ወርቁ ማሩ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የቆየውን ህገወጥነት መልክ ለማስያዝ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከነዚህም መካከል በተለይ በመሬት ወረራና ባለቤት አልባ ህንጻዎች እንዲሁም በኮንደሚኒየምና የቀበሌ ቤቶች ዙርያ በቅርቡ ያደረገው የማጣራት ስራ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ትልቅ መሰረት የሚጥል እንደሆነ ይታመናል።
ጥናቱ በሶስት ተከፍሎ የተካሄደ ። ከነዚህም ውስጥ አንዱ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የተካሄደውና በጋራ መኖርያ እና በቀበሌ ቤቶች ላይ ያተኮረው ተጠቃሽ ነው። በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የተጀመረው ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ለዚህም በሁለት ዙሮች ከአንድ ሚሊየን በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ተመዝግበው እጣ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። እስካሁን ባለው ሂደትም ከ171 ሺ በላይ ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል። ያም ሆኖ ግን በነዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዙሪያ በነዋሪዎች የሚነሱ በርካታ ቅሬታዎች አሉ።
ይህን ታሳቢ በማድረግም የኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ከከተማ አስተዳደሩ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ጥናት አካሂዶ ውጤቱን ይፋ አድርጓል። እኛም አጠቃላይ የጥናቱ ሂደት ምን እንደሚመስልና ከዚህ ጋር ተያይዞ በጥናት ወቅት ቡድኑ የታዘባቸው ነባራዊ እውነታዎች እንዲሁም የመፍትሄ ሃሳቦችን አስመልክተን ከጥናት ቡድን መሪው ዶክተር ቱሉ ቶላ ጋር ቃለምልልስ አድርገናል፤ እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፡– በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተደረገው የህገወጥ ተግባራትን ለማጣራት ሂደት መቼ ተጀምሮ መቼ ተጠናቀቀ፤ ጥናቱስ ምን ምን ጉዳዮችን ያካተተ ነው፤ ሂደቱስ ምን ይመስል ነበር?
ዶክተር ቱሉ፡– ጥናቱ አራት ወራት የፈጀ ነው። ክብርት ከንቲባዋ ገለልተኛ በሆነ መንገድ ዩኒቨርሲቲያችን ይህንን ጥናት እንዲያካሂድ መጠየቃቸውን ተከትሎ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን የኮሚቴው አባላትም ሃሳቡን መነሻ በማድረግ የመነሻ ሃሳብ ካዘጋጀንና ካስተቸን በኋላ ወደ ስራ ተገብቷል። በጥናቱም ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። በጥናቱ ፒኤችዲ እና ማስተርስ ያላቸው እና ተባባሪና ረዳት ፕሮፌሰሮች የተሳተፉበት ነው። ከዚህ ውጭ ግን ጥናቱን የሚያግዙ በርካታ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
እንደሚታወቀው ጥናቱ ባለፉት 15 አመታት ሲከናወኑ የነበሩ ህገወጥ ተግባራትን የሚዳስስ በመሆኑ በአጠቃላይ ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ነው። ከዚህ ባሻገር ትልቅ የሃገሪቱ ሃብት የፈሰሰበት ስራ ነው። እንዳየነው ስራውን በሀላፊነት የያዘው የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ላለፉት 15 አመታት ኦዲት አልተደረገም። ይህም ማለት ስራውን የሚቆጣጠር አካል የለም ማለት ነው።
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የተወሰኑ ህንጻዎች ጠፍተዋል ተብሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ ሃሳብ ከቀረበ በኋላ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች ጉዳዩን ለማጣራት በጋራ ኦዲት ማድረግ ጀምረው ነበር። ነገር ግን ስራው አስቸጋሪ ስለነበረ እስካሁን አልተጠናቀቀም።
እኛ ወደስራው ስንገባ ብዙ ምንጮችን መጠቀም ነበረብን። በዚህ መሰረት በመጀመሪያ ወደስራ ሲገባ ከ1996 ጀምሮ ተሰርተው ለተጠቃሚዎች የተላለፉት ቤቶች /የነዋሪውን እና የቤቶቹን ዝርዝር/ በሙሉ የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲሰጠን አድርገናል።
ቤት ሲተላለፍ በዋናነት በሶስት መንገድ ነበር። አንደኛው በእጣ፣ ሁለተኛ በልዩ ውሳኔ ሶስተኛ ደግሞ በጨረታ። ልዩ ውሳኔ ውስጥ በርካታ ጉዳዮች አሉ። አመራር አለ፤ አርሶአደር፣ የልማት ተነሺ፣ የመምህራን ማበረታቻ፣ ወዘተ ሁሉ በዚህ ውስጥ ነው። በዚህ መልክ ነው ቤት የተላለፈው። በዚሁ መሰረት እኛም በቅድሚያ ምን ያህል ቤቶች በልዩ ውሳኔ ተላለፉ፤ምን ያህል በእጣ፣ ምን ያህል በጨረታ የሚለው መለየት አንዱ ስራችን ነበር።
እሱን ከጨረስን በኋላ ወደመስክ ነው የወጣነው። በዚህ መሰረት አዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ከአንደኛ እስከ 12ኛ ዙር ድረስ ያስተላለፋቸው ቤቶች በሙሉ ነው በጥናቱ ውስጥ አስገብተን የሰራነው። በዚህም ከ10/90 እና 20/80 በተጨማሪ 40/60ንም ያካተተ ነው።
ይህም ሲሰራ በቅድሚያ ለነዋሪዎች መረጃው እንዲሰጣቸው ተደርጓል። ይህም በማህበራት አማካኝነት ፣በየህንጻው እንዲለጠፍና መረጃ ሰብሳቢዎችም እየዞሩ እንዲነግሩ በማድረግ ነው መረጃው እንዲኖራቸው ያደረግነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግም ወደ አምስት መረጃዎች እንዲሰጡን ነው ያደረግነው።
አንድ ሰው በማንኛውም መንገድ ቤት ሲደርሰው ከቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ውል ይፈራረማል፤ ከዚያ ወደባንክ ይሄዳል፤ ከዚያ ክፍያ ይቀጥላል፤ የቀበሌ መታወቂያ መስጠት ያስፈልጋል፣ ከባንክ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እግድ ስለመኖሩም ጭምር የማጣራት ስራ ይሰራል። እነዚህን መረጃዎች ካሰባሰብን በኋላ ወደ ኮምፒውተር አስገባን። እንግዲህ 171 ሺህ ቤቶችን መረጃ ወደኮምፒውተር መቀየር በጣም ከባድ ስራ ነው።
ከቤቶች የመጣው ዳታ ወደኮምፒውተር የገባበት እና እኛ ያስገባንበት ፎርማት የተለያየ ነበር። ያን የማመሳሰል ስራ ደግሞ በራሱ ሌላ ከባድ ስራ ነበር። ከዚያ ቀጣዩ ስራ ማንኛውም ሰው ቤቱን ገዛም፣ ደረሰውም በቀጣይ ወደባንክ መሄድ ስላለበት ህጋዊነቱ ባንክ ጋር መኖር አለበት ማለት ነው። በዚህ መሰረት በባንክ በቤት ዙሪያ ሁሉንም የተመዘገበውንም፣ ከፍሎ የጨረሰውንም በሙሉ መረጃ ተቀበልን። ይህም በሁሉም በ10/90፣ በ20/80 እና በ40/60 ያት ቤቶች ያካተተ ነው።
እዚህ ጋ ያጋጠመን ሌላው ትልቅ ስራ የባንክ ሰነዱ ያለው በእግሊዝኛ ነው። ቀደም ሲል ከቤቶች ያገኘነው መረጃና እኛም ኢንኮድ ያደረግነው ደግሞ በአማርኛ ነው። ስለዚህ እነዚህን ማናበብ አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን ወደመስራት ገባን። በዚህ መሰረት እኛ በአማርኛ የነበረውን መረጃ ወደ እንግሊዝኛ ቀየርን። የቋንቋ ባለሙያዎች በዋናነት በዚህ ላይ ተሳትፈዋል። ከዚያ ሁለቱን ሰነዶች አናበብን።
አንድ ሰው መስክ ላይ ቤት ደርሶኛል ካለ ባንክ ላይ ስሙ መኖር አለበት። በስም እንኳን ባይገኝ የቤት መገለጫ በሚል ያስቀመጥነው አለ። ይህም ለምሳሌ አንድ ቤት ቦሌ ከሆነ ያለው ቦሌ አልተቀየረም፤ ወረዳውም እዚያው ነው ያለው። ሳይቱም እዚያው ነው። ብሎክ ቁጥርም በተመሳሳይ፣ ከዚያ ፍሎር፣ የክፍል ቁጥር እዚያው ነው ያሉት። ከዚያ በዚህ መሰረት እያንዳንዱን ሰነድ በዚህ መሰረት አናበብን። የሚናበቡትን ለብቻ፣ የማይናበቡትን ለብቻ አድርገን ህጋዊነቱን አረጋገጥን።
ቀጥሎ ደግሞ ወደባንክ ነው የሄድነው። አንድ ሰው ቤቱ የኔ ነው ካለ ከመስክ የመጣው መረጃ ባንክ ውስጥ መገኘት አለበት። ስለዚህ ከቤቶች ያመጣነውን መረጃ ባንክ ውስጥ ካለው ጋር አናበብን። ባንክ ውስጥ የተገኙትንና ያልተገኙትን ለየን። ከዚያ ማንም ሰው እጣው ከደረሰው ማድረግ ያለበት እጣው ወጥቶ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ መታተም አለበት። ይህንንም መነሻ በማድረግ እዚያ ውስጥ መረጃዎችን ፈለግን። ይህንም መነሻ በማድረግ ህጋዊና ህጋዊ ያልሆነ በማለት ለየን። እንግዲህ አጠቃላይ ሂደቱ ይህ ነው። አድካሚው ስራ መረጃዎችን ማናበቡ፣ መተርጎሙ፣ ከመስክ ማምጣቱ፣ ኤዲት ማድረጉ፣ ወደሶፍት ኮፒ መቀየሩ ወዘተ ነው። በዚህ ስራ ላይ ከከንቲባ ጽህፈት ቤት እስከ ወረዳ ድረስ ያለው መዋቅር ተሳታፊ ነበር። ይህ ባይሆን ስራውን መስራት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ የመረጃ አሰባሰብ ሂደታችሁ ምን ይመስል እንደነበር ቢጠቅሱልን?
ዶክተር ቱሉ፡– አጠቃላይ በዚህ ስራ ላይ ከ3ሺ500 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል። በመረጃ አሰባሰብ ሂደቱም በየክፍለ ከተማው ትምህርታቸውን በዲግሪ፣ ማስተርስ እና ዲፕሎማ ጨርሰው የተቀመጡ ወጣቶችን አሰልጥነን አሳትፈናል። ከነዚህ ጋርም የክፍለ ከተማና የወረዳ ሱፐርቫይዘሮች አሉ። ከዚህ ባሻገር ስራው ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ሃይሎች በመኖራቸው የፀጥታ አካላት ተሳታፊ ነበሩ። ያም ሆኖ ግን በስራው ወቅት የተደበደቡ፣ የተባረሩ እና የታሰሩ ነበሩ።
አዲስ ዘመን፡–ጥናቱ ሙሉ ለሙሉ ሁሉንም ያካተተ ነው ወይስ ናሙና ነው?
ዶክተር ቱሉ፡– የኮንዶሚኒየም ቤት ከ1996 ጀምሮ የተገነባና ለነዋሪዎች የተላለፈ እንዲሁም ያልተላለፈን ጭምር ያካተት ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ቤት በጥናቱ ተካቷል። ስለዚህ ቆጠራ ነው ያደረግነው ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– በባለሙያ ደረጃ የተሳተፈው ምን ያህል ነው?
ዶክተር ቱሉ፡– በአጠቃላይ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ጥናቱን የመራነው አስር ነን። በቀበሌ ቤቶች ደግሞ ስድስት ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– ኮሚቴው የማጥራት ስራውን ሲያከናውን ምን ያህል ገለልተኛ ሆኖ ነው፤ ከዚህ ውጭ የመንግስት አካላትና በየደረጃው የህብረተሰቡ ትብብርስ ምን ይመስል ነበር?
ዶክተር ቱሉ፡– ስራው ራሱ ወደዚህ የመጣው ገለልተኛ ስለሆንን ነው። ምክንያቱም ይህ የትምህርት ተቋም ነው። እዚህ ያለው ባለሙያ ነው። ከኔ በታች ያለውም ባለሙያ ነው። ያም ሆኖ ግን አስተዳደሩ ድጋፍ ባያደርግልን ኖሮ ስራውን አንጨርሰውም ነበር። በተለይ ክብርት ከንቲባዋ ለስራው የሰጡት ትኩረት እና የተከታተሉበት መንገድ ለስራው ስኬታማነት ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። ለዚህም በክፍለከተማና በወረዳ ላይ የማይተባበሩና የሚያስቸግሩ ሃላፊዎችን ሪፖርት ስናደርግ ከሃላፊነታቸው እስከማንሳት የሄዱበት ሁኔታ ማሳያ ነው። ስለዚህ ስራችንን እንድናከናውን ድጋፍ እንጂ ጣልቃገብት ፈጽሞ አልነበረም፤ የሚታሰብ አልነበረም።
ክብርት ከንቲባዋ፤ ሪፖርት ካቀረብንላቸው በኋላ ጉዳዩን ሪፖርት ከማድረጋቸው በፊት እያንዳንዷን ነገር የሚጠይቁበትና የሚገመግሙበት ሁኔታ ነበር። ተነሳሽነታው፣ ቁርጠኝታቸው፣ ለስራው ያላቸው ተነሳሽነትና ሙያዊ ክህሎታቸው ጭምር በጣም የገረመኝ ነገር ነው። እንደባለሙያም በስራው ላይ ተስፋ እንዳደርግ አድርጎኛል። ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያሉ ሃላፊዎችም ሁሉ ለዚህ ተባባሪ ነበሩ። ያም ሆኖ ግን የችግሩ አካል የሆነ ሰው እንቅፋት መፍጠሩ ስለማይቀር በዚህ ደረጃ ችግር ለመፍጠር የሚጥሩ ነበሩ። ነገር ግን ከላይ ከከንቲባዋ ጀምሮ ከፍተኛ ሃላፊዎች ቁርጠኛ ስለነበሩ ችግሩን በቀላሉ መሻገር ችለናል።
ህዝቡን በተመለከተ ሁለት አይነት አመለካከት ነው የነበረው። በአንድ በኩል ተጠቃሚ አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተጎጂ አለ። ስለዚህ ተጎጂው በጣም ደስ ብሎት፣ ይህ ጉዳይ በመጠናቀቁ ደስተኛ ነው። ከችግሩ ጋር ግንኙነት ያለው ደግሞ ሌላ ነገር ማውራቱ አይቀርም። ቅድም እንዳልኩት መታሰሩ፣ መባረሩ፣ መደብደቡ የመጣው በዚህ የተነሳ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ግን ህዝቡ በጣም ደስተኛ ነበር። በስራው ወቅት በአካባቢው ብዙ ጊዜ የቆዩ ነዋሪዎችና የቤት ማህበራት በተዘዋዋሪ እንዲሳተፉ ያደረግንበት ሁኔታ ነበር። ስለዚህ በነበረው ሂደት ላይ ብዙ ድጋፍ ነበር።
አዲስ ዘመን፡– መረጃዎችን የመደበቅና የማሳሳት ሂደቶችስ ምን ያህል ስፋት ነበራቸው?
ዶክተር ቱሉ፡– አይችሉም። አንዳንድ ቦታ ላይ ይቁም ለማለት ይሞከሩ ነበሩ። ነገር ግን ስራው በቀጥታ በከንቲባ ጽህፈት ቤት የሚመራ በመሆኑና በክፍለከተማና በወረዳ ደረጃ ባለ መዋቅር የሚሰራ በመሆኑ በፍጹም ሊያፈናፍናቸው አልቻለም። ችግር መኖሩን ሪፖርት ስናደርግ ከንቲባዋ ወዲያውኑ ማታ በቨርቹዋል ከካቢኔዎቻው ጋር ውይይት አድርገው ጠዋት ጉዳዩ የሚፈታበት ሂደት ነበር የነበረው። በዚህ ሂደት ትልቁ አወንታዊ ጉዳይ ደግሞ ክብርት ከንቲባዋ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ የአመራር ለውጥ በማድረጋቸው ከጉዳዩ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሃላፊ አልነበረም። ስለዚህ ስራው የተሰራው ከተለወጠ አመራር ጋር በመሆኑ ንክኪ አልነበረውም። ቲሙም ጠንካራ ነበር። ታች ድረስ ወርዶ ይከታተል ነበር።
አዲስ ዘመን፦ ባለቤት አልባ ህንፃዎችም ተገኝተዋል፤ ይህ ማለት ምን ማለት ነው?
ዶክተር ቱሉ፡- ባለቤት አልባ ህንጻዎቹ በከንቲባ ጽህፈት ቤት በተሰራው ስራ ውስጥ የተገኘ ነው። በኛ በኩል የተገኙት በግዢ፣ በእጣ፣ በልዩ ውሳኔ፣ በልማት ተነሺ፣ በጨረታ፣ የተላለፈበት መንገድ ያልታወቀ፣ መረጃ ያላቀረቡ፣ ዝግ የሆነ ባዶ ቤትና ሰብረው የገቡ በሚል የተለየ ነው ።
ዝግ የሆነ ሲባል ደግሞ ስንሄድ ዝግ የሆነ ማለት አይደለም። ነገር ግን እስከ 11 አመት ዝግ ሆነው የቆዩ ቤቶች አሉ። ሰው ቤት አጥቶ በሚቸገርበት ከተማ ውስጥ በሃገር ሃብት ተሰርተው ይህን ያህል ጊዜ የተቀመጡ ቤቶች መኖር ማለት ከባድ ነው። ባዶ ማለት ደግሞ ለምን እንዳልተላለፈ የማይታወቅ፤ ነገር ግን ሰው የሌለበት ማለት ነው። መረጃ ያልቀረበበት ማለት ደግሞ ቤቱ የማን እንደሆነ ፣ በማን እንደተያዘ፣ ምንም አይነት መረጃ ያልቀረበበት ቤት ማለት ነው። ይህ እግዲህ ከ21 ሺ በላይ ነው። ይህም ደግሞ የሚኖሩበትም አለ፤ የማይኖሩበትም አለ። የተላለፈበት መንገድ ያልታወቀ የተባሉት ደግሞ በእጣ፣ በልዩ ውሳኔ ወይም በጨረታ መሆኑ ያልተገለጸና የተላለፈበት መንገድ ያልታወቀ ማለት ነው።
እንግዲህ መረጃዎችን በዚህ መልኩ በተለያየ አግባብ መለየቱ ወደፊት ለሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር እንዲያመች ነው። ስራው በጣም አሰልቺና ከባድ በመሆኑ የታመሙ ባለሙያዎች ሁሉ ነበሩ። አንዳንዶቹ የዲስክ መንሸራተት ሁሉ ያጋጠማቸው አሉ። ስራው ያለእንቅልፍ ቀንና ሌሊት ነው የተሰራው። ስለዚህ ስራው በጣም አድካሚና አስቸጋሪ እንዲሁም ውስብስብ ነበር።
የሚገርመው መረጃዎች እንዳይናበቡ ተደርገው ነው የተሰሩት። የቤት መገለጫም እኮ አይናበብም። 85 ሺህ የሚሆኑ ቤቶች በቤት መገለጫ የማይናበቡ ናቸው። ይህ ደግሞ የተሰራው ጉዳዩ ምን ያህል ታስቦበት እንዳይናበብ ተደርጎ እንደተሰራ ያሳያል። ለዚያ ነው አድካሚ የሆነውና ብዙ ዘመንም ተሞክሮ ያልተቻለው። ይህ ለ15 አመታት ሲቆይ ተሞክሮ አያውቅም። አሁን ነው የተሞከረው። ስለዚህ የተሰራው ስራ ትልቅ ስራ ነው። ስለዚህ ቁርጠኝነቱን ወስዶ ይህንን ያሰራውን አካል ማድነቅ ይገባል።
በተለይ ም/ከንቲባዋ ሌሊት ስድስት ሰዓት ጭምር ለዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዚዳንት መልዕክት በመላክ የሚከታተሉበት ሁኔታ ነበር። ይህን ማድነቅ ካልቻልን ከባድ ነው። አንዳንዴ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስራውን አሳንሰው የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ፤ ይህ ያሳዝናል።
አዲስ ዘመን፡– በአጠቃላይ በማጥራቱ ሂደት የመጨረሻውን ውጤት ሲመለከቱ በግል እርሰዎ ምን ስሜት ተሰማዎት?
ዶክተር ቱሉ፡– ሁላችንም ግራ ተጋብተን ነበር።እንደሚታወቀው በወሬ ደረጃ የምንሰማው ነገር አለ። ነገር ግን እዚህ ደረጃ ደርሶ እንዲህ ይሆናል ብለን በፍጹም አላሰብንም ነበር። የተረዳሁትም ሃገሪቷ በምን ያህል ሁኔታ ውስጥ እንደነበረች እና በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለፈች ነው፤ ህገወጥነቱ የት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ነው የሚያሳየው። ህንፃ እኮ ነው ያልተገነባው። በአጠቃላይ ወደ 400 ህንፃ እኮ ሳይገነባ ቀርቷል። ይህ ሁሉ ሲታይ ጉዳዩ ትልቅ መሆኑን ነው። ሳንቲም ተወራርዶበት ህንፃ የሚጠፋበት አገር ውስጥ እኮ ነው ያለነው። ዋና ከተማ ውስጥ ይህ ከተፈጸመ መረጃዎች በአግባቡ በማይደርሱበት ቦታ ላይ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።
እንግዲህ ለኮንዶሚኒየም ከአንድ ሚሊየን በላይ ህዝብ ነው የተመዘገበው። ስለዚህ ይህ ጉዳይ የዚህን ሁሉ ህዝብ ተስፋ ነው ያጨለመው። በሌላ በኩል ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው አድርጎታል። የሃገር ሃብትንም አባክኗል። የባከነው ገንዘብ ቀላል አይደለም። አሁን ቤቶች ኮርፖሬሽን ወደ 53 ቢሊየን ብር እዳ ነው ያለበት። ስለዚህ ይህ ቀላል ነገር አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– እንዲህ አይነት ስርዓት አልበኝነት በከተማችን መታየቱ እንደ አገር ምን የሚያሳየን ነገር አለ፤ በተለይ ሌብነት፣ ህገወጥነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር ምን ያህል በህብረተሰቡ ውስጥ ስር እንደሰደደ የሚያሳይ በመሆኑ ከዚህ ምን ትምህርት ሊወሰድ ይገባል?
ዶክተር ቱሉ፡– ሰው ገንዘብ ሲሰርቅ ዝም ከተባለ ወደነፍስ ማጥፋት ነው የሚያድገው። ስርቆት የሚጀመረው ህጋዊ ሆኖ አይደለም። ስለዚህ እዚያ ውስጥ ሲገባ ቀጥሎ ያን ወንጀል ለመሸፈን ወደነፍስ ማጥፋት መሄዱ አይቀርም። በዚያ አያበቃም፤ ሃገር ነው የሚያፈርሰው። አሁን በኛ ሂደት የሆነው ይኸው ነው። ገንዘብ ሰረቁ፣ ያን ወንጀል ለመደበቅ ብዙ ነፍስ አጠፉ።በመጨረሻም ወደአገር ማፍረስ ነው የሄዱት። ይህ ያስከተለው የስነልቦናና የሞራል ቀውስ ቀላል አይደለም። የነዋሪዎችን ተስፋ ማጨለም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ኑሮውን አጉድሎ ነገ ያልፍልኛል ብሎ ለቤት እየቆጠበ ባንክ ውስጥ የሚያስቀምጠውን ሰው ማደርያ ነው የሰረቁበት። የተረፈው ሰው አይደለም፤ ማደሪያ የሌለውን ነው የቀሙት። ስለዚህ ይህ ከሞራል አንጻር ሲታይ ቀላል ነገር አይደለም። ከዚህ በላይ የወረደ ስነምግባር የለም፤ ሰው ከዚህ በላይ ምንም ሊሆን አይችልም።
ይህንን ያመጣው ምንድነው ካልን ህገወጥነትን በየደረጃው መፍታት አለመቻላችን ነው። ሌብነቱ እያደገ እያደገ መጥቶ ህንጻ እስከመስረቅ ስለደረስን ነው። መንግስት ባለበት ሃገር ውስጥ ህንፃ ሲሰረቅ መሬቱ ከየት መጣ፣ ገንዘቡ ከየት መጣ፣ ተሰርቶ እስከሚያልቅ ድረስ ማን ፈቃድ ሰጠው፣ ከዚያም በኋላ ደግሞ የመንግስት ተቋማት ጭምር ሳይቀሩ ተከራይተው ሲሰሩበት የነበረበት ሁኔታ ነበር። ይህ ሁሉ ሲደማመር በሃገሪቷ ውስጥ ምን እየተሰራ ነበር የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል። ይህ ጉዳይ የሆነ ቦታ ላይ ባይገታ ምን ነበር የሚቀረን። ሃገር አትሸጥም ነበር ብሎ ማሰብ አይቻልም። መሬቷ ተነስታ መሄድ ብትችል ኖሮ እኮ ትሸጥ ነበር። ስለዚህ ሃገር የመጨረሻ የስነምግባር ቀውስ ውስጥ ነው የገባችው የሚል አንድምታ ነው የተረዳሁት።
አዲስ ዘመን፡– ይህ የሞራል ዝቅጠት ለምን ተፈጠረ?
ዶክተር ቱሉ፡– ምንጩ ብዙ ሊሆን ይችላል፤ የዘርፉንም ምሁራን ጥናት ይፈልጋል። ነገር ግን እኔ እንደ አንድ የኢንጂነሪንግ ዘርፍ ባለሙያ ስርዓቱ የፈጠረው ችግር ነው ብዬ ነው የማምነው። ስርዓቱ የተበላሸ ከሆነ ውጤቱም ይበላሻል፤ ስርዓት ሲባል ደግሞ ከትምህርት ስርዓቱ እስከ ማኔጅመንት ስርዓቱ ያሉትን ሁሉ የሚያካትት ነው። ይህ ደግሞ እስከቤተሰብ ድረስ ይወርዳል። የሚሰርቅ ቤተሰብ የሚሰርቅ ልጅ ነው የሚያፈራው። ደመወዝ 500 ብር ሆኖ አንድ ሺህ ብር ይዞ የሚገባ ቤተሰብ ካለ ልጁ አባቱ ከየትም እንደማያመጣ ስለሚያውቅ የአባቱን መንገድ ይከተላል። ስርዓቱ ብልሹ ሆኖ ስለተሰራ፤ ከዚህም በላይ ደግሞ ግለሰቦችን አካበተ እንጂ ሃገርን የሚያሳድግ ስርዓት አይደለም የፈጠርነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት እንዳሉት ስርዓት አፍርሰን መንግስት ደክሟል ብንል ግለሰብ ነው እንጂ መንግስት የለም ሊባል ይችላል። ስለዚህ ሌብነትም ስርዓት ነው።
እንደሚታወቀው ሃገርን የሚመሩት ህግ አውጭ፣ ህግ ተርጓሚና ህግ አስፈጻሚ ናቸው። እነዚህ አካላት አቅም እንዳይኖራቸው ወይም እንዳይሰሩ ካደረግን የተወሰኑ ቡድኖች ስርዓቱን ኮራፕት አድገውታል ማለት ነው። ያለውም ስርዓት ደካማ ነው፤ ያም ቢሆን ኮራፕት ተደርጓል።
በህዝብ ውስጥ የሰረፁ ስነቃሎቻችንም ቢሆኑ መስተካከል አለባቸው። “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚል አባባል በህብረተሰባችን ውስጥ ስር ሰዶ ይገኛል። ይህ በራሱ አደጋ ነው። ይህ ለሚሰማው የሚያስተላልፈው መልዕክት አለ። በተለይ ቀስ በቀስ እየቆየ ሲሄድ መስረጹ አይቀርም። ነገ ከስልጣን ስንሸራተት ምን እሆናለሁ የሚል እንድምታ ያስተላልፋል። ከዚያ ወደስርቆት ሊሄድ ይችላል።
በሌላም በኩል የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ይህንን ሁሉ ፋይናንስ እያስተዳደረ ለረጅም አመታት ኦዲት አልተደረገም። ይህ ደግሞ ተጠያቂነት እንዳይኖር አድርጎታል። እኔ ሰርቄ ከቦታ ቦታ የምዛወር ከሆነ ስርቆትን ስራዬ አድርጌአለሁ። ስለዚህ አእምሮዬ ምንም አይሰማውም። ከዚያም ደግሞ የቁጥጥር መሳሪያ ከሌለና የማይጠብቀኝ ከሆነ አደጋ ነው። በዚህ የተነሳ የምናውቃቸውና ተቋማትን የዘረፉ በርካታ ሰዎች ቦታ ሲቀይሩ ነው ስናይ የኖርነው፤ ተጠያቂነት የለም።
ተጠያቂነት ሲባል ደግሞ በልኩ መሆን አለበት። በሌሎች አገሮች እስከ ሞት ድረስ የሚያደርስ ተጠያቂነት ነው ያለው። በኛ አገር እኮ ስነምግባራችን በመውረዱ የተነሳ ለራስ ለመኖር ሰው ጄሶ እስከማብላት የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህንን አብልቶ ደግሞ ከሶስት ወር በኋላ ይለቀቃል። በዚያ ግን ስንት ትውልድ በሽተኛ ይሆናል። ይህ ከምን የመነጨ ነው ካልን ስርዓቱ ተጠያቂነት እንዳይኖር አድርጎ በመስራቱ ነው። ሌብነቱ ህብረተሰቡ ውስጥም ነው ያለው። ምክንያቱም ተጠያቂነቱ የለም። ተጠያቂነቱም ትክክለኛ ተጠያቂነት አይደለም። ይያዛል፤ ይታሰራል፤ ይለቀቃል። ምንም አይሆንም።ስለዚህ ይሰርቃል። ይቀጥላል። ይህ ነው ዋነኛው ምክንያት።
አዲስ ዘመን፡– እንዲህ አይነት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በቀጣይ በዘላቂነት ምን መሰራት አለበት፤ በጥናታችሁስ ያስቀመጣችሁት የመፍትሄ ሃሳብ ምንድነው?
ዶክተር ቱሉ፡– አሁን ሃገሪቷ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ይዛለች። ስለዚህ ከወዲሁ እነዚህን በህግ አግባብ በስርዓት ካልያዝን ይኸው ጉዳይ ነው የሚደገመው። ስለዚህ ነገሮች በህግና በስርዓት መመራት አለባቸው። በተለይ ፕሮጀክቶች ብዙ ሙስና የሚከናወንባቸው አካባቢዎች ናቸው። ስለዚህ የሚሰሩ ነገሮች በሙሉ በስርዓት መያዝና በዶክመንት መደገፍ መቻል አለባቸው። ዶክመንት ደግሞ አንድ ቦታ ብቻ መሆን የለበትም። የዚህ የኮንዶሚኒየም ጉዳይም ምናልባት የፋይናንስ ጉዳይ ቢታይ ከዚህ በላይ ጉድ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ዶክመንቶቹ ስለማይገኙ የፋይናንስ ስራው አልተፈተሸም።
የአገራችን የመረጃ አያያዝ ስርዓት በጣም ደካማ ነው። ሲፈልግ አንድ ሰው መረጃ ሊያጠፋ ይችላል። ከዚያ ያንን መረጃ ከየትም አታገኝም። ያ ሰው አይጠየቅም። ስለዚህ በመጀመርያ የምንሰራውን ነገር ከመነሻ እስከ መጨረሻ የሔድንበትን ሂደት የሚያሳይ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይገባል። ይህ እኮ ነገ ትውልዱ የሚማርበት ነው። በሌላው ዓለም እያንዳንዷ ዲዛይን ሳይቀር ለትውልድ ይቀመጣል። የዛሬ መቶ አመት ብትፈትሸው ያንን ታገኛለህ። ስለዚህ ያ ህንፃ በምን መልኩ እንደተሰራ ጠቀሜታውንም ችግሩንም ይማሩበታል፤ ጥናት ያካሄዱበታል። የኛ ግን ሲሰራም በትክልል ስለማይሰራ ኦዲት ለማስደረግም እንኳ ያን ዲዛይን አታገኝም። አሁን እነዚህ ቤቶች ዲዛይን ላይኖራቸው ይችላል። እና አሁን ወደመስመር ማስገባት ያስፈልጋል። ስራዎችን ስርዓት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ሃሪቷ ከዚህ መማር አለባት። ይህ ካልሆነ ግን እንዲህ አይነት ነገር ሄዶ ሄዶ ሃገር ያፈርሳል። ሃገር ሲፈርስ ደግሞ የሚሞተው ምንም ያልበላው ደሃው ነው።ሌባው ሌሎች በርካታ መውጫ መንገዶች አሉት።
ሌቦች ትላንት የደሃውን ኑሮ ሰረቁት፣ ነገ ደግሞ ቀውስ ሲፈጠር እነሱ ይኖራሉ፤ ዜጋው ይሞታል። እናም ይህ ወደመስመር መምጣት አለበት። ሁለተኛ ደግሞ ሰውና ስራ ማገኛኘት ያስፈልጋል።ሰው ወንበሩን አክሎ መገኘት አለበት። ይህ ሁሉ ሲሰራ ወንበራቸውን አክለው የተገኙ ሰዎች ቢኖሩ ብዙ ነገር ይተርፍ ነበር። ወንበሩ ላይ የተቀመጠው ለገንዘቡ እንጂ ለስራው አይደለም ማለት ነው። ይህን ማስተካከል ያስፈልጋል። ይህ ካልስተካከለ ታሪክ ራሱን እየደገመ እየደገመ ተስፋ እንጂ መሬት ላይ የሚታይ ነገር አይኖርም። ሃገሪቷ የሚቆረቆሩ፣ የሚደክሙ፣ የሚሰሩ ሰዎች አሏት። ነገር ግን ስርዓቱ ወደፊት እንዳይሄዱ ይመታቸዋል። ምክንያቱም ስርዓቱ በሙስና ስለሚያዝ የትም አይሄድም። ስለዚህ ይህች አገር ወደፊት እንድትቀጥል ስርዓቱን ማጥራት የግድ ነው። ይህ ግን ጊዜ፣ አቅምና መደራጀት ይፈልጋል። አማራጭ ግን የለም። ስለዚህ ይህን እያጠሩ መሄድ ከተቻለ በየጊዜው የሚፈጠሩ ጉዳዮችን እያስተካከሉ መሄድ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ ፖሊሲው ላይ ክፍተት አለ ይላሉ?
ዶክተር ቱሉ፡– አዎ። የቤቶች ልማት ፖሊሲ በዋናት የደሃውን ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ነው የተቋቋመው። ይህንን ለማሳካት የተሄደበት መንገድ በተለይ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ችግር ያለበት ነበር። ለምሳሌ የቤቶች ኮርፖሬሽን በፖሊሲ ተደግፎ ነው የተዋቀረው። ከዚያ ተቋማዊ መዋቅር ነው የሚያስፈልገው። እዚህ ላይ ግን በትክክል አልተሰራም። የሚገነባ አካል አለ፤ የሚያስተላልፍ አለ፤ ማኔጅመንት አለ። እነዚህ አካላት ራሳቸው ችለው መዋቀር አለባቸው። ነገር ግን የሆነው ምንድነው ቤቶች ኮርፖሬሽን ራሱ ይገነባል፤ ራሱ ያስተላልፋል፤ ራሱ ያስተዳራል። በዚህ መካከል ምንም አይነት የቁጥጥር ስርዓት የለም። ስለዚህ ያላለቀ ቤት ማስተላለፍ እችላለሁ ማለት ነው። መሰረተ ልማት ያልተሟላለትን፣ ግንባታ ጥራት የጎደለውን ቤት ማስተላለፍ እችላለሁ ማለት ነው።
ለምሳሌ በቅርቡ የተላለፉ ቤቶች ሁለት አመት አልፏቸዋል። ነገር ግን ገንቢውም፣ አስተላላፊውም፣ ማኔጅመንቱም አንድ ስለሆነ እስካሁን ድረስ አልተጠናቀቁም ማለት ነው። ህጉ ላይ አንድ ቤት 80 ከመቶ ካላለቀ አይተላለፍም ይላል።ነገር ግን ከ80 ከመቶ በታች የተጠናቀቁ ቤቶች ተላልፈዋል። ይህ ለምን ሆነ ገንቢውም፣ አስተላላፊውም፣ ማኔጅመንቱም ራሱ ስለሆነ ነው።
ሌላው ፖሊሲው ላይ ያለው ክፍተት የትኛውም አገር ላይ መንግስት ቤት ገንብቶ አይሰጥም። አይችለውምም፣ ሙስናው አለ፤ ጥራት አለ፤ ጊዜውም፣ ጉልበቱም ወዘተ ስላለ ማለት ነው። ስለዚህ ለዚህ አላማ ለሁሉ ነዋሪ የሚሆኑ ሪል ስቴቶችን ያዘጋጃል።
ይህንን አደራጅቶ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በሃገራችን ከ97 ዓ.ም ጀምሮ አደራጅቶ ወደስራ አስገብቶ ቢሆንና በትክክል ቁጥጥሩ ላይ ሰርቶ ቢሆን እስካሁን ይህ ቤት ተሰርቶ ያልቅ ነበር። ከዚህ በላይም መስራት ይቻላል። ነገር ግን ፖሊሲው ላይ ክፍተት ስላለ ይህን መፍቀድ አልተቻለም። ለምን ከተባለ ሙስናው ከጀርባው ስላለ ነው። ይህ ደግሞ የተፈለገው ፕሮጀክት ስኬታማ እንዳይሆን አድርጎታል። ውጤቱም አልመጣም። እስካሁን 176 ሺህ ነው ከአንድ ሚሊየን ቤት ፈላጊ ማስተላለፍ የተቻለው።ነገር ግን አሁን የመጣው አመራር ይህንን ክፍተት ለመሙላት እየታገለ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– በአዲስ አበባ ግን የተለያዩ የቤት አደረጃጀቶች አሉ?
ዶክተር ቱሉ፡– አሁን በአዲስ አበባ የቤቶች ልማት ቢሮ የሚባል አለ። በዚህ ስር ሶስት ተቋማት አሉ። የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የጋራ መኖርያ ቤቶችን የሚቆጣጠር፣ የሚያስገነባ የሚያስተላልፍ ማለት ነው፤ ሁለተኛ ዲዛይን ኢንተርፕራይዝ የሚባል አለ። ይህ ደግሞ የዲዛይን ስራዎችን፣ ያን ያህል ባይሆንም የቁጥጥር ስራ ይሰራል፤ ያከናውናል ሶስተኛ የኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የሚባል አለ። ይህ ደግሞ ድርሻው መገንባት ብቻ ነው። እነዚህ ሁለቱ የቢዝነስ ተቋማት ናቸው። ከዚህ አንጻር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የተባለው ቅድም እንዳልኩት ሁሉንም ስራ የሚሰራ ነው። ኮርፖሬሽኑ ሁሉንም ስራዎች ጠቅልሎ ይዟል።ሌሎቹ ከሱ ጨረታ ወስደው ሰርተው ይሰጡታል።
አዲስ ዘመን፡– ባንክ ጋ ክፍተት የለም?
ዶክተር ቱሉ፡– እነሱ ጋ የሰጡን መረጃ የተደራጀ ነው። ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በእያንዳንዱ የቤት አይነት የተመዘገቡትን ሰዎች በሙሉ ሰጡን። ከዚያ በኋላ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በመቆጠብ ላይ ያሉት ሰዎች ዝርዝር ሰጡን፣ ከዚያ በአሁኑ ጊዜ ያለ የጋራ መኖርያ ቤት ተበዳሪ በሚል መረጃ ሰጡን፣ ከዚያ ደግሞ እስካሁን የተበደሩ፣ የባንክ ብድር የጨረሱ፣ ቁጠባ ያቋረጡ ፣ ውዝፍ እዳ ያለባቸው በሚል በዝርዝር መረጃ አላቸው። ስለዚህ ባንክ መያዝ ያለበትን መረጃ በአግባቡ ይዟል።
አዲስ ዘመን፡– ይህ ስራ ይዞት የመጣው መልካም አጋጣሚ ነበር፤ ችግሮቹስ እስከመቼ መፍታት ይቻላል?
ዶክተር ቱሉ፡– መልካም አጋጣሚ የምለው የመንግስት ቁርጠኝነትን ነው። ይህ ችግር ከ15 አመት በላይ የቆየ ነው። ነገር ግን ችግሩ ሳይፈታ ይህንን ያህል ጊዜ ቆይቷል። ለምን ካልን ቁርጠኝነቱ ስላልነበረ ነው።
ሁለተኛ ህዝቡ ለዚህ ውጤት ያሳየው ምላሽ ሌላው ትልቅ መልካም አጋጣሚ ነው። በጥናቱ ወቅትም የታየው የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር። ጥቆማ የመስጠትና የተለያዩ አስተያየቶችን የመስጠት ድጋፎች ነበሩ። ሶስተኛ ይህ ችግር እንዲህ በዝርዝር ተጠንቶ መቅረቡ ለተጀመረው የሀገራዊ ሪፎርም ስራ ትልቅ ምሰሶ ነው።
ከጊዜ አንፃር ካየን አሁን ህጋዊ ያሆኑትን ወደመንግስት ካዝና መመለስ ነው። ይህ እየተሰራ ነው። ደብዳቤ ተበትኗል፤ ኮሚቴም ተዋቅሯል። ከዚያ መውጣት ያለበት ይወጣል፤ ከዚያ ዋጋ ወጥቶለት በእጣ ለተጠቃሚዎች ይተላለፋል። ከዚያ በኋላ ያሉትን ተጨማሪ ስራዎች ደግሞ ቤቶች ኮርፖሬሽን ራሱ የሚሄድበት ይሆናል።
ከዚያ ቀጥሎ ግን የዳታ ቤዝ ልማት ይሰራል። እንደሚታወቀው በዚህ ጥናት ላይ ትልቁ ፈተና የመረጃ እጦት ነው። መረጃው ምስቅልቅሉ የወጣ ነው። ዛሬ በኦንላይን ቤት መከራየት በተቻለበት ዘመን እዚህ መረጃ ለማግኘት ያለው ፈተና ከባድ ነው። ቤቶች ኮርፖሬሽን ግን ለ15 አመታት ራሱ የገነባውን ቤት ያለበትን ሁኔታ አያውቀውም። ስለዚህ ይህን የቤቶች ልማት ዳታ ቤዝ አዘጋጅተን ያንን ካደራጀን በኋላ በቀላሉ እስከከንቲባ ድረስ ማየት የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ይህ አሁን ከደረስንበት ቴክኖሎጂ አንጻር ቀላል ነው። ይህንን ማድረግ ይቻላል፤ መደረግ ያለበትም ይህ ነው።
በሌላ በኩል ይህ ሁሉ ቤት፣ ህንጻ ሲሰረቅ ሲመሩ፣ ሲያስተባብሩ የነበሩ ሰዎች ወደህግ መምጣት አለባቸው። የመጀመርያው እርምጃ ይህ ነው መሆን ያለበት። ዋና ኦዲተር ቢሮ የሰራውንና እኛ የሰራነውን አቀናጅቶ ወደህጋዊ መስመር ለማምጣት ሰዎች ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ሰው መረጃ አጥፍቶ ከተጠያቂነት አመልጣለሁ ብሎ ካሰበ አደጋ ነው። ለጠፋው መረጃ ተጠያቂ መሆን አለበት። ቅጣትም በአመራር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በባለሙያ ደረጃ መውረድ አለበት። በኮንትራክተርና በኮንሰልታንት ደረጃ መውረድ አለበት። ይህን ሲያበላሹ የነበሩ ኮንትራክተሮች እድሜ ዘመናቸው ከዚህ ዘርፍ መውጣት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። ተቋማቱ ካልጠነከሩ አሁን በደረስንበት የትውልድ የስነልቦና መዋቅር ደረጃ ይህን ወንጀል ማስቆም አይቻልም። የሃገሩን ኑሮ የሚሸጥ ባለሙያም እስከመጨረሻው ከሙያው መውጣት አለበት። በተማረበት ሙያ እንዳይሰራ አድርጎ ማስቀመጥ ይቻላል። ምክንቱያም እነሱም የስንቶቹን ህይወት አጨልመዋል። ስለዚህ ወደዚህ የምንሄድበትን ስርዓት መፍጠር አለብን። ይህንንም በህግና በመመሪያ መደገፍ አለብን።
አዲስ ዘመን፡– ከእጣ ጋር ተያይዞም ችግሮች እንደነበሩ ይነሳል፤ በናንተ በኩል ያደረጋችሁት ጥናት አለ?
ዶክተር ቱሉ፡– ሰው ቤት ደርሶታል፤ እጣ ሊስት ውስጥ የለም፤ የእጣ ስርዓቱ ራሱ ብዙ ጥያቄ ያለበት ነው። ለፎርማሊቲ ብቻ ቀድሞ ዲዛይን የተደረገና ለማን ቤት መውጣት እንዳለበት ተሰርቶ የመጣ ይመስላል። ይመስላል ያልነው አንዳንድ እጣ የወጣላቸውን በአዲስ ልሳን ላይ ስናይ የሉም፤ ቤቶች ኮርፖሬሽን ላይ የሉም፤ ስለዚህ ባንክ ሳይቆጥብ እጣ የወጣለት ሰው ሊኖር ይችላል። ለዚያ ነው ባንክ ውስጥ የማይገኘው። ስለዚህ የተሰራው ጉዳይ ከጀርባው ብዙ ውስብስብ ጉዳዮች አሉበት።
በአንድ ሰው ስም እስከ አስር ቤት ድረስ የተገኘበት ሁኔታ አለ። ህጉ ግን በአንድ ሰው አንድ መኖርያ ቤት ብቻ ነው ሊኖር የሚችለው። እኔ ቤት ገዝቼ ወይም ሰርቼ ማከራየት እፈልጋለሁ ካልክ ይህ ንግድ ነው። ከዚያ ውጭ ግን በአንድ ሰው ስም ይህንን ያህል ቤት ሊገኝ አይችልም። ንግድ ቤት ሊሆን ይችላል፣ መኖርያ ቤት ግን እንዴት ሆኖ ነው፤ ያልተሟላ መረጃ ለማጣራት ስንደውል የትኛው ቤት እያሉ በሙሉ ኮንፊደንስ የሚጠይቁ አሉ። ይህንንም ሲናገሩ አያፍሩበትም። ይህንን ያመጣው ወይ ሃገሪቷ ለነዋሪው መብትና ግዴታን አላሳወቀችም፤ አልያም የታወቀው እንዲህ ሆነ። ስለዚህ ሰዎች መብትና ግዴታቸውን ማወቅ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡– ለዚህ ዘላቂ መፍትሄው ምንድነው?
ዶክተር ቱሉ፤ ብዙ ምክረሃሳብ ጠቁመናል።አንዱ የጥናቱን ውጤት ማሳወቅ ነው። ለህግ አውጭው፣ ለህግ ተርጓሚውና ለህግ አስፈጻሚው፣ ለሚዲያ፣ ለነዋሪው ማሳወቅ ያስፈልጋል። ሃገሪቷ በምን ሁኔታ ነው የነበረችው፣ ምንድነው የሆነው፤ እንዴት መስተካከል አለበት፣ የሚለውን ሁሉ ያካተተ ማለት ነው።
ሁለተኛ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ላይ ያለውን ነገር መጀመርያ ምን ውስጥ አልፎ እንደነበርና ምን እየሆነ እንደሆነ መግባባት ያስፈልጋል። ከዚያ ደግሞ አደረጃጀት ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት።
ከዚያ በህገወጥ መንገድ ያሉ ሰዎችን፣ ተቋማትን፣ ድርጅቶችን ወዘተ ሁሉ ህጋዊ መንገድ እንዲይዙ ማድረግ፣ ተዘግተው የሚገኙ ባዶ ቤቶችን ቶሎ ለነዋሪዎች ማስተላለፍ፣ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃዎችን መውሰድ፣ ሳይገነቡ የቀሩ ህንጻዎች ለምን እንዳልተገነቡ ለይቶ ያንን ያደረጉ አካላትን ወደ መስመር ማምጣት፣የጋራ መኖርያ ቤቶችን እስከመጨረሻ ድረስ መንግስት እየገነባ መኖር የለበትም፤ ስለዚህ የጋራ መኖርያ ቤቶች በቀጣይ ችግሮቹ የሚፈቱበት ሁኔታ መፍጠር፣ አሁን የተመዘገቡትና የሚመዘገቡትም ጭምር ችግሮቻቸው የሚፈቱበትን መንገድ ማመቻት፣ ወዘተ ያስፈልጋል።
በኮንስትራክሽን ህግ የሚፈቀደው ትልቁ የዋጋ ግሽበት 20 ከመቶ ነው። አሁን በ40/60 ላይ ከመቶ ፐርሰንት በላይ የዋጋ ግሽበት ይታያል። ይህ አይፈቀድም። ይህ ጠያቂ ካለመኖሩ የመጣ ነው። ስለዚህ በቀጣይ እነዚህ ችግሮች የሚፈቱበትን ሁኔታ ማመቻቸትና በቀጣይም እየተገነቡ ያሉ ቤቶች ቶሎ ወደነዋሪው የሚተላለፉበትን መንገድ መፈለግ ያስፈልጋል። በልዩ ሁኔታ የሚተላለፉ ቤቶችም የራሱ የሆነ ዳታ ቤዝ ሊኖራቸው ይገባል። እንግዲህ እኛ ሁሉንም አንጨርስም፤ መንግስት በራሱ ከዚህ በላይ ሊሄድበት ይችላል።
የጋራ መገልገያ ለጋራዥ፣ ለሱቅ ወዘተ የተሸጡበት ሁኔታ አለ። በጋራ መኖርያ ቤት ያሉ ኮሚቴዎችም እንዲሁ ነጋዴ እና የማይነኩ መንግስት የሆኑበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ የማህበራቱ ሁኔታም መታየት አለበት።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።
ዶክተር ቱሉ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 01/2013