አስመረት ብስራት
ልጆች እንዴት ናችሁ። ሰላም ነው? የሀገራችን አባቶች በርካታ ተረቶችን ለልጆች በመንገር እንደሚያስተምሩ ታውቃላችሁ አይደል? አዎ ለዛሬም በአፋር አካባቢ የሚገኙ አባቶች ከፃፏቸው ተረቶች በጋሽ መሃመድ አህመድ የተተረከውን ተረት ተረት እንዲህ አቅርቤላችኋለሁ።
በአንድ ወቅት በአንድ ስፍራ የሚኖር ቤተሰብ ነበር:: በቤተሰቡ ውስጥ አንድ አባወራና ባለቤቱ ከሴት ልጃቸው ጋር ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን ሶስቱም መስማት የተሳናቸው ነበሩ:: ከእለታት አንድ ቀን አመሻሽ ላይ አባወራው አህያውን ወደ ወንዝ ወስዶ ውሃ ሊያጠጣው ፈልጎ አህያውን እየነዳ ወደ ወንዝ ወረደ::
ወንዙ አጠገብ እንደደረሰም ሌሎች ብዙ እረኞች ከብቶቻቸውን ውሃ ያጠጡ ነበር:: እነርሱም “ሰማህ አንተ ሰው? ከብቶቻችንን ውሃ ልናጠጣ ነው:: ያንተ ግን አህያ ስለሆነ የእኛ ከብቶች
ቀድመው ይጠጡ::” አሉት::
መስማት የተሳነውም ሰው “ይቅርታ አህያዬ የሚሸጥ አይደለም::” አላቸው::
እነርሱም “ሰውየው ምን ነካው?” ብለው አሰቡ:: እንዲህም አሉት “ያንተ አህያ ቢሸጥ ባይሸጥ ግድ የለንም:: ከከብቶቻችን ቀድሞ እንዳይጠጣ ነው የምንፈልገው::”
ሰውየውም ቀና ብሎ አይቷቸው “የምናገረውን አትሰሙም እንዴ? አህያዬ አይሸጥም አልኳችሁ እኮ::” አላቸው::
እረኞቹም “ሰውየው እብድ ነው?” ብለው አስበው ዝም አሉት::
አህያውም ውሃውን ጠጥቶ ወደ ቤታቸው ተመለሱ::
ሰውየው ወደቤት እንደደረሰም ወደ ኩሽና ሄዶ
ሚስቱን እንዲህ አላት “ይገርምሻል! ዛሬ ነጋዴዎችን መንገድ ላይ አግኝቼ ‘አህያህን ካልሸጥክልን’ ብለው ሲያስቸግሩኝ የሚሸጥ እንዳልሆነ ነገርኳቸው::” ሚስቱም ቀና ብላ አይታው እሷም እንዲህ አለችው “እንግዲያውማ ልትፈታኝ ከወሰንክ አንድም ቀን ካንተ ጋር ማደር ስለማልፈልግ ወደ ቤተሰቦቼ እሄዳለሁ::” አለች።
ትታውም ልትሄድ እቃዎቿን እየሰበሰበች እያለች ልጃቸው ወደ ቤት ስትገባ ሚስትየው ቀና ብላ አይታት “ይገርምሻል! ከእነዚያ ብዙ የትዳር ዓመታት በኋላ አባትሽ ሂጂልኝ አለኝ እኮ” አለቻት::
ልጅቷም የሃፍረት ፈገግታ አሳይታ ቀና ብላ እንግዲህ “እናንተ ወላጆቼ ናችሁ:: ልትድሩኝ ከፈለጋችሁ በሃሳባችሁ እስማማለሁ::” አለቻቸው ይባላል::
የዚህ ተረት መልዕክትም ሰው የሚሰማው መስማት የሚፈልገውን ነገር ብቻ እንደሆነ ያሳየናል:: ልጆች የሚመለከታችሁንና የተነገራችሁን ነገር በትኩረት በማዳመጥ ትክክለኛ ስራ እንድትሰሩ እመክራችኋለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013