አዲሱ ገረመው
ሂፓፕን የራሱ አድር በልዩነት ብቅ ያለበት የሙዚቃ ዘርፍ ነው። የሂፖፕ ሙዚቃ (ራፕ ሙዚቃ) በመባልም የሚታወቀው በ 1970ዎቹ ውስጥ በኒውዮርክ ሲቲ ብሮንክስ ተብላ በምትጠራው አካባቢ በአፍሪካ አሜሪካውያን እና ላቲን አሜሪካኖች የተጀመረ ተወዳጅ የሙዚቃ ዓይነት ስለመሆኑ መረጃዎች ያስረዳሉ። ሙዚቃው ከስልተ ምቱ በተጨማሪም ባህልን በተሻለ ሁኔታ ለመግለጽ ይበረታታል ይላሉ የዘርፉ አቀንቃኞች።
በዛሬው የዝነኞች የዕረፍት ውሎ አምዳችን በዘር ትልቅ እውቅናና ዝናና ያተረፈው ተወዳጁ ሚካኤል ታዬን አነጋግረን በስራውና በእረፍት ጊዜ ውሎው ላይ አጠር ያለ ቅኝት አድርገናል መልካም ንባብ። እርሱ ልዩ ክህሎቱ አጎልቶ ያሳየበት ሂፖፕ በዓለም ላይ በርካታ አድማጮች ያሉት ስልት ነው።
ሂፖፕ በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሙዚቃ ስልቱ ተቀባይነት እየሰፋ መጥቶ በአሁኑ ወቅት በተለይም ደግሞ በወጣቶች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ መሆን ችሏል። በአገራችን የሂፕ ሆፕ ሙዚቃ ጉዞ ጀርባ ስሙ አብሮ የሚነሳ አርቲስት ሚካኤል ታዬ (ልጅ ሚካኤል) መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል።
በ1995 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በሚሰናዱ ፕሮግራሞች ላይ መድረክ በመምራትና የሂፓፕ ስልት ሙዚቃዎችን በመዝፈን የጀመረው ልጅ ሚካኤል በ2008 ዓ.ም ለህዝብ ያቀረበው የሙዚቃ አልበም ታላቅ ተቀባይነትንና ተወዳጅነትን አትርፎለታል።
አልበሙ ከወጣ በኋላም በአገራችንና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት በሚገኙ ከተሞች በመዘዋወር ሥራዎቹን በማቅረብ፤ የአገሩን የሂፓፕ ስልት ያስተዋወቀ ሲሆን፤ ከተለያዩ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ታላላቅ አርቲስቶች ጋር የሠራቸው ነጠላ ዜማዎች ደግሞ አርስቱ የዝናውን ማማ እንዲቆናጠጥ አድርገውታል።
በአገራችን የሂፓፕ ሙዚቃ ስልት እምብዛም በነበረበት ወቅት ከልጅ እስከ አዋቂ እንዲያዳምጠው ሆኖ የተሰራው “ዛሬ ይሁን ነገ” የተሰኘ የሂፓፕ አልበሙን ይዞ የመጣው ሙዚቀኛ ልጅ ሚካኤል በሂፓፕ የሙዚቃ ስልት ያበረከተው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ ነው። ከአልበሙ በኋላ በተለያዩ የዓለም አገራት በመዘዋወር በርካታ ኮንሰርቶችን የሠራ ሲሆን፤ በዚህም አገሩንና የአገሩን የሂፓፕ ሙዚቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የራሱን አሻራ ያስቀመጠ አርቲስት ነው።
በመድረክ ስሙ ልጅ ሚካኤል ወይም ፋፍ በመባል የሚታወቀው አርቲስት ሚካኤል ታዬ በሂፓፕ ሙዚቃ ትዕይንት ውስጥ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያለ ኢትዮጵያዊ አርቲስት ነው። የኢትዮጵያን የሂፓፕ ሙዚቃ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ካስቀመጡት አርቲስቶች አንዱ ነው።
ልጅ ሚካኤል የሙዚቃ ፍቅር ያደረበት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይዘጋጁ በነበሩ የሙዚቃ ትርዒቶች ላይ ሲሳተፍ በነበረበት ወቅት ነው። ከዚያ በኋላ ሙዚቃን ከፍ ባለ ደረጃ ለመጀመር ጉጉት ያደረበት ሲሆን፤ ታዳሚን በሚያነቃቃ ችሎታው በማዝናናት የኢትዮጵያን እና የሂፓፕ ሙዚቃን ቅመም ልዩ በሆነ ኢትዮጵያዊ ዘዬ ማስተዋወቅ ችሏል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፋፍ በኢትዮጵያ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ላይ አስደናቂ ተጽዕኖ አሳድሯል። እኤአ በ 2016 የመጀመሪያውን 15 ዘፈኖችን ያካተተ “ዛሬ ይሁን ነገ” የሚል አልበሙ ግጥሞች የጻፈውም እርሱ እንደነበር ይናገራል።
የእርሱ ዓላማ የኢትዮጵያን ሂፓፕ ሙዚቃ ለዓለም ማስተዋወቅ ስለነበር በከፍተኛ ተነሳሽነት የሰራቸው ምርጥ ምርጥ ስራዎቹ ተፅዕኖ ፈጣሪ አድርገውታል።
የመጀመሪያ አልበሙን ከሰራ ከአምስት ዓመታት በኋላ 15 ሙዚቃዎችን ያካተተ ሁለተኛ አልበሙን ይዞ የመጣው አርቲስቱ “አትገባም አሉኝ” ሲል በሰየመው አልበሙ አርቲስቱና እዩኤል ብርሃኑ በግጥምና ዜማ ሲሳተፉ፤ ዮናስ ነጋሽ በሙዚቃ
ቅንብሩ ተሳትፏል። ሙዚቃውም የፊታችን ማክሰኞ ለህዝብ እንደሚቀርብ አርቲስቱ በሰጠው መረጃ አሳውቋል።
አርቲስቱ በእረፍት ጊዜው
አርቲስቱ ብዙ ጊዜ ለጤንነቱ በጎ አስተዋጽኦ የሚያደርግለትን ስፖርት ያዘወትራል። ከዚህ በሻገር ከጓደኞቹ ጋር ልዩ የእረፍ ጊዜያትን ያሳልፋል።
መጽሐፍ ማንበብ የአርቲስቱ ልዩ የመዝናኛ ምርጫዎች ቀዳሚው ነው፤ በእረፍት ጊዜው የሚደጋግመው ተግባሩም አብዛኛውን ሙዚቃዎቹን ግጥሞች እንዲጽፍም ምክንያት የሆነው የካበተ የንባብ ልምዱ መሆኑን ይናገራል። በእረፍት ጊዜው ግጥም መጽሐፍም ያዘወትራል።
ያልተፋለሰና ትክክለኛ ታሪክን ጠንቅቀው ከሚያውቁ ሰዎች ጋር በማሳለፍ ጊዜውን ይጠቀማል። ይህም በታሪክ አረዳድ ላይ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ይገልጻል። ከስራ ውጪ ባገኘው አጋጣሚ አካባቢው ላይ ካሉት ታላላቅ ሰዎች ጋር በማሳለፍ ያልገባውን በመጠየቅ ጊዜውን እንደሚያሳልፍ አርቲስቱ ይናገራል።
ከሙዚቀኞች የባህሩ ቃኜ አድናቂ ነኝ የሚለው ልጅ ሚካኤል፤ “ዘፋኙ ለኔ ታሪክ ነው፤ ለዚህ ነው ባህሩ ቃኜን የሚመስል በቀለ አረጋ የሚባለውን ዘፋኝ የምወደው” በማለት የእሱን ስሜት የሚቀርብለት የሙዚቃ ባለሙያ ይገልፃል። ዘፋኙን የመውደዱ ምስጢር ደግሞ ዘፈኑን ስለሚጫወት ነው።
አርቲስቱ ማህበራዊ ኃላፊነትነም በመወጣት የሚጠበቅበት እየተወጣም ይገኛል። በተለይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማገዝም የጎላ ተሳትፎ በማድረግም ላይ ይገኛል።
የዝነኛው መልዕክት ለወጣቱ
“ወጣቱ ሠላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን በልቡ ከያዘ ሁሉንም ሳንካዎች እናሻንፋለን። በዚህ ረገድ ብዙ አርቲስቶች የሚጠበቅባቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። ወደፊትም ይህ እሳቤ ተግባራዊ እንዲሆን እመኛለሁ” ሲል ለወጣቱ ምክሩን አስተላልፏል።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013