አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
ከሰሞኑ እንደሰማነው ወሬ ሱዳን ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሀ ሙሌት እንዳትሞላ ስትል አስጠንቅቃለች። ኡ… ኡ…ቴ ድንቄም አልኩ በልቤ ። ከቶ እሷ ማንናትና ነው ይሄን ለማለት የደፈረችው! ደግሞ በሀሳቤ መለስ አልኩ።
እውነት ነው ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል የሚባለው ለካ፤ እሷም የኢትዮጵያ የውስጥ ሰላም ተናውጧል፤ አንድነት የላቸውም፤ ከውስጥም ከውጪም የሚደግፉኝ አለኝ ብላ በመተማመን እንደሚሆን መገመት ደግ ነው። ግን እኮ ሱዳን የመሰላትን የኢትዮጵያ ችግር ብላ አነበበች እንጂ እውነታውን የተረዳችው አይመስልም።
ወይም ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ዘንግታናለች ።እንኳን ለራሳችን ለእሷም ሰላም ጠንካራ ጀግኖች ልጆች እንዳሉን ማሰብ ተስኗት ይሆን? ነገሩ ግን እንዳሰቡት ሳይሆን የኢትዮጵያውያን አንድነትና ጀግንነት ዘላለማዊ መሆኑን ካለመረዳት የየዋሆች አስተሳሰብ የሚመነጭ መሰለኝ።
የዋህ የነገሩት ሁሉ እውነት ይመስለዋል። የሞከረው ሁሉ የሚሳካለት መሰሎ ይሰማዋል። የገጠመውን ሁሉ የሚያሸንፍም ያህል የልብ ልብ ይሰማዋል። ምክንያቱም በሞሉት በነገሩት ልክ ነውና ነው የሚያስበው።
ግብጽም ብትሆን ዳር ሆኖ ጃስ ማለቱን የተካነችበት ጥበቧ ነው። ለሽብር ገንዘብ ማፍሰስ፣ መሳሪያ መቁጠር ፣የወታደራዊ ትጥቅ ማሳየት፣ ዘመናዊ የውጊያ መሳሪያዎችን የሚያከማቸው ሁሌም አለ ፤ አሁንም ቀጥሏል። ሁልጊዜ ግን ይሄ ብቻነው ለውጤት የሚያበቃው ብሎ ማሰብ የኢትዮጰያንና የጣሊያንን ጦርነት መዘንጋት ነው።
ካልሆነ የዓደዋው ጦርነት ዘመናዊ መሳሪያ በታጠቀ ሀይል፣ ጦርና ጋሻ ይዞ በወጣ ህዝብ መካከል የተደረገ ጦርነትና በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት የተደመደመ ድል መሆኑን ማንሳት ይገባልና። እንዳው ለትውስታ ብዬ አነሳሁት እንጂ ሌሎች ሀገራችን ሳትደርስባቸው ዘራፍ እያሉ ሽንፈታቸውን የተካኑበትን መጥቀስ ይቻላል። ሁሉንም ግን ሱዳኖችም ሆኑ ግብጾች ጠንቅቀው ያውቁታልና ከዘነጉት ታሪክን መለስ ብለው እንዲያነቡ ለእነሱ ልተወው።
ጁንታው ቡድንና ርዝራዡ ከውስጥና ከውጪ ከጀርባ ሆኖ የሀገርን ሰላም ለማደፍረስ አብሮ እያሴረ ከሆነ ለእሱም በአስራ አምስት ቀን ተጀምሮ የተጠናቀቀውን ጦርነት ጠቀስ አድርጎ ማለፉ አስፈላጊ ነው። የሰራዊቱን አቅምና ብቃት የህዝቡን አንድነትና ተባባሪነት በአጭር ጊዜ አይቶቷልና። ከዚህ በኋላ ዳግም መነሳሳት አበው እንዳሉት መንፈራገጥ ለመላላጥ ይሆናል።
ሁሉም ግን ኢትዮጵያን እናምሳለን፤ እናፈርሳለን፤ እንበጠብጣለን በለው ቢያስቡና ቢመኙ ይችላሉ፤ ሙከራ መሞከር ሀሳብን ማሰብ አይከለከልምና ። ነገር ግን ድሉ እውነትንና ሀቅን ለያዘው የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ብቻ መሆኑን አውቀው አደብ ቢገዙ ስል ምክረ ሀሳብና ማስጠንቀቂያዬን ጣል ሳላደርግ አላልፍም።
የሱዳን ሚኒሻም ይባል መደበኛ ወታደር በድንበር ሰበብ ጦር መስበቅ ያማረው፣ በራሱ ተነሳሽነት ወይም በሱዳን ጦር መሪዎች ትእዛዝ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያን ትርምስ በሚሹት ጠላቶቻችንን የግብፅ ገዥ መደቦች ገፋፊነት መሆኑን ለመገመት ጠንቋይ መሆን አይጠይቅም ።
ሴራው የተደራጀ መሆኑን ምንም መረጃ ሳያስፈልገው በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ድርድር ለማስተጓጎል በተራ በተራ የሚያደርጉትን ማደናቀፊያ ማስተዋል ብቻ በቂ ነው። ይህ የከሰረ የፖለቲካ ስሌታቸው ሃብታቸው ያልሆነውን የዓባይን ውሃ ጠቅልለን ለመጠቀም ሲሉ ለዘመናት የሰሩበት ሴራ ነው። በዚህም በዚያም ኢትዮጵያን መወጠር የሚለው እስትራቴጂያቸው በጥበብና በቆራጥነት እንዲሁም በዲፕሎማሲው አደብ እንደሚገዛ ማሰብ ጥሩ ነው።
ግብፅ በሱዳን ፖለቲካ እንዳሻት ገብታ ስታተራምስ ከመኖሯ ባሻገር ፣ የእኛዎቹ የህወሓት ጁንታዎችም በአገራችን ተመሳሳይ እድል እንድታገኝ ሲያመቻቹላት ቆይተዋል ።አሁን ተስፋ በቆረጡበት ወቅትም የቆየ ሽርክናቸውን ለማስቀጠል መመኘታቸው አልቀረም። ይሄ የሚሳካ አይደለም የተበላ እቁብ እንደሚባለው የሀገርኛ አባባል ነው። የተበላ እቁብነቱን በተግባር ማሳየት ይገባል።
እነሱ ትናንት አላረፉም ዛሬም አይተኙም ። ምክንያት ባገኙ ቀዳዳ ጠላት ያለ በመሰላቸው ቁጥር ጭር ሲል አልወድም አይነት ሴራቸውን ከመቆስቆስ አይቦዝኑም። ማስፈራሪያ ፣ ጦርነት ጉሰማ ሌላም ሌላም።
በመሠረቱ ግብፅ በአገራችን ያለውን የማንነትና የሃይማኖት ብዝሃነት ተጠቅመው ለማተራመስ ደጋግመው ሞክረዋል ፡፡አሁንም ገፍተውበታል። ሽብርተኞችን እየደገፉ ሊያዳክሙንም ጥረዋል ።የአሁኑ በሱዳን በኩል የሚታየው የጦርነት ጉሰማ የዚያው አካል ነው።
ግብፃውያን የቀጥታ የጦርነት ቀመር ሊሳካ እንደማይችል ሲያውቁና ተላላኪዎቹ ጁንታ አናቱ መመታቱን ሲረዱ ነው ለተወሰነ ጊዜ በሽግግር መንግሥትነት የተቀመጠን የካርቱም አስተዳዳር ወታደራዊ ክንፍ ተጠቅመው አገራችንን ወደግጭት አዙሪት ለመክተት የከጀሉት ።
ለዚህ መፍትሄው ኢትዮጵያዊን እስከመጨረሻው የሰላም እጃችንን ዘርግተን በመነጋገር ሁሉንም ነገር ለመፍታት መትጋት ነው። የጠላቶቻችን ሴራ ማምከን የሚቻለው እንደ ትናንቱ ዛሬም አንድ መሆን ስንችል ነው።
ለማተራመሻ የሚሰጡ አጀንዳዎችን አሽቀንጥረን በመተው በትናንሽ ትርክቶች እንደማንንበረከክ ማሳየት እንደምንችል በተግባር በማረጋገጥ ነው። ከሁሉም በላይ የአንድነት ክንዳችንን ካጠናከርን የቱንም ሀይል የታሪክ ተረት ከማድረግ የሚያግደን አይኖርም።
ዛሬም ነገም ከነገ ወዲያም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ፣ ለማንበርከክ ለሚሹ የውስጥም የውጪም ኃይል መድሀኒቱ የአንድነትን ክንድ ማበርታት ነው። ችግሮች ሲያጋጥሙ መረዳዳት፤ የሀሳብ ልዩነት ሲያጋጥም መነጋገር ፤ ከምንም በላይ ግን የሀገርን አንድነትና ሰላምን ማስጠበቅ ከሁሉም ይጠበቃል። ያኔ ሁሉም በአንድነት መድኃኒት አደብ ይገዛል። ይገዛል!። ቸር የሰማን! ቸር ያሰራን !።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013