አሥመረት ብሥራት
የሚጥል ሕመም (ኢፒለፕሲ) በተመለከተ መረጃ ይሰጡን ዘንድ ያነጋገርናቸው የጭንቅላት፣ የሕብረሠረሠርና የነርቭ ቀዶ ህከምና እስፔሻሊስት ዶክተር ዘነበ ገድሌ ስለሕመሙ ያጋሩንን እነሆ በማህደረ ጤና ገፃችን ልናካፈላቸሁ ወደድን። የሚጥል ሕመም (ኢፒለፕሲ) ማለት በአንጎል ነርቮች ላይ ተገቢ ባልሆነና በበዛ የኤሌክትሪክ ፍሰት የሚከሰት ቢሆንም ምልክቶቹም በተለምዶ የሚታወቀው በሚጥልና ራስን ስቶ በመውደቅ ሲሆን፤ አንዳንድ ጊዜ ራስ ሣያስት እንዲሁም ሣይጥል በአንድ ጎን ማንቀጥቀጥ ብቻ ሊከሰት ይችላል።
የሚጥል በሽታን የሚያመጡ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። እነዚህም ከወሊድ በፊትና በወሊድ ጊዜ ሕፃኑ ላይ የሚደርስ አደጋ ዋነኛ ምክንያት ነው። ይህም ብዙ ጊዜ ከእናት ሕመምና አስቸጋሪ ምጥ ጋር ሊያያዝ ይችላል። ሌላው ደግሞ በአንጎል ውስጥ በተፈጥሮ ያልተሥተካከለ ወይም የጎደለ ክፍል ሲኖር በሕፃንነት ጊዜ የነበሩ ሐይለኛ የትኩሣት በሽታዎች የአንጎል ኢንፌክሽን ለምሣሌ እንደ ማንጅራት ገትር የአንጎል ወባ ወዘተ አንጎል ውስጥ የሚያድጉ ዕጢዎች በሠውነት ውስጥ የሚገኙ ሠውነትን የሚጠቅሙ ንጥረ ነገሮች በልክና በትክክል አለመገኘት ማለት ነው።
ለምሣሌ በደም ውስጥ የሥኳር መጠን ማነስ፣ በተለያየ አደጋ ጭንቅላት ሲመታና አንጎል ላይ አደጋ ሲደርስ፣ የአካል በመርዝ መበከል ለምሣሌ ራስን ለማጥፋት ተብለው የሚወሰዱ እንደ ማላታይን የመሣሠሉ መድሃኒቶች፣ የአንጎልን ነርቭ የሚጎዱ ሕመሞች ለብዙ ዓመታት አልኮል መጠቀም፣ በዘር መተላለፍና የመሣሠሉት የሚጥል በሽታ መነሻ ምክንያቶች ናቸው። የሚጥል ሕመም እንደየባህሪዎቻቸው የተለያዩ ዓይነቶች ናቸው።
ግራንድ ማልሲዠር፤ ይህ ዓይነቱ የሚጥል ሕመም ያለባቸው ሰዎች ከመውደቃቸው ከተወሠነ ደቂቃ፣ ሰዓት ወይንም ቀን በፊት የሚሠሙ የመረበሽ ሥሜቶች ከመውደቃቸው ከጥቂት ሴኮንዶች በፊት የሚፈጠር ሥሜት። ይህ ሥሜት የሚገለፀው ለምሣሌ የፍርሃት ሥሜት መሠማት ወዘተ…ሊሆን ይችላል። በአጠቃላይ ውስጣቸው የመረበሽ ምልክቶች ያሣያል።
ሲዠር (ማንቀጥቀጥ)፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የጡንቻ መሣሣብ የሠውነት መገታተር እና መንቀጥቀጥ እንዲሁም ራስን እንደሣቱ መቆየት፣ ሽንት መልቀቅ፣ አረፋ መድፈቅ ይከሠታሉ። ከነቁ በኋላም የመርሣት፣ ከባድ እንቅልፍ እና የራስ ምታት ሥሜቶች ተከትለው የሚከሠቱ ናቸው።
ፔቲትማል (አብሰንስ)፤ ይህ ዓይነቱ ደግሞ በብዛት የሚፈጠረው በሕፃናት ላይ ነው። ምልክቶቹ ከመፈጠራችው በፊት ምንም ሥሜት አይሠማቸውም። ነገር ግን በድንገት ንቃተ ሕሊናቸውን ያጣሉ። ይህም ማለት ራስን አለማወቅ ውስጥ ይገባሉ ማለት ነው፣ መንቀሳቀስ ያቆማሉ፣ መነጋገር ያቆማሉ፣ ወደ አንድ አቅጣጫ ዓይናቸው ይቀየራል። የዓይን ሽፋሽፍት፣ የፊት ጡንቻ እና የጣት መንቀጥቀጥ ይታይባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ከንፈር መምጠጥ እና ማኘክ ይታይባቸዋል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች የሚቆዩት በአብዛኛው ለ10 ሰከንድ ያህል ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ሊከሰት ይችላል። በተወሰነ የሠውነት ክፍል ላይ ብቻ የሚከሰት ኢፒለፕሲ ዓይነቶች (ሲምፕል ፓርሻል ሲዠር) ይባላል።
ሲምፕል ፓርሻል ሲዠር የፓርሻል ሲዠር ዓይነት ሲሆን፤ ምልክቱም በአንድ አቅጣጫ አንገት እና ዓይንን መጠምዘዝ፣ በአንድ ጎን እጅና እግርን ማንቀጥቀጥ ሲሆን፤ ነገር ግን ራስን መሣትም ሆነ መሬት ላይ መውደቅ አይከሠትም።
ኮምፕሌክስ ፓርሻል ሲዠር ሌላኛው የፓርሻል ሲዠር ዓይነት ነው። ምልክቶቹም ሕመሙ ሲጀምር የተለያዩ ሥሜቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ለምሣሌ ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ (የሌላ) ድምጽ መስማት፣ ማየት እና የእይታ መጭበርበር ነው። አካባቢን በአግባቡ የመረዳትና የመገንዘብ ችግር የተለያዩ በባህሪ ለውጥ የሚገለጹ ምልክቶች ለምሣሌ ከንፈር መምጠጥ፣ መሣቅ፣ መሮጥ፣ ራቁት መሆን፣ መቆጣትና ሥሜታዊነት ከላይ ከተጠቀሱት ምልክቶች በኋላ የሚከሰቱት በአብዛኛው መርሣት፣ ከባድ እንቅልፍ እና ራስ ምታት የመሣሠሉት ናቸው።
ስታተስ ኢፒለፕቲክስ፤ ይኼኛው በተደጋጋሚ የሚከሰት የሚጥል በሽታ /የኢፒለፕሲ ምልክት ነው። ብዙ ጊዜ የሚከሰተው መድሃኒት በድንገት በማቋረጥ ወይም በመመረዝ ምክንያት ነው። ይህ ችግር ሲከሰት ፈጥኖ ሐኪም ቤት ካልተወሰደና ተገቢውን አስቸኳይ የመድሃኒትና ሌላ የሕከምና ዕርዳታ ካልተደረገለት ሞትን ሊያስከትል ይችላል።
ፌብራይል (ከትኩሳት ጋር የተያያዘ)፤ ይኼኛው ዓይነት ሕመም የሚከሰተው ሕፃናት ላይ ነው። ይህንን ሕመም የሚያስከትሉ የትኩሣት በሽታዎች ናቸው። ይህም ማለት እንደ ጉንፋን፣ የጆሮ ኢንፌክሽንና ሌሎች ከባድ ትኩሣት ለያስከትሉ የሚችሉ ሕመሞች ናቸው። በዚህ ወቅት በቀዝቀዛ ፎጣ ትኩሣትን ማብረድ እና ሕፃኑን ለምርመራ መውሠድና ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኝ ማድረግ የግድ ነው።
ሕመምተኛው ማድረግ ያለበት ጥንቃቄ፤ የአካልና የአዕምሮ ጤንነትን መጠበቅ፣ በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገሮችን አለመጠቀም፣ ጭንቀትን ማራቅ፣ መጠነኛ የሆነ ስፖርትን አዘውትሮ መሥራት፣ በሽታውን ከሚያባብሱ ነገሮችን ማራቅ ማለትም ብርሀን የበዛበት ነገር እንደ ቴሌቪዥን የመሣሠሉት ነገሮች ላይ ረዥም ቆይታ አለማድረግ ናቸው።
በግራንድማል ሲዠር (ሰዎች ራሳቸውን ሠተው በወደቁ ሰዓት የሚደረጉ ጥንቃቄዎች) ሕመምተኛውን ከውሃ አካባቢ፣ ከእሣት አካባቢ እና ከመኪና መንገድ ማራቅ ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮችን ከሕመምተኛው አካባቢ ማራቅ ልብሶቹን ማላላት፣ መነጽር ማውለቅ ከጭንቅላት ሥር ለስላሣ ነገር ማድረግ ሕመምተኛውን በአንድ ጎን ማስተኛት ሕመምተኛው እስኪነቃ ድረስ ከሕመምተኛው ጋር መቆየት አስፈላጊ ነው። በግራንድማል ሲዠር (ራሳቸውን በሣቱበት ሰዓት የማይደረጉ ነገሮች) በአፍ ውስጥ ምንም ዓይነት ነገር አለመክተት፣ ክብሪት ጭሮ አለማሽተት፣ የሚጠጣ ነገር አለማጠጣት፣ ማንቀጥቀጡን ለማስቆም አለመሞከር፣ ለሚጥል ሕመም (ኢፒለፕሲ) የሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶች የሚጥል በሽታ ሕክምና ከጥቂት ዓመታት እስከ ዕድሜ ልክ ክትትል ሊያስፈልገው የሚችል የሕመም ዓይነት ነው። የቅርብ ክትትልና ቁጥጥርም ያስፈልገዋል። አንድ ጊዜ ሕክምና ከተጀመረ ሐኪሙ መድሃኒቱን መውሰድ አቁም እስከሚል ድረስ ታማሚው መድሃኒቱን በታዘዘለት መጠን እና ሰዓት መውሰድ አለበት።
መድሃኒቱን በድንገት ማቋረጥ ሀይለኛ የሚጥል በሽታ እንዲያገረሽ ያደርጋል። በሽታው መጣሉን ቢተውም እንኳን መድሃኒቱን ማቋረጥ አይገባም። ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች መድሃኒቱን ሕፃናት በማይደርሱበት ቦታ ማስቀመጥ ሩቅ መንገድ ከሄዱ መድሃኒቱን ይዞ መሄድ መድሃኒቱን ሙሉ በሙሉ ከመጨረሱ በፊት ሌላ ተጨማሪ ማሣዘዝ ናቸው።
ህብረተሰቡም የሚጥል ሕመም የማይተላለፍባቸው መንገዶች በአግባቡ በማወቅ ሕመሙ ያለባቸውን ሰዎች አደጋ እንዳይደርስባቸው መርዳት ይገባዋል። በሽታው የማይተላለፍባቸው መንገዶች በንክኪ፣ በምራቅ፣ በሕመሙ ምክንያት የወደቀውን ሰው በመርዳት አይተላለፍም። የሚጥል በሽታ እርግማን አይደለም። ሕክምናም አለው። በሕክምና ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል መቆጣጠር ይቻላል። የሚጥል በሽታ መድሃኒት በየቀኑ ሣይቋረጥ ረዘም ላለ ጊዜ መወሠድ አለበት። ለሁሉም ሕመሞች ቅደመ ጥንቃቄ የማይተካ አማራጭ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 08 /2013