናገኛቸው ግለሰቦች ለሌላው ጤና ግድ አይሰጣቸውም። ሲያስነጥሱም ሆነ ሲያስሉና ሲያወሩ ለእናንተ የሚያደርጉት ጥንቃቄ የለም።በነዚህ አጋጣሚዎች የሚወጣው ትንፋሻቸው አየሩንና አፍንጫዎን ከመበከል አልፎ የምራቃቸው ፍንጥቅጣቂ ፊትዎትና የሰውነት ክፍሎቾ ላይ ያርፋል።
ምን ይሄ ብቻ አንዳንዴ መከላከል ባልቻሉበት ሁኔታና ደረጃ ከሆኑ አፍና አፍንጫቸውን በክርናቸው በመሸፈን መጠንቀቅ ቀርቶ ጎንበስ እንኳን ሳይሉ በቁማቸውና በቅምጣቸው በሚለቁበት አንጥሼና ሳል ውስጥ ያለው ምራቃቸው ድንገት አፎት ውስጥ ሁሉ ሊገባ ይችላል።አበስኩ ገበርኩ! እነዚህ ግለሰቦች በትንፋሻቸው አማካኝነት የሚተላለፈውን በሽታ ቀርቶ የአንዱ ምራቅና ትንፋሽ ለሌላው ጽዩፍ ስለመሆኑ እንኳን ግንዛቤ ያላቸው አይመስሉም።
ጉንፋንና ሳል በያዛቸው ወቅትማ ለሌላው ያለመጠንቀቅ ጉድለታቸው እርሶን ለማስያዝ ዕቅድ የያዙና እልህ የገቡ እስኪመስሎት ድረስ ያስቀይሞትና ያሳዝኖታል። ነገሮችን ማመዛዘን የተሳነው እንስሳ ወይም አላዋቂና የአዋቂ አጥፊ አድርገው እንዲቆጥሯቸው ያስገድዶታል።
ብቻም ሳይሆን የግለሰቦቹ ሁኔታ እርሶም በወቅቱ ዝግጁ ካልነበሩ ይሄኔ ነው ጭንብል የሚል ትምህርት እንዲወስዱና የጭንብል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስተምሮታል።
እርግጥ ነው!ጭንብል ውለታው ፈርጀ ብዙ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። በዓለም ላይ ቁጥር አንድ ገዳይ የሆነውን ቲቢን ወይም የሣንባ በሽታን ለመከላከል አብዝቶ ያስፈልጋል። በሽታው ከ190 በላይ ዝርያዎች ያሉት ማይክሮ ቫክቴሪያ መያዙ አስፈላጊነቱን ያጎላዋል። በእርግጥ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በእኛ ሀገር የሚገኙት የቫክቴሪያ ዝርያዎች ሁለት ብቻ ናቸው።
ሆኖም የባክቴሪያ ዝርያዎቹ ማነስ በሽታውን በጭንብል መከላከሉን አያስቀረውም። እንደውም አንዱ ዝርያ የቆዳና የአጥንት እንዲሁም የነርብ ጫፎችን በመጉዳት የአካል ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ መከላከሉን ይበልጡን ያጎላዋል እንጂ አይቀንሰውም። ሁለተኛው ዝርያ በዋናነት ሳንባን ያጠቃል።
ሳንባ ሣይበቃው ሙሉ በሙሉ የሰውነት ክፍሎችን ይጎዳል።ይሄ ዓይነት የሳንባ በሽታ ከላይኛው መተንፈሻ አካል ጀምሮ ከፀጉር እስከ ጥፍር ድረስ ማጥቃት በሚችል ቫክቴሪያ የሚተላለፍ ነው።
ቫክቴሪያው እንትፍ ተብሎ በሚተፋ አክታ ወይም በምራቅ ውስጥ በሚገኝ ትንፋሽ ውስጥ ነው የሚኖረው ።በአየር አማካኝነትም ትንፋሹ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።እናም ይሄ ቫክቴሪያ እንደ ማንኛውም የመተንፈሻ አካል በሽታ በትንፋሽ የሚተላለፍ መሆኑ ደግሞ የአፍና አፍንጫ ጭንብልን ተጠቅሞ በሽታውን መከላከሉን የበለጠ አስፈላጊ ያደርገዋል።
ጎበዝ! ይሄ ቀላል አይደለም። ከአንድ ቲቢ ታማሚ በትንፋሽ አማካኝነት የሚወጣ ቫይረስ በአንድ ጊዜ መአት ሰዎችን የመበከል አቅም እንዳለውም ልብ ማለት ይገባል። በዚህ ላይ እንዲህ ያለ የቲቢ ታማሚ ቁጥር በሀገራችን ቀላል አይደለም።የ2017 የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ 125 ሺ 836 ታካሚዎች በቲቢ እንደተያዙ አረጋግጣለች።
ሕክምና መስጠትም ጀምራለች። እንደዚሁ ሪፖርት ዝርዝር ሀሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ100 ሺ ሰዎች 177ቱ በቲቢ በሽታ ይጠቃሉ። ከነዚህ መካከልም 25 በመቶው ይሞታሉ። ለሞታቸው ዋናው ምክንያት ተብሎ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው በአቅራቢያቸው ወደ አለ ህክምና ተቋም ሄዶ ምርመራ አለማድረግ ነው። ምርመራ አድርጎም መድሃኒት አለመጀመርም እንዲሁ በምክንያትነት ተጠቅሷል።
የሚገርመው ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡት 36 በመቶዎቹ መድሃኒቱን ለመውሰድ የሚመጡ አለመሆናቸው ደግሞ የበሽታውን ስርጭት የሚያሰፋ መሆኑ ነው።እኔ በበኩሌ የእነዚህ ህመምተኞች ጉዳይ በእጅጉ ያሳስበኛል።
መቼም ጨረቃ ላይ አይኖሩ። ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው ነው የሚኖሩት።በዚህ ላይ እነዚህ እያልን እኛ ጣታችንን በመቀሰር የምንጠቁማቸው አይበለውና ወይም እኮ እኛ ራሳችን ሆነነው እንገኝ ይሆናል።
በመሆኑም ወይም በመሆናችን ዕለት በዕለት በሚያደርጉት ወይም በምናደርገው እንቅስቃሴና ማህበራዊ መስተጋብር በሽታውን በከፍተኛ ደረጃ ከሰው ወደ ሰው የማስተላለፍ ዕድላቸውና ዕድላችን እጅግ ከፍተኛ ነው።
በዚህ ላይ እንኳን እነዚህ ህሙማን ጤናማ ነኝ ብሎ ደረቱን ነፍቶ የሚናገረው የሕብረተሰብ ክፍል ለሁለተኛ ወገን ሲያደርግ ከሚታየው የጥንቃቄ ልምድ ማነስ አንፃር የበሽታው ስርጭት በፍጥነት መስፋፋቱ አይቀርም። ስለዚህ ቢቻል ለሌላውም ከማሰብ ካልሆነም ደግሞ ለራስ ሲባል ጭንብልን መጠቀም ባህላችን እናድርግ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2013