(ክፍል አንድ)
ድሀ የሆነው በእርግማን አይደለም። ኋላቀር የሆነው በአፍሪካ አህጉር ስለምንገኝ አይደለም። ድርቅ መላልሶ የሚጎስመን በከባቢ አየር ሙቀት ብቻ አይደለም። ርሀብተኛ የሆነው ከሰሐራ በታች ስለተገኘን አይደለም።
የታረዝነው በአፍሪካ ቀንድ ስለምንገኝ አይደለም። ፈጠራ የራቀን በረዷማ በሆነ አካባቢ ስላልተፈጠርን አይደለም። ፈጣሪ ያልሆነው ደደብ ሆነን አይደለም።
የሰነፍነው ተፈጥሮአችን ሆኖ አይደለም። ቆጣቢ ያልሆነው አባካኝ ስለሆን አይደለም። ጥሪት ያልያዝነው ስላልፈለግን አይደለም። የቆረቆዝነው ጥቁር ስለሆን አይደለም። የጎሰቆልነው ነዳጅ ስለሌለን አይደለም።
ያልበለፀግነው አልማዝ ስላላገኘን አይደለም። ተመጽዋች የሆነው ለም መሬት ስለሌለን አይደለም። ተረጂ የሆነው በመስኖ የሚለሙ ወንዞች ስለሌሉን አይደለም። ተገዥ የሆነው ተሽጠን አይደለም። ተገዥ የሆነው ባርነት ወዶልን አይደለም።
ፈላጭ ቆራጭ የተፈራረቀብን ዕጣ ፈንታችን ሆኖ አይደለም። አምባገነን የፈነጨብን ታዝዞልን አይደለም። አሽከር የሆነው በይሁንታ አይደለም። ጭሰኛ የሆነው የ40 ቀን እድላችን ሆኖ አይደለም። አጥንተ ጎዶሎ የተባልነው ከቁጥር ጎሎ አይደለም።
ፀጥ ለጥ ብለን የተገዛነው ሥዩመ እግዜአብሔር ስለሆኑ አይደለም። ለዙፋኑ ያደርነው ፈቅደን አይደለም። ሶሻሊስት የተባልነው አምነን አይደለም። የአልባንያን መንገድ የያዝነው መርጠን አይደለም።
የማንነት ታርጋ የተሰጠን ጠይቀን አይደለም። ሟርተኛ የሆነው ተፈጥሮአችን ስለሆን አይደለም። ሴራ የሚጠናወተን ምሣችን ሆኖ አይደለም። የምንጠላለፈው አሰናካይ ሆነን ተፈጥረን አይደለም። የምንጠራጠረው አልተማመን ብለን አይደለም።
ምቀኛ የሆነው ወርሰን አይደለም። አይነ ጠባብ የሆነው በተፈጥሮ አይደለም። አንድነት ያጣነው መለያየትን መርጠን አይደለም። ሠላም የራቀን ጥል ቀርቦን ተወዳጅቶን አይደለም። ሙሰኛ የሆነው ተፈጥሮአችን ሆኖ አይደለም።
ኢፍትሐዊነት የነገሰው ቀብተነው አይደለም። እኩል ያልሆነው በአምሣሉ መፈጠራችን ጠፍቶን አይደለም። ዴሞክራሲያዊ ያልሆነው የዘር ሐረጋችን ከግሪክ ስለማይመዘዝ አይደለም። ጥንታዊት ሀገር ይዘን ሀገረ መንግሥታችን ተሠርቶ ያላለቀው በእኛ ሥንፍና አይደለም። ጥላቻ የተንሰራፋው ተፈጥሮአዊ ሆኖ አይደለም።
የምንጋጨው ሱስ ሆኖብን አይደለም። የምናፈናቅለው ሀገር አንሶን አይደለም። የምንጠፋፋው አንዳችን ለሌላው ሥጋት ሆነን አይደለም። ሀብት የምናወድመው የእኛ መሆኑ ጠፍቶን አይደለም፤ ወዘተረፈ… በዚህ አንቀጽ “አይደለም” የተደጋገመው አጽንኦት ለመስጠት ነው።
ላለፉት ሦስት ሺህ ዓመታትም ሆነ ከዚያ በላይ ትውልድ ለድህነታችንና ኋላቀርነታችን ምክንያት ናቸው ብሎ ደጋግሞ የደረደራቸው ሰበቦች አሠልችና ገልጃጃ ከመሆናቸው ባሻገር ውሃ የማያነሱ እና ስህተት መሆናቸውን አጽንኦት ለመስጠት “አይደለም”ን ገልጃጃ አድርጌ እንደ ዘፈን አዝማች ደጋግሜዋለሁ። የመጣንበት መንገድ ተደጋጋሚ እና ኡደታዊ ቢሆንም ከቀለበቱ ሠብሮ መውጣት ያልቻለ አሠልቺ መሆኑንም ለማመላከት ነው ።
እነዚህን ህልቆ መሣፍርት የሌላቸውን “አይደለሞቻችንን” ሰብሰብ አድርገን ስናያቸው፦ የመጀመሪያው የምንገኝበት አህጉር ወይም ሀገር ለድህነታችንም ሆነ ለውድቀታችን ምክንያት አለመሆኑን ለመሞገት በመሠናዘሪያነት ቀርበዋል። በአህጉራችን የምትገኘው ቦትስዋና ለዚህ ጥሩ አብነት ናት።
ኢኮኖሚዋ ከአፍሪካ አልፎ ከበለፀጉ ሀገራት ጋር መነጻፀር ጀምሯል። ዓመታዊ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርቷም ሆነ የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከእነ ማሌዥያ፣ ሲንጋፓርና አውሮፓ ሀገራት ተርታ መጠቀስ ከጀመረ ከራርሟል።
“አይደለሞቻችን” የወከሉት ሁለተኛው ነጥብ፤ የሀገራችን ወይም የአህጉራችን የአየር ንብረት ለኋላቀርነታችንም ሆነ ለድህነታችን ሰበብ አለመሆኑን ያሳያል።
ዓመት እስከ ዓመት ፀሐይ መሆኑና በርሀማ መሆኑ ለእኛ ድህነትና ኋላቀርነት ምክንያት እንዳልሆነ ሁሉ ቀዝቃዛውና በረዷማው እንዲሁም የምዕራብ አውሮፓ፣ የአሜሪካ፣ የካናዳና የአውስትራሊያ የአየር ንብረት ለብልጽግናቸው ምክንያት አይደለም። ምንም እንኳ እነዚህ አህጉራት አብዛኛዎቹ የተለያየ የጊዜ አቆጣጠር /time zone/ ስላላቸው ወቅታቸውና የአየር ንብረቱ የተለያየ ሊሆን እንደሚችል ታሣቢ ቢደረግም።
በረዷማ በሆኑ የምሥራቅ አውሮፓ፣ የሰሜን አሜሪካና ካናዳ እንዲሁም በርሀማ በሆነ የአውስትራሊያ አካባቢዎች የሚኖሩ ቀደምቶች ወይም አብሮጂኒስ /indigenous / የበለፀጉ እንዳልሆኑ ሁሉ፤ የአየር ንብረት የዕድገትም የውድቀትም መነሻና መድረሻ ሊሆን አይችልም።
በመጀመሪያው አንቀጽ እንደ ዘፈን ግጥም አዝማች የደጋገምናቸው “አይደለሞቻችን” ለማሣየት የሞከሩት ሦስተኛ ነጥብ፤ ድሃና ኋላቀር የሆነው አንዳንድ አክራሪና ዘረኛ ነጭ ልሒቃንና ፓለቲከኞች እንደሚሳደቡት የጥቁር በአጠቃላይ ከእነሱ ውጭ የሆነ የሰው ዘር በመላ አስተሳሰብ በተፈጥሮ ዝቅተኛ ማለትም አይኪው IQ /Intelligence quotient/ አነስተኛ ስለሆነ አይደለም።
የሰው ልጅ አይኪው 99 በመቶ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ተቀራራቢ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። ናዚው አዶልፍ ሒትለር ይኼን የአርያም /highest/ ዘርነት የፈጠራ ትርክት ወደፊት ያመጣው የሌለውን ኃጢያት ተሸካሚ /scapegoat/ ስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያንን መስዋዕት በማድረግ ሥልጣን መንበር ላይ ለመቆናጠጥ እንደ እርካብ ተጠቀመበት እንጂ የሰው ልጂ ሁሉ በእሱ አምሳል ነው የተፈጠረው።
ይቺን አደገኛ ጨዋታ መለስ ዜናዊ በተንሸዋረረ እይታ “ከዚህ ወርቅ ሕዝብ በመፈጠሬ እኮራለሁ።” ብሎ የተቀረኖቹን ወደ መናኛ ብረት አውርዶን ስናዝን ባጅተን፤ በቅርቡ ደግሞ ራሳቸውን “የሰው ውሃ ልክ” ሲሉ ሌሎች ደግሞ በተራ “የሰው ግንድ ነን” እያሉ ራሳቸውን በወርቅ ሚዛን ለማስቀመጥ ቢሞክሩም ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው ከኢትዮጵያዊነታችን አላጎደሉንም።
አልጨመሩልንም “አይደለም” እያልሁ እንደ ውዳሴ ማርያም የደጋገምሁበት ሌላው አራተኛ ምክንያት፤ ለዘመናት ላለፍንበትም ሆነ ዛሬም ላለንበት ችጋርና ቸነፈር የተዳረግነው ጥቁሩን ወርቅ ነዳጅ ስላላገኘን አይደለም።
ቬኒዞላ፣ ሊቢያ፣ ናይጀሪያ፣ ሩሲያ፣ ኢራን፣ ኢራቅ ወዘተረፈ…ነዳጅ ስላላቸው አልበለፀጉም። በአጠቃላይ በድህነት አለንጋ የምንገረፈው በተፈጥሮ ሀብት ስላልታደልን አይደለም። እንደ ወርቅ፣ ጨው፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ድንግል መሬት ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞችና ሌሎች ሀብቶች ቢኖሩንም ከድህነትና ኋላቀርነት አልተላቀቅንም።
“አይደለም” በሚል አጽንኦት መስጠት የፈለግሁበት የመጨረሻውና አምስተኛው ምክንያት፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማቆም ያልቻልነው ስለማይገባን አይደለም የሚለውን አጉልቶ ለማሳየት ነው።
የሀሳብ ነጻነት ልዕልናን ያላሰፈነው፤ የሰብዓዊ መብቶችን ያላከበርነው፤ በሀገራችን ለዚህን ያህል ጊዜ ፍትሐዊነትንና እኩልነትን ማረጋገጥ ያልቻልነው፤ ከጭቆና እና ከአፈና ቀንበር ነጻ መውጣት የተሳነን ፈላጭ ቆራጭነትና አምባገነንነት በሰራ አካላታችን ስለተወሀደን አይደለም።
ታዲያ የድህነታችንና የኋላቀርነታችን ምክንያት ምንድን ነው? ጥንታዊ የሀገረ መንግሥት ልምምድ እያለን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ላይ ለምን ወገቤን አልን? የራሳችን ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ የፓለቲካ ሥርዓት፣ ፊደል፣ ዘመን አቆጣጠር፣ እውቀት፣ የአስተዳደር ልምምድ ወዘተረፈ…እያለን ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማደርጀት ለምን ተስኖን ኖረ?
እንደ ቋጥኝ ለሚከብዱ ለእነዚህ ጥያቄዎች ከተረዳንበት እይታ አኳያ የየራሳችንን መልስ፣ ትንታኔና መላምት ልንሰጥ እንችላለን። መልሶቻችን ግን ሁሉንም ጥያቄ በአንድ ጊዜ ስለመመለሳቸው እርግጠኛ መሆን አንችልም።
እንዲሁም መልሳችን የማያዳግም ሊሆን ካለመቻሉ ባሻገር ብዙኃኑን የሚያረካ ሊሆን አይችልም። እስኪ ከፍ ብዬ የአነሳኋቸውን ጥያቄዎች እየመለሳችሁ በዚያውም መልሶቻችሁ ምን ያህል ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደሚችሉና እንደሚያረኩ አስቡት።
በግሌ ሀገራት ለምን ወደቁ? ለምን ደኸዩ ? ለምን አልበለፀጉም? ለምን ዴሞክራሲያዊ አልሆኑም? ለሚሉ የጥያቄ ናዳዎች ለራሴም ሆነ ለሌሎች ቁርጥ ያለና ሁሉንም የሚያግባባ መልስ ለመስጠት ከመቸገሬ ባሻገር ከአክሱማዊ ሥልጣኔ ማማ ወድቀን የተፈጠፈጥንበት ምክንያት ለእኔም ዛሬ ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነብኝ አለ ።
የሚያግባባ የጋራ ታሪክ እንኳ እንዳይኖረን ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በተለይ ላለፉት 30 ዓመታት ቀን ከሌት በመሠራቱ የሀገራችን ታሪክ ከካም ይመዘዝ ከኩሽ ወይም ከኢትዮጲስ ይሁን ከሣባ አልያም ከማክዳ፣ ከቀዳማዊ ምኒልክ ወይም ከሣባውያን፣ ከሐበሻ ይሁን ከአግዓዚ ወዘተ… መቀባበል ባንችልም ሀገራችን በወቅቱ ሥልጣኔ ማማ ላይ ተቆናጣ እንደነበር የቆዩን የሥልጣኔ አሻራዎች ጮኸው ይናገራሉ።
ሆኖም የታሪክ ሠነዶች እንደሚያትቱት ከእስክንድርም ይሁን ከፕቶሎሚ አልያም ከግሪክ መናገድ እንዲሁም ዲፕሎማሲ አሀዱ ያልነው ከዚያ ሩቅ ዘመን አንስቶ ነው። ቀዳሚው የግንብ ቤተ መንግሥትም ባኪንግሀም አልያም ኋይት ወይም ብሉ ሐውስ ሳይሆን አክሱም ነው የተገነባው።
በዩኔስኮ በቅርስነት የተመዘገቡት እስከ 33 ሜትር የሚረዛዝሙ ከአንድ ድንጋይ የተቀረፁ ሐውልቶች፤ በቦና ጊዜ የተገነባው ምን አልባትም የመጀመሪያው የውሃ ማከፋፈያ፤ ዘብን በማቆም ንግድ መናገድ፤ የፅህፈት ሥርዓት የተጀመረው፤ ከሁሉም በላይ በተለይ ንጉስ አፍላስ ከሱዳን የተወሰነው ክፍል፤ ቀይ ባህርን ተሻግሮ ደቡብ ምዕራብን ቆርሶ ከማስተዳደሩ ባሻገር የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥታዊ አገዛዝ መሥራች እንደነበር የታሪክ ድርሣናት ያብራራሉ።
ከእሱ በኋላ የነገሱት ኢላ አሚዳ፣ ኢዛና እና ካሌብ የአክሱምን ሥልጣኔ አስቀጥለዋል። ሦስቱ አብርሀማዊ እምነቶች ክርስትና፣ አይሁድና እሥልምና ወደ ሀገራችን የገቡትም በዚሁ ዘመን በዚሁ በር ነው። የመጀመሪያዎቹ የመሐመድ ተከታዮች በነብያቸው ምሪት ተሠደው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እጁን ዘርግቶ የተቀበላቸው የክርስቲያን ንጉስ የአክሱም ሥርወ መንግሥት ንጉስ ነው።
ከፍ ብዬ ለማንሳት እንደሞከርሁት የእነ ዳረን አኪሞግሉ እና ጄምስ ሮቢንሰንን፤ “WHY NATIONS FAIL” እስካነብ ድረስ ከዚያ የግንባታ፣ የኪነ ሕንጻ፣ የንግድ፣ የአስተዳደር፣ የውጭ ግንኙነት፣ የዲፕሎማሲ፣ ወዘተረፈ.. የሥልጣኔ ከፍታ ወርደን ለምን እንደተንኮታኮትን የጎርዲዮስን ቋጠሮ እንደ ማፍታታት ከብዶኝ ኖሬያለሁ።
በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተከሰተው “ጥቁር ሞት” የተሠኘ ወረርሽኝ የተነሳ እንግሊዝን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ሕዝብ እንደ ቅጠል በመርገፉ ከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረት በመከሰቱ ከእልቂቱ የተረፉ ሠራተኞች አጋጣሚውን በመጠቀም የመብት ጥያቄና የክፍያ ማሻሻያ እንዲደረግላቸው ጫና በማድረግ አሀዱ የተባለው እንቅስቃሴ በሒደት የእንግሊዙን የግሎሪየስ አብዮትን ያዋልዳል።
ድህረ አብዮቱን ተከትሎ ንጉሳዊ ቤተሰቡ፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ የሠራተኞቻቸውን የሥራ ሁኔታ፣ ደመወዝና ዕዳ በመሠረዝ ምርታማነታቸውንና የፈጠራ ተነሳሽነታቸውን ማነቃቃት ችለዋል።
ይህ ለኢንዱስትሪ አብዮት መሠረትና እርሾ የሆኑ ፈጠራዎችን ማበርከት አስችሏል። በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ በእንግሊዝ የተቀጣጠለው የኢንዱስትሪ አብዮት ወደ አውስትራሊያ በመቀጠልም አትላንቲክን ተሻግሮ አሜሪካንና ካናዳን አዳረሰ።
ለዛሬ በዚህ እልባት ላድርግና በቀጣዩና ሁለተኛው ክፍል አብዮቱ ሁሉ አፍራሽና ሥር ነቀል እንዳልሆነ በማሣያነት የሚወሳውን የፈረንሣይ አብዮት አንስቼ በዚያው የጥቅምቱን የቦልሸቪክ የሩሲያውን አብዮት ዳስሼ የዚህ ቅጂ ወደ ሆነው የእኛ አብዮት እመለስና በትህነግ / ኢህአዴግ “አብዮት” በኩል አድርጌ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በሀገራችን ስለተለኮሰው ለውጥ እና የዴሞክራሲ ተቋማት አነሳሳለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሐቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013