ብስለት
ሰባ በመቶ የሀገራችን ህብረተሰብ ከፍል ወጣት ነው የሚል ነገር ሲነገር ይደመጣል። ወጣት መሆን ጉልበት ድፍረት እልህና አቅም እንድሆነ እንደመለከት ያደረገኝ እውነትም ወጣት የነብር ጣት እንድል ያደረገኝ የዘንድሮው ጥምቀት በዓል ላይ ይህ ትኩስ ሃይል ሙሉ ፍቅርና ጉልበት፤ ሃይማኖት ያልለየ የስራ ክፍፍልን ያሳዩንን የወጣት ማህበራት ስመለከት ነው።
አዲስ አበቤው እንደቀደመ በባህሉ ታቦት በደጁ ሲያልፍ ውሃ ከማቀበልም በላይ ሙስሊም ክርስቲያን ብሄር ሳይለይ በፍቅር ጉልበቱን ሳይሰስት የአካባቢውን ጽዳትም ጸጥታንም በገራ ሲያስቃኘን የነበረውን ወጣት ነው እንግዲህ የሀገር ሀብት ወጣት እንድል ያደረገኝ።
ከዳር እስከ ዳር ስለእምነት የተነቃነቀውን ይሄን ፍቅርና አቅም ጉልበትና ድፍረት በመልካም መሪ እየተቃኘ የአንድ ቀን ሳይሆን የዘላለም ማድረግ ይሳነን ይሆን?
ለፍቅር ለእምነት ምንጣፍ እየተሸከመ አስፓልት እየጠረገ ሰላም እያስከበረ በፍጹም ቅንዓት ላቡን ያፈሰሰው ይህ ወጣት በፍጹም ፍቅርና ክብር ቀርቦ የሚሰበሰበው ያገኘ ለታ ታሪክ ስለመስራቱ ምን ጥያቄ አለው።
ይህን የመከፋፈል በጎጠኝነተና በዘር አመለካከት የጠለሸው ልብ በእምነትና በፍቅር ፃእዳ የለበሰ እንደሆን ለኢትዮጵያዬ ትልቅ አቅም ትልቅ ጉልበት ላይሰጣት ይችል ይሆን? ወይስ…? ወጣቱስ የአንድ ቀን ሳይሆን በሀገሩ ታሪክ ሰሪ ይሆነ ዘንድ ሸብቦ የያዘውን ልጓም ከተላቀቀለት እንደ ቀደሞቹ ወጣቶች የነበር ጣትነቱን የማሳየት አቅም አይኖረው ይሆን የሚል ጥያቄ በውስጤ አምሰለስላለሁ።
መልሶ መላልሶ ለሚመጣብኝ ጥያቄ ይህ ወጣት በነብር ጣት መመሰል ያንሰው እንደሆን እንጂ አይበዛበትም የሚል ምላሽ ውስጤ ይነግረኛል። የኢትዮጵያም ወጣት በየዘመኑ የለውጥ ሃይል የህዝብ አቅም የነብር ጣት ሆኖ ሲታይ ኖሯል።
አገራችን በጣልያን ፋሽስቶች በተወረረችበት ወቅት የጠላት ግዙፍ ኃይልና ፕሮፖጋንዳ ሳይበግራቸው፤ በአይሮፕላን የመጣን ወራሪ በውጅግራና ምንሽር ለማባረር ቆርጠው የተነሱ፤ የወቅቱን የአውሮፓ ኃያል መንግሥት ሠራዊትን በአበርኝነት ተፋልመው ነፃነትን ያቀዳጁን ጀግኖቻችን በወቅቱ በእድሜ ገና ለጋ ወጣቶች የነበሩ ናቸው። ከ1950ዎቹ ጀምሮ የተደረጉ ህዝባዊ ንቅናቄዎች በሙሉ የተጠነሰሱትና የተመሩት እድሜያቸው ከሠላሳ ዓመት በታች በሆኑ ወጣት ሃይሎችም እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይዘክራሉ።
የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ሆኖ በታሪክ ማህበር የተከተበው የ1997 ምርጫ ታሪካዊ እንዲሆን ያደረጉ፤ የሚያዝያ 30 ቀን 1997ን ታላቅ ሰልፍ ያደራጁ፤ ድምፃችንንም አናስነጥቅም ብለው የተለያዩ ትግሎችንም ያደረጉት እነዚሁ ወጣቶች ናቸው። በነፃነት ጉዳይ ፊት ተሰላፊ ትኩስ ጉልበት የሆኑ በየዘመናቸው ብቅ ብለው እንደሚያበሩ ከዋክብት የፈነጠቁልን ወጣቶች ከትግል ውጪ የእድገት ጀገኖች ለማድረግስ አይቻለን ይሆን ብዬ እጠይቃለሁ?
ወጣቱ ለሀገሩ የሚያበረክተውን ቁልፍ ሚና ጠንቅቆ ስለሚያውቅም ነው አስፈልግበታለሁ ብገኝበት ለስኬት አበቃዋለሁ ብሎ ያሰበው ቦታ ላይ ተግኝቶ ግንባር ቀደም ተሰላፊ የሚሆነው። ጀግኖች አባቶቸቻችን ጠላትን አሳፍረው ከሀገራችን ያበረሩበት ወቅት የነበራቸው የወጣት ወኔ ዛሬም በበቂው ልክ ስለመኖሩ በተለያየ ጊዜ ፈርጣም ክንዶቻቸውን የሚያሳርፉበት ጊዜ ላይ ለመመልከት ተችሏል።
ግን ግን ወኔ ሰላቢው ድህነት ኢትዮጵያዊ ወጣት ክብሩንና ነፃነቱን ለገንዘብና ለተሻለ የሥራና የትምህርት እድል ሲል አሳልፎ እንዲሰጥ ሲደለል ቆይቷል። ሌላም ጊዜ ደግሞ ኩርማን እንጀራ ነጥፎበት የተሻለ ህይወት ፍለጋ ባህር የበላውንም ቤቱ ይቁጠረው።
በዚህም ሆነ በተለያየ ምክንያት አንዳንዱ ወጣት የማያምንበትን እየሰበከ፤ ከህሊናው ጋር ተጣልቶ ሲኖር ከመክረሙም በሻገር በጫትና ሌሎችም ሱሶች አእምሮው የደነዘዘው ወጣት ቁጥርም ከልክ በላይ መሆኑ አቅሙን ሸርሻሪ ወኔ ሰላቢ ጉዳይ ሆኖ ነው የኖረው።
ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ወጣቱን በዘር በማደራጀት ወጣቱ እርስ በርሱ እንዲጣላ መደረጉ ነው። በየጊዜው በሚፈለፈሉ “የወጣቶች ፎረሞች” አማካይነት የወጣቱ ወኔ ተሰልቦ አድርባይነትን እንዲለማመድ ተደርጓል።
የሊባኖስ ወጣቶች ለግብፃውያን የእድሜ እኩዮቻቸው የድጋፍ ሰልፍ ሲወጡ እኛ አገር ግን የጎንደሩ ለባሌ፤ የሸዋው ለአሩሲ፤ የትግራዩ ለባህርዳር የሃረሩ ለጅጅጋው ባዕድ እንዲሆን፤ በጥርጣሬም እንዲጠባበቅ፤ በሰበብ አስባቡም እንዲቆራቆስ ተደርጓል።
ይህ ወጣቶችን በወጣቶች ላይ የሚያዘምት እርኩስ ኃይል በቀና መሪ ከተቃኘ የወጣት ክንድ የተሳሰረ የለውጥ አካል ላለመሆኑ ምን ምክንያት ይጠቀስ ይሆን እያለኩ አስባለሁ።
በየትም አገር ቢሆን የወጣቱ የወደፊት እድል ያለው በራሱ በወጣቱ እጅ ውስጥ ነው። ወጣቱን ይህ ክፉ ትውልድ እያሉ ለጥፋት ከማሳለፍ ይልቅ በሚገባው ልክ ከፊት በተግባር እያሳዩ መምራት የትላልቆቹ ትውልዶች ግዴታ መሆኑ አያጠይቅም። ይህ ወጣት ከመልካም መሪ ጋር ከተገናኘ የእረኛውን ድምፅ እየሰሙ እንደሚከተሉት የበግ መንጋ በተቃኘለት መስመር የሚሄድ መሆኑ አይቀሬ ነው።
ይህን ትልቅ አቅም ለሀገር እድገት ተግተን ልናተጋው ካለቻልን ይህ የለውጥ ሃይል የሆነው ወጣት የጥፋት ሃይል እንደማይሆንብንስ ምን ዋስትና ሊኖረን ይሆን። ይህን ጊዜ በአግባቡ ከልያዘናት ሀገር እንደ ሀገር ለማስቀጠል ሃሳብ ሃሳብ ብቻ ሆኖ እንዳይቀርብን ስጋቴ ነው።
ወጣት ሀብት ወጣት ጉልበት መሆኑን ለማየት ሁሉም በየሃላፊነቱ ለትውልዱ የሚበጅ ጠንካራ መሰረት እየጣለ ተከታዩ ትውልድ በተመሰረተለት የማይናወጥ መሰረት ላይ የራሱን ጡብ አስተካክሎ ከገነባ አንዱ ሰሪ አንዱ አፍራሽ ሳይሆን በተሰናሰለ አቅም በተጣመደ ፍቅር ሳይበጠስ እስከወዳኛው የሚቀጥል ሀገርም የማይወቃቀስ ትውልድም እንደሚኖረን እተማመናሁ።
ወጣቱም ከልብ በመነጨ ፍቅርና ከውስጥ በፈለቀ ትጋት የነብር ጣትነቱን አሳይቶ ያልፍ ዘንድ ምኞቴ ነው። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2013