አስመረት ብሰራት
ሰው የልጅነቱ ልጅ ነው የሚለውን አባባል በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ እያለሁ ነበር ያደመጥኩት። እድሜዬ ወጣትነትን እየተሻገረ እንኳን የልጅነት ማንነቴ በህይወቴ ሲገለጽ ይህ አባባል እውነት ነው እያልኩ አስባለሁ።
ሰው የልጅነቱ ልጅ መሆኑን ያስመሰከረች፣ በጠንካራ የስራ ባህል ታንፃ ያደገች እና ጠንካራ የስራ አመራር ለመሆን የበቃችውን ሴት ልናስቃኛችሁ ወደናል።
እሷን ያሳደገው ቤተሰብ፤ ቤተሰባዊ ትስስር ለማያቆም የስራ እድገት መሆኑን ያሰበ የቤተሰብ መልክ ያለው ይመስላል።
የዋሪት ሙሉ ጥላ ድርጅት ባለቤቶች የሆኑት ቤተሰቦቿ ልጆቻቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ስራን ባህል እንዲያደርጉ ከስራም ባሻገር የሚያገኙትን ገንዘብ በሙሉ በአግባቡ እንዲጠቀሙ የማስተማር ስራ ሲሰሩ መቆየታቸው ይነገራል። ፍፁም ስራና ውጤት ብቻ የሚያስበው ይህ ቤተሰብ ከአብራኩ የተገኙ አራት ልጆቹን በፍላጎቱ ቃኝቶ አሳድጓል።
ከእነዚህ አራት ልጆች መካከል መጀመሪያ የተገኘችው ልጅ ከልጅነቷ ጀምሮ ቀስ በቀስ ነበር የስራ ባህልን ያዳበረችው። ይህን የስራ ባህል በትምህርት ያሳደገችው ይህች ወጣት ቤተሰቦቿ በላባቸው ያፈሩትን ድርጅት አንዴ አድጓል፣ ጥሩ ስም አለው ሳትል እሷ ማስተዳደር ከጀመረች ጀምሮ ተጨማሪ ከፍታዎች ላይ እንዲደርስ ያደረገች ጠንካራ ሴት ናት። ይህችን የጥንካሬ ተምሳሌት ለዛሬ የሴቶች ገጽ እንግዳችን አድርገናታል።
ወይዘሮ ትህትና ሙሉ ሸዋ ለገሰ ትባላለች የዋሪት ሙሉ ጥላ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናት። ወይዘሮዋ በድርጅቱ ውስጥ ከ 20 ዓመታት በላይ መስራቷን ትናገራለች። ሃላፊነት ደረጃ ላይ ከገባችም ከስምንት ዓመታት በላይ ሆኗታል።
ድርጅቱ የተሰማራበት የስራ ዘርፍ በቤት ቁሳቁስ ማምረት ስራና አስመጪነት ላይ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሀገር ውስጥ የሚመረቱ የቤት ውስጥ ቁሳቁስን ማምረትና ማቅረብ ላይ ተጠምዷል። ሌላው ደግሞ በጋራ ፍራሽ የማምረት ስራ ላይ የተሰማራ ደርጅት ነው። ድርጅቱ የኔ ነው በሚል መዘናጋት ሳይሆን በጥንካሬ ወደ ከፍታ ለማድረስ የምትጣጣረው ወይዘሮ ስለስራዋና ስለህይወቷ እንዲህ አጫውታናለች። መልካም ንባብ።
ወይዘሮ ትህትና አዲስ አበባ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መርካቶ መስጊድ አካባቢ ከዛሬ አርባ ሶስት ዓመታት በፊት ነበር ተወለደችው። አራት ዓመት እስኪሆናት በዛ ከቆየች በኋላ በአዲስ አበባ ቦሌ አስራ ዘጠኝ ቀበሌ አካባቢ መኖሪያ ቦታቸውን በመቀየር የልጅነት ጊዜዋን አሳለፈች።
የቅድመ መደበኛ ትምህርት ፒተር ፓን የሚባል ትምህርት ቤት ከዛ ደግሞ ቀሪውን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በናዝሬት ትምህርት ቤት ከተማረች በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በሳይኮሎጂ የትምህርት ዘርፍ ተቀብላለች።
የመጀመሪያ ዲግሪዋን ካገኘች ከተወሰኑ ወራት በኋላ በእንግሊዝ ሀገር ለንደን በሚገኝ ሂር ኦን አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ በሚባል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሁለተኛ ዲግሪዋን ያዘች። ከትምህርት መጠናቀቅ በኋላ በለንደን ካንድን ካውንስል በሚባል የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ በመስራት በአስተዳደር ዘርፍ የስራ ልምድ አግኝታ ወደ ሀገሯ ተመለሰች።
ሀገር ቤት ከተመለሰች በኋላ ድርጅቱ የቤተሰቤ ነው በማለት ሃላፊነት ቦታ ላይ ሳይሆን የተመደበችው በድርጅቱ አስፈላጊ ቦታዎች ላይ በመስራት በትክክለኛው የስራ አካሄድ ልምድን እያካበተች ወደ ላይ መውጣት ችላለች።
በልጅነቷ በቤተሰቦቿ ነዳጅ ማደያ ውስጥ ነዳጅ እየቀዳች፤ የመኪና እጥበት አገልግሎት እየሰጠች፤ ከዛ በኋላ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ንግድ ውስጥ ቤተሰቦቿ ሲገቡ የሽያጭ ሰራተኛ በመሆን ሰርታለች። ይህ በስራ ላይ እያገኘች ያደገችውን ልምድ በትምህርት ከሳደገች በኋላ ነው እንግዲህ በትምህርትና በበቂ የስራ ልምድ የተቃኘ አስተዳደራዊ ህይወት ውስጥ የገባችው።
ሰዎች በድህነት ሲያድጉ ስራ ላይ ይጠነክራሉ ነገር ግን በጥሩ መደላደል ያደገ ልጅ ጥረቱ አነስተኛ ስለሆነ አይጠነክርም ሲባል መስማት ለትህትና ትርጉም የማይሰጥ መሆኑን ትናገራለች። ከታች ታግሎ ስለመነሳት ስታወሯ በቤተሰቧ ድርጅት ውስጥ ለመቀጠር እንደማንኛውም ሰራተኛ ተፈትና አልፋ የመጀመሪያ ደሞዟ 120 ብር ሆኖ ስራ የጀመረችበትን አጋጣሚ ታስታውሰዋለች።
በደሞዟ ግን እንደፈለገች ለማድረግ የማትችልበትን ሁኔታ የምትናገረው ትህትና ደሞዛቸውን በመቶኛ ተሰልቶ በሰሩት ልክ ለእናታቸው ስለሚከፍሉ ገንዘብ አለአግባብ ማባከን የማይቻል መሆኑን እሷና ወንድሞቿ ተምረው ማደጋቸው ለገንዘብ አያያዝ ጥሩ መሰረት እንደሆነላት ነው የምታስረዳው።
ሃላፊነትን ጥቂት በጥቂት ስትለማመድ ያደገችው ይች ልጅ የስራ ቦታ ላይ የእናት አባቴ ድርጅት ነው ብሎ ማርፈድ ደሞዝ እንደማንኛውም ሰራተኛ የሚያስቆርጥ፤ ከቀረችም የስነ ምግባር እርምጃ የሚያስወስድባት መሆኑን ስለምትረዳ እንደ ማንኛውም ሰራተኛ ሰዓቷን በአግባቡ መጠቀምን ተለማምዳ አድጋለች።
የቤተሰብ ቤት ነው ስለተባለ ብቻ ቁጭ የማለት እድል ሳይሆን ለፍቶ ጥሮ፣ ግሮ ገንዘብ ማፍራት ድርጅቱን ማሳደግ የግድ በሚል መመሪያ ስር ማደጓ ጠንከራና መልካም መሪ እንድትሆን እንዳደረጋት ትናገራለች።
የድርጅቱ ስያሜ በአባቷ ወላጅ እናት ማለትም በአያቷ ስም የተሰየመ ቢሆንም ጥረህ ግረህ ብላ በሚል መመሪያ የሚተዳደር መሆኑን የምትናገረው ትህትና የመጣር ብሎም ወደ ስኬት የመድረስን እሳቤ ከውስጧ አስቀምጣ ወደ ልጆቿ ለማድረስና ድርጀቱንም ከፍ ለማድረግ ትታትራለች።
ከስራዋም በተጨማሪ ኤውብ ኢትዮጵያ የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ግን ጠንክራ በእውቀት የመምራት አቅም ያላቸውን ሴቶች ያሰባሰበ ድርጅት ውስጥ የቦርድ አባል ሆና የምታገለገል መሆኗን ትናገራለች። ወደ እዚህ ህብረት ለመቀላቀል ያነሳሳትን አጋጣሚ ትህትና እንዲህ ትናገራለች።
ሃላፊነት በተሰጠኝ ወቅት ከሌሎች ሰዎች ጋር ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ምን መደረግ አለበት የሚል ሃሳብ ለመካፈል ጉጉት ላይ ነበርኩ የምትለው ትህትና እነዚህ ሁሉ ጠንካራ ሴቶች የተሰባሰቡበትን ሃሳብ ስቀላቀል ሌሎች ሴቶችን ለሃላፊነት ለማብቃት በመሆኑ ከልፋቱ በርከታ ነገሮችን የተማርኩበት ነው ስትል አጫውታናለች።
ሴቶች በሃላፊነት ቦታ ላይ ሲሆኑ የሚገጥማቸው ተግዳሮቶች ቢኖሩም በፍቅርና ቤተሰባዊነት ስሜት የበታች ሰራተኞችን ማየት፣ በተቻለ መጠን ከሁሉም ጋር መቀራረብ ከአለቃና ምንዝር አስተሳሰብ ይልቅ በፍቅር መምከር፣ የሚሰራ ሰው ሲሳሳት ለማስተማር፣ እንዳይሳሳት ቀድሞ መርዳት፣ የተስተካከለ የስራ አካሄድን በማሳየትና በትክክለኛ መስመር ማስኬድ ላይ ውጤታማ ናቸው። ቅጣትም ካስፈለገ በተገቢው መጠን መወሰድ አለበት ባይ ናት። ሰራተኞችን እንደልጆቿ በማየት በፍቅር በመግባባት እና በማስተማር ስራ ሳይበደል የምታስኬድ መሆኑን ትናገራለች።
ይህ በስራም በትምህርትም የተቃኘ ማንነት የራሱን ቤተሰብ ለመመስረትም አልከበደውም። ትህትና ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናት። ይህች ሴት ከእናት ከአባቷ እየተማረች ያደገችበትን መንገድ ልጆቿ ላይ መተገበር ጀምራለች። ትህትና ልጅ በልጅነቱ ብዙ ነገሮችን በአግባቡ አውቆ ካደገ ለነገ ህይወቱ ጠቃሚ መሰረት ጣለ ማለት መሆኑን ታምናለች። ሁሌም የመፍትሄ ሰው እንዲሆኑ ቤት ውስጥ ምግብ መስራትን ሌሎች ነገሮችን እንዲሞክሩ በማድረግ የሚያጋጥማቸው ጉዳት ለነገ እንዳይደገሙ ለማድረግ የሚያግዛቸው መሆኑን ነው የምትናገረው።
ሁለት ወንድሞችና እንድ እህት እንዳላት የምትናገረው ትህትና ቤት ውስጥ በነበረው አስተዳደግ የሚፈልጉትን ነገር ሲጠይቁ በተለያየ ምክንያት እጃቸው ላይ ከደረሰው ገንዘብ ለሚፈልጉት ነገር 25 በመቶውን ልጆቹ፣ 75 በመቶውን ወላጆቻችው እንዲሸፍኑ የሚደረግበት የአስተዳደግ ሂደት መሆኑን ተናግራ የሷም ልጆች ማግኘት ለሚፈልጉት ነገር ቅድሚያ ምን እንደሰሩ ይጠየቃሉ። ቤት ማጽዳትና እንደ አልጋ ማንጠፍ የመሳሰሉትን ነገሮች በመስራት ማበረታቻቸውን ያገኛሉ ማለት ነው።
ሌላው ደግሞ ልጆቿ በነፃነት በፈለጉት ልክ ከሷም ከአባታቸውም ጋር የመነጋገር እድል አላቸው። ተቆጪ ከመሆን ይልቅ አስተማሪ መሆንን አልያም ምክርን ቀዳሚ የአስተዳደግ መመሪያ አድርጋለች።
ድርጅቱ እንዲያድግ ተከታታይነት ያለው ጠንካራ የአስተዳደር መሰረት እንዲኖረው ተሰርቶበታል። እሷና ወንድሞቿ በተለያየ ዘርፍ የስራ ልምምድን አድርገው ማደጋቸው እነሱ በደረሱበት ወቅት ሃላፊነትን ለመሸከም እንዳይከብዳቸው መሆኑን ነው የምትናገረው።
ስለዚህም የቤተሰቡ ሁለተኛ ትውልዶች የስራ ባህልን አዳብረው እንዲያድጉ አሷም ወንድሞቿም ትክክለኛ የአስተዳደግ መስመር እያስያዙ ያሉበት ሁኔታ አለ። ቤተሰቡ በጋራ ስለስራ ሲያወራ ሰርቶ ማግኘትን እንዲያውቁ ማዳመጣቸው ይፈለጋል። ሌላው ደግሞ የተለያዩ የስራ ልምምዶች እንዲኖራቸውም የስራ ዩኒፎርም ለብሰው ፍላየሮችን እንዲሰጡ ለደንበኞች አቅጣጫ እንዲጠቁሙ ያደርጋሉ። “ለዚያም ነው እንግዲህ የስራን ባህል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያሸጋገር ጠንካራ መሰረት ላይ ነው ያደኩት” ትላለች ትህትና።
ትህትና እንደምትለው እርሷ ወደ አስተዳደር እርከኑ ከመጣች በኋላ ስራዎች እንዲያድጉ የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጓን ትናገራለች። ይህም ሲባል ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ቦታ የሚሰጥ ሃሳብ ማለትም እቃ ታሽጎ የሚመጣባቸውን ካርቶኖችን በድጋሚ ለመጠቀም በነፃ የማቅረብ ስራን የማገዝ፣ ከዛ ደግሞ የቤት ውስጥ ቁሳቁሰ ማምረቻ ስራ የተጀመረውም እሷ ወደ ሃላፊነት ቦታ ከመጣች ወዲህ መሆኑን በተለይም የዶላር እጥረት ችግርን ዋሪት ተቋቁሞ በራሱ ምርት እንዲሰራ ለማድረግ ተችሏል ብላለች።
ሰው ሲባል ሁሌም ተግዳሮቶችን አይወድም። ከስኬት ለመድረስ ዋናው መሳሪያ ተግዳሮት ነው። ሰው ይሄንን መጥላት ሳይሆን እንዴት ልጠቀምበት የሚለውን በማሰብ ታግሎ በማሸነፍ ውስጥ የሚጠቅም ጥንካሬ የሚሰጥ ነው” ትላለች። ተግዳሮቶች ስኬትን ለመጎናፀፍ ጥሩ ማነቃቂያና የስራ ጉልበት ነው” ትላለች።
አሁን ላለችበት ቦታ መጨረሻም ባይሆን ወደፊት ለምደርስበት ደረጃ መንገዱን በማሳየት የስኬት መሰረት የሆኗት ቤተሰቦቿ አትችይም ሳይሆን ትችያለሽ ብለው ብርታት ስለሆኗት፤ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጓደኞቿም በመዝናናት ውስጥ ያለምንም መደናቀፍ ስለስኬት ብቻ በማሰብ አንድም ጊዜ ሳይቋረጥ ለቀጠለው ወዳጅነታቸው ታመሰግናለች። ከስኬት ለመድረስ ከውድቀት መማር፣ በውድቀት ሂደት ማደግ መቻልን መርኋ አድርጋ እየኖረች ትገኛለች።
በማንኛውም ዘርፍ ተሰማርተው በጥንካሬ ወደፊት የሚገሰግሱ፣ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለተከታዮቻቸውም የሃላፊነትን መስመር ለሚጠርጉ ጥሩ ተምሳሌት ለመሆን ችላለች፤ ትህትና።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013