አስመረት ብስራት
ወላጆች የተለያዩ የሥነ ልቦና ፀሀፍት ስለልጆች አስተዳደግ ከፃፉት ላይ ለዛሬ ልጆችን ገደብ ማስያዝ ምን ያህል በልጆች አስተዳደግ ላይ ያለውን ጠቀሜታ ያስመለክተናል መልካም ንባብ።
ገደብ እና ሥነ ሥርዓት ባንድም በሌላ ተያያዥነት አላቸው። ይህም ማለት በእለት እለት የህይወት ሥርዓት ያለው ልጅን ገደብ የማስያዝ ጥያቄ ውስን ነው ። ምክንያቱም በፕሮግራም ስለሚንቀሳቀሱ ነው።
ሌላው ደግሞ ከልጆቻችን ጋር ጤናማ ግንኙነት ካለን ገደብ ማስያዝ ቀላል ነው። ሥነ ሥርዓት ለምሳሌ ሰውን ማክበር የተረዳ ልጅ ሰውን አክብር አታክብር ጥያቄ ውስጥ አይገባም ።
በመጀመሪያ ግን ልንጠይቀው የሚገባው እኔ እራሴ እንደ ወላጅ ለእራሴ እና ለድርጊቴ ገደብ አለኝ ወይ? ልጆችን በቃ አሁን ቁጭ በሉ ከማለቴ በፊት እኔ እራሴ ከመንቀዥቀዥ ህይወት አርፌለሁ ወይ? በሁኔታዎች በባህሪ ከሰዎች ጋር ባለኝ ማህበራዊ ህይወት ስለ ገደብ ጤናማ ግንዛቤ አለኝ ወይ? ገደብ ወይም ህገ ደንብ ገብቶኛል ወይ? ማለት ይኖርብናል።
ገደብን በትራፊክ መብራት እንኳን ብንመስለው የትእግስቴ ልክ የትድረስ ነው? የት ድረስ ነው እንደፈለኩ የምሆነው? በአስተሳሰቤም በድርጊቴም ሆነ ለስሜቴ ገደብ አለኝ ወይ? ማስጠንቀቂያስ ለራሴ አለኝ ወይ? ከዛ ደሞ ወደ ቀይ መብራት ስደርስ ምንድን የማደርገው? ወደ ራሳችን ከቆየን በኋላ ወደ ልጆቻችን እናያለን ያኔ በመሪው የሚመራ ልጅ ይኖረናል ማለት ነው።
በቅድሚያ በተለምዶ እና በጎጂ ባህል የመጡትን የገደብ ማስያዝ ተጽእኖ ማስወገድ ይህም ሲባል አስደንጋጭ ቁጣ፣ ዱላ፣ መቆንጠጥና ማንበርከክ ወዘተ ጉዳታቸው የከፋ ነው!
እንዴት ገደብ እናስይዝ ግልጽ ቆራጥ እና አጭር መርህ ፦ በምንከለክለው ጉዳይ ላይ ግንዛቤ የተሞላበት እና ቆራጥ አቋም ማለትም ከዚህ ሰአት እስከዚህ ሰአት ብቻ ነው ጌም የምትጫወተው! አዎ ወይም አይ !
ጥንቃቄ የተሞላበት ፦ የምንጠነቀቀው የልጆቹን ስሜት እና ስነልቦና ጫና እንዳያመጣ ነው። በማሸማቀቅ እና በማሳቀቅ ሌላ ስብራት እንዳንጥል መገንዘብ ወሳኝ ነው። ገደቡ ሳይሆን የምናስቀምጥበት ዘዴ ፍቅር እና እክብሮት የተሞላበት ቢሆን ፤ ገደብ ስናስቀምጥ ወይም ስንከለክል ሌላ የሚያደርጉት ውስን አማራጭ ማዘጋጀት ለምሳሌ የትምህርት ቤት ስራቸውን እንዲሰሩ ሊሆን ይችላል።
ማስረዳት ወይም ማብራራት ፦ ይህንን ነገር አይሆንም ያልንበትን ነገር በነጥብ በነጥብ ማስረዳት። ትክክል እና ትክክል ያልሆነን ጥሩ እና መጥፎን ነገር እንዲለዩ ማድረግ። ለምሳሌ አንድ እናት የደረሰች ሴት
ልጇን የፍቅር ዘፈኖች መስማት ማዘውተሯን አስተውላ ልጅቷን እንድትቆጠብ ወይም እንድትገደብ ትነግራታለች ልጅቷም ጨዋነት በተሞላበት መልኩ ገደቡን ተቃውማ እና እንዲብራራላት ትሞግታታለች። እናትየው በሰፊ እውቀት እና ፍቅር ታብራራላታለች /ትመክራታለች ።
የፍቅር ዘፈን በራሱ ችግር የለውም ነገር ግን አዘውትረሽ እና በጣም ተስበሽ በሰማሽ ቁጥር እድሜሽን የማይመጥን የስሜት ቀስቃሽ ነገር ውስጥ ትገቢያለሽ፡፡ ጥልቅ ስሜት ውስጥ ደግሞ ስንሆን ነገሮችን የማሰብ እና የማገናዘብ አቅማችን ይቀንሳል በሚል ጭብጥ ምክር የገደቡን አላማ ታስረዳለች፡፡ ልጅቷም ገደቡን እንድታስብበት እና በራስዋ እንድትወስን ይጠቅማታል ማለት ነው።
ልጆች ሲተገብሩ ወይም ሲታዘዙ ማመስገን ማበረታት ስለሰማህ/ሽ ስለታዘዝከኝ/ሽኝ እመሰግናለሁ ። ዘርዘር ያለ ማበረታቻ መስጠት ለምሳሌ አየህ/ አየሽ ጌሙን በማቆምህ ወክ አደረክ ፥ አጠናህ ፥ ተጫወትክ ወዘተ …
ገደብ ስናስቀምጥቅ ግን ከጉዳዩ ይልቅ ከልጆቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ትልቅ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርብን መዘንጋት የለበትም።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013