ከትንሣዔው እንማር !

የትንሣኤ በዓል በመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ብዙ ትርጉምም ያለው በዓል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ያን ሁሉ መከራ አሳልፎ የሞትን ችንካር ሰብሮ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተበት፣ ዲያቢሎስን ድል የነሳበት፣ ሕያውነቱን ያስመሰከረበት፣ መቃብር መስበር የሚያስችል ሥራ የተሠራበት ነው። ትንሣዔ የመከራው ግልባጭ የድል አክሊል የተቀናጀበት ነው። በዕለተ ዓርብ የፈሰሰ ደም እና የተቆረሰ ሥጋ እሁድ ዕለት ትንሣዔው ታይቷል።

በዚህም የሰው ልጆች የዕዳ ደብዳቤ በኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕት ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ የሰው ልጅ ከዲያብሎስ አገዛዝ ነፃ የወጣበት ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ኃጢያትን ያጠፋበት፣ የሰው ልጆችም የደም ዋጋ ተከፍሎላቸው ነፃነት ያገኙበት ነው። ከምንም በላይ ፍቅር ጥላቻን አሸንፎ የወጣበት፣ ከበቀል ይልቅ የይቅር ባይነትን ዋጋ ያየንበት ነው። ግን በተግባር ያላዋልነውና ዛሬም ነገም እንደ አዲስ ልንማርበት የሚገባ ነው።

ዘመናችን ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ የምንሰብክበት፣ አንዱ ባንዱ ላይ የሞት አዋጅ የሚያውጅበት እና የጦር ነጋሪት የሚጎስምበት ሆኗልና ከዚህ ለመውጣት መማር ያለበት ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርን፣ ታማኝነትን፣ ቃል ጠባቂነትን፣ ደግነትን፣ ሩህሩህነትን፣ አዛኝነትን፣ ታጋሽነትን፣ ግልጸኝነትን፣ ራስን ዝቅ ማድረግን፣ ቂም አለመያዝን፣ ጠላትን መውደድን አስተምሯል።

የኢየሱስ ክርስቶስ የድኅነት ሰነድ ወንጌል የዓለምን ሕግ ሁሉ ቅርጽ ማስያዝ የሚችል ኃይል ያለው ነው። ጦር ሰብቆ፣ ዘገር ነቅንቆ ቢመጣብህ በፍቅር አብርደው። ፍቅር ኃያል እና ጉልበታም ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለበደለኞች ድኅነት የመሰቀሉ ምክንያት የሰው ልጆች በይቅርታ ማለፍን፣ ከመግደል ይልቅ አንዱ ስለ አንዱ ተላልፎ መሞትን፣ እየሞቱም ቢሆን ማስተማር እንደሚገባ ለማሳየት ነው። ሁሉን ማድረግ እየተቻለው ማስተማርን መርጧልና፤ የሰው ልጅ ማድረግ ስለቻለ ብቻ ጥፋትን ሁሉ ማድረግ እንደሌለበት ሊማር ይገባል።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ልንማር የሚገባው ፍቅርን፣ ትውልድ ማሻገርን፣ ለወገን ማሰብን እና በጎ ማድረግን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ ኃጢያት ሳይኖርበት ለሰው ልጆች ጥፋት እና ኃጢያት ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፤ እኛ የሰው ልጆች ግን የኢየሱስን አርዓያነት በከፊል እንኳን መከተል ተስኖን ከደግነት ይልቅ ክፋትን እንፈጽማለን፤ ከክርስቶስ ብዙ ነገሮችን ነው መማር ያለብን።

የሰውን ልጅ እንደ ድልድይ ሆኖ ማሻገር ሲገባን የሰውን ልጅ እንደ ድልድይ ተጠቅመን ለመሻገር የምናደርገውን ድርጊት ክርስቶስ አይወደውም። ምዕመኑ መተዛዘንን፣ መረዳዳትን፣ አንዱ ለአንዱ መድረስን፣ ለተሰደዱ እና ለተፈናቀሉ በአጠቃላይ በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች የተለመደ ደግነቱን ማድረግ ይኖርበታል።

በዓሉን ስናከብር ለኛ ለሰው ልጆች ሲል ያለ ኃጢያቱ የሞተልንን ክርስቶስን እያሰብን መሆን አለበት። የሱን መልካምነት እና ሞቶ በትንሣዔው የመነሳቱን ምስጢር በልባችን ውስጥ በማኖር እኛም ለአምሳያዎቻችን ፍጹም ደጎች መሆን ይጠበቅብናል። ይቅር ማለትንም ከኢየሱስ ክርስቶስ መማር ይኖርብናል። በበዓሉ ለተጎዱ እና ርዳታችንን ለሚፈልጉ ሰዎች ያለንን በማካፈል ደግነታችንን ማሳየት ይኖርብናል።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የመረዳዳት ባህል አለን፣ የተቸገረን መደገፍ፣ የታመመን የመጎብኘት ልምድ አለን። ለበጎ ሥራ ደግሞ በቀዳሚነት የሚያስፈልገው መልካም ልብ ብቻ ነው። በጎነት ለራስ ሐሴትን የሚሰጥ፤ በፈጣሪ ዘንድም ውድ ዋጋ ያለው ነው። የትንሣዔ በዓልም ይህ አኩሪ ባህላችን ጎልቶ ከሚወጣባቸው አጋጣሚዎች ትልቁ ነው።

በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ይህን በዓል በማስመልከትም ሁሉም ኢትዮጵያዊ አቅም የሌላቸውን በመርዳት፣ ያለው ለሌለው በማካፈል መንፈስ በዓሉን ሊያከብረው ይገባል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች በማሰብና ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል። በተለይም ወጣቶች የአቅመ ደካሞችን

ቤት በማደስ፣ ለተቸገሩ ማዕድ በማጋራትና በመሳሰሉት በጎ ተግባራት በዓሉን ሊያከብሩ ይገባል። በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች በነበረው የሰላም ዕጦት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በችግር ውስጥ እንደመሆናቸው፣ እነዚህን ወገኖችን በዚህ ታላቅ በዓል በመመገብ፣ በማጠጣት እና በማልበስ ከጎናቸው ልንቆም ይገባል።

በክርስቶስ ትንሣዔ ሁሉም ሰው ክፋትን ከልቡ በማስወገድ በክርስትና ሕይወቱ ውስጥ ክርስቶስን መምሰል አለበት። ከተበላሸ ሕይወት በመፅዳት የፈጣሪን አብነት መከተልና የሰላም መሣሪያ መሆን ያስፈልጋል።

በዚህም በዓሉን በመተሳሰብና በፍቅር ማክበር ምዕመኑ የትንሣዔ በዓልን ሲያከበር የተቸገሩና አስታዋሽ ያጡትን በማሰብና በመርዳት መሆን ይኖርበታል።

ከፈጣሪ የተቀበልነውን ወንጌል ከቃል ባለፈ በመተግበር እርስ በርስ ተከባብሮ በፍቅርና በሰላም መኖር ይገባል። መላው የወንጌል አማኞች ምዕመናን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ፆምና ጸሎታቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉበትም መሆን አለበት።

ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለው መከራና ስቃይ ለሁሉም በመሆኑ የትንሣዔ በዓል ደጋፊ የሚያሻቸውን በማሰብና በመርዳት ሊከበር ይገባል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ካስተማረው አንደኛው ለራስ ሳይሆን ለሌሎች መኖርን ነው። በመሆኑም በዓሉ ሲከብር እርስ በርስ መረዳዳትና በመተሳሰብ ማሳለፍ ሁሌም ሊለየን አይገባም።

የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣዔን በዓል ሲከበር ከመጠጥና ከስካር ነገሮች በመራቅ እንጂ ወደ ሞት በመሄድ ሊሆን አይገባም። ትንሣዔ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ሲል ብዙ መከራ ተቀብሎ ይቅርታ እና ፍቅርን ያስተማረበት በዓል በመሆኑ ምዕመናን በዚህ ተምሳሌት መተሳሰብ እና በጎ ተግባርን ማጠናከር ይገባል። ትንሣዔ ለሰው ልጆች ሁሉ ከመከራ የመነሳት የተስፋ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ እኛም አሁን የገጠሙንን የውስጥና የውጭ ችግሮች ተቋቁመን ፈተናዎችን በፅናት ለመሻገር መነሳት ይኖርብናል። እንደ ሀገር የገጠሙንን ፈተናዎች ለማለፍ ምሳሌ ይሆነናልና ።

አሁን ላይ የገጠሙንን ፈተናዎች አልፈን የምንሻገር እንድንሆን ተስፋን የምንሰንቅበት በዓል ነው። በሀገራችን እያየን ያለነው ጥላቻ እና መገፋፋት የክርስቲያኖች መለያ አይደለምና በትንሣዔ በዓል ፍቅርን እና አንድነትን በመስበክ ማክበር ይገባናል።

ብሌን ከ6 ኪሎ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You