አብርሃም ተወልደ
ልጅ ኢያሱ ጥር 27 ቀን 1889 ዓመተ ምህረት ተወለዱ። አባታቸው ራስ በኋላ ንጉስ የሆኑት ሚካኤል እናታቸው የአጼ ምኒልክ ልጅ ወይዘሮ ሸዋረጋ ናቸው። ዳግማዊ ምኒልክ ሕመም ሲጸናባቸው ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓመተ ምህረት ወራሼ ኢያሱ ሚካኤል ነው ብለው አዋጅ አስነገሩ። ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደውንም ሞግዚት እና እንደራሴ አድርገዋቸው የመንግስቱ አስተዳደር በራስ ቢትወደድ ተሰማ ስር ሆነ።
ራስ ቢትወደድ ተሰማ ሚያዚያ 3 ቀን 1903 ዓመተ ምህረት ከሞቱ በኋላ ስልጣን በልጅ ኢያሱ እጅ ሆነ።ግንቦት 23 ቀን 1906 ዓመተ ምህረት ለአባታቸው ለራስ ሚካኤል ዘውድ ሰጥተው ንጉስ ወሎ ወትግሬ ተባሉ።በአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ልጅ ኢያሱ የጀርመንና የቱርክ ፖለቲካ ደጋፊ ነበሩ።ይህና ሌሎችም ነገሮች በሸዋ መኳንንት ዘንድ መጠላትን ፈጠረባቸው።
ልጅ ኢያሱ ሰለሙ ተብሎ ስለተወራው መስከረም 17 ቀን 1909 ዓመተ ምህረት የሸዋ መኳንንት ልጅ ኢያሱን ሽረው የዳግማዊ ምኒልክ ልጅን ወይዘሮ ዘውዲቱን ንግሥተ ነገሥታት ደጃዝማች ተፈሪ ራስ ተብለው አልጋ ወራሽ እና እንደራሴ እንዲሆኑ አደረጉ።
ንጉስ ሚካኤል የልጅ ኢያሱ መሻርን ሲሰሙ የወሎን ጦር አስከትለው ወደ ሸዋ ዘመቱና ጥቅምት 17 ቀን 1909 ዓመተ ምሕረት ሰገሌ ላይ ጦርነት ሆኖ ብዙ ሰው ከአለቀ በኃላ ንጉስ ሚካኤል ተማረኩ። ከዚያ በኋላ ልጅ ኢያሱ ከሁለት ዓመት በኋላ ትግራይ ውስጥ ተይዘው መጀመሪያ በኮላሽ ቀጥሎም በኮረማሽ ከታሰሩ በኋላ ወደ ፍቼ ተዘዋውረው ራስ ካሳ ሃይሉ ዘንድ በእስራት ተቀመጡ። ከፍቼ አምልጠው እንደገና ከተያዙ በኋላ ጋራ ሙለታ በእስር ላይ እንዳሉ በ1928 ዓመተ ምህረት ሞተዋል።
ልጅ ኢያሱ በ1903 ዓመተ ምህረት ትግሬ ላይ ተይዘው ወደ ሸዋ በመጡ ጊዜ መጀመሪያ ኮማረሽ ላይ በእስረኛነት እየተጠበቁ ስድስት ወር ያህል ተቀምጠው ነበር። በኋላ ግን ፍቼ ከተማ ላይ ባለፎቅ የሆነ ልዩ ቤት ተሰርቶላቸው በ1914 ዓመተ ምህረት ህዳር 29 ቀን ወደዚያ ተዘዋውረው በልዑል ራስ ካሳ እጅ እየተጠበቁ በምቾት ስፍራ እንዲቀመጡ ተደረገ።
በዚያም ሳሉ የቀድሞ ወዳጆቻቸው እና ባለሟሎቻቸው እርሳቸውን ከእስር ቤት ለማስወጣት እና በመንግስት ስልጣን ላይ መልሶ ለማቆም በየጊዜው ይሞክሩ ነበር።ለምሳሌ እነወይዘሮ ጸሐይ ወርቅ ዳርጌ በልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ ላይ አደጋ ለማስጣል እና ልጅ ኢያሱን መልሶ ለማቆም በ1917 ዓመተ ምህረት ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀርቶ እንደታሰሩ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ የዘመን ታሪክ ተጽፎ ይገኛል።
የአማርኛ ቅኔ አዋቂው ወዳጃቸው አቶ ተሰማ እሸቴ ምኞቱን በግጥም ሲገልጽ በምስጢራዊ አነጋገር እንዲህ ብሎ ነበር።
የበላሁት ጮማ ሆዴን ቆረጠ እንደምን አድርጌ ተፍቼ ላውጣው።
አሁንም በዚህ ዘመን ልዑል ራስ ኃይሉ ልጅ ኢያሱን ከታሰሩበት ለማስፈታት ለማስወጣት ሲጻጻፉና በገንዘብ ሆነ በምክር ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ነገሩ ተገልጦባቸው ተያዙ።
የራስ ኃይሉ ልጅ ወይዘሮ ሰብለወንጌል ከልጅ ኢያሱ አንዲት ልጅ ወልደው ነበር።እሳቸውም ወይዘሮ የዓለም ጸሐይ ኢያሱ የተባሉ ናቸው።ራስ ኃይሉ ለዚህ ነገር ተግተው የተነሱት በጋብቻ ዝምድናው ምክንያት ነው እየተባለ በዚህ ዘመን ይወራ ነበር።
ልጅ ኢያሱ በፍቼ ከተማ ታስረው ከአስር ዓመት በላይ ከተቀመጡ በኋላ ልዑል ራስ ካሳ ለልዑል አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ሰርግ አዲስ አበባ መጥተው ሳሉ የሚጠብቋቸውን ዘበኞች በገንዘብ ሸንግለው በልዩ ዘዴ ግንቦት 10 ቀን 1924 ዓመተ ምሕረት ረቡዕ ማታ ከነበሩበት ቤት ወጥተው አመለጡ።ስለ አወጣጣቸው ለልጅ ኢያሱ መኖሪያ ይሆን ዘንድ ፍቼ ላይ በልዑል ራስ ካሳ ግቢ ውስጥ የተሰራ ባለ ፎቅ ቤት ነበር። ዙሪያው በሁለት አጥር የተከበበ ነው።የፎቁ ምድር ቤት የዘበኞች መቀመጫ ሆኖ ልጅ ኢያሱ የሚኖሩት ፎቁ ላይ ብቻ ነበር።
ፎቁ ብዙ ክፍል ስላለው ልጅ ኢያሱን በማገልገል ይረዱ ዘንድ ከልዑል ራስ ካሳ የታዘዙላቸው ሶስት የውስጥ ስራ ተላላኪዎች በግማሹ ክፍል ይኖራሉ።እነርሱም መኮንን በላይነህ፣መኩሪያ፣ተሰማ የተባሉ ናቸው።እንዲሁም ደግሞ መብልና መጠጥ ከልዑል ራስ ካሳ ግቢ የሚያመላልሱ እና የሚያቀርቡ አራት የውጭ ስራ ተላላኪዎች ታዘውላቸዋል።
ፎቁ በሁለት በፊት በረንዳ ስላለው ልጅ ኢያሱ ለዕረፍት ይቀመጡበታል ወይም ሽር ሽር ይሉበታል ደግሞም የመድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በፊት ለፊቱ የሚታይ ስለሆነ በበረንዳው ላይ ሆነው ይሳለማሉ ወይም ጸሎት ያደርሳሉ።
ወደ ቤቱ የሚያሳልፈው የአጥሩ በር አንድ ብቻ ነው።ይኸውም ጧት በቁርስ ሰዓት በእኩለ ቀን በምሳ ሰዓት ማለት ነው።ከእነዚህ ሰዓት ውጭ ተላላኪዎች ምግብ እና መጠጥ ይዘው እስከ ፣ምድር ቤት ይመላለሳሉ፤ምድር ቤት ውስጥም የሚቀመጡት የውስጥ ዘበኞች በእነዚህ ሰዓት እየተቀያየሩ በትጋት ይጠብቃሉ።
እነርሱም ከሰላሌ ባላባቶች ከሌሎች ሰዎች በታማኝነት የተመረጡ ናቸው።ልጅ ኢያሱ ባመለጡበት እለት ከነበሩት የውስጥ ጠባቂዎች በነገሩ ላይ ገብተው የተገኙበት የላስታው ቀኝአዝማች ሰሎሞንና የሰላሴው ባላምባራስ ደገፉ ናቸው።
የአጠባበቁ ሥነ ሥርዓት ይህን ያህል በጥንቃቄ ተይዞ ልጅ እያሱ ከፍቼ ለመውጣት እና ለማምለጥ የቻሉት በአንድ በኩል ከልዑል ራስ ኃይሉ የተላከው ገንዘብ የጠባቂዎችን እምነት በማዳከሙ ፤በሌላ በኩል ካህናት ህልም አየን እያሉ የላኩላቸውን ተስፋ በመተማመን ነበር።የህልሙም ነገር እንደሚከተለው ነበር።
ከፍቼ ከተማ ጥቂት ርቆ የሚገኝ ወጠጤ የተባለ ሜዳ አለ።አለቃ ተክለ ጊዮርጊስ የተባሉ የእለተ ማሪያም አለቃ ከዕለታት በአንድ ቀን ሌሊቱን ተኝተው ሳሉ ወጠጤ ሜዳ ላይ ትልቅ ድንኳን ተተክሎ በህልማቸው አይተው ነበርና የህልሙን ፍቺ “ውጣ አጤ” ብለው ስለተረጎሙት የመውጫ ጊዜ ደረሰ ብለው ለልጅ ኢያሱ ላኩባቸው።
ልጅ ኢያሱ ይህን የህልም ተስፋ ከመስማታቸው በላይ ከአዲስ አበባም የራስ ኃይሉ እና የቀድሞ አሽከሮቻቸው ከነዘውዱ እርገጤ በየጊዜው መልእክት እና ገንዘብ ይደርስባቸው ስለነበር በነገሩ ተማምነው ለመውጣት እና ለማምለጥ ተደፋፈሩ።
የአወጣጣቸው ሁናቴ የራስ ኃይሉ መልዕክተኞች እጅ የተላለፈ ፍቼ ሲደርስ በገንዘብ የተሸነገሉት የውጭ ተላላኪዎች እኔን ወይ አንተን ይቀበላሉ።እነሱም ምግብ መጠጥ ለማቀበል በሚገቡበት ጊዜ ወረቀቱን በመሶብ ልብስ ውስጥ በረቀቀ ዘዴ ከተው ለወስጥ ተላላኪዎች ለነመኩሪያ ይሰጣሉ።ልጅ ኢያሱም ወረቀቱን አይተው መልስ ለመስጠት መልዕክቱ በዚህ አኳኋን ይተላለፋል።
የውስጥ እና የውጭ ተላላኪዎች መልዕክቱን በዚህ ዓይነት እያቀባበሉ ሲያስተላልፉ ከቆዩ በኋላ ለማስወጣት በአቀዱበት ዕለት በዚያው ዕለት ልጅ ኢያሱን የሴት ልብስ አልብሰው እና ሴት ወይዘሮ አስመስለው አዘጋጇቸው።
ቀጥሎ ዋናው በር ለእራት ሰዓት ሲከፈት ወይ አንተ እና አበበ ይጨነቁ ምግብ ይዘው ይግቡ።የፎቁ በር ተከፍቶ እነ መኩሪያ ምግቡን ሲቀበሉ ልጅ ኢያሱንም ወደ ምድር ቤት አውርደው እንደ ጓዳ በሆነ ስፍራ ውስጥ ይደብቋቸው።
ወዲያው ለዓይን ድንግዝግዝ ሲል በጨለማው ሰዓት አበበ ይጨነቁ ተከትሏቸው ልጅ ኢያሱን በዋናው በር ወጥተው ሄዱ። ሴት ወይዘሮ መስለው ነበርና የውጭው ዘበኛ አንዳች ጥያቄ አልጠየቃቸውም።የምድረ ግቢው አደባባይ ከአለፉት በኋላ ከውስጥ ዘበኞች አንዱ ባላምባራስ ደገፉን በቅሎ አደራጅቶ ይጠብቅ ነበር እና ልጅ ኢያሱን ተቀብሎ አበበ ይጨነቁን እና ሌሎች ሶስት ሰዎችን ጭምር ወደ ቤቱ ወስዶ አሳደራቸው።
ቤቱ ግራር በተባለ ቀበሌ በርስቱ ላይ ነው። ሃሙስ በቤቱ ደብቆ አዋለ እና በማግስቱ ዓርብ ወደ ጉለሌ ወስዶ ከወይዘሮ ጎመጀ ሸዋ ቤት አስገባቸው።ሴቲቱም የመጣባቸው እንግዳ ልጅ ኢያሱ መሆናቸውን በአወቁ ጊዜ ደንግጠው እየተጨነቁ “ባላምባራስ ደገፉ ምነው እንዲህ አደረግኸኝ” እያሉ የልባቸውን ስጋት ገለጡለት።ይሁን አንጂ በሚገባ አስተናግደው አሳደሩና ከቤታቸው እንዲሸኙ አደረጉ።
ልጅ ኢያሱም በየቦታው ሲጠባበቋቸው ከነበሩት ከቀድሞ አሽከሮቻቸው ከእነ ዘውዴ እርገጤ ጋር ግንቦት 13 ቀን ተቀላቀሉ እና ከፍቼ ከተከተሏቸው አራት አሽከሮች ጭምር በሙገር ቆላ በኩል ወደ ሜጫ ጉዞ ሲጀምሩ ባላምባራስ ደገፉ ወደ ፍቼ ተመልሶ የዘበኝነት ስራውን ይቀጥል ጀመር።
አበበ ይጨነቁ ከልጅ ኢያሱ ጋር ከሄደ በኋላ የደረሰበት ሳይታወቅ እንደጠፋ ቀርቷል። ልጅ ኢያሱ ሜጫ ውስጥ በአንድ ስፍራ ተደብቀው ተቀመጡ ደብዳቤ ወደ ራስ ኃይሉ ላኩ።
ይድረስ ከራስ ኃይሉ
የአባቶቼ አምላክ በግንቦት 10 ቀን የመስቀል ዕለት አወጣኝ።ሁለት ቀን በእግሬ ስሄድ ጊዜ ከደስታዬ ብዛት እግሬ አበጠ። ትሰማው ብዬ ነው።እንግዲህ የተክለ ሃይማኖትን አምላክ ክርስቶስን አምነህ ለእኔ ቁርጥ ነገር ስራ፤ከእምነቴ የተነሳ ጻፍኩልህ ደስ ይበልህ።የአባቶቼ አምላክ እንደዚህ ልጆቻቸውን ወዶአልና ለእኔ እንደ ምናሴ ላንተ ሕዝቂያስ ሆነልን።እንግዲህ ፊርማዬ ከአንተ አይደለምና አንተ እንደዚህ ይሁን ግባ በዚህ ሂድ በለኝ።ለደጃች ባልቻም ደስ እንዲለው አሳውቀው።አንተን ለሚወዱ ሁሉ ደስ እንዲለው ግለጥለትና እንዲረዳ ይሁን።እግዚያብሔር አወጣኝ።
ፊርማ
ልጅ ኢያሱ
ልጅ ኢያሱ ደግመው ከተያዙ እና በአዲስ አበባ ከታሰሩ በኋላ ህዳር 12 ቀን 1928 ዓመተ ምሕረት አርፈው አዚያው ተቀብረዋል።ሞታቸው በአዲስ አበባ በተሰማ ጊዜ ስለ ክብራቸው 7 ጊዜ መድፍ ተተኩሶ በቤተ መንግስት ሀዘን ተደርጓል።
ምንጭ፡- መርስኄ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ የሐያኛው ዘመን መባቻ።
አዲስ ዘመን ጥር 30/2013