ይበል ካሳ
ነባራዊ መነሻ
ድሮ ድሮ ኢትዮጵያውያንን አብዝቶ የሚያስ ጨንቃቸው ከአላፊው ይልቅ ዘላለማዊው፣ ከምድሩ በላይ የሰማዩ ቤት እንደነበረ በጽሁፍ ከተቀመጡ ቀደምት የታሪክ መዛግብትና ከትውልድ ትውልድ በቃል ከተላለፉልን የህዝብ ሥነ ቃሎች እንረዳለን። “አሟሟቴን አብጀው” የሚለው የአበው ጸሎትና “ቤት የእግዚአብሔር ነው” የሚለው የብዙሃኑ ብሒል ብቻ ለዚህ ከበቂ በላይ ማሳያ ነው። አሁን ላይ ግን ነገሩ ሁሉ የተገላበጠ ይመስላል።
ከሰማይ ቤት በላይ የዛሬዎቹን ኢትዮጵያንን አብዝቶ የሚያስጨንቀን ምድራዊው ኑሯችን በተለይም መኖሪያ ቤት ሆኗል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱና በጣም እየከፉ ከመጡ ማኅበራዊ ችግሮች መካከል አንደኛውና ዋነኛው የመኖሪያ ቤት ችግር ነው። ችግሩ ከሞላ ጎደል አገራዊ መልክ ያለው ቢሆንም በተለይ በከተሞች፤ ከከተማም በመዲናችን አዲስ አበባ ዜጐችን በእጅጉ ከሚያሳስቧቸው ችግሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚወሳው የመኖሪያ ቤት ችግር ነው። ለኑሮ ተስማሚ ካልሆኑት ጎስቋላ መንደሮች አንስቶ ከነጭራሹ ቤት የሌላቸው በኪራይ ቤቶች መከራቸውን እያዩ የሚኖሩ ዜጎች አያሌ ናቸው።
የመኖሪያ ቤት ችግር ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችንም ጭምር የሚፈታተን ነው። በወጣትነታቸው ትዳር መመሥረት ተስኗቸው የቤተሰብ ሸክም የሆኑ ብዙ ናቸው። ብዙዎቹ የመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው ከግማሽ የሚበልጠውን ለመኖሪያ ቤት ኪራይ እያዋሉ ከዛሬ ነገ የማይለወጥ የድህነት አዙሪት ውስጥ ለመኖር ተገደዋል።
ከአቅማቸው በላይ በኪራይ ቤት እየከፈሉ ነገን ተስፋ አድርገው ከሌላቸው እየቆጠቡ የሚኖሩ ዜጎች መንግሥት በስፋት አቅዶ በተለያዩ ፕሮጀክቶች እየገነባቸው ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለረጅም ዓመታት በተስፋ እየተጠባበቁ ቢቆዩም ላም አለኝ በሰማይ ሆኖባቸዋል። በዚህ ረገድ በ1996 ዓ.ም. የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ባለፉት 12 ዓመታት ባደረገው አዝጋሚ ጉዞ ከመቶ ሺህ ያህል ቤቶች ተገንብተው ለዕድለኞች ቢተላለፉም አሁንም ፍላጎትና አቅርቦት አልተጣጣሙም።
ችግሩን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች
“የከተማ መልሶ ማልማት በኢትዮጵያ፣ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶች እና የወደፊት አቅጣጫዎች” በሚል ርዕስ በ2009 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማእከል የከተማ ልማት ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ዘርፍ የተጠና ጥናት የሚያመላክተውም ይህንኑ ነው። “ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ገና በመልማት ላይ ያለች በመሆኗ ያላት የክትመት ደረጃ ዝቅተኛ ነው” ይላል ይህ ጥናት የኢትዮጵያ የከተሜነት ደረጃ 19 በመቶ መሆኑንም የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የ2014 ትንበያን ጠቅሶ ያስቀምጣል።
ሌሎች ጥናቶችም ቢሆን ለምሳሌ ሀገራዊ እስፓሻል ጥናት በ2015/16 የኢትዮጵያ የከተሜነት ደረጃ ከ20 በመቶ ያልበለጠ መሆኑን ያሳያሉ። ይህ ጥናት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር (2007) መረጃን ጠቅሶ እንደጻፈው ከሃያ ሺ ህዝብ በላይ ያላቸው ከተሞች ከ112 አይበልጡም፤ አብዛኞቹ ከ1,500 በላይ ከተሞች ደግሞ ገና በአነስተኛ ደረጃ ያሉ ናቸው።
በከተሞች የመኖሪያ ቤት እጥረት ለዘመናት የተከማቸ መሆኑ የተለያዩ አካላት በተለያዩ ጊዜያት የተከናወኑ ጥናቶች ያመለክታሉ። በከተሞች ሰፊ መልሶ ልማት እንዲከናወን ካደረጉት ቁልፍ ምክንያቶችም የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱ በየወቅቱ ስላልተመለሰ ከተሞቹ በአብዛኛው በህገወጥነት፣ ህጋዊም ቢሆን ያለ ፕላን የተመራ ስለነበር ከጅምሩ ጎስቋላ ሰፈሮች መስፋታቸው ነው።
“ስለዚህ መልሶ ልማት ለዘመናት የተከማቸ ይህንን ቁልፍ ችግር መፍታት ከቀዳሚ ግቦቹ አንዱ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል”። ባለፉት ሁለት አስርታት ሲተገበር የቆየው “የመልሶ ማልማት መርሃ ግብር” ችግሩ አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰባትን አዲስ አበባን ጨምሮ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የከተሞች የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግርን ፈቶ ይሆን? እስኪ የጥናቱን ውጤት እንከታተል።
በመልሶ ማልማቱ የተፈጠሩ ቤት አልባዎች
እንደ ጥናቱ ውጤት “ለዘመናት የተከማቸውን የከተሞች የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግር መፍታትን ከቀዳሚ ግቦቹ አንዱ አድርጎ ባለፉት ሁለት አስርታት አዲስ አበባን ጨምሮ በከተሞቹ ሲካሄድ የቆየው የመልሶ ማልማት መርሃ ግብር” በአወንታም በአሉታም የሚገለጹ ውጤቶች ታይተውበታል።
በአወንታዊ ጎኑ በመልሶ ልማት ምክንያት የሚፈርሱ ቤቶች በጋራ የመኖሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም የልማት ተነሺዎቹ በከተማው የሽንሻኖ ደረጃ ቤት እንዲገነቡ በማድረግ ለመተካት ሞክሯል።
“ይሁን እንጂ አጠቃላይ የቤት አቅርቦቱ በየጊዜው የሚፈጠረው ፍላጎት መመለስ ይቅርና በመልሶ ልማቱ ምክንያት ለሚፈርሱ የሚተካ አይደለም” ይላል የጥናቱ ውጤት። የዚህ ምክንያትም በሁለት አቅጣጫ የሚታይ ነው። አንዱ ምክንያት በመልሶ ልማት የሚከናወን የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ መጓተት ነው።
ለምሳሌ ባለፉት ስምንት ዓመታት አዲስ አበባ ላይ የተከናወኑት 24 የመልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች ከመኖሪያና ሥራ ቦታቸው ከ25ሺ በላይ አባወራዎች እንዲፈናቀሉ ሲያደርጉ ከነዚህ የልማት ተነሺዎች የኮንዶሚኒየም ቤት ያገኙት 11,998 ብቻ ናቸው። ይኸው ብቻም ሳይሆን በከተማይቱ በተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች የተመዘገበው የቤት ፈላጊ ከ800 በላይ ሆኖ ላለፉት አስር ዓመታት የተገነቡት የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ብዛት ግን ከ350 በላይ አይደለም።
ሁለተኛው ምናልባትም ዋናው ጉዳይ ደግሞ ከመሬት አጠቃቀም ፕላን ለውጥ ተያይዞ የሚከሰት ነው። በሁሉም ከተሞች ሲከናወኑ የቆዩ የመልሶ ልማት ፕሮጀክቶች መኖሪያ ሰፈሮች ወደ ንግድ አገልግሎት የቀየሩ ናቸው።
ይህንን ችግር በሁሉም ከተሞች በተመሳሳይ ደረጃ የሚታይ ቢሆንም ተጨባጭ ምስሉ የተሟላ መረጃ ከተገኘባቸው የደሴና መቐለ ከተሞች በማሳያነት ወስዶ መረዳት ይቻላል።
የስራ አጥነትና ድህነት ለመቅረፍ እያስቻለ አይደለም። የልማት ተነሺዎች በቋሚነት የተሰማሩባቸው የስራ መስኮች እንዲያጡ እያደረገ ይገኛል። ግንባታና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚፈጥሩዋቸው የስራ ዕድል ስፋት እጅግ ጠባብ ከመሆናቸው በላይ ጊዜያዊ ናቸው። ስለዚህ የልማት ተነሺዎች ያጡት ስራና ገቢ በእነዚህ ዘርፎች ስለማይካካስ በከተማ ደረጃ ድህነትና ስራ
አካታችነት እና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን በተመለከተም በዚህ ጥናት በከተሞች የሚካሄደው መልሶ ማልማት አካታችነቱን ምን ያህል እንደሆነ ለማመላከት ተሞክሯል። ለዚህም ነባር ነዋሪዎችን ተሳታፊ ማድረግ፣ ነባር የከተማ አገልግሎቶችን ከአዲሱ ልማት ጋር አዋህዶ ማስቀጠል፣ ድሃና ሀብታም፣ ዘመናዊና ባህላዊ የከተማ ሕይወት፣ ከፍተኛና ዝቅተኛ እርከን የከተማ አገልግሎት ተጣጥመው ጎን ለጎን አብረው የሚኖሩበትን ሁኔታ የሚመለከቱ መለኪያዎችን ተጠቅሟል።
“ሆኖም ለጥናቱ በናሙናነት ከተወሰዱ ከተሞች አንዱ በሆነው በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄዱ ባሉ የመልሶ ልማት ፕሮጀክቶች ተዘዋውረን ስንመለከት አካባቢው ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ነው የምናገኘው” ይላል የጥናቱ ውጤት።
እንዲያውም ልማቱ ታሪካዊ ቅርሶችን ጭምር የሚያጠፋ ነው የሚል ትችት ይሰነዘርበታል። የመኖሪያ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ንግድ ማዕከልነት የተቀየሩበት፣ ዘመናዊና ባህላዊ ኢኮኖሚ፣ ድሃና ሃብታም፣ መኖሪያና ቢዝነስ ተዋህደው የኖሩባትን አዲስ አበባ ወደ አዲስ መልክና ቅርጽ የቀየሩ የመልሶ ልማት ፕሮጀክቶች ጥቂት አይደሉም።
የመፍትሔ መንገዶች
አንገብጋቢ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት መንግሥት ዋነኛው አካል ቢሆንም፣ ይመለከታቸዋል የሚባሉ ባለድርሻ አካላት ከዕቅድ እስከ አፈጻጸም ድረስ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል። መንግሥት የተቆጣጣሪነት ኃላፊነቱን እየተወጣ የግንባታውን ሙሉ ኃላፊነት በጨረታ ብቃት ላላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች መስጠት ይኖርበታል።
በመላ አገሪቱ እየተገነቡ ያሉትንና የነበሩትን መንገዶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ኩባንያዎች በሚሰጠው አሠራር መሠረት፣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታም በዚህ መንገድ ካልተመራ ችግሩ ቀውስ ያስከትላል። በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የተለያዩ ግብዓቶችን እያቀረበ በሥራ ተቋራጮች የሚያስገነባበት አሠራር ወጪ ቆጣቢ አይደለም፤ ለሙስናም የተጋለጠ ነው።
ከፍተኛ የሆነ የጥራት መጓደልም ይፈጠራል። ይህም በተግባር እየታየ ነው። በመሆኑም በብዛት ቤቶችን ገንብተው መጠቀም የሚፈልጉ ኩባንያዎች በጥንቃቄ ተመርጠው ሥራ ይሰጣቸው። ለዚህም ጠቃሚ ልምዶች ይገብዩ። በዘርፉ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ዕድሉ ይሰጣቸው የሚሉት ከዘርፉ ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦች ናቸው።
የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ አሁን ባለው ሁኔታ አዝጋሚ ጉዞውን የሚቀጥል ከሆነ፣ ለዘመናት ወገቡን አስሮ፣ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ የቆጠበው እያለ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ለሌላ የሚሰጥ ከሆነ ተመዝግበው ወረፋ የሚጠብቁትን ብቻ ሳይሆን ነገን በተስፋ የሚጠባበቁ ታዳጊዎችን ጭምር ተስፋ ያስቆርጣል። አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ደግሞ ከኪራይ ብዝበዛ ጀምሮ ኑሮን መቋቋም ሲያቅታቸው ቀውስ አይፈጠርም ብሎ አለመስጋት በራሱ አጠያያቂ ነው።
በቅርቡ ለባለ ዕድለኞች በመተላለፍ ላይ የሚገኙ ቤቶች በሚገባ ባለመጠናቀቃቸው ሳቢያ ተጨማሪ ወጪ እያስወጡ ነው። ከኑሮ፣ ከቤት ኪራይ፣ ከቁጠባና ከመሳሰሉት ምን ተርፎ ነው በአግባቡ ተጠናቆ መረከብ የሚገባን ቤት ለተጨማሪ ወጪ የሚዳረጉበት? ይህ ዓይነቱ አሠራር በቀጠለ መጠን መሸማቀቁም አብሮ ይቀጥላል።
በሌላ በኩል ቤቶቹ በኩባንያ ቢገነቡ ግን ከዕቅድ፣ ከዲዛይን፣ ከወጪ ቆጣቢነት፣ ከጥራት፣ ከተጠያቂነትና ከመሳሰሉት አንፃር ብርቱ ቁጥጥር ስለሚኖር ይህ ዓይነቱ አካሄድ ተመራጭ ይሆናል።
ብሩህ ተስፋ
ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እያስገነባቸው ያሉ ዘጠኝ ሳይቶች
እና የገርጅ ዘመናዊ አፓርታማ መንደር የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች ጥሩ ማሳያዎች ይሆናሉ። በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማትና ኮንትስራክሽን ቋሚ ኮሚቴ አባላትት ምልከታ የተደረገባቸው ኦቪድ ኮንስትራክሽን በተባለ የግል ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ እየተገነቡ የሚገኙት እነዚህ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መሰረት ግንባታቸው በመከናወን ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የቦሌ ሳይቶች የፊንሽንግ ስራዎች መጀመራቸውን የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተመልክተዋል። ኮርፖሬሽኑ የሚያስገነባው የገርጅ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክት በአራት ወራት ውስጥ የ 16 ህንጻዎች የህንጻ መሰረት በማጠናቀቅ የአልሙኒየም ፍሬምዎርክ ሥራ መጀመሩ ከውለታ ጊዜው በፊት ለማጠናቀቅ በሚያስችል መልኩ ግንባታው እየተካሄደ መሆኑን መመልከታቸውንም የቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል።
በመጠናቀቅ ላይ እና በግንባታ ሂደት ያሉ የኮርፖሬሽኑ ግንባታዎች ለሀገራችን የግንባታ ፕሮጀክቶች አዳዲስ የአሰራር ስልቶችን እና ጠንካራ የሥራ ባህል ያስተዋወቁ መሆናቸውንም የቋሚ ኮሚቴው አባላቱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ይህ ቤቶች በግል ኩባንያዎች ቢሰሩ የበለጠ ውጤታማ ሥራ መስራት ይቻላል የሚለውን አመክንዮ አስፈላጊነትና ትክክለኛነት መልካም ማሳያ ይሆናል። ስለሆነም እንዲህ ዓይነቱ ጅምር የመኖሪያ ቤት እጥረት ጋር ያሉ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋልና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።
በአጠቃላይ መንግሥት በቤቶች ልማት ፕሮጀክት አማካይነት የጀመረው ጥረት በበጎ ቢወሳም፣ ስትራቴጂውን እየፈተሸና እየከለሰ ተመራጭ መፍትሔዎችን ካልፈለገ በመኖሪያ ቤት ችግር እየተፈተኑ ያሉ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ሊደርስላቸው አይችልም። በተጨማሪም ከአቅም በላይ እየሆነ የመጣውን የኑሮ ጫና እየተጋሩ ያሉ ዜጎች፣ በአከራዮቻቸው ማናለብኝነት የሚደርስባቸው ግፍ ከመጠን እያለፈ በመምጣቱ አገራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር አማራጮችን በቅን ልቦና ማየት የግድ ይሆናል።
በአዲስ አበባ ከተማ በአራቱም አቅጣጫዎች የሚሰማው የመኖሪያ ቤት ችግር እሮሮ አዳማጭ ይፈልጋል። መንግስት አሁንም ለመኖሪያ ቤት ጉዳይ ልዩ ትኩረትና ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።
መኖሪያ ቤት እስከ መቼ የዜጎች ችግር ሆኖ ይቀጥላል? በምቾት ለመኖር ሳይሆን በህይወት ለመኖር፣ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ የሆነው የሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት ቤት እስከመቼ ድረስ አጥብቀው የሚፈልጉት ሰማይ ጽድቅ ሆኖ ይቀጥላል። ዜጋው እስከመቼ በገዛ ሀገሩ ላይ ቤት አልባ ይሆናል?
አዲስ ዘመን የካቲት 06/2013