ሰላማዊት ውቤ
ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ታስገባለች። ለዚሁ ስንዴ ግዢም በየጊዜው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ታወጣለች። መንግስት ወጪውን ለማስቀረት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በስንዴ ምርት ልማት ላይ ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል።ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የምግብ ዘይት ጨምሮ ሌሎችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካትም ጥረት እየተደረገ ነው። በተለይ ከውጭ የሚመጣውን ስንዴ ለመተካት በሶማሌ፣ አፋርና ደቡብ ክልል ላይ የተጀመረው ቆላማ አካባቢዎችን በመስኖ በማልማት ስንዴን በብዛት ማምረት ጅማሮ አበረታች ውጤቶችን እያስገኘ ነው
ከዚሁ ጎን ለጎን በመስኩ የተሰማሩ ባለሀብቶችም አበረታች ስራዎች በመስራት ህዝብና መንግስትን በማገዝ ላይ ናቸው። ከእነዚህ ባለሀብቶች መካከል አንዱ በሰፋፊ እርሻ ሥራ የተሰማሩት አቶ ሀብታሙ ሲላ ናቸው። ባለሀብቱ ከጥገኝነት ለመላቀቅ በመጀመሪያ ደረጃ በእርሻ ስራ ላይ ቀጥሎ በኢንዱስትሪው እንዲሁም ደግሞ ቴክኖሎጂ ላይ መሰራት እንዳለበት ይታመናል።
ከሀገራችን የቆዳ ስፋት ጋር ስትነጻፀር የበሬ ግንባር የሚያክል የእርሻ መሬት ባለቤት የሆነችው እስራኤል ከእርሻ ብቻ ከመቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ ውጭ መላኳ ሀገራችን ልትቀስመው የሚገባ ምርጥ ተሞክሮ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በቆዳ ስፋት የእስራኤልን 30 እጥፍ የምትሆነው ኢትዮጵያ የምትልከው ሦስት ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ ለውጥ እንደሚያሻውም ያሳስባሉ። ይሄን ታሪክ ለመቀየር ብዙ በምርምር የታገዙ ምርታማ የሆኑ አዝርቶችን ማብዛት ቀዳሚውና አዋጭ መንገድ መሆኑን ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ በውሃና በለም መሬት የታደለች ናት። ጉልበት ያለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይልም አላት። ይህ ሁሉ ተዳምሮ ለስኬት ያበቃታል። ስለዚህ ድህነትንና ረሀብን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የእርሻ ልማት አብዮት መካሄድ አለበት ይላሉ
አቶ ሀብታሙ እንደሚሉት ስንዴን ጨምሮ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾና ጥጥ በማምረት ሥራ ላይ የተሰማረው ኩባንያቸው ከአዲስ አበባ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደቡብ ኦሞ ውስጥ ከትሟል። ኩባንያቸው ከሚያመርተው ምርት ሰሊጥን እሴት ሳይታከልበት ከ300 እስከ 400 ኩንታል ወደ ውጪ ይልካል። ይሁን እንጂ በቀጣይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብም በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። በተለይም ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ የዘይት መጭመቂያ አቋቁሞ የዘይት ምርት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ለማቅረብ ነው ዕቅዱ።የእርሻ ውጤቶችን ወደ ኢንዱስትሪ በማስገባት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ሀገርን ከወጪ ለመታደግ ነው ፍላጎቱ።
ኩባንያው ከእርሻው 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የስኳር ፋብሪካ ሞላሰስ በመጠቀም ከእርሻ ተረፈ ምርቱ ጋር በመቀላቀል ለከብቶች መኖ እንዲውል እየሰራ ይገኛል።ይህ ደግሞ ከብት በማድለብ ንግድ ላይ የተሰማሩትን ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። የደቡብ ኦሞ ወንዝንና ኢትዮጵያ 35 በመቶ የምትጋራውን ቱርካና ሐይቅን ተጠቅሞ አሣ ማርባትም የኩባንያው የወደፊት ዕቅድ መሆኑን አቶ ሐብታሙ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ሀብታሙ ማብራሪያ በእርሻ ሥራዎች በተለይም በስንዴ ምርት ላይ አንደ ሀገር የሚሰራው አንድም በምግብ ራስን የመቻል፤ ሁለትም የውጭ ምንዛሪ ወጭን የማዳን ጥንድ ተልኮዎች አሉት። ተልዕኮዎቹ መንግስት እንደ አቅጣጫ ያስቀመጣቸው እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው የሚገኙ ናቸው። ኩባንያቸው ይሄን ተልዕኮ መሰረት አድርጎ በስንዴ ልማት ከተሰማራ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል። መንግስትም ያስቀመጣቸውን ሁለቱን አቅጣጫዎች ተከትሎ ስንዴን በመስኖ ማልማት ከጀመረ ሁለት ዓመት መሆኑን ያስታውሳሉ። እሳቸው እንደ ግለሰብ በሁለት ዓመት ውስጥ በስድስት ሺህ ሄክታር ያለሙት ስንዴ መንግስት እንደ ሀገር ያስቀመጠውን አቅጣጫ ዳር ለማድረስ የሚያግዝ መሆኑን ያምናሉ።
ዘመናዊ ግብርና የገጠሩን አርሶ አደር፣ አርብቶ አደርና አጠቃላይ የገጠሩን ሕብረተሰብ ሕይወት ከሥር መሰረቱ ለመለወጥ ዓይነተኛ መሣሪያም ነው ባይ ናቸው። አሁን ላይ መንግስት ይሄን ሀሳባቸውንና ተግባራቸውን ደግፎላቸው አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ፈቃዱን የሰጣቸው መሆኑን አልሸሸጉም። የስንዴ እርሻ ልማታቸው መንግስት ዓላማውን ለማሳካት ከመረጣቸው ኩባንያዎች አንዱ ለመሆንም በቅቷል። በአንድ ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የስንዴ እርሻ ልማቱን አብሯቸው ለማከናወንም ፍላጎት አሳይቷቸዋል።
መንግስት ከባለሀብቱ ጋር ተቀናጅቶ መሥራቱ ባለሀብቱ የበለጠ ተጠናክሮ ምርታማነቱን እንዲጨምር ያደርገዋል። መንግሥትም የያዘውን ዕቅድ ከግብ እንዲያደርስ ያግዛል። በዚህ መልኩ የተጠናከረው የበጋ መሥኖ ልማት ባለፈው ዓመት የተገኘው 54 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ማሳያ ነው። በያዝነው ዓመት በ200 ሺህ ሄክታር ማሣ ላይ ከሚካሄደው የስንዴ የመስኖ እርሻ ልማት የሚጠበቀውን 60 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘትም ያስችላል።ባለሀብቱ በአሁኑ ወቅት የስንዴ ልማቱን እያካሄዱ ካሉበት ከስድስት ሺህ ሄክታር ማሣ በተጨማሪ ሰባት ሺህ ሄክታር ማሣ ጨምረው ለማልማትና የእርሻ ሥራውን ለማስፋፋት ጥያቄ አቅርበዋል።
አቶ ሀብታሙ እርሻው የሀገሪቱን ችግር በመፍታት ትልቅ አስተዋጾ ያመጣል ብለው በማመናቸው ነው በስፋት ለመሥራት ፍላጎት ያሳዩት። መንግስት በስንዴ ልማቱ የያዘውን ፖሊሲና የሚከተለውን አቅጣጫ ይደግፋሉ። ‹‹የሚያሰራ ፖሊሲ ነው›› ሲሉም አድናቆታቸውን ከመግለጽ አላለፉም። እሳቸውን ጨምሮ ባለ ሀብቱ በስንዴው ልማት ዘርፍ መሰማራቱ ሀገራዊ ጥቅሙን ከፍ ያደርገዋል። በስንዴ ልማት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ልማት ላይ ተሳትፎው መጎልበት እንዳለበት ያምናሉ። የመንግስትና የግል ባለሀብቱ ጥምረት ሀገርን በመለወጥ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ያምናሉ። ይሄን ለማሳካትም ጠንክረው በመስራት ስኬታማ ለመሆን ችለዋል። ቀጣይ እቅዶቻቸውን ወደ ተግባር ለውጠውም ለሀገር የሚያኮራ ለራሳቸውም የሚያረካ ስራ እንደሚሰሩ ያምናሉ። ምክንያቱን ሲያብራሩም ያለ እርሻ በሕዝቡ ሕይወትም ሆነ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የተጨበጠ ለውጥ ማምጣት አይቻልም። ህዝቡ በምግብ ሰብል ራሱን እንዲችል ለማድረግ ኢትዮጵያ ሰፋፊ የእርሻ ማሣ እያላት አልምታ ህዝቦችዋን መመገብ ባለመቻሏ የከፋ ድህነት እንዲሰራፋ አድርጓል። ከውጭ የዕርዳታ ስንዴ ጠባቂም ለመሆን በቅታለች። ይህ ደግሞ በራስዋ የማትተማመንና ለጋሾች እንደፈለጉ የሚያሽከረክሯት ሀገር እንድትሆን መንገድ ከፍቷል።በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዋ ላይ ጣልቃ በመግባት ጫና ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል።
ለአብነት የአውሮፓ ሕብረት በዓመት 800 ሚሊዮን ዶላር በብድርም በድጋፍም መስጠቱን ያስታውሳሉ ባለሀብቱ አቶ ሀብታሙ። ይሁንና ይሄን ገንዘብ ሀገሪቱ እኛ ያልነውን እንድታከናውን ፈቃደኛ ከሆናችሁና ከፈጸማችሁ ታገኛላችሁ ካልሆነ ግን ይያዛል ። በሚል መደራደሪያ ነው የሚያደርጉት። እንዲህ አይነት አሳዛኝ ሁኔታ በእርዳታ ሰጪዎቻችን አለ።ይሄንን መስበር የሚቻለው ታዲያ በራሳችን የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ ስንችል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ጠንክሮ መስራት ለድርድር የሚቀርብ አይሆንም።
እርሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ባለሀብቶች ሀገራችን ለዘመናት ሲለጠፍባት የነበረውን የረሀብ፣ የድህነትና የጦርነት ስም ለመፋቅ ከመንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆነው በእርሻው ዘርፍ መሥራት አለባቸው። ባለሀብት በመሆን ብቻ ሳይሆን ባለጸጋ ሆነው ሀብት ንብረታቸውን ከቅንነት እና ከሀቀኝነት ጋር ሙሉ ለሙሉ በእርሻ ላይ በመሥራቱ ሀገሪቱንና ህዝቡን ከተረጂነት ማላቀቅ ነው። አሁን እየደገፉን ላሉት ሁሉ መትረፍም ያስችላል። ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የለገሳትን ሀብት መጠቀም ይኖርባታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚህ ሀብት በመጠቀም ሀገሪቱን ለመለወጥ ያላቸው ራዕይም እጅግ የሚበረታታና ምቹ ነው። እንደ አቶ ሀብታሙ ‹‹ምቹነቱ የኢንዱስትሪው መሰረት መሆን ያለበት እርሻ ነው ›› የሚል መርህ መከተሉ ነው።በእርግጥም ከእርሻ ተነስቶ ነው ወደ ኢንዱስትሪው መኬድ አለበት። እርሻ ላይ በደንብ ካልተሰራ ኢንዱስትሪ ማቋቋም ብቻ ዋጋ የለውም። ምክንያቱም ኢንዱስትሪው የሚመገበውን ግብዓት ማግኘት የሚቻለው ከእርሻ ነው።
አቶ ሀብታሙ መፈታት አለባቸው ያሏቸውንም ችግሮችም ጠቁመዋል። እርሳቸው እንዳሉት መንግስት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ሆኖ መሥራት አለበት። የደህንነትና የፋይናንስ ችግሮችን ከታች ከቀበሌ እስከ ላይኛው መዋቅር መቅረፍ ይገባል። በተጨማሪም ሁሉም ዜጋ ሀገሩን ከድህነት ለማውጣት ድርሻ ሲወጣ የሚፈለገው ውጤት ላይ መድረስ ይቻላል።
በግላቸው ከነልጅ ልጆቻቸው ለብዙ ዓመት የሚበቃ ጥሪት አላቸው። ሆኖም ይሄን ማድረግ ችያለሁ ብለው እጃቸውን በማጣጠፍ ቁጭ አላሉም። በእርሻው ዘርፍ የተሰማሩት የገጠሩን አካባቢን ሕብረተሰብም ሀገርንም ለመጥቀም ነው። ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ይሄን መተግበር ካስቻሏቸው ዋነኞቹ ሞተሮቻቸው ናቸው። ዘወትር ከባህር ማዶ ሆነው ‹‹ሀገርና ሕዝብን ተጠቃሚ ካላደረክ ሰራህ አንልህም›› ይሏቸዋል። ከስንዴውም ሆነ ከአጠቃላይ ከእርሻውና ከንግድ እንቅስቃሴያቸው እንደ ሀገር ለውጥ የሚያመጣ ተጨባጭ ውጤትና ዕድገት እንደሚፈልጉ ሰርክ ይገልፁላቸዋል። በዓመት ከፍተኛ ግብር ይከፍላሉ። ለብዙ ሰው የሥራ ዕድል ፈጥረውና የድህነትን ስም ፍቀው ማለፍ እንጂ ገንዘብ መሰብሰብ እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸውና ልጆቻቸው አይፈልጉም። እስካሁን ባለው እንቅስቃሲያቸው ለሶስት ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ይሄን ዕድል በእርሻው መስክ ለማስፋት የሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋጾ ያስፈልጋል። አንድ ነገር መጣል በራሱ ትልቅ አስተዋጾ ነው። የባለቤታቸውና የልጆቻቸው ሀሳብም ይሄው ነው። ኢትዮጵያ እንዲህ አጋር የሚሆኗት ዜጎች እንደሚያስፈልጓት ከባለሀብቱ ጋር በነበረን ቆይታ ለመገንዘብ ችለናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013