
በሁሉም የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት የትንሣዔ ወይም የፋሲካ በዓል አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ የትንሣዔ በዓል የክርስትና እምነት መሠረት የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከመቃብር የተነሳበት ዕለት የሚታሰብበት ሲሆን ይህ ክብረ በዓል ከረጅም ቀናት ፆም፣ ስግደት እና መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓቶች በኋላ የሚከበር ነው። የፋሲካ በዓል የሁዳዴ ፆም መፍቻ በዓል በመሆኑ በፆም ውስጥ ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከአላስፈላጊ ተግባራት ተቆጥቦ የቆየ ሰውነት ወደ ተለመደው የአመጋገብ ሥርዓት የሚመለስበትና ከወዳጅ ዘመድ ጋር ማዕድ አብሮ በመቋደስ በደስታ የሚዋልበት ቀን ነው፡፡
የትንሣኤ በዓል ክርስቲያኖች በጽኑ ፆም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምሕላ እና በተማፅኖ ከፈጣሪያቸው ጋር ለሁለት ወራት ግድም ሲያደርጉት የቆዩትን ትስስር አጠናቀው የኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሳት በማሰብ በተቻላቸው ሁሉ በደስታና በተድላ የሚያሳልፉበት ነው። በዓሉ ከመንፈሳዊ ክዋኔው ባለፈም በመረዳዳት፣ በመተጋገዝ፣ በመተሳሰብ፣ በመጠያየቅ የሚከበር ነው።
ፋሲካ ማለት ደስታ ማለት ነው። ክርስቲያኖች የጌታቸውን ከሞት የመነሳት ብሥራት የሚያስቡበትና ሁለት ወራት ለሚጠጉ ቀናት በትጋት ሲያከናወኑት የነበረውን የፆም ጊዜ ጨርሰው በዓላቸውን የሚያከብሩበት የደስታ ወቅት ነው፡፡ በዚህ የደስታ በዓል ላይ ወዳጅ ከወዳጁ ይጠያየቃል፤ የተራቡና የታረዙ ወገኖች ይጎበኛሉ፤ ሁሉም ያለውን ያካፍላል፤ ደስታ በሁሉም ቤት ይገባል፡፡ ፋሲካ ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ በዓሉን በጋራ የሚያሳልፍበት የአብሮነት በዓል ነው፡፡
የፋሲካ በዓል መላው የእምነቱ ተከታዮች የተቸገሩትን በመርዳትና የሌላውን ሸክም በመሸከም ክርስቲያናዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት ጊዜ ነው፡፡ ደቀመዛሙርቱ በተጨነቁበት ጊዜ ክርስቶስ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ብሎ እንዳበሰራቸው ሁሉ ዛሬም ብዙ ወገኖቻችን በጭንቅ፤ በችግር ውስጥ በመኖራቸው የተቸገሩበትን ነገር በማገዝ ሰላማቸው እንዲመለስ መሥራት አለብን፡፡ የታመሙትን ልንጠይቅና ልንረዳቸው ይገባናል፡፡
በዕለተ ፋሲካ ከተቸገሩ ሰዎች ጋር በዓሉን ማሳለፍ፤ ያለንን ማቋደስ፤ መተዛዘን እና መረዳዳት በዓሉን ምሉዕ ያደርገዋል፡፡ ያጡና የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት አንዱ የበዓሉ እሴት ነው፡፡ በዓለ ትንሣኤ የእግዚብሔር ፍቅር መገለጫና የተስፋችን ማሳያ በመሆኑ በዓሉን በመተሳሰብ መንፈስ ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለታረዙት፣ ለታመሙትና ለታሰሩትም ሁሉ ካለን ከፍለን በመስጠት አቅመ ደካሞች በመንፈስና በሞራል በዓለ ትንሣኤውን እንዲያሳልፉ ማድረግ ከእያንዳንዱ ክርስቲያን የሚጠበቅ ተግባር ይሆናል፡፡
አጠቃላይ የፋሲካ በዓልን ስናከብር የበዓሉን እሴቶች በመጠበቅ እና በተለይም የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፤ የታረዙትን በማልበስ፤ የተራቡትን በማብላት እና በግጭት የተፈናቀሉትን ወገኖች ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሊሆን ይገባል፡፡
ከዚሁ ባሻገርም የትንሣኤ በዓል ሲከበር የችግሮች ሁሉ መውጫ ቁልፍ ሰላም ብቻ በመሆኑ በትንሣኤው ብርሃን ለሀገርና ለሕዝብ የሰላም መሣሪያ በመሆንና ለሰላም በመጸለይ ሊሆን ይገባል፡፡ ሀገራችን ወደ ተሟላ ሰላሟ እንድትመጣ በዚሁ ዕለት ሁሉም ወደ እግዚአብሔር መጸለይ እና ለሰላም መስፈንም የበኩሉን ድርሻ የሚወጣበት ቀን ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የእምነቱ መርሕ ለሆነው ሰላም ሁሉም ክርስቲያን የድርሻውን መወጣትም ይጠበቅበታል፡፡ ይህንንም አንድም ራሱን ከግጭት ጠማቂዎች ቅስቀሳ በመራቅ በሌላም በኩል ነፍጥ አንስተው ላልተገባ ዓላማ ከንቱ ድካም የሚደክሙትን ይሄ መንገድ አያዋጣም ወደ ሰላም ተመለሱ በማለትም ይሆናል፡፡
ትንሣዔ ከስቃይና ከመከራ ከክቡር መስዋዕትነት በኋላ የተገኘ የአሸናፊነት እና የደስታ ቀን በመሆኑ ጥላቻን፤ መለያየትን፤ መራራቅን እና ክፉ ተግባራትን የምናሸንፍበት እና በምትኩም መተዛዘን፤ መረዳዳት፤ ሰላም እና ፍቅር የምናነግሥበት ሊሆን ይገባል፡፡ በመሆኑ ሁሉም ክርስቲያኖች በሀገራችን የተሟላ ሰላም፤ ፍቅር እና መተሳሰብ እንዲሰፍን ከርስቲያናዊ ግዴታውን የሚወጣበት ዕለት ሊሆን ይገባል፡፡ በዓሉን ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት ከወዳጅ ዘመድ ጋር በፍቅርና በደስታ ማክበሩ እንደተጠበቀ ሆኖ በክርስቶስ ትንሣዔ ሁሉም በፍቅር ልብና በይቅርታ ለሰላምና አብሮነት በመፀለይ በዓሉን ማክበር ይጠበቅበታል! ከሁሉም በላይ ግን በትንሣዔው ለሰዎች መስዋዕት የመሆን ክቡር መርሕ አቅመ ደካመ ወገኖቻችን በዓሉን ተደስተው እንዲሳልፉ ማድረግ በሰማይም በምድርም ክቡር ዋጋ ያለው ትልቅ ተግባር ይሆናል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም