አስመረት ብስራት
ልጆች እንዴት ናችሁ? ባለፈው ሳምንት የጠፈር ተመራማሪ መሆን ስለሚፈልገው ልጅ የፃፍኩትን ፅሁፍ አንዳንድ ልጆች እንደወደዱት ነግረውኛል። ልጆች በዛሬው ፅሁፌ ደግሞ ጋዜጦችንና መፅሄቶችን በማንበብ የንባብ ባህላችሁን እንድታዳብሩ እመክራችኋለሁ።
ልጆች ለጋስ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ታወቃላችሁ? ካላወቃችሁ እኔ ልንገራችሁ። ለጋስ መሆን አቅማችሁ የሚችለውን በጎ ነገር ማድረግ፤ ለሌሎች መስጠት ማለት ነው። ልጆች መስጠት ሲባል ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ፍቅርን መስጠት፤ ያለንን ጊዜ ለታላላቆች በመታዘዝ ጊዜንና ጉልበትንም መስጠት ሊሆን ይችላል። ለዛሬ ልግስናን በልጅነታቸው ከተለማመዱት ልጆች መካከል አንዱን ይዤላቸሁ ቀርቤያለሁ መልካም ንባብ።
ታሪኩ እንዲህ ነው ከዛሬ 12 ዓመት በፊት አንድ የወራቶች ዕድሜ ያለው ጨቅላ ህጻን በሙዝ ቅጠል ተጠቅልሎ ከአንድ የዛፍ ጥላ ሥር ተጥሎይገኛል።
ከተጣለበትም ቦታ ሰዎች አንስተው አዲስ አበባ ወደሚገኝ የህጻናት ማሳደግያ ተቋም እንዲገባ ያደርጉታል። እዛም ለጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ በማደጎ መልክ ለአሳዳጊዎቹ ተሰጥቶ ወደ አሜሪካ ይሄዳል።
ይህ ህጻን 5 ዓመት ሲሞላው በኪሮሽ አማካኝነት በእጅ የሚሰሩ የዳንቴል አልባሳትን መስራት መለማመድ ይጀምራል። ከፍ እያለ ሲመጣም ሞያውን ከማወቅ ባለፈ በእሱ ዕድሜ ሊታሰብ በማይችል መልኩ በርካታ አልባሳትን በማዘጋጀት ለገበያ ማቅረብ ይጀምራል። ከዛም የራሱን መሸጫ ሱቅ ከመክፈትም አልፎ የድርጅቱ ልዩ የንግድ ምልክት ወይም ብራንድ በመላው አሜሪካ ታዋቂ ለመሆን በቅቷል።
በአሜሪካ ብሄራዊ ቴሌቪዥን የቴሌቪዥን ሾው አዘጋጅ በመሆን በቅርቡ ሥራ ጀምሯል። በትላልቅ ሾዎች ላይም በመገኘት አነቃቂ ንግግሮችን በማቅረብ የዕድሜ እኩዮቹን ብቻ ሳይሆን አዋቂዎችንም ጭምር አስገራሚ አስብሏል።
ይህ ብላቴና ጆና ላርሰን ይባላል። ህፃን እያለ የተለያትን የትውልድ አገሩን ኢትዮጵያን ባገኘው መድረክ እና አጋጣሚ ሁሉ ያነሳል። ኢትዮጵያዊያን የዕድሜ እኩዮቹ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ እንደሚፈልግና በዚህ ላይ የእሱ ድርሻም እንዳለ ይገልጻል።
ባሳለፍነው ዓመት በአንድ የኢትዮጵያ ገጠራማ ሥፍራ ሁሉን ያሟላ ዘመናዊ ቤተ መፃህፍት በራሱ ወጪ አስገንብቶ አስረክቧል። የሳይንስ ቤተ ሙከራ ግንባታንም አስጀምሯል።
በተጨማሪም ተጽዕኖ ፈጣሪነቱን ተጠቅሞ በሚያሰባስበው ገንዘብ በ“ኮባ ቅጠል” ተጠቅልሎ ከወደቀበት ሥፍራ አንስቶ የታደገውን የህጻናት ማሳደግያ ማዕከል ይደግፋል።
ጆና ላርሰን በቅርቡ በታዋቂው የአሜሪካ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኤን ቢሲ ኒውስ ላይ በሚተላለፈው ዘ አፕሳይድ ሾው /the upside show/ ላይ ቀርቦ “ወደፊት ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ፡፡” በሚል ከአዘጋጁ ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው መልስ “የቀዶ ጥገና ሀኪም ሆኜ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ነፃ አገልግሎት መስጠት እፈልጋለሁ” በማለት ተናግሯል።
ልጆች ማንንም ገንዘብ ሳይጠይቅ በራሱ ሰርቶ ሌሎችን ለመርዳት ህፃን መሆን አላገደውም። ስለዚህ ልጆች አቅማቸሁ በሚችለው ሁሉ ለሀገራችሁ ጥቅም ላይ የሚውል ነገር እንድታከናውኑ እመክራለሁ። ቻው።
አዲስ ዘመን ጥር 30/2013