
ብርሃን ፈይሳ
በኢትዮጵያ የስፖርት ክለቦች ምስረታ፣ የተለያዩ ስፖርቶችን በማስፋፋት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሃገርን የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን በማፍራት የጦሩን ያህል ታሪክ ያስመዘገበ የለም። በዚህ ወቅት በርካቶቹ ክለቦች ቢፈርሱም ጣሊያን ከሃገር በወጣ ማግስት በ1938 ዓ.ም የተመሰረተው የመከላከያ ስፖርት ክለብ ግን አሁንም ድረስ በውጤታማነቱ እንደጸና ይገኛል።
ከጀግናው አበበ ቢቂላ የሚጀምረው የክለቡ አትሌቶች የድል ታሪክ አሁንም ድረስ ቀጥሎ ሌትናት ኮሎኔል ኢማና መርጋ፣ ሻለቃ አሊ አብዶሽ፣ ሻምበል ሱሌ ኡቱራ፣ ሻምበል ድሪባ ጋሪ፣ ሃምሳ አለቃ አልማዝ አያና፣ አምሳ አለቃ ሙክታር እድሪስ፣ ሃምሳ አለቃ ኢብራሂም ጄይላን፣ አስር አለቃ ጌታነህ ሞላ እና አስር አለቃ ሃዊ ፈይሳን የመሳሰሉ አትሌቶች እያፈራ ይገኛል። ከወራት በኋላ ለሚካሄደው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክም 11 አትሌቶችንና አንድ አሰልጣኝን በማስመረጥ ከክለብ አልፎ የሃገርን ስም ለማስጠራት በዝግጅት ላይም ነው።
ይህ ክለብ በአትሌቲክስ ብቻም ሳይሆን እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ እና እጅ ኳስ ስፖርቶችም ተወዳዳሪ ነው። በሃገር ውስጥ ውድድሮች የተሻለ አቋም ከሚያሳዩት መካከል ተጠቃሽ ሲሆን፤ በአንጻራዊነት በሃገሪቷ ካሉ የስፖርት ክለቦችም የተሟላ ካምፕና የተደራጀ የስፖርት ስልጠና ቁሳቁሶች ያሉት ክለብም ነው። ይሁን እንጂ ክለቡ አሁን ካለበት ሁኔታ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ዘመናዊ አሰራሮችን መተግበር አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድም እንቅስቃሴ መጀመሩን የመከላከያ ስፖርት ክለብ ዳሬክተር ኮሎኔል ደረጀ መንግሥቱ ይጠቁማሉ።
ክለቡ ቀድሞ ምን ነበር አሁንስ ምን ላይ ይገኛል በሚለው ላይ እየተሰራ መሆኑን የሚጠቅሱት ዳይሬክተሩ፤ ከነበረው ጥንካሬ አሁን ያለበት ጉድለት ምንድነው የሚለውን በመለየት እንደ ተቋምም ሆነ እንደ ክለብ ለማስተካከል እቅድ መያዙን ይገልጻሉ። የመከላከያ ስፖርት ክለብን ለማዘመንና ውጤታማ ለማድረግ ሁሉንም ስፖርቶች ሊያማክል የሚችል የስፖርት ሜዳ መገንባትም ከተግባራቱ መካከል ቀዳሚው ነው። ይኸውም በተቋሙም ሆነ በክለቡ የስራ አመራር ቦርድ ትኩረት ተሰጥቶት የሜዳ ማስፋፋትና የዲዛይን ስራው እየተሰራ ሲሆን፤ የሚያስፈልገው በጀትም ታውቆ ወደ ስራ ለመግባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ያረጋግጣሉ።
በውድድሮች ላይ ተፎካካሪ ለመሆንና ውጤት ለማስመዝገብ ብቁ አሰልጣኞችን ማፍራት አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው። ከወንድ እና ሴት የእግር ኳስ ቡድኑ ውጪ ያሉት የክለቡ ተወዳዳሪዎችና አሰልጣኞቻቸው የሰራዊቱ አባላት ናቸው። በመሆኑም በሲቪል የሚመሩት ቡድኖች የተሻሉ አሰልጣኞች እንዲኖራቸውና በተቋሙ አባላት የሚመሩ ቡድኖች አሰልጣኞችም ብቃታቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም ተወዳዳሪና ተፎካካሪ እንዲሆኑ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ የአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኞችን ዓለም አቀፍ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ነው።
ከዚህ ቀደም ከክለቡ አቅም ውጪ በሆኑ አካላት የመጠቀም ችግር እንደነበረም ዳሬክተሩ ይጠቁማሉ። ለአብነት ያህልም አሰልጣኞች ባላቸው አቅም ከሚሰጡት ስልጠና ላይ ተጨማሪ እውቀት እንዲያገኙ አለማድረግ በስፋት የሚስተዋል ችግር ነበረ። አሁን ግን ከክለቡ አቅም በላይ የሆኑትን ሊደግፉ የሚችሉ ስልጠናዎችን ከፌዴሬሽኖች ጋር በትብብር መስጠት ተጀምሯል። ከዚህ ባሻገር ግን አጫጭር ስልጠናዎችን ከፌዴሬሽኑ ጋር በመሆን በተደጋጋሚ መሰጠት ነው። ሌላው በታዋቂ ስፖርተኞችና አሰልጣኞች የሥነ-አዕምሮ ድጋፍ እንዲያደርጉ ወደ ክለቡ በመጋበዝ የሚሰራ ይሆናል። በዚህም አስፈላጊ የሆኑ መልዕክቶችን ማስተላለፍ ተችሏል።
በኢፌዴሪ ሃገር መከላከያ የኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተርና የመከላከያ ስፖርት ክለብ ሥራ አመራር ቦርድ ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ተሰማ፤ የክለቡ አመራሮች ክለቡን ለማጠናከር በቅርበት እየሰሩና በስነ-ምግባር የታነጸ ስፖርተኛን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ክለቡ አሁን ካለበት በተሻለ ሁኔታ እንዲገኝ ለማድረግ እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል አንዱ የክለቡን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ችግር ማቃለል ነው። በዚህም ክለቡ የራሱ የተሟላ ሜዳ እንዲኖረው የሃገር መከላከያ ሚኒስትርን በማስፈቀድ ዲዛይን እየተሰራለት ይገኛል። የክለቡ አባላት በአንድ ስፍራ ሆነው ልምምዳቸውን እንዲያደርጉ ካምፕ እንደተሰራው ሁሉ ሁሉንም ስፖርቶች ያጠቃለለ የስፖርት ሜዳ በአንድ ጊቢ ውስጥ እንዲኖር ፕሮጀክት በመንደፍ እየተሰራ ነው። ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሳካ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ሜጀር ጀነራል መሃመድ ተሰማ ይጠቁማሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 01/2013