ክቡር ዶክተር አሊ ቢራ
“ቢራ” ትርጓሜው የብርሀን ፍንጣቂ ፤ ጨለማን ገርሳሽ እንደ ማለት ነው። እርሱ ወደ ሙዚቃው ዓለም ብቅ ብሎ ለዘርፉ አዲስ ግኝት ለሙዚቃው አዲስ ክስተት በመሆኑ ያገኘው ስያሜ ነው። ትክክለኛ ስሙ አሊ ሙሀመድ ሙሳ ነው።
ገና በ14 ዓመቱ አፌንቀሎ የተባለ የሙዚቃና የባህል ቡድን ተቀላቅሎ መድረክ ላይ ወጥቶ ባሳየው ልዩ ችሎታ ብዙዎች ተገረሙ። ድምፀ ስርቅርቅነቱ ተመልክተው፤ ሙዚቃን ሲጫወት ልዩ መሆኑን አስተውለው ከስሙ ጋር “ቢራ” የተሰኘ ታላቅ ትርጉም ያለው ቃል አክለው መጠሪያው አደረጉት።
ዛሬ በዝነኞች የዕረፍት ውሎ አምዳችን ዝነኛውና እውቁ የሙዚቃ ሰው አሊ ቢራ አነጋግሮ የዕረፍ ጊዜ ቆይታውን፣ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው ተሳትፎ አጠቃላይ ስራውና አሁን ያለበት ሁኔታ የተመለከተ ጽሁፍ በሚከተለው መልኩ አቀረብንላችሁ መልካም የዕረፍት ቀን ንባብ።
አሊ ቢራ በሙዚቃው ፍቅርን ሰብኳል፣ በሙዚቃው የአንድነት ጥቅምን አብዝቶ ነግሯል። በመዝፈኑ እስር ቤት ገብቷል፤ ከሚወዳት አገሩ ርቆም ተሰዷል፣ ስለ ሰው ልጆች ሰላምና ነፃነት በማቀንቀኑ ከአገሩ ርቆ እንዲኖር ተፈርዶበትም ነበር።
እርሱ ግን መኪሊቱን አግኝቶ ነበርና ሙዚቃ ውስጥ ሆኖ ብዙ አሳለፈ። በሙዚቃ ብዙ ማለት ችሏል። ከአቋሙ ግን ንቅንቅ ሳይል ላመነበትና ለወደደው ሀሳቡ ታግሏል። በመጨረሻም ለስኬት በቅቷል።
የሙዚቃ ማጫወጫ በሌለበት፤ ሬዲዮ ዋንኛ የሙዚቃ ማድመጫ በሆነበት ዘመን የጥላሁን ገሰሰና የአሰፋ አባተ ዘፈኖችን እየሰማ መልሶ በመዝፈን በሚሰሙት ሰዎች ጆሮ ውስጥ በመግባት ለምን ዘፈን አትሞክርም የሚል ሀሳብ ይቀርብለት ነበር። እርሱም ከአፈንቄሎ ጋር ሆኖ ህልሙን ለማሳካት ጥረት ማድረግ ጀመረ።
ቆይቶም መድረክ ላይ ባሳየው ተዓምራዊ የአዘፋፈን ስልት ብዙዎችን ያስደመመው ታዳጊ እስከዛሬ በኪነጥበቡ ነግሶ በሙዚቃ ስራው ከፍ ብሎ ከመንበሩ ሳይወርድ ቆየ።
በግጥምና ዜማዎቹ በአዘፋፈን ለዛው የሰሙት ሁሉ የሚደመሙበት፤ያደመጡት ሁሉ የሚያደንቁት እንቁ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል። ልጅ ሆኖ መድረክ ላይ ሲዘፍን በመገረም “ቢራ” ያሉት ወጣት ለሙዚቃው የተፈጠረ ብርሀን፤ለኪነ ጥበቡ ስጦታ የቀረበ ልዩ ሰው መሆኑን ገብቷቸው ነበርና ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በሙዚቃው ነግሶ ዛሬ ድረስ አለ።
ይህ ከወደ ምስራቋ ፀሀይ መውጫ ድሬዳዋ የተገኘ እንቁ፤ በኦሮምኛ ቋንቋ ዘመናዊ የሙዚቃ ስልት በማስተዋወቅ ለዘርፉ ታላቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል። በ1958 መጨረሻ በክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ በመቀጠር ከእውቅ ድምፃዊያን ጋር የመገናኘት እድል ገጠመው።
በአዲስ አበባ የተለያዩ የምሽት ሙዚቃ ክለቦች ተዘዋውሮ ለወቅቱ አዲስ በሆነ አዘፋፈን ስልት ተወዳጅነትን አተረፈ። በጥረቱም ቀጥሎ በ1960 ዓ.ም የመጀመሪያ ስራውን ለህዝብ በማሳተም አቅርቦ ዝናው ናኘ።
ከዚያ በኋላ ይህ እውቅና ዝነኛ አርቲስት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ከሚጠቀሱ ተፅዕኖ ፈጣሪ አርቲስቶች አንዱና ዋንኛው በመሆን ለዘርፉ ዕድገት የአንበሳውን ሚና በመጫውት ለሙዚቃው አርነትም ተጠቃሽ ሰው ሆኗል። ዜማዎቹ በብዙዎች የሚወደዱ፣ በሙዚቃዎቹ አያሌ ጉዳዮችን ያነሳ በስራዎቹ በብዙዎች የሚደነቅ አንጋፋ ሙዚቀኛ ነው።
የዝነኛው የዕረፍት ጊዜ
ብዙዎች የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበትና ተዝናንቶን የሚያተርፉበት ሙዚቃ መዝፈንና መስማት እርሱንም የሚያዝናናውና የሚያስደስተው ነው። ከሙዚቃው ባልተናነሰ ከልጅነቱ ጀምሮ እጅግ በጣም ማንበብን የሚወደው አሊ ቢራ ዛሬም የማንበብን ያህል የሚያዝናናው ተግባር የለም። ዛሬ ድረስ ታሪክ
አዘል የሆኑ መፅሀፍት ከያሉበት እየሰበሰበ ያነባል። በልቦለድ መልክ የሚፃፉ የተመረጡ መፅሀፎችም የመዝናኛ ጊዜ ቆይታውን የሚያደምቁለት መዝናኛውም የተመቸ እንዲሆን የሚረዱት የሚወዳቸው መፅሀፍት መሆናቸውን በአንደበቱ መስክሯል።
እርግጥ ዛሬ ላይ አለም ወደ ዲጂታል እየተቀየረ ስለሆነ ብዙውን ጊዜ ለመዝናናት የሚመርጠው ፊልሞችን በመመልከት ነው። ዶክመንተሪና የፍቅር ትዕይንቶችን መሰረት አድርገው የሚሰሩት ይመለከታል። በፊልም ምልከታው ወቅት ቋንቋን አይመርጥም። ከሚሰማውና ከሚናገራቸው ቋንቋዎች ውጪ ያሉት ፊልሞች እንኳን መመልከት እንደሚወድ ይናገራል።
ሰዎች በእረፍት ጊዜያቸው አገርና ሰዎችን እንዲሁም ባህላቸውን ማወቅ በዚያም መዝናናት ይገባቸዋል የሚለው አሊ ቢራ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ልዩ ልዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦችን በመጎብኘት የእረፍት ጊዜውን ያሳልፋል። ከከተማ ወጣ ብሎ ልዩ ልዩ አካባቢዎችን መጎብኘትና ከሰዎች ጋር ወዳጅነት መፍጠርም ያስደስተዋል። ማህበራዊ ተሳትፎም ላይ ንቁና ነገሮችን ቀለል አድርጎ ከሰዎች ጋር መግባባት የሚችለው አሊ ቢራ በእረፍት ጊዜው ከሰዎች ጋር በመሆን አዝናኝ እና ጥሩ ቆይታ ማድረግ ያስደስተዋል።
የዝነኛው መልዕክት
“አንድ እናት ናት ያለችን። ያቺ እናት ከተለያዩ አባቶች ብዙ ልጆችን ወልዳለች እነዚያ ልጆች ወንድማማቾች ናቸው። የሚለያቸው ምንም የለም። ልጆችዋ የተሳሰሩ ናቸው። ይቺ እናት ልጆችዋን ሁሉ በእኩል ትወዳለች። ነገር ግን ልጆችዋ እርስ በርስ ሲጋጩና እርስ በርስ ሲጣሉ ይከፋታል።
ይቺ እናት ልጆችዋ በፍቅር አንድ እንዲሆኑና እንዲዋደዱ ትመኛለች፤ትፈልጋለችም።ያቺ እናታችን አገራችን ነች። ልጆች በእናት አንድ ናቸውና እናታቸውን መንከባከብ ይገባቸዋል።
ኢትጵዮጵያ ውብ አገር ነች። በፍቅር ተሳስበን በጋራ ተጠቃሚነት በእኩልነት እንገንባት እንጠብቃት።” በማለት ታላቅ መልዕክቱን አስተላልፏል። እኛም ከዝነኛው ጋር የነበረን ቆይታ በዚሁ አበቃን መልካም የዕረፍት ውሎ።
አዲስ ዘመን ጥር 30/2013