አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ያለው የአስተዳራዊ ወሰንና የማንነት ጥያቄ በጥናትና በህዝብ ይሁንታ ካልተፈታ አገር ሊያፈርስ እንደሚችል በፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ዳይሬክተር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በምክር ቤቱ የህግና የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ አቶ ሙልዬ ወለላው ገለጹ።
በአገሪቱ የአስተዳደራዊ ወሰንና ማንነትን መሰረት አድርገው የተነሱ ግጭቶችን ለመፍታት በአብዛኞቹ ላይ መሳተፋቸውን የሚያነሱት ባለሙያው፤ ሁሉም በሚባል ደረጃ የዜጎች ህልፈት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል፣ የኢኮኖሚ ውድመት አድርሰዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜም ችግሩ በአብዛኛው ክልሎችና የአገሪቱ ክፍሎች እየተባባሰ መጥቷል። ይህ ሁኔታ በጥናትና በህዝብ ይሁንታ ካልተፈታ አገሪቱን ወደ ማፍረስ እንደሚሻገር አስጠንቅቀዋል።
አሁን ያሉት ክልሎች በህገ መንግስቱ ስርዓት፣ በጥናትና በህዝብ ይሁንታ አለመዋቀራቸውን የሚያነሱት አቶ ሙልዬ፤ ይህም ለችግሩ መነሻ መንስዔ ነው። ከዚያም በኋላ በህገ መንግስቱ መሰረት ለሚቀርቡ የክልል፣ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ አለመሰጠቱ ችግሩን አባብሶታል።
በአሁኑ ወቅት ሁሉም ክልሎች ችግሩ የሁላችንም ነው ብለው ወደመፍትሄ መምጣት አለባቸው። በቀናነትና በእውነት፣ በጥናት ላይ የተመረኮዘ መፍትሄ መስጠት አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ