ዋቅሹም ፍቃዱ
ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር ሆኖ አንድነቷን ጠብቃ እንዳትቀጥል የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቿ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። በተለይ በሃይማኖትና በብሔር አገሪቷን ለማተራመስና ብሎም ለማፍረስ ብዙ ርቀት ሄደው ነበር ። ከ80 ወይም ከዚያ ዓመት በፊት ሙስሊሙና ክርስቲያኑ እንዲዋጉ ተደርጓል።
ነገር ግን ጦርነቱ ጠላቶች በገመቱት ልክ ሳይሆን ሁለቱም ወገኖች ጉዳዩ ስህተት መሆኑን ተረድተው ከታረቁ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ አብሮ በሰላምና በፍቅር ዘልቀው ኢትዮጵያን ማስቀጠል ችለዋል። ጦርነቱ በዓይነቱ ልዩ እንዲሆንና ኢትዮጵያ እንዲያበቃላት በተለይ የውጭ ሃይሎች ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ ቢሆንም ህዝባችን አስተዋይ በመሆኑ ባሰቡት ልክ የተበታተነች ኢትዮጵያን ማየት አልቻሉም።
አሁን ደግሞ ስልታቸውን ቀይረው ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ህዝቡ በብሔር እንዲባላ በየክልሉ የጠነሰሱት የግድያ፣ የሁከትና የብጥብጥ እንዲሁም የመፈናቀል ሴራ በህዝባችን አስተዋይነት ሊመክን ችሏል። ባለፉት 27 ዓመታት፣ ይቅር በክርስቲያንና በሙስሊም መካከል፣ በክርስቲያንና በክርሲቲያን መካከል እንዲሁም በሙስሊምና በሙስሊም መካከል የተዘራው ጥላቻና ያለመተማመን አደገኛ ነበር።
ግን አገሪቱ ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብሮችና ታሪካዊ ትስስሮች ስላላት የታሰበው ሊሆን አልቻለም። በእርግጥ፣ የተጠነሰሰው ሴራ የኢትዮጵያን እድገትና ማህበራዊ መስተጋብሮችን አልጎዳም ማለት አይቻልም። ከላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች አስመልክተን ከሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ጋር ያደረግውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ለማቅረብ ሞክረናልና ተከታተሉት።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ህዝቦች ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው እንደመሆናቸው መጠን በሰላምና በፍቅር አብረው የመኖር ታሪካቸውን እንዴት ያዩታል?
ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል፡- ኢትዮጵያ የ88 ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ናት ሲባል እንዲሁ ዝም ተብሎ የሚገለጽ ጉዳይ አይደለም። እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች የግብዣ ጥሪ ደርሶአቸው እዚህ መጥተው የቀሩ ሳይሆን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነታቸውን ለማስቀጠል ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው አንዱ ሌላውን ለማትረፍ ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው።
በውጭና በውስጥ ኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን በጋራ በመመከት ዛሬ የደረሱ ናቸው። አድዋና ከዚያ በፊት በኢትዮጵያ ላይ የታወጁ ጦርነቶች፣ ሁሉም አንድነታቸውን ጠብቀው ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ኢትዮጵያን ለዛሬ ትውልድ አስረክበዋል። ህዝቡ አንድ እንዳይሆን የተሰራ ሥራ ቀላል ባይሆንም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በማንነቱ ምክንያት ወደኋላ የቀረ በታሪክ የለም።
ለህዝቡ አንድነትና ለአንድነቱ ጠንካራ መሰረት የሆኑ ባህላዊ ድንጋጌዎች አሉን ። ያጠፋውን አደብ የሚያስገዙ፣ የተበደለውን የሚክሱ ናቸው ። የተጣሉትን ለማስታረቅ የተለያዩ ባህላዊ ክንዋኔዎች ይደረጉ ነበር።
ከእነዚህም አብረው የመብላት፣ ዳግም መሰል ችግር እንዳይከሰት በጋብቻ መዛመድና ደም ማድረቂያ ካሳ ይከፈል ነበር። የብሔር ብሔረሰቦች ብዛት 88 በላይ ይሁን እንጂ አንዱ ከሌላ የማይለይበት ሁኔታዎች አሉ።
በተለያዩ ጊዜያት ከመሀል ወደ ዳር አካባቢዎች፣ ከዳር አካባቢዎች ወደ መሀል ሲደረጉ በነበሩ እንቅስቃሴዎች ያልተጋባና ያልተዋለደ የለም። ስለዚህ በደም የተሳሰሩ ህዝቦች ለመለያየት ሲደረግ የነበሩ ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተዋል። በነገራችን ላይ፣ በምስራቅ፣ በደቡብና በመካከለኛ አፍሪካ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ የብሔር ብሔረሰቦች ያሉት አገራት የሉም።
እነዚህ ብሔሮች ኢትዮጵያ ምቹ ባትሆንላቸው ኖሮ ወደ ሌላ አገር ይሰደዱ ነበር። ነገር ግን አብረው የመኖር ስርዓት ስለተበጀላቸው፣ ተቻችለው አብረው ለመዝለቅ ችለዋል።
አዲስ ዘመን፡- ታሪካዊ ትስስራችን የጠለቀ እንዲሁም አብረው የመኖር ሥርዓታችን ዘመን ያስቆጠረ ከሆነ ዛሬ ላይ በየቦታው የሚናየው መገዳደል፣ መጨካከንና መፈናቀል እንዴት ሊከሰት ቻለ ?
ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል፡- ጥያቄው እንዴት ተከሰተ ሳይሆን ምን ያህል እንደሆነና እንማንን አሳተፈ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ የ 110 ሚሊዮን የህዝብ ቁጥር ባለቤት ናት። በተመሳሳይ መልኩ በቆዳ ስፋቷም ትታወቃለች።
ነገር ግን መፈናቀልና መገዳደል ውስጥ የሚሳተፉ አካላት በቁጥር እጅግ ዝቅተኛ ናቸው። 110 ሚሊዮኑ ህዝብ የጥፋቱ ተሳታፊ ቢሆኑ በታሪክ እጅግ ዘግናኝ ክስተቶች ይፈጠራሉ፣ ኢትዮጵያም አገር ሆና አትቀጥልም ነበር።
እነዚህ መገዳደሎችና መፈናቀሎች የሚከሰቱት በሁሉም አካባቢዎች ሳይሆን በጣም ውስን አካባቢዎች ላይ ነው። ባለኝ መረጃ የጥፋት ጠንሳሾችም ሆኑ ተሳታፊዎች ቁጥራቸው ሚሊዮን እንኳ አይሞላም፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ናቸው። ይህ ማለት የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት አይጎዳም ሳይሆን በሚወራ ልክ ለአገር መፍረስ አስተዋጽኦ አያደርግም ማለቴ ነው።
ለምሳሌ ጸብ አጫሪዎች ኦሮሞና አማራ፣ አማራና ትግሬ ፣ ሶማሌና አሮሞ፣ ቤኒሻንጉልና አማራ የለየለት ግድያ ውስጥ እንደ ገቡ አድርገው ይነግሩናል። ሆኖም ግን በኦሮሚያ ውስጥ በሰላም የሚኖር አማራ፣ በአማራ ውስጥ በሰላም የሚኖር ኦሮሞ፣ በመላው አገር በሰላም
የሚኖር ሶማሌና ሌሎች እናያለን። ታዲያ እንደተባለው ሁሉም ዘርና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገው ጥቃት ቢፈጽም ይቅር ለመኖር ለማውራትም እድሉ ይጠብ ነበር።
መጋጨት የትም አለ፣ ለወደፊትም ይኖራል። ምንም እንኳ የተለያዩ ባህልና ቋንቋ ቢኖረንም አንድነታችን ጠንካራ መሰረት ላይ ስለተገነባ ወደ መጠነ ሰፊ ቀውስ የሚወስደን ግጭት እስካሁን አልተከሰተም ለወደ ፊትም አይከሰትም።
አዲስ ዘመን፡- በተለይ ከለውጡ ማግስት እንኳ ያየናቸው ሁከትና ብጥብጥ፣ የጠፋ የሰው ህይወት፣ የሰማናቸው መፈናቀሎች በብዙዎች ዘንድ ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካም ወደሚተርፍ ቀወስ ውስጥ ትገባለች ተብሎ ሲነገር ነበር። ህዝባችንም ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ነበር። ያጋጠመን ክስተት ለእርስዎ ምን ትርጉም ነበረው?
ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል፡– ለእኔ ክስተቱ፣ መጠነኛ ክስተትና በፊትም ሲያጋጥመን የነበረው ክስተት ነው። ሆኖም ግን ጉዳዩን ለየት የሚያደርገው የቴክኖሎጂ ዘመን ክስተት መሆኑ ነው። በፊት በሰሜን የተከሰተውን ድርጊት በደቡብ የመስማቱ ዕድል በጣም ዝቅተኛ ነበር። በምስራቅ የተከሰተውን በምዕራብ የመሰማቱ ዕድሉ እንዲሁ። አሁን ላይ ግን በኢትዮጵያ ጫፍ የተከሰተው ነገር ወዲያውኑ ሌላኛው የኢትዮጵያ ጫፍ ይደርሳል።
ባህላችን ጠንካራ፣ በእምነታችንም ትጉ ህዝቦች ስለሆን በቴክኖሎጂ በኩል የሚደርሰን መረጃ አንዳንዴ ያልተለመዱ በመሆናቸው እጅግ ያስደነግጡናል። እውነታው ግን የመረጃ እጥረት ስለ ነበረው ነው፣ ቀደም ባለውም ጊዜ በግጦሽ፣ በውሃ፣ በድንበርና በመሳሰሉ ጉዳዮች መጋጨትና መገዳደሎች ነበሩ።
ለምሳሌ አንድ ፀጥ ያለው አካባቢ ውስጥ ኮሽታ ድንጋጤን እንደሚፈጥር ሁሉ በቴክኖሎጂ እጥረት ምክንያት ያልሰማናቸው ሁሉ ዛሬ ላይ ስንሰማቸው እኛን መፈታተናቸው የማይቀር ነው።
በተለይ በጥቂት ቡድኖች የሚመረቱና የሚሰራጩ መረጃዎች በመጀመሪያ ላይ ድንጋጤና ረብሻ ቢፈጥሩም ከድንጋጤ በኋላ ህዝቡ የማጣራት እርምጃ መውሰዱ አይቀርም። ዛሬ ላይ የደረስነውም በዚህ መልኩ ነው። ህዝቡ በጥቂቶች የሚቀነባበረውን ሴራ በደንብ ተረድቷል። ህዝቡ በተደጋጋሚ ፣አቃጥሉት፣ ግደሉትና ዝረፉት የሚለው የአመጽ ጥሪ ተባባሪ ቢሆን ኖሮ የሚያጋጥመን ፈተና ከባድ ነበር።
በአጠቃላይ እነዚህ ጥቂት የጥፋት ሃይሎች አንዳንዴ መጠነኛ ክስተትን አግዝፈው በማቅረብ በህዝቡ መካከል ሽብር እንዲፈጠር ያደርጋሉ፤ አሊያም ያልተደረገው እንደተደረገ አድርገው በውሸት መረጃ አገር ለማተራመስ ጥረት ያደርጋሉ። መረጃ አቀናባሪም አቅራቢም ስለሆኑ ኢትዮጵያ አደጋ ላይ መሆኗን የሚጠርጥሩ አካላት አይጠፉም።
ሰፊው ህዝባችን ግን የቴክኖሎጂ ዘገባ በመላመድ አሁን ላይ የተለያየ የአመጽ ጥሪ ቀርቦለት ምላሽ ያልሰጠበት ሁኔታዎች ነው ያሉት። ለምሳሌ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ሊፈጸም የታቀደው ውድመት እጅግ ከፍተኛ ነበር። ጉዳዩን በጠፋው የሰው ህይወትና የወደመው ንብረት ብቻ ያበቃል ብሎ ያሰበው ሰው አልነበረም። ህዝቡ ህመሙን ችሎ ተጨማሪ ጥፋትና ውድመት እንዳይፈጠር ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ የሚዲያዎቻችን አዘጋገብ ችግር ያለበት ነው። ለምሳሌ ያህል በክርስቲያኑ በዓላት ጊዜ ከዝግጅቱ ጀምሮ የሚያስተባብሩ በርካታ ሙስሊሞች አሉ። በሙስሊሙ በዓላት ጊዜም የሚተባበሩ በርካታ ክርስቲያኖች አሉ። እንደ አጋጣሚ ሆነ በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል የሆነች ትንሽ ጠብ ቢፈጠር፣ ሚዲያዎቻችን የሚዘግቡት ሙስሊሙና ክርስቲያኑ በመተባበር ከሰሩት በርካታ በጎ ስራዎች ይልቅ የተፈጠረውን ችግር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከባህላችንና ከሃይማኖታችን ያፈነገጡ ጸያፍ ድርጊቶች ከመቋቋም ረገድ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ላይ ያሉ ክፍተቶች እንዴት ቢታረሙ ጥሩ ይሆናል?
ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል፡- የአገራችን ሃይማኖታዊ አስተምሮዎች ጠንካራ ባይሆን ኖሮ የዛሬ ኢትዮጵያን አናገኝም ነበር። ለእኔ ጸያፍ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ሃይማኖት አላቸው ብዬ አላምንም። የትኛውም ሃይማኖት ግደሉት፣ ስቀሉት፣ አፈናቅሉት አይልም። ይልቁንስ የገዛ ወንድሙና እህቱን የሚገድልና የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው። ህዝባች ይህንን በደንብ ስለ ተረዳ ነው ዛሬ ከሞት ተርፈን ለመኖር የበቃ ነው።
የብሔር ብሔረሰቦቻቸው ቁጥር ብዙ ያልሆኑ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የተገዳደሉ እንደ ሩዋንዳ ያሉ አንዳንድ አገራትን ማንሳት ይቻላል። የቅርብ እንኳ ብናነሳ በማይካድራና በመተከል ላይ የተፈጸመው ጅምላ ግድያ ህዝቡ ሃይማኖተኛ ህዝብ ባይሆን ኖሮ ለሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚተርፍ ሴራ ነበር። ከመተከል ተነስቶ አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌና ሌሎች አካባቢዎች የማይደርስበት ምክንያት የለም። ድርጊቱ በመሰረቱም አስነዋሪ በመሆኑ ወደ ሌላ እንዳይዛመት ህዝቡ አንቆ በመያዙ እዚያው እንዲያበቃ ተደርጓል።
በእውነቱ ህዝባችን ሰላሙን ለማረጋጋት የሚያደርገው ጥረት የሚመሰገን ተግባር ነው። አንድ መታወቅ ያለበት ነገር በጊዜ ሂደት አገርም ሆነ ህዝብ እየደከመ እየበረታ፣ እየወደቀ እየተነሳ ኑሮውን ይገፋል። ኢትዮጵያ ዘመን ያስቆጠረች አገር ናት፣ ብዙ ፈተናዎችንም አስተናግዳለች። ብዙውን ጊዜ ሽማግሌዎች ከበሽታ ሲተርፉ በደህና ጊዜ የበሉት ምግብና በደህና ጊዜ የሰሩት ስፖርት እንደረዳቸው ይወራል።
ኢትዮጵያም በደህና ጊዜ በሃይማኖትና በባህላዊ ረገድ በጣለችው ጠንካራ መሰረት ከተነሳባት ከብዙ ማዕበል መትረፍ ችላለች። ሆኖም ግን ጥቂት ግለሰቦች በሃይማኖት ተነስተው ኢትዮጵያን አልጎዱም ማለት አይደለም። ጥቂት ሰዎች በክርስቲያን ስም ጥፋት ቢሰሩ፣ የክርስትና አስተምህሮት ችግር ስላለ ሁሉም ክርስቲያኖች ችግር እየፈጠሩ ነው ማለት መሰረታዊ ስህተት ነው፤ በሙስሊሙም አኳያም እንዲሁ።
ለምሳሌ በውጭ አገራት ወንጀል ሰርተው የተያዙ ጥቂት ኢትዮጵያውያን አሉ። ይህ ማለት 110 ሚሊዮኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ወንጀለኛ ነው ማለት አይደለም። በተመሳሳይ መልኩ፣ ጥቂቶች ከሃይማኖት ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ በስመ ሃይማኖት ጥፋት ስለ ሰሩ መላው ምእመናንን ጥፋተኛ ማድረግ አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- ጥቂት የሚባሉት ጥፋተኞች በጊዜው ካልታረሙ ለመላው አገሪቱ የሚተርፍ አደጋን ሊደቅኑ ይችላሉ። የጥቂቶቹ ጥፋት ወደ ብዙሃኑ እንዳይዛመት ምን መደረግ አለበት?
ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል፡– እሱማ አያጠያይቅም። ትልቅ ቁስል የሌላ ሰውነታችን ክፍል ሰላም እንደሚያነሳ ሁሉ ጥቂቶቹ የኢትዮጵያን ሰላም ማናጋት ይችላሉ። ለምሳሌ እባብ እግር ከነደፈ፣ መርዙ ወደ ሌላ ሰውነት እንዳይተላለፍ፣ በመጀመሪያ ደረጃ የተነደፈውን ቦታ በማሰር በስለት ቆራርጠው መርዙ እንዲወጣ ይደረጋል። ከዚያ እንዲድን መታከም ዓይነተኛ መፍትሔ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ያደረገውም ይህንኑ ነው። እባቦች ኢትዮጵያን ሲነድፏት፣ መርዙ ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳይዛመት ግጥም አድርገው አሰሩት። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የተጎዳውን አካባቢ መርዙን የማውጣት ስራ ጀመሩ። ይሄን በሚያደርግበት መከራና ዋጋ መክፈል አጋጥሞታል።
ከመከራው የሚያርፈው ቁስሉ ሲድን ብቻ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል። እባቡንም ቀጥቅጦ ገድሎታል፣ ግልገሎቹንም አጥፍቶታል፣ እባቡን ያፈራው አካባቢውንም አጸድቶታል። ይህን ደግሞ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ድርጊት ነው።
ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብም እንደ ወትሮው ለጥቂት የጥፋት ሃይሎች ዕድል ሳይሰጥ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለሰላሙና ለልማቱ ከተጋ የጥፋት ሃይሎቹ የሚደርቁበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- ተካፍሎ የመብላት ባህላችን፣ በአድዋ ላይ ያሳየናቸው አድነታችን፣ ፍቅራችን በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ አሴቶቻችን እየተመናመኑ መሆናቸው በበርካቶች ዘንድ ይነገራል። ዛሬ ላይ የሚስተዋሉት ራስ ወዳድነት፣ መጨካከንና ጥላቻ፣ የባለፉት 27 ዓመቱ የዞረ እዳ ይሆን?
ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል፡– ለእኔ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን አልተሸረሸሩም። ሆኖም ግን ሁለት ነገሮችን፣ ቅጽበታዊና ነባራዊ መነሻዎችን ማንሳት ይቻላል። ነባራዊ መነሻው፣ በአገረ መንግስትና በብሔረ መንግስት ግንባታ ላይ በጅምር የቀሩ ያልተሰሩ ስራዎች አሉ። ከአጼ ምኒልክ በፊት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ብዙ መንግስታት ነበሩ።
ያም ሆኖ ግን አገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ላይ ክፍተቶች ነበሩ። የኢትዮጵያ ብሔሮች ማንነታቸውን በሚገባ ተገንዝበው አገራቸውን የሚያሳድጉበት ሁኔታ ላይ በርካታ ስራዎች አልተሰሩም።
ለቅጽበታዊ ክስተቶች ደግሞ ያለፉት 27 ዓመት ማንሳት ይቻላል። በእርግጥ ባለፉት 27 ዓመታት በህዝቡ መካከል የተዘራው መርዝ ቀላል አይደለም፣ ህዝቡ ግን በተፈለገው ልክ ቀውስ ውስጥ ሳይገባ ሁሉን ችሎ በትዕግስት አሳልፏል። አንድነታችን ተሸርሽሯል የሚሉ ወገኖች የአድዋ ላይ የታየው አንድነት በህዳሴ ግድብ ላይ መደገሙን ካለማየት የተነሳ ጥያቄ ይመስለኛል።
በችግር ጊዜ ሌላው ወገን እንዳይሞትና እንዳይፈናቀል የደበቁት ደግ ሰዎች በዘመናችን እያየን ፍቅር የለም ብሎ መደምደም ያስቸግራል። በኢትዮጵያ ታሪክ መጠነኛ ግጭቶች ነበሩ፣ ነገር ግን ህዝቦችን የከፋፈለ፣ አገር ለውድቀት የዳረገ ጥፋት ተከስቶ አያውቅም፣ ለወደፊትም አይከሰትም።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ህዝቦች በበለጠ የቆየውን አንድነታቸውን ጠብቀው፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶቻችን አከብረው አብረው ለመኖር ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?
ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል፡- ከሁሉም በላይ ለወሬኞችና ለጽንፈኞች ጭንቅላታቸውን ከማከራየት መጠንቀቅ ይጠበቅባቸዋል። አሁን ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ስራዬ ብለው ጥላቻን የሚሰብኩ፣ ህዝቦች መካከል ጥርጣሬና ያለመተማመን እንዲኖር ወገባቸውን ታጥቀው የሚሰሩ በርካቶች ናቸው። እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ሃሳባቸውን የሚጋራ ሰው ካጡ በራሳቸዉ ጊዜ መለፍለፉን ይተዋሉ።
በአገራችን የኢተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር ከ10 ሚሊዮን የማይበልጥ ቢሆንም እውነተኛው መረጃ አጣርቶ ጭንቅላቱን ለማይረቡ ጉዳዮች ለማከራየት ሊገደድ ይችላል። ችግሩ የሀሰት መረጃ መጠቀም ብቻ ሳይሆን የማባዛት ችግርም ይስተዋላል። ነገር ግን አብዛኛው ህዝብ መረጃን የማጣራት ችሎታው ጥሩ በመሆኑ ብዙ የአመጽ ጥሪዎች አምክኗል። ሁሉም የዓላማ ሰው መሆን ይጠበቅበታል።
ለምሳሌ አውሮፕላን የሚያበር ሰው በምድር ላይ ለሚሰሙና ጫጫታዎችንና በሰማይ ላይ ላሉ ድምጾች ቦታ ሳይሰጥ ለበረራው ስኬታማነት ጠቃሚ ለሆኑ ሰዎች ብቻ ጆሮ በመስጠት ጉዞውን ይቀጥላል።
እኛ ሁላችንም ኢትዮጵያ የምትለውን አውሮፕላን ስለተሳፈርነው ለአንድነታችን፣ ለልማታችንና ለአብሮነታችን የሚያግዘን መልካሙን ነገር በመያዝ ኢትዮጵያን ዳር ለማድረስ ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን አስተያየት ከልብ አመሰግናለሁ
ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013