አስቴር ኤልያስ
ቅርሶች የየዘመኑን አሻራ ጥለው ስለሚያልፉ የዚያን ዘመን ምንነት ተናጋሪና አመላካቾች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የብዙዎችን ቀልብ የመሳብ አቅም አላቸው። ያለፈ ማንነትን ከመግለጽና ቀልብ ከመሳብ ጎን ለገን ለቱሪስት መዳረሻ ምክንያትም ስለሚሆኑ የአንድን አገር ኢኮኖሚ ለመደጎም የማይናቅ ሚና አላቸው። ቅርሶች በዚህ መልኩ ድርሻው ጉልህ እንደመሆኑ ምን ዓይነት ጥንቃቄና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል? ከሚያንዣብብባቸው አደጋስ እንዴት ነው መታደግ የሚቻለው? የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች በመያዝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የአርክቴክቸር የከተማና የኮንስትራክሽን ኢንስቲትዩት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ትምህርት ክፍል መምህር ከሆኑት ከአርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ ግርማይ ጋር አዲስ ዘመን ቃለ ምልልስ አድርጎ ተከታዩን አጠናቅሯል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡– በአገር አቀፍ ደረጃ ታሪካዊ ህንጻዎችና ታሪካዊ ሃውልቶች ናቸው የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– በኪነ ሕንፃ ዙሪያ ያሉ ቅርሶች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። ነገር ግን ጎላ ጎላ ብለው የሚታዩና ከጥንት ጀምሮ በቅደም ተከተል የተወሰኑትን ብቻ እንይ ብንል የየሃ ቤተ መቅደስ አንዱ ነው። በአደዋ አካባቢ የሚገኘው የሃ የምትባለው ጥንታዊ ከተማ በቅድመ አክሱም ዘመን የነበረ ቅርስ ነው። ቀጥሎም የአክሱም አርኪዮሎጂካል ታሪክ የምንላቸው ውስጥ ያሉ ቅርሶች ናቸው።
ከእነዚህም ቀጥሎ የትግራይ ውቅር አብያተ ክርስትያናት፣ በዛጉውዬ ስርዎ መንግሥት የነበሩና በጣም የሚደነቁ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት እንዲሁም በዚያው ዙሪያ ብዙ ያልተነገረላቸውና ያልታወቁ በትግራይ አካባቢ ያሉ ቤተክርስትያናት ቅርሶች አሉ። በተጨማሪም የጎንደር ቤተ መንግሥት የፋሲለደስ ግቢ፣ የሐረር ጀጎል ግንብ እና ሌሎችም ታሪክ ያላቸው ሕንፃዎችን መጥቀስ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– ቅርስ ያለፈ ማንነትና የቀደመ ስልጣኔ አሻራ እንደመሆኑ ለዚህ ሀብት እየተደረገ ያለ ጥንቃቄ እንዴት ይገለጻል?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– ቅርስ በጣም ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ ነው። ቅርስን ለመከባከብ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ፋይናንስ እስከመመደብ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ጎን ለጎን ትምህርት ወሳኝ ጉዳይ ነው። ያደጉ አገራት በራሳቸው ያሏቸውን ቅርሶቻቸውን ለመጠበቅ በእጅጉ የሚፈተኑበት ሁኔታ አለ። ምክንያቱም ቅርስን መንከባከብና መጠበቅ ቀላል ተግባር አይደለም።
\
ከዚህ አንጻር ወደእኛ አገር ስንመጣ መጠነ ሰፊ የሆኑ ቅርሶች አሉን። እነዚህ ቅርሶች ግን ጥንቃቄ እየተደረገላቸው ነው ወይ ብትይኝ አዎ እየተደረገላቸው ነው ለማለት አያስደፍርም። እንዲህ ሲባል ግን ምንም እየተሠራ አይደለም ማለት አይደለም። መንግሥትም ሆነ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት፣ በማህበረሰቡም ሆነ በኃይማኖት ተቋማትም ጨምሮ እውቀትና አቅማቸው በፈቀደላቸው መልኩ የተቻለውን ያህል ሙከራዎች በመደረግ ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– በቅርሶች ላይ እያንዣበበ ያለው አደጋ ምን ዓይነቱ ነው? ከዚህ ዓይነት ስጋት መላቀቅ የሚቻለው እንዴት ነው? መፍትሔው ምንድን ነው?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– ሁሉም ቅርሶች በሚያስብል መልኩ በአመዛኙ አደጋ ላይ ናቸው ማለት ያስደፍራል። ይህ አደጋ የሚባለው የቱ ነው ከተባለ አንደኛውና ዋነኛው የተፈጥሮ አደጋ ነው። እንዲህም ሲባል በየዕለቱ እንክብካቤ ስለማይደረግላቸው በተፈጥሮ በሚያጋጥማቸው ሁነት እየፈራረሱ፣ እየወደቁና እያረጁ መምጣታቸው ነው። ሁለተኛው አደጋ ደግሞ ሰው ሠራሽ አደጋ የምንለው ነው። ይህም ጦርነት ተጠቃሽ ሲሆን፣ ሰዎች ባሉበት አካባቢ በሚፈጠሩ የእርስ በእርስ ግጭቶችም ጭምር ነው።
ለአብነት ያህል በቅርቡ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበሩን ሂደት ተከትሎ የተደረገ ውጊያ ለቅርሶች አደጋ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል። በዚህ ውጊያ የተለያዩ ቤተ እምነቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው መረጃዎች አመላክተዋል። ከዚህ ዓይነት አደጋ ባሻገር ደግሞ ሰዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚያደርሱት አደጋ ሲሆን፣ ግንዛቤው ከሌለ የከተሞች እድገትና መስፋፋትም ለቅርሶች አደጋ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል። ምክንያቱም የከተማውን ማደግ ተከትሎ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ይሠራሉ። በዚህ ጊዜ የተለያዩ ቅርሶች ሊወድሙ ይችላሉ። ዕድገትንና የቅርሶችን ጥበቃ ግን ጎን ለጎን ማስኬድ ይቻላል። ነገር ግን የከተማውን ዕድገት የሚያሳልጡ አካላት ሳያውቁትም ሆነ አውቀው በቅርሶች ላይ ውድመት ሲከሰት ዝምታን ሊመርጡ ይችላሉ። ይህ የሚመጣው ታሪካዊ የሆኑ ቅርሶች ፋይዳቸውን ካላማወቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በትግራይ ክልል ህግን በማስከበሩ ሂደት በቅርስነት ተመዝግበው ከፈረሱ ቤተ እምነቶች መካከል የሚጠቅሱት ይኖር ይሆን?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– አዎ! ለምሳሌ ቤተ እምነት ካልኩሽ መካከል አንዱ የአል ነጃሺ መስጂድ ተጠቃሽ ነው። ይህ በቅርስነት የተመዘገበው ቤተ እምነት በተለይ በሙስሊሙ ህብረተሰብም ሆነ እንደ አገር ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ቅርስ ነው። በመሆኑም በተካሄደው የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ወቅት ጉዳት ደርሶበታል።
አዲስ ዘመን፡– በአሁን ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉትን ቅርሶች አያያዝ ምን ይመስላል? በአያያዙ በኩል ጉድለት አለበት የሚሉ ከሆነ መስተካከል ያለበትስ እንዴት ነው?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– በእርግጥ አያያዛችን ላይ ብዙ ጉድለቶች አሉ። ይህም ጥያቄ የለውም። የጉድለቶቹ መንስዔ አንደኛ ለዘርፉ በቂ የሆኑ ግንዛቤዎች ባለመኖራቸው ነው። ዘርፉን በሚመለከቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከዚህ ቀደም እምብዛም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይስተዋሉም ነበር። በኛ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንኳ ብንወስድ በዘርፉ ዙሪያ እንቅስቃሴ ከጀመርን አራት ዓመት እንኳ አልዘለልንም። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኋላ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ ክፍለ ትምህርቶች ጉዳዩን በመዳሰስ ላይ ናቸው። እንደዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ችግሩን ወደፊት ሊፈታው ይችላል።
ከዚህ ቀደም እንዳልኩሽ በቅርስ ዙሪያ የሚያስተምሩ ዩኒቨርሲቲዎች ብዙም ባለመኖራቸው በተጨማሪም ብዙ ባለሙያዎችም ስለሌሉ በተለምዶና የቅርስ ጥበቃ እንዲሁም ቅርሱን በቅርበት የሚያስተዳድሩ የተለያዩ አካላት ናቸው ኃላፊነት ወስደው ሲሠሩ የነበረው።
እንደሚታወቀው የቅርስ አያያዝ ትልቅ ዲሲፕሊን ነው። ብዙ እውቀትን የሚጠይቅም ነው። ስለዚህ ማናቸውም በቅርስ ዙሪያ የሚሠሩ አካላት በቂ የሆነ ትምህርት ቢያገኙ መልካም ነው። ትምህርቱ ከታሪካዊ ፋይዳ ጀምሮ ያሉትን ነገሮችና በተለያዩ ጊዜ የደረሱባቸውን ችግሮች በአግባቡ መሰነድ ያስፈልጋል። ችግሮቹ ከተሰነዱ በኋላ መንስዔዎቹ ደግሞ ምንድን ናቸው የሚሉት ከተለዩ በኋላ ነው ወደመፍትሔው መሄድ የሚቻለው። ከዚህ ቀደም ይህ ሁሉ ሲደረግ የነበረው በአብዛኛው በልምድ ነበር። በልምድ የሚሠሩ ነገሮች ደግሞ ብዙ ርቀት ሊያስኬዱ አይችሉምና በተለያዩ ተቋማትም አካላትም በተመሰከረ እውቀት የተደገፈ እንዲሁም ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ የግድ ይላል። ሁሌም ቢሆን የጥገናም ሆነ የተለያየ ተግባራት ሲፈጸሙ በተቻለ መጠን ያለውን በማቆየት ብንጀምር ጥሩ ነው። ወይም ደግሞ ብዙ ላለመንካት መጣር አሊያም ደግሞ መንካት ግዴታ ከሆነብን የነካነውን መልሰን ወደነበረበት መመለስ በሚያስችል መንገድ ቢሆን ተመራጭ ነው። ወደፊት የሚመጣ የተሻለ እውቀት ስለሚኖር የተሻለ መፍትሔ ያገኛል።
አዲስ ዘመን፡– ይህ ሁሉ የቅርስ አጠባበቅም ሆነ እንክብካቤ ቅርሶች ከፍ ያለ ፋይዳ ስላላቸው መሆኑ ይታመናል፤ አንድን ማህበረሰብም ሆነ አገርን የሚወክሉት ግን የት ድረስ ነው ማለት ይቻላል? ከዚህስ አኳያ እውን ትኩረት ተሰጥቶታል?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– ቅርሶች ሲባሉ የታሪካዊ እድገታችን መገለጫ የሆኑና ካላፈው ላይ ተነስተን እንደ መስፈንጠሪያ በመጠቀም ዛሬን ኖረን ነገን ብሩህ ለማድረግ የሚጠቅሙን ትልቅ የሀገር መገለጫዎች ናቸው። ቅርስ ማለት በተለያየ ዘመን አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ያስቀመጡትን ታላላቅ የአገሪቷን ጥበብ፣ እውቀትና ሀብት የሚወክል ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ብለን ስናነሳና ኢትዮጵያ ማን ናት ብንል ያለፈውን ይዘን ነው የአሁንና የወደፊቱን መናገር የምንችለው። ያሉንን ቅርሶች ውክልና ለኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን ለአፍሪካ ብሎም ለዓለምም ጭምር ነው። ያሉን ታላላቅ ቅርሶች ለዚህም ነው ኢትዮጵያን በዓለም መድረክም ጭምር ሲወክሏት የሚስተዋለው።
አዲስ ዘመን፡– አትዮጵያ ያሏት ቅርሶች ከአገርም ከአፍሪካም አልፎ በዓለም መድረክም ጭምር እንደሚወክሏት ታሳቢ ተደርጎ ነው ትኩረት እየተሰጠው ያለው ብለው ያስባሉ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– ከታላቅ ነታቸው አንጻር አይደለም ትንንሾቹ ለምንላቸውም እንኳን ምንም ዓይነት ትኩረት አልተሰጣቸውም፤ ምክንያቱም ትኩረት ሰጠን የምንለው በቅርሶቹ ዙሪያ ጥናት የምናካሂድባቸው የተለያዩ ኢንስቲትዩቶች ስንፈጥር፤ በዚያም ዙሪያ ብዙ ሰዎች ትምህርት ሲያገኙና በተማሩ ሰዎች ሲተዳደሩ ነው። ከዚያ ውጪ እንዲሁ በጸሎት ወይም ደግሞ በቸርነት የሚኖሩ ከሆነ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡– አብዛኛዎቹ ቅርሶች በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል እንደመሆናቸውና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ እንደመገኘታቸው ህዝቡ የማንነቴ መገለጫዎች ናቸው በሚል እሳቤ ለደህንነታቸው ምን ያህል አስተማማኝ ጥበቃ እያደረገ ነው? የህዝቡ ግንዛቤ የት ድረስ ነው? ምን ዓይነትስ ግንዛቤ እንዲኖረው ይጠበቃል?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– ህዝቡ በቅርስ ዙሪያ ግንዛቤ አለው። ቅርሶች ያላቸው ፋይዳ ትልቅ መሆኑንና የማንነት መገለጫው እንደሆኑ በደንብ ያውቃል። ግንዛቤ የለውም የምንለው በምን መልኩ እንያዛቸው? እንዴትስ እንከባከባቸው? በምን መልኩ የቆይታ ዕድሜያቸውን እናራዝመው? በሚለው ዙሪያ ስንመጣ ግን ግንዛቤው ብዙ የለም።
ለምሳሌ ማን ነው ቅርሶችን ለመጠገንና ለመንከባከብ መመደብ ያለበት ቢባል ሁሉም ሰው የሚችል ነው የሚመስለውና ከዚህ
አንጻር ግንዛቤው የለም ልንል እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡– ስለዚህ ይህ ነገር ቀጣይ እንዳይሆን መደረግ ያለበት ምንድን ነው? ምክንያቱም ቅርስን ባልተገባ መንገድ ለማደስም ለማስተካከልም በእነዚሁ አካላት ሙከራ ሲደረግ ይስተዋላልና እርስዎ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– ቅርስን ለማደስም ሆነ ለመንከባከብ በመጀመሪያ የሚያስፈልገው እውቀት ነው። እንዲህም ሲባል ቅርሱ መቼ? በማን? ለምን አገልግሎት ተሠራ? አንድ አገር በምን ደረጃ ላይ ስትሆን ለቅርስነት የሚያበቃ ታሪክን መሥራት የምትችለው? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። አንድ አገር ለረጅም ዘመን ሰላም ስትሆን እንዲሁም በተለያየ መንገድ አቅም ሲኖራት ነው ኪነ ሕንፃዎች ልትሠራም ሊኖሯትም የሚችለው።
ከዚህ አንጻር ለማደስ አገሪቱ ያሏት ቅርሶች ከምን ዓይነት ቁስ ተሠሩ? የደረሱባቸው ችግሮች ምን ምን ናቸው? ችግሮቹ ሊደርስባቸው ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው? ለዚህስ መፍትሔው ምን ሊሆን ይችላል? መፍትሔው ከየት ተነስቶ የት ድረስ ይዘልቃል? ምን ያህል ጊዜና ገንዘብ ይወስዳል? ታሪካቸው የሚናገረው ምንድን ነው? የሚሉት ነገሮች ሁሉ ከተጠኑ በኋላ ሁለት ዓይነት ሐሳቦች ይነሳሉ።
አንደኛ ወደነበረበት መመለስ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ በጊዜ ብዛት ታሪክ ይሠራል። ስለዚህ አንድ ቅርስ ላይ በተለያየ ዘመን የተለያዩ አገልግሎቶች ሊኖሩት ይችላሉ። እንዲሁም የተለያዩ የጥገና ሁነቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እነዛን በየዘመኑ የተደረጉትን ነገሮች ተገልጸው እንዲቀመጡ ማድረግ ቢቻል ረጅም ዘመን ያለፉበትን ታሪክ ለማወቅ ይቀላል ብለው የሚያስቡ አሉና ሁለቱም ዓይነት አተያዮች ያስኬዳሉ።
አዲስ ዘመን፡– በተለያዩ አካባቢዎች ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ አሊያም በግዴለሽነት ቅርስ ፈረሰ ሲባል ይደመጣል፤ አሊያም ደግሞ አንድ ቦታ ለልማት ተፈልጓል በማለት በአካባቢው ያለ ቅርስ እንደዋዛ ሊፈርስ ነው ይባላል። ይህን ዓይነቱን አካሄድ አደብ ለማስገዛት ምን መደረግ አለበት?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– ቅርሶች ያለአግባብ እንዳይጎዱ ለማድረግ ዋና ነገር ህግ ማውጣት አንዱ ነው። የወጣውን ህግ ማስፈጸም ደግሞ ሌላው ነገር ነው። በተወሰነ መልኩ ህጉ ክፍተት አለው። ህግ ሲጣስ ምን ይደረጋል በሚለው ላይ ህጉን በተመለከተ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ ነው፤ ለምሳሌ አንድ ቅርስ በሆነ አካል ፈረሰ ብንል ከፈረሰ በኋላ ያ አካል በህግ ሊጠየቅ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡– ግዙፍነት ያላቸው ቅርሶች ከአሁን ዘመን ኪነ ሕንፃ ጋር ሲነጻጸር በተሠሩበትም ቁስ ይሁን በንድፋቸው ልዩነታቸው እንዴት ይገለጻል?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– አንድ የኪነ ሕንፃ ውጤት በቅርስነት ሊመዘገብ የሚችለው የተለያዩ መስፈርቶችን ማሟላት ሲችል ነው። ከእነዚህም መካከል በተሠራበት ወቅት ዓለም ላይ የነበረው የኪነ ሕንፃ እውቀት ወይም ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ መመልከት ያስፈልጋል። በሃገራችን የነበረው የኪነ ሕንፃ እውቀት ወይም ቴክኖሎጂ ውስን ነበር። ለምሳሌ በወቅቱ የነበሩትን የእኛን አገር ሐውልቶችና ቤተ ክርስትያናት ስንመለከት በዚያን ቴክኖሎጂ ባላደገበት ዘመን በእጅ መሳሪያዎች እንደ መሮና መዶሻ ተጠቅመው የተሠሩ ነበሩ። እንደገና የአብዛኛዎቹ ግንባታ ደግሞ የተለመደው ከታች ወደ ላይ የሚለውን ሳይሆን ከላይ ወደታች ተቃራኒ በሆነ መንገድ መሆኑ ነው። እንዲሁም በጣም ጠንካራ የሆኑ ድንጋዮችን መጠቀማቸውና በጣም ኃይለኛ የሆነን የድንጋይ ዓይነት መብሳት መቻል አስደናቂ ነገር በመሆኑ ነው ሊመዘገቡ የቻሉት። ስለዚህ አብዛኛዎቹ ከዘመናቸው ጋር ሲታዩ እጅግ የሚገርሙ በመሆናቸው ነው በቅርስነት የተመዘገቡት ማለት ይቻላል።
ወደ አሁኑ ዘመን ስንመጣ በዓለም ላይ በየጊዜው የሚመጣ ትውልድ የየራሱን አሻራ እየተወ ያልፋል። እነዛ አሻራዎች ደግሞ በአብዛኛዎቹ የሠሯቸው አካላት ካለፉ በኋላ ነው አስደናቂነታቸው እየተመዘነ ወደ ቅርስነት የሚመጡት። ወደ እኛ አገር ስንመጣ አሁን ባለው ሁኔታ የነበሩትን እድገቶች በቅርስ ዙሪያ ብዙ እያስቀጠልን ነው ብሎ ማለት አያስደፍርም።
አንዳንዴ ታሪካዊ ያልናቸውን ቅርሶቻችንን ሙሉ በሙሉ ሳንረዳቸው ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው እንጂ እነርሱን ሙሉ በሙሉ አጥንተን ስንተነትናቸው ታሪካዊ አሻራነታቸው በደንብ ጎልቶ መውጣት ይችላል። የነበርንበትን የከፍታ ዘመን በሚወክል መልኩ በአሁኑ ሰዓት እያስኬድነው ግን አይደለም። የቅርሶቻችንን ታሪካዊ ዳራ ትተን ግንባታ እያደረግን ያለነው ግን አብሮ መሄድ የማይችል ነገር ነው። ለምሳሌ በግንባታ ሥራ መስተዋትን በማስገባቱ በኩል ያለቅጥ እንጠቀማለን። በሌሎቹ አገሮች መስተዋት የመጠቀማቸው ምክንያት ጨለማ በሚበዛባቸው ወራት ብርሃን ለማግኘት፣ ሞቃታማ የሆኑ ቦታዎች ደግሞ ሙቀቱን መቋቋም እንዲያስችላቸው በማሰብ ነው።
እኛ ግን እንደወረደ መልኩን ብቻ በመውሰድ በማይመች አኳኋን መስታወቱን እንጠቀማለን። ለዚህም በየመንገዱ ስንሄድ አንጸባራቂ ነገሮች ዓይናችንን ሊያጠፉት ነው የሚደርሱት። ውስጥም ገብተን የምንጠቀምባቸው ሕንፃዎች ሙቀቱ አያስቀምጥም። እንደ እነአክሱም፣ ጎንደርና ላሊበላ ዘመን የነበሩ የሕንፃ ግንባታ ዓይነት ሥራ በፍጹም ልናመጣው አልቻልንም። በወቅቱ በእጅ ተሠርቶ ጥገና ራሱ ሳያስፈልጋቸው ለዘመናት የዘለቁ ቅርሶች መሆን የቻሉ ናቸው። አሁን ግን አምስትና አስር ዓመት ሳይቆዩ የሚበላሹ ሕንፃዎችን የሚያሳዩን ብዙ ነገሮችን እየጣልን ስለመምጣታችን ነው። ምክንያቱም ከታሪካችን መማር አልቻልንም ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– የአርኪዮሎጂ ጥናት ሊከናወንባቸው የተገባቸው ቦታዎች ሙሉ ለሙሉ ተለይተዋል ማለት ይቻላል?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– በፍጹም አልተለዩም፤ ተለይተው እንኳ ሊያልቁ ቀርቶ ገና ብዙዎቹ አልተጠኑም። ለምሳሌ አክሱም ታዋቂ የሆነ የአርኪዮሎጂካል ቦታ ነው። ነገር ግን አክሱም ራሱ ምን ያህል በመቶ ተለይቷል ቢባል ብዙ አይደለም ነው የምንለው። እርግጥ ነው በመለየት ደረጃ ተለይቷል፤ ግን ስንለይ እንዴት? በምን መልኩ የሚለው ነገር ብዙ ጥናት የሚጠይቅ ነው። እንዲያውም በዘርፉ ራሱ ያሉን ጥቂት ባለሙያዎች ናቸው። አብዛኛዎቹ ጥናቶች የሚሠሩት በውጭ አገር ዜጎች ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው ትልልቅ ሙያተኞች እየወጡ ያሉት።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የአርኪሎጂካል ቦታዎች ቢኖሩም ሁሉም ተለይተዋል ማለት አይቻልም። በደፈናው ግን አክሱም፣ ለጋ ኦዳ፣ መካከለኛው አዋሽ እያልን የተለያዩ ቦታዎችን ልንጠቅስ እንችላለን። ነገር ግን ጥናት ተደርጎ ሁሉም ተለይተዋል አያስኘንም።
አዲስ ዘመን፡– ስለቅርሶችስ ተገቢ የሆነ መረጃ በተገቢው ሰዓት ማግኘት ይቻላል?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– በአብዛኛው አይቻልም ነው መልሴ፤ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የተጠናቀረ ሰነድ የለንም። ብዙዎቹ ነገሮችን በቀላሉ የምናገኛቸው አይደሉም። በጥቂቱ የተሻለ መረጃ የምናገኘው በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡትን ነው። እነርሱም በዩኔስኮ ስር በመሆናቸው አገር በቀልም ሆኑ የውጭ ባለሙያዎች መደበኛ ጥናቶች አድርገዋል። ነገር ግን ከሌሎቹ አገራት ቅርሶች አንጻር ስናይ ምንም ነገር የለም ማለቱ ነው የሚቀለው።
አዲስ ዘመን፡– የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ማለት ይቻላል? ካልተወጣ ማነቆ የሆነበት ነገር ምንድን ነው?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– ይሄ ከባድ ጥያቄ ነው፤ እንደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሥራውም ኃላፊነቱም ቅርስን በተመለከተ ብዙ ሥራ መሥራትን የሚጠይቅ ነው። ከዚህ አንጻር እየሠራም ነው፤ እየሠራም አይደለም ለማለት ይከብዳል። ነገር ግን ምን ምን ሠርቷል? ምን ምንስ ይቀሩታል? ስንል የተሠሩ ነገሮች አሉ። ብዙ ደግሞ የሚቀሩ ነገሮች አሉ።
የቀረውን በአግባቡ መተግበር ያስችለው ዘንድ ደግሞ መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል። በአገሪቱ ለቅርሶች ድጋፍ አለ ለማለት ይከብዳል። ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ናቸው ብዙውን ጊዜ ድጋፍ የሚያደርጉት። አሁን ስናስተውል መቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ በተለያየ ጊዜ ግድብ ስንገነባ፣ ጦርነት ሲነሳ ሆ ብሎ እንደሚነሳው ሁሉ በተለያየ መንገድ የሚያደርገውን ዓይነት ድጋፍ ለቅርሶች ድጋፍ ማድረግ እንዲችል መንግሥት ቢያበረታታው ብዙ ጥናቶችና የተለያዩ ሥራዎች ሊሠሩ ይችላሉ። ከዚህ አንጻር ስናየው ለቅርስ የሚበጀተው በጀት በራሱ በጣም ትንሽ ነው ማለት ስለሚቻል ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት ባለስልጣኑ ይቸገራል።
አዲስ ዘመን፡– በዘርፉ አሉ የሚባሉ የህግ ማዕቀፎች በአግባቡ እየተተገበሩ ናቸው ማለት ይቻላል?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– በፍጹም አይቻልም፤ ተተግብረዋል ማለት አያስደፍርም። አይደለም በሌሎች ከተሞችና ገጠሮች አካባቢ ያሉትን እንተዋቸውና አዲስ አበባ እንኳ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ተመዝግበው የሚገኙ ቅርሶች ሲፈርሱ ምንም ነገር ሲደረግ አላየንም።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ እንደ አንድ የዘርፉ ባለሙያ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– እንደ ባለሙያ እኔ የምሰጠው ሐሳብ በመጀመሪያ ደረጃ ያሉን ቅርሶች መለየት መቻል አለባቸው። ምን ምን ቅርሶች አሉን የሚለው ነገር መታወቅ አለበት። ያሉን የቅርሶች ብዛት፣ መጠንና ዓይነት እንዲሁም ቅርሶቹ ያሉበትን ሁኔታ ሁሉ ካላወቅን ምንም ማድረግ ስለማንችል ለዚህ መጠነ ሰፊ ጥናት እንዲደረግ አስፈላጊውን በጀት መንግሥት መድቦ እንዲጠና ማደረግ ይኖርበታል። ከተጠኑ በኋላ እንደየችግሮቻቸው እና እንደሚፈልጉት ነገር መፍትሔ መስጠት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– ቅርሶችን በተመለከተ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እየተተገበሩ ናቸው?
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– ኢትዮጵያ የዩኔስኮ አባል በሆነችበት ጊዜ አንዱ መስፈርት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብላ ተግባራዊ ማድረግ መቻሏ ነው። ነገር ግን እሱ ማለት ሁሉም አገሮች እነዚያን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሙሉ ለሙሉ ይተገብራሉ ማለት ተዓማኒነት የሌለው ነው የሚሆነው። ጥረት ይደረጋል። ተግባራዊ ባልሆነበት ጊዜ ደግሞ ራስን ለመከላከል ጥረት ለማድረግ ይሞከራል። ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ ነገሮች ሲሠሩ እናያለን። ለምሳሌ ዓለም አቀፍ ቅርሶች አካባቢ ዓለም አቀፍ ቅርሱን የሚያኮስስ ወይም ደግሞ የበለጠ ጫና የሚፈጥር ነገር ማድረግን አይፈቅድም። ግን አንዳንድ ቦታዎች ሲደረጉ እናያለን።
ጥገናም ሲካሄድ ዓለም አቀፍ ህጎችን ተከትሎ ማስኬድ ሲገባ ካለማወቅና ከባለሙያ እጥረት የተነሳ የተለያዩ ህጎችን የሚጥሱ ነገሮች ሲፈጸሙም ይስተዋላል። ዓለም አቀፍ ህጎችን ማክበር ግዴታ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ እየተተገበረ ነው ማለት አያስደፍርም። ምክንያም ያሉትን ህጎች ሙሉ በሙሉ ለመተግበር የሚያስፈልጉ ሙሉ በሙሉ ግብዓቶች ከባለሙያ፣ ቴክኒክና ፋይናንስ ጀምሮ መሟላት ግድ ይላል።
ስለዚህ እዚህ ላይ መንግሥት ትኩረት ማድረግ አለበት። ምክንያቱም ብዙ አገሮችን ስናይ ባላቸው ቅርስ ኑሯቸውን እስከ መመስረት የደረሱ አሉ። ለአብነት ያህል እነ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ ፈረንሳይ በቅርብ ጊዜ አንድ ታሪካዊ የሆነ ቤተ ክርስትያን ተቃጥሎባት ነበር። ከእሱ የተገኘ ገንዘብ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ነው። እሱ የሚያሳየው ቅርስን ለዓለም በሚገባ ማስተዋወቅና በጥንቃቄ ይዞ ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ እንዲሁም ለጥናትም ክፍት ማድረግ የአንድን አገር ኢኮኖሚ እንደሚያሳድግ ማስተዋል ይቻላል። ቱሪዝምን ስናስበው ጢስ አልባ ኢንዱስትሪ የምንለው በዚሁ ጉዳይ ነው።
በጥቅሉ ቅርሶች የማንነታችን መገለጫዎች ናቸው። ካለፈው ማንነታችን ተነስተን ዛሬን በኩራት እየኖርን ወደፊት ደግሞ እንዴት የበለጠ በኩራት እንደምንኖር የሚረዱን ናቸው። ያለፈው ማንነታችንን በደንብ ስናውቅ የወደፊቱ ብሩህ እንደሚሆን ተስፋ የምናደርግባቸው ናቸው። የአገራችንን ኢኮኖሚ ልናበለጽግባቸው የሚያስችል አንደኛው መንገድ ነው።
ስለዚህ ከዚህ አንጻር ቅርሶችን በየትኛውም ሁኔታ አለመግባባቶች እንኳ ቢፈጠሩ ቅርሶች ላይ ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል። ምክንያቱም ቅርሶች የአንድ ግለሰብ ወይም አካባቢ ወይም አገር ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ማህበረሰብም ጭምር ሀብት ናቸው። ቅርሶች በገንዘብ የማይተመኑና ዋጋ የማይወጣላቸው በመሆናቸው ችግር ቢያጋጥም እንኳ እነርሱን መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
አርክቴክት አርኪዮሎጂስት ታደሰ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013