(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ) gechoseni@gmail.com
“የኢትዮጵያውያን መገለጫ ከሆኑት መልካም ባህሎቻችን መካከል አንዱ የመከባበር እሴታችን ነው።” የሚለው የኩራት ትምክህታችን ጓዝ ጉዝጓዙን ሰብስቦ ከነጭራሹ ሊሰናበተን ዳር ዳር ማለት ብቻም ሳይሆን ፊቱን አዙሮብን ከተኳርፍን ዓመታት ነጉደዋል። መከባበር፣ መቀባበል፣ መደማመጥና መደናነቅማ የቃላቱን ድንጋጌዎች ካልሆነ በስተቀር ከተግባራቱ ጋር ከተፋታንም እንዲሁ ሳንሰነባብት የቀረን አይመስለኝም።
ለሃይማኖት አባቶችና ለአረጋውያን ያለን ክብር፣ ለታላላቆች ምክርና ቁጣ ያለመደንገጣችን፣ እውነታችንን በትዕግሥት ለማስረዳትና “ጆሮ ለመስጠት” የነበረን ዝግጁነት እንዲሁ እየጠወለጉብን መወየባቸው የአደባባይ ምሥጢር መሆን ብቻ ሳይሆን በግላጭ ተበትነው ያስተዋልንባቸው አጋጣሚዎችም ብዙዎች ናቸው።
ቋንቋችን ተደበላልቆ ባቢሎናውያንን እንድናስታውስ የተገደድንባቸውን የየግል አጋጣሚዎችና በጋራ የሰማናቸውን ምስክርነቶች ወይንም በሌሎች ላይ የደረሱ ሁነቶችን እየዘረዘርን እንተርክ ብንል፤ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው መልሳችን ሊሆን የሚችለው ለካስ “በዙሪያችን እንደ ደመና የከበቡን ሀገራዊ ፍርስራሾቻችን ተዝቀው የማያልቁ ቁልሎች ከሆኑ ውለው አድረዋልና!” በማለት ትካዜ ውስጥ ልንገባ እንችላለን።
የአብዛኞቹ ፖለቲከኞችና “አክቲቪስት” ተብዬዎች የቋንቋ አጠቃቀም ማሸማቀቅ ብቻም ሳይሆን አሳፍሮ አንገት ያስደፋል። “የሃይማኖት አባቶቻችን” ብለን ነፍስና ሥጋችንን አደራ እስከ መስጠት የደረስነው “አንቱዎቻችንም” የረገጡት መሬት ቅልት ብቻም ሳይሆን ቀልባችንን የሚያቀል ድርጊታቸውን ስናስተውል “ወየው ለመጨረሻችን” ብለን በፍርሃት እንንዘረዘራለን። ቅዱሳት መጻሕፍት “የመጨረሻው ዘመን ያሉት አስደንጋጭ ጊዜ በእርግጡ ከደጃፋችን የመድረሱ ምልክት ይሆንን?” በማለትም እስከ መጠራጠር እንደርሳለን።
እንዲያገለግሉን መንግሥት የሾመብን ብዙዎቹ “ገዢዎቻችንም” ያልሰሩትን ሰራን፣ ያልፈጸሙትን በስኬት አጠናቀቅን ብለው በፀሐይና በጨረቃ ፊት ሲዋሹን፣ ለማሉለት የሕዝብ አደራ ሳይሆን ለሥጋቸው እረፍት ሲተጉ እያስተዋልን “እግዚኦ ማህረነ ክርስቶስ” እያልን በማማተብ ለእነርሱ እኛ አፍረን ከሚዲያዎቻችን ጋር በጥላቻ እንናቆራለን።
ሕዝብ ይታዘበኛል! ሕዝብ ምን ይለኛል! ሕዝብ “አንቅሮ ይተፋኛል!” የሚሉ ሥጋቶች “ምን እንዳይመጣ!” በሚል ድፍረት ተለውጠው “ሕዝብ ምን ያገባዋል!” በሚሉ ትዕቢቶች መለበጣቸውን ነጋ ጠባ እያስተዋልን ነው። ስለዚህም “ደጀ ፈጣሪ” እየተገኘን እንደየእምነታችን ከአምላካችን ጋር ለመገናኘት መንፈሳችን ተስፋ እየቆረጠ ባዛኝ ሆነናል።
ፖለቲከኞቻችንን “እህ!” ብለን እንዳንሰማ እምነት ጎድሎናል። የመገናኛ ብዙኃንን ዜናዎች ልብ ተቀልብ ሆነን እንዳናደምጥ “ተናንቀናል”። “በአክቲቪስቶች” ቀረርቶም እንዳንጽናና “ምክራቸው የስድብ ቁልል” እየሆነ ትከሻችንን አጉብጦናል። በሀገር ሽማግሌዎች ምክር በትህትና ጎንበስ ብለን እንዳንለዝብም “ነገራቸው ሁሉ ቀለለብን እኮ ምን እንሁን!?” እያልን ግራ ተጋብተናል። በግልና በቡድን ወቅታዊ ስሜታችን ህመምተኛ ሆኖ የምናቃስተው እነዚህ ምክንያቶች ለስብራት ስለዳረጉን ነው።
ሕዝብ የናቁ መንግሥታዊ ተቋማት፤
“እንደ ሀገር መቅለል የጀመርነው በሕግ አምላክ የቀለለ ዕለት ነው።” ይህንን ለጥቅስ የሚበቃ ኃይለ ቃል በወርሃዊ የሠፈራችን የእድር ስብሰባ ላይ በሚያስገመግም ድምጻቸው ያስመዘገቡን ጋሽ ደጀኔ ለይኩን ናቸው። “ንግግርዎትን ለጽሑፍ ላብቃው?” ብዬ ፈቃደኝነታቸውን ስጠይቃቸው የሰጡኝ መልስ “ደራሲ ምን ፍቃድ ይጠይቃል? እስከ ዛሬ ስትጽፉ የኖራችሁት የእኛን ፈቃድ እየጠየቃችሁ ነው” የሚል ነበር። እርግጥ ነው አሳፍረውኛል።
ለነገሩ ባይፈቅዱልኝስ እኔው ራሴ ብናገረው ማን ከልካይ አለኝ። “ስሙን እንጂ ግብሩን ለማናውቀው ዕድሜ ለሀገሬ ዴሞክራሲ!” የፈለገንን አውርተን፣ ያሻንን ተርትረን፣ የጠላነውን በአደባባይ አምተን ካስፈለገም “በሬ ወለደ!” ታሪክ ፈጥረን ብናሰራጭ ማን ተቆጭ አለን፤ ማንስ ሃይ ብሎ ያርመናል። “ሁሉ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ!” ተብለን ተመክረን የለ። “ማነው የመከረን?” ካላችሁ ብሂላችን ብዬ መልስ እሰጣለሁ።
የንባብ ቀልባችንን ሰብስበን እህ እንድንባባል በቅድሚያ አንባቢያንን ቃል ላስገባ። መልካም! “እንደ ጋሽ ደጀኔ” ቀጥል ካላችሁኝ ዕድሜ ሳያስገድደን ለነጭ ፀጉር፣ ብስጭቱ ሲያይልብንም ለጨጓራ ህመም ከዳረገን ከኢትዮጵያ አሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የዕለት ተዕለት ድርጊቶች ልጀምር። መቼም የኤሌክትሪክ ኃይል ሳይቆራረጥ ከመስከረም እስከ መስከረም፣ ከእሁድ እስከ ቅዳሜ በብርሃን እንደተጥለቀለቅን እንኑር ብዬ ብከራከር “የድሃ ቅንጡ!” እንደምትሉኝ አይጠፋኝም።
ግዴለም ግድ ከሆነ ሰኞ፣ ማክሰኞና ረብእ መብራት አግኝተን ሐሙስና አርብ ለሌላው ቢዳረስ ችግር የለውም። ፕሮግራም ተበጅቶልን “እነከሌ ሠፈሮች በዚህኛው ቀናት፣ ወዲያኞቹ ደግሞ በእነዚያ ቀናት” ተብሎ ቁርጣችን ቢነገረን ባልከፋ። ምክንያቱም “ድሆች ነና!” ብሂላችን እንዳስተማረን “የድሃ ቅንጡ በጾም ቅቤ አምጡ!” እያልን መሟገቱ እንደማይጠቅም እኮ እናውቃለን።
ችግሩን ፍርጥ አድረገን እንናገር ካልን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሕዝቡን ከናቀና ምን እንዳያመጡ ብሎ ከጨከነ የሰነባበተ ይመስለኛል። በጥገናም ሆነ በእጥረት ምክንያት በፍጹም የመብራት አገልግሎት አይቋረጥብን ማለት እንዳይደለ በሚገባ አስረግጬ ማስመር እፈልጋለሁ።
ችግር ነው የምንለው ለምን ቀድሞ አያሳውቀንም፣ ለምንስ በፕሮግራም አያገለግለንም ወይንም “ይቅርታው አንኳን እንደ ቅብጠት ይቆጠርና” ድንገተኛ የኃይል መቆራረጥ ሲከሰት ለምን አየሩን በሞሉት ሚዲያዎች ፈጥኖ እንድንዘጋጅ አይነግረንም? የብእሬ ቁጣ ምክንያት ግልጽ ሆኖ ይሆን?
እቀጥላለሁ። ቅድመ ክፍያ ፈጽመን የምንገ ለገልበትን ካርድ ለመሙላት ሌሊት ተነስተን ሰልፍ ስንይዝ፣ በፀሐይና በውርጭ ስንለበለብ፣ ለመከረኛው ኮቪድ በሚያጋልጥ “ትቅፍቅፍ” ሙሉ ቀን በሰልፍ ተጥደን እየዋልን አሳራችንን ስንበላ “ችግሩን በቅርቡ እንቀርፋለን!” በሚል ምጸት ላይፈጽሙት ለምን በንቀት ይሸነግሉናል? ለምንስ ይዘባበቱብናል። በሕዝብ ላይ የሚፈጸም ጭቡ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል “ባለ ከረባት አሳማሪ” የተቋሙ ሹሞች ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም። ከዚህ በላይ ሕዝብን መናቅ ምን ስም ሊሰጠው ይቻላል?!
በዚሁ ተቋም ውስጥ ያሉት “የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ ተብዬዎች” ሥራስ ምን ይሆን? በእውነቱ ከሆነ ከሀገሬ ካዝና ተዝቆ ለእነዚህ መሰል ባለሙያዎች የሚከፈለው ደሞዝ (የደም ወዝ) የሥራ ውጤት ሳይሆን የስንፍና ሽልማት እንደሆነ ቢገለጽላቸው ተገቢ ይመስለኛል።
የሃይል መቋረጥ ለቀናትና ለሳምንታት የአንድ አካባቢ ዜጎችን በጭለማ ዳፍንት ውስጥ አውሎ ሲያሳድር ምን ነበረበት በየሚዲያው እየቀረቡ ምክንያቱን በማስረዳት ሌላ አማራጭ እንዲፈለግ የማይገልጹት? ወይንም የማያሳውቁት? የፈለገውን ቀናት ያህል ቢሆንም ችግሩ ቢያይል እንኳን “መብራት እንደሚቋረጥ” ቀድመው ቢያስጠነቅቁን ምን ይጎልባቸዋል፤ ምንስ ይከብዳቸዋል።
መቼስ ሕዝብ መንግሥትን ከናቀ፤ መንግሥትም ሕዝብን ከናቀ ውጤቱ ይህ ሆኖ እንጂ በሚደማመጥ ሀገርና ሕዝብ ዘንድ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነቱ “በሕዝብ ላይ የሚፈጸም ንቀት” የተቋሙን ባለስልጣናትና የሚመለከተውን ክፍል ሰራተኞች ከሥራ በማሰናበት መቅጣት ብቻም ሳይሆን ፍርድ ቤት ድረስ ገትሮ ኪሳራ የሚያስጠይቅ ድርጊት በሆነ ነበር።
በሀገሬ ሰማይ ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ የሕዝብ ጩኸት በርክቶ ብሶተኛ ከመብዛቱ የተነሳ መደማመጥ ስላልተቻለ እንጂ ሰከን ብለን ብናስተውለው የሀገሬ መሠረታዊ የበሽታ ምክንያት ለአቅመ ኃላፊነት የማይበቁና ለሕዝብ ደንታ የማይሰጡ “ምን ግዴዎች” በስልጣን ወንበሮች ላይ ተንፈራጠው ስለተጠቀመጡ ይመስለኛል።
አንዱ አብነት ይሄው ከላይ የጠቀስነው “ምን ግዱ” የመብራት ኃይል መ/ቤት ነው። በጥገና ጉዳይ፣ አዲስ ቆጣሪ ለማስገባት ያለውን ቢሮክራሲ፣ የዘቀጠውን የተቋሙን አንዳንድ ሰራተኞች ብልሹ ባህርያት ወዘተ. እያልን ብንዘረዝር አንባቢያንን እንዳያሰለች ሰግተን አንጂ ገመናውን መዘክዘኩ ከብዶ አይደለም።
“የበላይ ተቆጣጣሪ ተቋማትስ ቢሆኑ ምን እየሰሩ ነው?” ብለን መጠየቁም እንዲሁ አግባብ ይመስለኛል። ለእነዚህ ተቋማት ኃላፊዎች ሹመት የሚሰጠውና ሹመቱን የሚያጸድቀው ክፍልስ ይሄን መሰሉ የሕዝብ እሪታ በእርግጡ ጠፍቶት ነው? በግሌ በፍጹም አይጠፋውም ባይ ነኝ። ችግሩ ሥር የሰደደው “የመንግሥትና የሕዝብ መናናቅ” ውጤት ካልሆነ በስተቀር አንዴት ለሕዝብ ጩኸት ጆሮ ዳባ ልበስ ይባላል።
ጭክን ብለን የልባችንን ኀዘን እንዘርገፈው ካልንም ሪፖርት ተቀባዩ የተወካዮች ምክር ቤት ባለሥልጣናቱን አስቀርቦ ስራቸውን “ገመገመ” ከመባል ውጭ እኒህን መሰል የሥራ ኃላፊዎች በብቃት ማነስና “ሕዝብን በማስለቀሳቸው ምክንያት ከኃላፊነታቸው አሰናበታቸው” የሚል ዜና አድምጠን እናውቅ ይሆን!? በግሌ መልሴ እንጃ ነው። ስለዚህም ይመስላል የተቋሙ ጥያቄና አስተያየት መቀበያ አጭር ቁጥር (995) ስሙ እንጂ ግብሩ የማይታወቀው። የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬቱም ይሁን ክፍሉ የሕዝቡን ብሶት ለመስማትና መረጃ በወቅቱና በአግባቡ ለሕዝብ ለማድረስ ጆሮውንና ልቡን የደፈነው።
ብሶታችን ተሰምቶ ሕግ የሚከበር ከሆነ “በሕግ አምላክ!”፣ “ሕዝብ የሚፈራ ከሆነም በሕዝብ አምላክ!”፣ ምን እንዳልሆን የሚባል ከሆነም “በጉልበት አምላክ!” የኢትዮጵያ መብራት ኃይል በሕዝብ እምባ ከመታጠብ ይታቀብ። ከውሸት ይልቅ እውነቱን ይንገረን! ከመደለል ይልቅ እቅጩን ያሳውቀን! መብራት መጥፋቱንም ይሁን ለተወሰነ ጊዜ መቋረጡን አስቀድሞ ያሳውቀን።
ብሶታችን ካላራራውም በየቤቱ በመብራት እጦት ምክንያት የሕጻናትን እንክብካቤ የሚመለከቱና ከመብራት ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች ብዙ መሆናቸው ትዝ ይበለው። ከትምህርት ገበታ ላይ ተለይተው ወደ ትምህርት ቤት የተመለሱ ልጆቻችን ለማካካሻው ትምህርትና ፈተና በውጥረት ላይ እንዳሉ ይሰማው። “ሆድ ይፍጀው” ይሉኝታ ይዞን እንጂ የችግሮቹን መጠን አስፍተን መዘርዘር ይቻል ነበር።
የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ የፍርድ ቤቶችና የፍትሕ ተቋማት፣ የገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች፣ የመንገድ ትራንስፖርት፣ መንግሥታዊ የጤና ተቋማት፣ የቀበሌ፣ የወረዳና የክፍለ ከተሞች ጽ/ቤቶች ወዘተ. በማለት እየዘረዘርን ከብእራችን ቀለም ጋር እምባችንን እናዝራ ብንል ብዙ ስለሚያጽፈን ለጊዜው እዚሁ ላይ አቁሞ ሌሎቹን ተቋማት በዝርዝር ለመፈተሽ ቀጠሮ መያዙ ይበጃል።
እንባ ቀለባቸው የሆኑ ተቋማት የመብዛታቸውን ያህል “ምሥጋና ቁርስና ምሳቸው” የሆኑ ጥቂት መንግስታዊ መ/ቤቶች መኖራቸውን ባንጠቅስ አግባብ አይሆንም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ (የተቋሙ አንዳንድ እጥረቶች እንደተጠበቁ ሆነው) የኢትዮ ቴሌኮም መስተንግዶና አገልግሎት አሰጣጥ በከፍተኛ መሻሻል ላይ ስለሆነ ምስጋናችን ይድረሰው። የበርካታ ሠራተኞቹ ሥነ ምግባር ብቻም ሳይሆን የደንበኞች አቀባበሉም የተሻለ ስለሆነ በርቱልን እንላለን።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎትም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መሻሻልና ለውጥ ላይ ስለሆነ ሊመሰገን ይገባል። የሰነዶች ማረጋገጫ መ/ቤትም ብልጭ ያለው መልካም የለውጥ እርምጃው “ድርግም” ብሎ ሕዝብን ለምሬት እንዳይዳርግ ጥንቃቄ ማድረጉ እንደማይከፋ በመጠቆም በአንጻራዊ መልኩም ቢሆን ስለ አገልግሎት አሰጣጡ ሊመሰገን ይገባል።
“ጎበዝ ተናንቀናል እኮ!” ያሉት አንድ የሀገራችን መሪ ነበሩ። ለጊዜው ስማቸው ይቆይ። ለማንኛውም ግን መናናቅ ለማንም አይበጅም። በተለይም “ሕዝብን ማንኳስስና ምን እንዳይመጣ ነው!” ብሎ መታበይና “ይጩኹ! ይለፍልፉ!” ብሎ አስተያየት ሰጪዎችንና ደፋር ማኅበራዊ ሃያሲያንን መናቅ ውጤቱ አይበጅም።
የተናቀ የሕዝብ ጩኸትማ ምን ውጤት እንዳስከተለ የሩቁና የቅርቡ ታሪካችን የሚያስተምረን ብዙ ነው። እኛም ምስክሮች የሆንባቸው የበቀደም እለቱ ገጠመኞቻችን ለማሳያነት አያንሱም። ለካስ ምርጫ ደርሷልና! ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን የካቲት 06/2013