አስናቀ ፀጋዬ
በኢትዮጵያ በርካታ በተፈጥሮና በሰው የተተከለ ሰፊ የደን ሃብት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።በዚህ ሰፊ የደን ሃብት ውስጥም ለቁጥር የሚታክቱ የዱር እንስሳት እንደነበሩም የታሪክ መዛግብት ያስነብባሉ ።
ይሁንና በህገወጥ ሰፈራና ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ የደን ሃብቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣቱንና ይህን የደን ሃብት መጠለያቸው የደረጉ የዱር እንስሳትም ቁጥራችው እያሽቆለቀለ መሄዱ በየዘመናቱ የሚታይ ሀቅ ነው።በዚሁ የደን ሃብት መመናመን የተነሳም የሃገሪቱ የአየር ሁኔታ ተለዋውጦ በተለያዩ ግዜያት ድርቅና ረሃብ ተከስቷል።
እየተመናመነ የመጣውን የደን ሃብት መልሶ ለመተካት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የተደረጉ ርብርቦች ቢኖሩም ያን ያህል አርኪ እንዳልበሩም በደን ሃብት አጠባበቅ ዙሪያ የሚሰሩ ባለሞያዎች በተደጋጋሚ ይገልፃሉ።
በቅርቡ የተጀመረው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ መርሃግብር በርካታ ሰዎችን በአንድ ግዜ በማሳተፍ በእጅጉ የተመናመነውን የደን ሃብት በፍጥነት ለመመለስ አስተዋፅኦው የጎላ መሆንኑንም ያስረዳሉ።ይሁንና ይህ መርሃ ግብር የአንድ ወቅት ዘመቻና ወረት በሚመስል መልኩ የሚቀየር ከሆነ የተራቆተውን የደን ሃብት ወደነበረበት ለመመለስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት አዳጋች ሊሆን እንደሚችልም ባለሙያዎቹ ይጠቁማሉ።
ምንም እንኳን የተፈጥሮና በሰው የተተከሉ የደን ሃብቶች በተለያዩ ምክንያቶች የተራቆቱ ቢሆንም በኢትዮጵያ አሁንም ድረስ የደን ክምችት በስፋት የሚገኝባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።በስፋት የደን ሃብት ከሚገኝባቸው የሀገሪቱ ክልሎች ውስጥ አንዱ የኦሮሚያ ክልል ተጠቃሽ ነው።
የክልሉ የደንና የዱር እንስሳት ድርጅት መረጃም የጅማ ዞን የተፈጥሮና በሰው የተተከለ የደን ሃብት መገኛ መሆኑን ያረጋግጣል።በዚህ ዞን የሚገኘው ሰፊ የደን ሃብት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ተራቁቶ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ግዜ ወዲህ በተሰሩ ስራዎች መልሶ እያገገመ ስለመምጣቱም የድርጅቱ መረጃ ያሳያል።ይሁን እንጂ አሁንም የደን ሀብቱ በርካታ ማነቆዎች ያሉበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደቀድሞው ደረጃ እንዳይመለስ ስጋቶች አሉ ።
በኦሮሚያ ደንና የዱር እንስሳት ድርጅት የጅማ ቅርንጫፍ ሃላፊ አቶ ክበበ ጌራ እንደሚገልፁት በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ባሉ ወረዳዎች ውስጥ 295 ሺ 88 ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተፈጥሮና በሰው የተተከለ ደን ይገኛል።ከዚህ ውስጥ 287 ሺ 74 ያህሉ የተፈጥሮ ደን ሲሆን 8 ሺ 13 ያህሉ ደግሞ በሰው የተተከለ ደን ነው።ይህም የደን ሃብት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሰጠው ስልጣን መሰረት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት እያስተዳደረው ይገኛል።
የፅህፈት ቤት ዋነኛ ስራ የተፈጥሮና በሰው የተተከሉ ደኖችን በመንከባከብና በመጠበቅ አልምቶ ለአካባቢው ማህበረሰብ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ ሲሆን በሰው የተተከሉና የደረሱ ዛፎችን ቆርጦ ለልማት ያውላል።
ያረጁ ዛፎችን በመሸጥና በአራት ቀጠናዎች ውስጥ ባሉት አራት የእንጨት መሰንጠቂያ ፋብሪካዎች በማቀነባበርና ወደጣውላ በመቀየር ለገበያ ያቀርባል።
በሌላ በኩል ደግሞ ፅህፈት ቤቱ የተፈጥሮና በሰው የተተከሉ ደኖችን የሚንከባከብና ጥበቃ የሚያደርግ ሲሆን በተለይ ደግሞ የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍና በማህበራት ጭምር በማደራጀት የተፈጥሮ ደኖች እየጠበቀ ይገኛል።በዚሁ መሰረትም በአራት ቀጠና ውስጥ ከ146 በላይ ማህበራት በ145 ሺ 947 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት ላይ 23 ሺ 880 አባወራዎችን በማደራጀት ደኑን እንዲጠብቁና እንዲንከባከቡ አድርጓል። የራሱን የጥበቃ ሰራተኞችንም ቀጥሮ በሰው የተተከሉ ደኖችንም እያስጠበቀ ይገኛል።በዚህም ተራቁቶ የነበረውን የዞኑን የደን ሃብት ክምችት ቀስ በቀስ እየመለሰ ይገኛል።
እንደ ሃላፊው ገለፃ በደኖቹ አካባቢ ያለው ህብረተሰብ በማህበራት እንዲደራጅ ተደርጎ በተለይ በተፈጥሮ ደኖች ውስጥ ቡና፣ኮረሪማና ሌሎች ቅመማቅመሞችን በጋራ በመልቀም ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል። በደን ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ቡና በመልቀምና በማህበራቸው በኩል ወደ ውጪ ሀገር በመላክ ተጨማሪ ገቢ እያገኙም ነው።
ከዚህ ባሻገር ፅህፈት ቤቱ ከኦሮሚያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ህብረተሰቡ በሰው ከተተከሉ ደኖች በምን መልኩ ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት የራሱን መመሪያ ያወጣ ሲሆን በዚሁ መመሪያ መሰረት በየዓመቱ ከሚገኘው አመታዊ የዛፍ ሽያጭ ገቢ 5 ከመቶ ያህሉ በገንዝብ ተተምኖ በእያንደንዱ ቀበሌ በከፈቱት አካውንት እየገባላቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑም ተደርጓል።
ሃላፊው እንደሚሉት ከዞኑ የተፈጥሮና በሰው የተተከሉ ደኖች ጋር በተያያዘ በስፋት ከሚስተዋሉ ችግሮች ውስጥ ደንን የመመንጠር፣ በደን ውስጥ የመስፈርና መሰል ችግሮች በስፋት ይታያሉ።ይህን ተግባር በሚፈፅሙት ላይም በተቻለ አቅም ህብረተሰቡን በማሳመንና ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ደኑን ለቀው እንዲወጡ በርካታ ስራዎች እየተሰራ ነው።የድርጊቱ ፈፃሚዎች በህግ ተጠያቂ ሆነው ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድባቸው እየተደረገም ይገኛል።
በነዚህ ስራዎችም የሚፈለገው ውጤት የመጣባቸውም ያልመጣባቸውም ቦታዎች አሉ። ለአብነትም ባለፈው ዓመት 116 የሚጠጉ አርሶ አደሮች ይዘውት የነበረው 246 ሄክታር መሬት ማስለቀቅ ተችሏል።ይህም በተሰራው ስራ ውጤት መምጣቱን ያሳያል።
ነገር ግን ስራው በቂ ባለመሆኑ በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም የደን ወረራ ችግሮች ይታያሉ። ከህግ አኳያም ከአንድ ቀበሌ ወደ 90 የሚሆኑ አርሶ አደሮች ተከሰው በፍርድ ቤት በተወሰኑ ተጠያቂዎች ላይ ብይን ተሰጥቶ ከደኑ ውስጥ እንዲለቁ ተደርጓል።ሌሎችም ጉዳያቸው በከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።
አሁንም ነባርና መልሰው በማይገኙ ደኖች ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ከባድ ውድመት እየደረሰ የሚገኝ በመሆኑ ህብረተሰቡም ሆነ ማንኛውም የህግ አካል እንዲሁም የመንግስት መዋቅር እነዚህ ነባር የሆኑ ደኖችን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ አስፈላጊውን ሁሉ ትብበር ሊያደርጉ ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 01/2013